መክብብ 4:1-16

  • ግፍ ከሞት የከፋ ነው (1-3)

  • ለሥራ ሚዛናዊ አመለካከት መያዝ (4-6)

  • የጓደኛ ጥቅም (7-12)

    • “አንድ ከመሆን ሁለት መሆን ይሻላል” (9)

  • የንጉሥ ሕይወት ከንቱ ሊሆን ይችላል (13-16)

4  ከፀሐይ በታች የሚፈጸመውን ግፍ ሁሉ በድጋሚ ተመለከትኩ። ግፍ የተፈጸመባቸውን ሰዎች እንባ ተመለከትኩ፤ የሚያጽናናቸውም ሰው አልነበረም።+ ግፍ የሚፈጽሙባቸውም ሰዎች ኃይል ነበራቸው፤ የሚያጽናናቸውም አልነበረም።  እኔም ‘ዛሬ በሕይወት ካሉት ሕያዋን ይልቅ በቀድሞ ዘመን የሞቱ ሙታን ይሻላሉ’ አልኩ።+  ደግሞም ከሁለቱ ይልቅ ገና ያልተወለደው፣+ ከፀሐይ በታች የሚፈጸሙትንም አስጨናቂ ድርጊቶች ያላየው ይሻላል።+  እኔም በሰዎች መካከል ያለው ፉክክር፣ ከፍተኛ ጥረት እንዲያደርጉና* የተዋጣለት ሥራ እንዲያከናውኑ እንደሚያነሳሳቸው ተመለከትኩ፤+ ይህም ከንቱና ነፋስን እንደማሳደድ ነው።  ሞኝ ሰው ሥጋው እየመነመነ ሲሄድ፣* እጁን አጣጥፎ ይቀመጣል።+  ብዙ በመልፋትና ነፋስን በማሳደድ ከሚገኝ ሁለት እፍኝ ይልቅ ጥቂት እረፍት በማድረግ የሚገኝ አንድ እፍኝ ይሻላል።+  እኔም ከፀሐይ በታች ያለውን ሌላ ከንቱ ነገር እንደገና ተመለከትኩ፦  ብቸኛ የሆነና ጓደኛ የሌለው ሰው አለ፤ ልጅም ሆነ ወንድም የለውም፤ ይሁንና የሚሠራው ሥራ ማብቂያ የለውም። ዓይኖቹ ሀብትን አይጠግቡም።+ ሆኖም ‘እንዲህ በትጋት የምሠራውና ራሴን* መልካም ነገር የምነፍገው ለማን ብዬ ነው?’ ብሎ ራሱን ይጠይቃል?+ ይህም ቢሆን ከንቱና አሰልቺ ሥራ ነው።+  አንድ ከመሆን ሁለት መሆን ይሻላል፤+ ምክንያቱም ሁለት ሆነው የሚያከናውኑት ሥራ ጥሩ ውጤት* ያስገኝላቸዋል። 10  አንዱ ቢወድቅ ሁለተኛው ባልንጀራውን ደግፎ ሊያነሳው ይችላልና። ይሁንና ደግፎ የሚያነሳው ሰው በሌለበት አንዱ ቢወድቅ እንዴት ይሆናል? 11  በተጨማሪም ሁለት ሰዎች አብረው ቢተኙ ይሞቃቸዋል፤ ሆኖም አንድ ሰው ብቻውን ሆኖ እንዴት ሊሞቀው ይችላል? 12  ደግሞም አንድ ሰው ብቻውን ያለን ሰው ሊያሸንፈው ይችል ይሆናል፤ ሁለት ከሆኑ ግን ሊቋቋሙት ይችላሉ። በሦስት የተገመደ ገመድም ቶሎ አይበጠስም።* 13  የተሰጠውን ማስጠንቀቂያ ተግባራዊ እንዳያደርግ ማስተዋል ከጎደለው በዕድሜ የገፋ ሞኝ ንጉሥ+ ይልቅ ድሃ የሆነ ጥበበኛ ልጅ ይሻላል።+ 14  በእሱ ግዛት ውስጥ ድሃ ሆኖ የተወለደ ቢሆንም* ከእስር ቤት ወጥቶ ንጉሥ ይሆናል።+ 15  እኔም ከፀሐይ በታች የሚመላለሱት ሕያዋን ሁሉ እንዲሁም በንጉሡ ቦታ የሚተካው ልጅ ምን እንደሚገጥማቸው አጤንኩ። 16  ስፍር ቁጥር የሌላቸው ደጋፊዎች ቢኖሩትም በኋላ የሚመጡት ሰዎች በእሱ አይደሰቱም።+ ይህም ቢሆን ከንቱና ነፋስን እንደማሳደድ ነው።

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “ጠንክረው እንዲሠሩና።”
ቃል በቃል “የገዛ ሥጋውን ይበላል።”
ወይም “ነፍሴን።”
ወይም “የተሻለ ጥቅም።”
ወይም “በቀላሉ አይበጠስም።”
ጥበበኛውን ልጅ የሚያመለክት ሊሆን ይችላል።