መዝሙር 72:1-20

  • ሰላም የሰፈነበት የአምላክ ንጉሥ አገዛዝ

    • “ጻድቅ ይለመልማል” (7)

    • ከባሕር እስከ ባሕር ድረስ ተገዢዎች ይኖሩታል (8)

    • “ከግፍ ይታደጋቸዋል” (14)

    • “በምድር ላይ እህል ይትረፈረፋል” (16)

    • የአምላክ ስም ለዘላለም ይወደስ (19)

ስለ ሰለሞን የተዘመረ መዝሙር። 72  አምላክ ሆይ፣ ፍርዶችህን ለንጉሡ ስጥ፤ጽድቅህንም ለንጉሡ ልጅ አጎናጽፍ።+   ስለ ሕዝብህ በጽድቅ ይሟገት፤ለተቸገሩ አገልጋዮችህም ፍትሕ ያስፍን።+   ተራሮች ለሕዝቡ ሰላም ያምጡ፤ኮረብቶችም ጽድቅን ያስገኙ።   በሕዝቡ መካከል ላሉት ችግረኞች ጥብቅና ይቁም፤*የድሃውን ልጆች ያድን፤ቀማኛውንም ይደምስሰው።+   ፀሐይ ብርሃኗን እስከሰጠች፣ጨረቃም በሰማይ ላይ እስካለች ድረስ፣ከትውልድ እስከ ትውልድ+ አንተን ይፈሩሃል።   እሱ በታጨደ ሣር ላይ እንደሚዘንብ ዝናብ፣ምድርንም እንደሚያጠጣ ካፊያ ይወርዳል።+   በእሱ ዘመን ጻድቅ ይለመልማል፤*+ጨረቃም በምትኖርበት ዘመን ሁሉ ሰላም ይበዛል።+   ከባሕር እስከ ባሕር ድረስ፣ከወንዙም* እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ ተገዢዎች ይኖሩታል።*+   በበረሃ የሚኖሩ ሰዎች በፊቱ ይሰግዳሉ፤ጠላቶቹም አፈር ይልሳሉ።+ 10  የተርሴስና የደሴቶች ነገሥታት፣ ግብር ያመጣሉ።+ የሳባና የሴባ ነገሥታት፣ ስጦታ ይሰጣሉ።+ 11  ነገሥታትም ሁሉ በፊቱ ይሰግዳሉ፤ብሔራትም ሁሉ ያገለግሉታል። 12  እርዳታ ለማግኘት የሚጮኸውን ድሃ፣እንዲሁም ችግረኛውንና ረዳት የሌለውን ሁሉ ይታደጋልና። 13  ለችግረኛውና ለድሃው ያዝናል፤የድሆችንም ሕይወት* ያድናል። 14  ከጭቆናና ከግፍ ይታደጋቸዋል፤*ደማቸውም በዓይኖቹ ፊት ክቡር ነው። 15  ረጅም ዘመን ይኑር፤ የሳባም ወርቅ ይሰጠው።+ ስለ እሱም ሁልጊዜ ጸሎት ይቅረብ፤ቀኑንም ሙሉ ይባረክ። 16  በምድር ላይ እህል ይትረፈረፋል፤+በተራሮችም አናት ላይ በብዛት ይኖራል። የንጉሡም ፍሬ እንደ ሊባኖስ ዛፎች ይንዠረገጋል፤+በከተሞቹም ውስጥ ሰዎች በምድር ላይ እንዳሉ ዕፀዋት ያብባሉ።+ 17  ስሙ ለዘላለም ጸንቶ ይኑር፤+ፀሐይም እስካለች ድረስ ስሙ ይግነን። ሰዎች በእሱ አማካኝነት ለራሳቸው በረከት ያግኙ፤+ብሔራት ሁሉ ደስተኛ ብለው ይጥሩት። 18  እሱ ብቻ አስደናቂ ነገሮችን የሚያደርገው፣+የእስራኤል አምላክ ይሖዋ ይወደስ።+ 19  ክብራማ ስሙ ለዘላለም ይወደስ፤+ምድርም ሁሉ በክብሩ ትሞላ።+ አሜን፣ አሜን። 20  የእሴይ ልጅ+ የዳዊት ጸሎቶች እዚህ ላይ አበቁ።

የግርጌ ማስታወሻዎች

ቃል በቃል “ይፍረድ።”
ቃል በቃል “ያቆጠቁጣል።”
ኤፍራጥስን ያመለክታል።
ወይም “ይገዛል።”
ወይም “ነፍስ።”
ወይም “ነፍሳቸውን ይዋጃል።”