በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

 የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ፦ የዓለም መጨረሻ ሊያስፈራህ ይገባል?

የዓለም መጨረሻ ሊያስፈራህ ይገባል?

የዓለም መጨረሻ ሊያስፈራህ ይገባል?

በማያዎች የቀን መቁጠሪያ መሠረት ብዙዎች ዓለም አቀፍ ለውጥ ይመጣል ብለው ይጠብቁ የነበረበትን ዕለት ይኸውም ታኅሣሥ 21 ቀን 2012ን በተመለከተ ምን ተሰምቶህ ነበር? ምናልባት በዚህ ዕለት መጥፎ ነገር እንደሚከሰት ጠብቀህ ከነበረ አሁን እፎይ ብለህ ይሆናል፤ አሊያም ለየት ያለ ነገር እንደሚኖር በማሰብ ጓጉተህ ከነበረ ነገሮች እንደጠበቅኸው ባለመሆናቸው ቅር ብሎህ ይሆናል፤ በሌላ በኩል ደግሞ ከዚያም በፊት መጨረሻው እንደሚመጣ የጠበቅህባቸው ወቅቶች ከነበሩ እንደዚህ ባሉ ትንቢቶች ተስፋ መቁረጥ ጀምረህ ይሆናል። ታዲያ ይህ ሁኔታ፣ ስለ ዓለም መጨረሻ የሚነገሩ ትንቢቶች የተሳሳቱ እንደሆኑ የሚያሳይ ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ ስለ “ዓለም መጨረሻ” የሚናገረውን ትንቢት በተመለከተስ ምን ማለት ይቻላል? (ማቴዎስ 24:3 አ.መ.ት) አንዳንዶች ምድር በእሳት ትጋያለች ብለው ይፈራሉ። ሌሎች ደግሞ በዚያ ወቅት ምን እንደሚፈጸም ለማየት ይጓጓሉ። ብዙዎች ግን የዓለም መጨረሻ እንደቀረበ የሚገልጹ ትንበያዎችን መስማት ሰልችቷቸዋል። ታዲያ የዓለም መጨረሻ የሚባለው ነገር በፈጠራ ላይ የተመሠረተ ይሆን? ወይስ እውነት ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ዓለም መጨረሻ ምን እንደሚል ስታውቅ ትገረም ይሆናል። መጽሐፍ ቅዱስ ይህን ጊዜ በጉጉት እንድንጠባበቅ የሚያደርጉንን ምክንያቶች የሚገልጽ ከመሆኑም ሌላ አንዳንዶች ጊዜው የዘገየ ሲመስላቸው ሊሰላቹ እንደሚችሉም ይናገራል። የዓለም መጨረሻን በተመለከተ ለሚነሱ አንዳንድ የተለመዱ ጥያቄዎች መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠውን መልስ እንድትመረምር እንጋብዝሃለን።

 ምድር በእሳት ትጋያለች?

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? “[አምላክ] ለዘላለም እንዳትናወጥ፣ ምድርን በመሠረቷ ላይ [አጸናት]።”—መዝሙር 104:5

ምድር በእሳትም ሆነ በሌላ በማንኛውም መንገድ አትጠፋም። እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስ፣ ይህች ፕላኔት የሰው ልጆች የዘላለም መኖሪያ እንደሆነች ይገልጻል። መዝሙር 37:29 “ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ፤ በእርሷም ለዘላለም ይኖራሉ” ይላል።—መዝሙር 115:16፤ ኢሳይያስ 45:18

አምላክ ምድርን ከፈጠረ በኋላ የፍጥረት ሥራው “እጅግ መልካም” እንደሆነ ተናግሯል፤ ዛሬም ቢሆን ስለ ምድር ያለው አመለካከት አልተለወጠም። (ዘፍጥረት 1:31) አምላክ ምድርን የማጥፋት ሐሳብ የለውም፤ እንዲያውም “ምድርን እያጠፉ ያሉትን [በማጥፋት]” ይህች ፕላኔት ዘላቂ ጉዳት እንዳይደርስባት ይጠብቃታል።—ራእይ 11:18

ታዲያ በ2 ጴጥሮስ 3:7 ላይ ያለው ሐሳብስ? ጥቅሱ “አሁን ያሉት ሰማያትም ሆኑ ምድር ለእሳት . . . ተጠብቀው ይቆያሉ” ይላል። ይህ ጥቅስ ምድር በእሳት እንደምትጋይ የሚጠቁም ነው? “ሰማያት፣” “ምድር” እና “እሳት” የሚሉት ቃላት አንዳንድ ጊዜ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ምሳሌያዊ በሆነ መንገድ ወይም አንዳንድ ነገሮችን ለመወከል ተሠርቶባቸዋል። ለአብነት ያህል፣ ዘፍጥረት 11:1 (የ1954 ትርጉም) ላይ “ምድርም ሁሉ በአንድ ቋንቋና በአንድ ንግግር ነበረች” ሲል “ምድር” የሚለው ቃል ሰብዓዊውን ኅብረተሰብ ይወክላል።

2 ጴጥሮስ 3:7 ዙሪያ ከሚገኘው ሐሳብ መረዳት እንደምንችለው እዚህ ላይ የተጠቀሱት ሰማያት፣ ምድርና እሳት ምሳሌያዊ ትርጉም ያላቸው ናቸው። ቁጥር 5 እና 6 ላይ ሰማያትና ምድር የሚጠፉበት ጊዜ በኖኅ ዘመን ከነበረው የጥፋት ውኃ ጋር ተመሳስሏል። በዚያ ወቅት የነበረው የጥንቱ ዓለም ጠፍቷል፤ ፕላኔታችን ግን እንዳልጠፋች የታወቀ ነው። ከዚህ ይልቅ የጥፋት ውኃው ያጠፋው ‘በምድር’ የተወከሉትን ዓመፀኛ የሆኑ የሰው ልጆች ነው። (ዘፍጥረት 6:11) የጥፋት ውኃው በወቅቱ የነበረውን ማኅበረሰብ የሚያስተዳድሩትን ‘በሰማያት’ የተመሰሉ ሰዎችንም አጥፍቷል። በተመሳሳይም 2 ጴጥሮስ 3:7 የሚናገረው ክፉው የሰው ዘር ማኅበረሰብና ምግባረ ብልሹ የሆኑት መንግሥታት ልክ በእሳት የመጥፋት ያህል ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እንደሚወገዱ ነው።

የዓለም መጨረሻ ሲመጣ ምን ይፈጸማል?

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? “ዓለምም ሆነ ምኞቱ በማለፍ ላይ ናቸው፤ የአምላክን ፈቃድ የሚያደርግ ግን ለዘላለም ይኖራል።”1 ዮሐንስ 2:17

እዚህ ላይ እንደሚጠፋ የተገለጸው “ዓለም” ምድርን ሳይሆን ከአምላክ ፈቃድ ጋር በማይስማማ መንገድ የሚኖሩትን በዓለም ላይ ያሉ ሰዎች የሚያመለክት ነው። አንድ የቀዶ ጥገና ሐኪም የታማሚውን ሕይወት ለማዳን ሲል በካንሰር የተጎዳውን ክፍል ከታማሚው ሰውነት ውስጥ ቆርጦ እንደሚያወጣው ሁሉ፣ ጥሩ ሰዎች በምድር ላይ  ተደስተው መኖር እንዲችሉም አምላክ ክፉዎችን ‘ያጠፋቸዋል።’ (መዝሙር 37:9) ከዚህ አንጻር ሲታይ “የዓለም መጨረሻ” መምጣቱ የሚፈለግ ነገር ነው።

አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች “የዓለም መጨረሻ” የሚለውን ሐረግ “የዚህ ሥርዓት መደምደሚያ” ወይም “የዘመኑ መጨረሻ” ብለው ማስቀመጣቸው ይህን ጊዜ በተመለከተ አዎንታዊ አመለካከት ሊኖረን እንደሚገባ ይጠቁማል። (ማቴዎስ 24:3የታረመው የ1980 ትርጉም) የዓለም መጨረሻ ሲመጣ የሚጠፉት ምድርና ሁሉም የሰው ልጆች ስላልሆኑ ከዚያ በኋላ አዲስ ዘመን ወይም አዲስ ሥርዓት ይመጣል ብሎ መጠበቁ ምክንያታዊ አይሆንም? መጽሐፍ ቅዱስም ቢሆን ወደፊት ‘ስለሚመጣው ሥርዓት’ ይናገራል።—ሉቃስ 18:30

ኢየሱስ ወደፊት የሚመጣው ይህ ወቅት “ሁሉም ነገር የሚታደስበት ጊዜ” እንደሚሆን ተናግሯል። በዚያን ጊዜ ኢየሱስ፣ የሰው ዘር ከአምላክ የመጀመሪያ ዓላማ ጋር በሚስማማ ሁኔታ መኖር እንዲችል ያደርጋል። (ማቴዎስ 19:28 ኒው ኢንተርናሽናል ቨርዥን) በዚያ ወቅት ምን ዓይነት ሁኔታ ይኖራል?

“የአምላክን ፈቃድ” ይኸውም እሱ የሚጠብቅብንን ነገር የምናደርግ ከሆነ የዓለም መጨረሻን የምንፈራበት ምንም ምክንያት የለም። እንዲያውም ያን ጊዜ በጉጉት ልንጠባበቅ እንችላለን።

የዓለም መጨረሻ ያን ያህል ቀርቧል?

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? “እነዚህ ነገሮች ሲከሰቱ ስታዩ የአምላክ መንግሥት እንደቀረበ እወቁ።”ሉቃስ 21:31

ሪቻርድ ካይል የተባሉት ፕሮፌሰር ዘ ላስት ዴይስ አር ሂር አጌን በተባለው መጽሐፍ ላይ እንዲህ ብለዋል፦ “ስለ ዓለም መጨረሻ የሚገልጹ መላ ምቶች እንዲፈጠሩ ምክንያት የሚሆነው በማኅበረሰቡ ውስጥ ድንገተኛ ለውጥ ወይም ማኅበራዊ ቀውስ መከሰቱ ነው።” በተለይ ደግሞ እነዚህ ለውጦች ወይም ቀውሶች ለምን እንደተከሰቱ ማወቅ በማይቻልበት ጊዜ ስለ ዓለም መጨረሻ የሚገልጹ መላ ምቶች ይሰነዘራሉ።

የመጽሐፍ ቅዱስ ነቢያት ግን ስለ ዓለም መጨረሻ የጻፉት፣ በዘመናቸው የተፈጸሙ ግራ የሚያጋቡ ክስተቶችን ምክንያት ለማብራራት አልነበረም። ከዚህ ይልቅ እነዚህ ነቢያት፣ መጨረሻው መቅረቡን የሚጠቁሙ ሁኔታዎችን የተናገሩት በአምላክ መንፈስ ተመርተው ነው። ከእነዚህ ትንቢቶች አንዳንዶቹ ከታች ተዘርዝረዋል፤ እነዚህ ትንቢቶች በዘመናችን ፍጻሜያቸውን እያገኙ መሆናቸውን ራስህ እንድትመረምር እንጋብዝሃለን።

  •   ጦርነት፣ ረሃብ፣ የምድር መናወጥ እንዲሁም ገዳይ የሆኑ በሽታዎች ወረርሽኝ።—ማቴዎስ 24:7፤ ሉቃስ 21:11
  • የወንጀል መስፋፋት።—ማቴዎስ 24:12
  • የሰው ልጆች በምድር ላይ የሚያስከትሉት ውድመት።—ራእይ 11:18
  • ሰዎች ራሳቸውን፣ ገንዘብን እና ተድላን የሚወዱ በአንጻሩ ደግሞ ለአምላክ ፍቅር የሌላቸው መሆናቸው።—2 ጢሞቴዎስ 3:2, 4
  • የቤተሰብ መፈራረስ።—2 ጢሞቴዎስ 3:2, 3
  • ሰዎች በአጠቃላይ በቅርብ ለሚመጣው የመጨረሻ ቀን ግድ የለሽ መሆናቸው።—ማቴዎስ 24:37-39
  • ስለ አምላክ መንግሥት የሚገልጸው ምሥራች በመላው ዓለም መሰበክ።—ማቴዎስ 24:14

ኢየሱስ እንደተናገረው “እነዚህን ሁሉ ነገሮች” ስናይ መጨረሻው እንደቀረበ ማወቅ እንችላለን። (ማቴዎስ 24:33) የይሖዋ ምሥክሮች መጨረሻው መቅረቡን የሚጠቁሙ አሳማኝ ማስረጃዎች እንዳሉ ይሰማቸዋል፤ በመሆኑም በ236 አገሮች ውስጥ ስለ እምነታቸው ለሌሎች ይናገራሉ።

ሰዎች የጠበቋቸው ነገሮች ሳይፈጸሙ መቅረታቸው መጨረሻው መቼም እንደማይመጣ የሚጠቁም ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? “‘ሰላምና ደኅንነት ሆነ!’ ሲሉ የምጥ ጣር እርጉዝ ሴትን እንደሚይዛት ያልታሰበ ጥፋት ድንገት ይመጣባቸዋል፤ ደግሞም በምንም ዓይነት አያመልጡም።”1 ተሰሎንቄ 5:3

መጽሐፍ ቅዱስ፣ ዓለም የሚጠፋበትን ሁኔታ ከምጥ መምጣት ጋር ያመሳስለዋል፤ አንዲት ነፍሰ ጡር ሴት በምጥ መያዟ የማይቀር ከመሆኑም ሌላ ምጡ የሚጀምራት በድንገት ነው። ወደ ዓለም መጨረሻ የሚያመሩት ክስተቶች ከእርግዝና ጋርም ይመሳሰላሉ፤ አንዲት ነፍሰ ጡር ሴት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመሩ የሚመጡትን የመውለጃዋ ጊዜ መቅረቡን የሚጠቁሙ ምልክቶች ታውቃቸዋለች። ሐኪሟም የምትወልድበትን ቀን በግምት ይነግራት ይሆናል፤ እሱ ባለው ቀን ባይሆንም እንኳ በዚያው ጊዜ አካባቢ መውለዷ እንደማይቀር እናትየው እርግጠኛ ናት። በተመሳሳይም ሰዎች በጠበቁት ጊዜ መጨረሻው ባይመጣም ያለነው “በመጨረሻዎቹ ቀኖች” ውስጥ መሆኑን አንጠራጠርም፤ ምክንያቱም የመጨረሻው ቀን ምልክቶች በትክክል እየተፈጸሙ ነው።—2 ጢሞቴዎስ 3:1

‘መጨረሻው እንደቀረበ የሚያሳየው ምልክት ይህን ያህል ግልጽ ከሆነ ብዙ ሰዎች ይህ ቀን መቅረቡን የማያስተውሉት ለምንድን ነው?’ ብለህ ትጠይቅ ይሆናል። መጽሐፍ ቅዱስ፣ መጨረሻው እየቀረበ ሲሄድ ብዙዎች ምልክቱን ለማስተዋል ፈቃደኞች እንደማይሆኑ ይገልጻል። በመጨረሻዎቹ ቀኖች መሠረታዊ የሆኑ ለውጦች እየተካሄዱ መሆናቸውን አምነው ከመቀበል ይልቅ “አባቶች በሞት ካንቀላፉበት ጊዜ ጀምሮ ሁሉም ነገር ከፍጥረት መጀመሪያ አንስቶ እንዳለ ይቀጥላል” እያሉ ያፌዛሉ።  (2 ጴጥሮስ 3:3, 4) በሌላ አባባል የመጨረሻዎቹ ቀኖች ምልክት ግልጽ ቢሆንም ብዙዎች ችላ ይሉታል።—ማቴዎስ 24:38, 39

መጨረሻው መቅረቡን ከሚጠቁሙት ቅዱስ ጽሑፋዊ ማስረጃዎች መካከል በዚህ ርዕስ ላይ የተመለከትነው ጥቂቶቹን ብቻ ነው። * ስለዚህ ጉዳይ የበለጠ ለማወቅ ትፈልጋለህ? ከሆነ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ተገናኝተህ መጽሐፍ ቅዱስን ያለ ክፍያ ለምን አትማርም? በቤትህ ወይም ሌላ በሚመችህ ቦታ አሊያም በስልክ መጽሐፍ ቅዱስን በቋሚነት መማር ትችላለህ። እንዲህ ዓይነቱን ትምህርት ለማግኘት የሚጠበቅብህ ነገር ቢኖር ጥቂት ጊዜ መመደብ ብቻ ነው፤ ይህን በማድረግህ ግን በዋጋ ሊተመኑ የማይችሉ በረከቶች ታገኛለህ።

^ စာပိုဒ်၊ 39 ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች በተዘጋጀው ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? በተባለው መጽሐፍ ላይ “የምንኖረው ‘በመጨረሻው ዘመን’ ውስጥ ነው?” የሚለውን ምዕራፍ 9ን ተመልከት።