በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

 መጽሐፍ ቅዱስ የሰዎችን ሕይወት ይለውጣል

“በመጨረሻ እውነተኛ ነፃነት አግኝቻለሁ።”

“በመጨረሻ እውነተኛ ነፃነት አግኝቻለሁ።”
  • የትውልድ ዘመን፦ 1981
  • የትውልድ አገር፦ ዩናይትድ ስቴትስ
  • የኋላ ታሪክ፦ “አባካኝ ልጅ” የነበረ

የቀድሞ ሕይወቴ፦

የተወለድኩት በሰሜናዊ ዌስት ቨርጂኒያ፣ ዩናይትድ ስቴትስ በኦሃዮ ወንዝ ዳርቻ ላይ በምትገኝ ማውንድዝቪል የተባለች ግርግር የማይበዛባት ከተማ ውስጥ ነው። በቤተሰባችን ውስጥ ካሉት አራት ልጆች ሁለተኛ ነኝ፤ ሦስታችን ወንዶች በመሆናችን ቤታችን ጸጥ የሚልበት ሰዓት አልነበረም ማለት ይችላል። ወላጆቼ ታታሪ፣ ሐቀኛና ሰው ወዳድ ነበሩ። ሀብታሞች ባንሆንም የሚያስፈልገንን አጥተን አናውቅም። ወላጆቻችን የይሖዋ ምሥክሮች ስለሆኑ ገና ከልጅነታችን ጀምሮ የመጽሐፍ ቅዱስን መመሪያዎች በውስጣችን ለመቅረጽ የተቻላቸውን አድርገዋል።

የጉርምስና ዕድሜ ላይ ስደርስ ግን ወላጆቼ ካስተማሩኝ ነገር እየራቅሁ መሄድ ጀምሬ ነበር። የመጽሐፍ ቅዱስን መመሪያዎች መከተል ትርጉም ያለውና የሚያረካ ሕይወት ለመምራት የሚያስችል መሆኑን እጠራጠር ጀመር። እውነተኛ ደስታ ማግኘት የምችለው የፈለግሁትን ለማድረግ ነፃነት ሲኖረኝ ብቻ እንደሆነ አሰብኩ። ብዙም ሳይቆይ በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ መገኘት አቆምኩ። ታላቅ ወንድሜና ታናሽ እህቴም እንደ እኔ ዓይነት ጎዳና መከተል ጀመሩ። ወላጆቻችን እኛን ለመርዳት ያላደረጉት ጥረት አልነበረም፤ እኛ ግን የእነሱን እርዳታ ለመቀበል ፈቃደኞች አልነበርንም።

ይሁንና ነፃነት ያስገኛል ብዬ የተከተልሁት ጎዳና በሱስ ተተብትቤ እንድያዝ እንደሚያደርገኝ አልተገነዘብኩም ነበር። አንድ ቀን ከትምህርት ቤት እየተመለስኩ ሳለ አንድ ጓደኛዬ ሲጋራ ሰጠኝ። እኔም ተቀብዬ አጨስኩ። ከዚያ ቀን በኋላ ምንም ሳላቅማማ ጎጂ የሆኑ ድርጊቶች መፈጸሙን ተያያዝኩት። ቀስ በቀስ ዕፅ መውሰድና ከመጠን በላይ መጠጣት እንዲሁም ሥነ ምግባር የጎደለው አኗኗር መከተል ጀመርኩ። ዓመታት እያለፉ ሲሄዱ ይበልጥ ኃይለኛ የሆኑ ዕፆችን መውሰድ የጀመርኩ ሲሆን ውሎ አድሮም የብዙዎቹ ዕፆች ባሪያ ሆንኩ። ከጊዜ ወደ ጊዜ በሱስ ይበልጥ እየተዘፈቅሁ ስለሄድኩ ሱሴን ለማርካት የሚያስፈልገኝን ገንዘብ ለማግኘት ስል ዕፅ መሸጥ ጀመርኩ።

በዚህ ሁሉ ጊዜ የሕሊናዬን ወቀሳ ችላ ለማለት ብሞክርም እንኳ አኗኗሬ ትክክል እንዳልሆነ ሁልጊዜ አስብ ነበር። ያም ቢሆን ግን ከዚህ ሁሉ በኋላ ሕይወቴን መቀየር እንደማልችል ይሰማኝ ነበር። በጭፈራ ቦታዎችና በሙዚቃ ዝግጅቶች ላይ ስገኝ በዙሪያዬ ብዙ ሰዎች ቢኖሩም አብዛኛውን ጊዜ በብቸኝነትና በትካዜ እዋጣለሁ። ሥርዓታማና ጥሩ ወላጆች እያሉኝ እኔ እንዴት ይህን ያህል ርቄ ልሄድ እንደቻልኩ አንዳንድ ጊዜ አስብ ነበር።

 መጽሐፍ ቅዱስ ሕይወቴን የለወጠው እንዴት ነው?

እኔ ለውጥ ማድረግ እንደማልችል ቢሰማኝም ሌሎች ግን እንደዚያ አልተሰማቸውም። በ2000 ወላጆቼ የይሖዋ ምሥክሮች በሚያደርጉት የአውራጃ ስብሰባ ላይ እንድገኝ ጋበዙኝ። እያቅማማሁ በስብሰባው ላይ ተገኘሁ። የሚገርመው ነገር እንደ እኔ ዓይነት ጎዳና ተከትለው የነበሩት ወንድሜና እህቴም በስብሰባው ላይ ተገኙ።

በስብሰባው ላይ እያለሁ፣ ከአንድ ዓመት ገደማ በፊት የሮክ የሙዚቃ ዝግጅት ለማየት ወደዚህ ቦታ መጥቼ እንደነበር ትዝ አለኝ። አሁን ያለው ሁኔታ በወቅቱ ከነበረው ምን ያህል እንደሚለይ ስመለከት ስሜቴ በጥልቅ ተነካ። በሙዚቃ ዝግጅቱ ላይ ወለሉ በቆሻሻ ተሞልቶ እንዲሁም ቦታው በሲጋራ ጭስ ታፍኖ ነበር። በዝግጅቱ ላይ ከተገኙት ሰዎች አብዛኞቹ የማይቀረቡ ከመሆናቸውም ሌላ የሙዚቃው መልእክት ጥሩ ስሜት የሚፈጥር አልነበረም። በስብሰባው ላይ ያሉት ሰዎች ግን እውነተኛ ደስታ የነበራቸው ሲሆን ለዓመታት አግኝተውኝ ባያውቁም ሞቅ ባለ መንፈስ ተቀበሉኝ። ቦታው ንጹሕ ሆኖ ነበር፤ የሚተላለፈው ትምህርትም ተስፋ የሚፈነጥቅ ነበር። የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት በሰዎች ሕይወት ላይ የሚያሳድረውን በጎ ተጽዕኖ ስመለከት ከዚህ እውነት ርቄ የሄድኩት ለምን እንደሆነ ራሴን ጠየቅሁ።—ኢሳይያስ 48:17, 18

“መጽሐፍ ቅዱስ፣ ዕፅ መውሰድም ሆነ መሸጥ አቁሜ የተሻልኩ ሰው እንድሆን ረድቶኛል”

ወደ ክርስቲያን ጉባኤ ለመመለስ የወሰንኩት ስብሰባው እንዳበቃ ነበር። ወንድሜና እህቴም በስብሰባው ላይ የተመለከቱት ነገር ልባቸውን ስለነካው እንደ እኔ ዓይነት ውሳኔ አደረጉ። ሦስታችንም መጽሐፍ ቅዱስን እንድናጠና የቀረበልንን ግብዣ ተቀበልን።

ከምንም በላይ ልቤን የነካው በያዕቆብ 4:8 ላይ የሚገኘው “ወደ አምላክ ቅረቡ፤ እሱም ወደ እናንተ ይቀርባል” የሚለው ጥቅስ ነው። ወደ አምላክ መቅረብ ከፈለግሁ አኗኗሬን ማስተካከል እንዳለብኝ ተገነዘብኩ። ለምሳሌ ያህል፣ ከትንባሆና ከዕፅ መራቅ እንዲሁም ከመጠን በላይ መጠጣቴን ማቆም ነበረብኝ።—2 ቆሮንቶስ 7:1

ከድሮ ጓደኞቼ ጋር የነበረኝን ግንኙነት ያቋረጥሁ ሲሆን ከይሖዋ አገልጋዮች መካከል አዳዲስ ጓደኞችን አፈራሁ። በተለይ መጽሐፍ ቅዱስን ያስጠናኝ የነበረው የጉባኤ ሽማግሌ በጣም ረድቶኛል። አዘውትሮ ይደውልልኝ እንዲሁም መጥቶ ይጠይቀኝ ነበር። ይህ ክርስቲያን እስከ አሁንም ድረስ በጣም ከምቀርባቸው ጓደኞቼ አንዱ ነው።

ራሴን ለአምላክ ወስኜ በ2001 የጸደይ ወቅት ተጠመቅሁ፤ ወንድሜና እህቴም ተመሳሳይ እርምጃ ወሰዱ። ቤተሰባችን በመጨረሻ አንድ ላይ ይሖዋን ማምለክ ሲጀምር ወላጆቼና ይሖዋን በታማኝነት ያገለግል የነበረው ታናሽ ወንድሜ ምን ያህል እንደተደሰቱ መገመት ትችላላችሁ።

ያገኘሁት ጥቅም፦

የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎች ነፃነት የሚነፍጉ እንደሆኑ ይሰማኝ ነበር፤ አሁን ግን በዋጋ ሊተመን የማይችል ጥበቃ እንደሚያደርጉልን ተገንዝቤያለሁ። መጽሐፍ ቅዱስ፣ ዕፅ መውሰድም ሆነ መሸጥ አቁሜ የተሻልኩ ሰው እንድሆን ረድቶኛል።

የይሖዋ አምላኪዎች ዓለም አቀፍ የወንድማማች ኅብረት አባል የመሆን መብት አግኝቻለሁ። እነዚህ ሰዎች እርስ በርሳቸው ከልብ የሚዋደዱ ከመሆኑም ሌላ አምላክን በአንድነት ያመልካሉ። (ዮሐንስ 13:34, 35) በጣም የምወዳትንና የማከብራትን ባለቤቴን አድሪያንን ያገኘሁትም የዚህ የወንድማማች ማኅበር አባል በመሆኔ ነው፤ እሷን በማግባቴ ልዩ በረከት እንዳገኘሁ ይሰማኛል። እኔና አድሪያን አንድ ላይ ሆነን ፈጣሪያችንን ማገልገል በጣም ያስደስተናል።

ራስ ወዳድነት የሚንጸባረቅበት አኗኗር ከመከተል ይልቅ አሁን የሙሉ ጊዜ ወንጌላዊ ሆኜ ሰዎችን ከአምላክ ቃል እንዴት ጥቅም ማግኘት እንደሚችሉ አስተምራለሁ። ይህ ሥራ ከሁሉ የላቀ ደስታ አስገኝቶልኛል። መጽሐፍ ቅዱስ ሕይወቴን እንድለውጥ እንደረዳኝ አፌን ሞልቼ መናገር እችላለሁ። በመጨረሻ እውነተኛ ነፃነት አግኝቻለሁ።