በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

 ወደ አምላክ ቅረብ

‘ለሕፃናት ገለጥክላቸው’

‘ለሕፃናት ገለጥክላቸው’

ስለ አምላክ ማንነት፣ ስለሚወዳቸውና ስለሚጠላቸው ነገሮች እንዲሁም ፈቃዱ ምን እንደሆነ እውነቱን ማወቅ ትፈልጋለህ? ይሖዋ አምላክ ስለ ራሱ የገለጸውን እውነት በሙሉ በቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ማግኘት ይቻላል። ይሁንና መጽሐፍ ቅዱስን አንብቦ ይህን እውነት ሙሉ በሙሉ መረዳት የሚችለው ሁሉም ሰው አይደለም። ለምን? ምክንያቱም እንደዚህ ዓይነቱን መንፈሳዊ እውነት መረዳት ልዩ መብት ነው፤ ማንኛውም ሰው የሚያገኘው ነገር አይደለም። ኢየሱስ ስለዚህ ጉዳይ ምን እንደተናገረ እስቲ እንመልከት።—ማቴዎስ 11:25ን አንብብ።

ማቴዎስ 11:25 ላይ የሚገኘው ጥቅስ የሚጀምረው “በዚያን ጊዜ ኢየሱስ እንዲህ አለ” በማለት ነው። በመሆኑም ኢየሱስ በዚህ ጥቅስ ላይ ያለውን ሐሳብ እንዲናገር ያደረገው ከዚህ በፊት የተከናወነ ነገር መኖር አለበት። ኢየሱስ ይህን ከመናገሩ በፊት በገሊላ በሚገኙ ሦስት ከተሞች ውስጥ የሚኖሩ ሰዎችን አውግዞ ነበር፤ በእነዚህ ከተሞች ውስጥ ያሉ ነዋሪዎች ኢየሱስ የፈጸማቸውን ተአምራት ቢመለከቱም እሱን ለመቀበል ፈቃደኞች አልነበሩም። (ማቴዎስ 11:20-24) ‘አንድ ሰው፣ ኢየሱስ የፈጸማቸውን ተአምራት እየተመለከተ የእሱን ትምህርቶች ለመቀበልና እሱን ለመከተል ፈቃደኛ ሊሆን የማይችለው እንዴት ነው?’ ብለህ ታስብ ይሆናል። በወቅቱ የነበሩት ሰዎች እምቢተኛ የሆኑት ደንዳና ልብ ስለነበራቸው ነው።—ማቴዎስ 13:10-15

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘውን ስለ አምላክ የሚገልጸውን እውነት ለመረዳት ሁለት ነገሮች ይኸውም የአምላክ እርዳታና ትክክለኛ የልብ ዝንባሌ እንደሚያስፈልግ ኢየሱስ ያውቅ ነበር። ኢየሱስ ስለዚህ ጉዳይ ሲናገር እንዲህ አለ፦ “የሰማይና የምድር ጌታ አባት ሆይ፣ እነዚህን ነገሮች ከጥበበኞችና ከአዋቂዎች ሰውረህ ለሕፃናት ስለገለጥክላቸው በሕዝብ ፊት አወድስሃለሁ።” በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙ መንፈሳዊ እውነቶችን መረዳት ልዩ መብት ነው የተባለው ለምን እንደሆነ አስተዋልክ? ይሖዋ “የሰማይና የምድር ጌታ” እንደመሆኑ መጠን ግለሰቦች ይህን እውነት መረዳት የሚችሉት እሱ ከፈቀደ ነው። ይሁንና አምላክ በዚህ ረገድ አያዳላም። ታዲያ አምላክ፣ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት የመረዳትን ልዩ መብት ለእነማን እንደሚሰጥ የሚወስነው እንዴት ነው?

አምላክ ትሑት የሆኑ ሰዎችን የሚወድ ሲሆን ትዕቢተኞችን ይጠላል። (ያዕቆብ 4:6) በዓለም ‘ጥበበኞችና አዋቂዎች’ የሚባሉት የተማሩ ሰዎች በአብዛኛው ኩራተኛ ከመሆናቸውም ሌላ በራሳቸው ጥበብ የሚተማመኑና የአምላክ እርዳታ እንደማያስፈልጋቸው የሚሰማቸው በመሆናቸው አምላክ እውነቱን አይገልጥላቸውም። (1 ቆሮንቶስ 1:19-21) ይሁን እንጂ “ሕፃናት” ለሆኑ በሌላ አባባል እንደ ትንሽ ልጅ ራሳቸውን ዝቅ አድርገው ወደ እሱ ለሚቀርቡ ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች እውነቱን ይገልጥላቸዋል። (ማቴዎስ 18:1-4፤ 1 ቆሮንቶስ 1:26-28) የአምላክ ልጅ የሆነው ኢየሱስ ትሑትም ሆነ ትዕቢተኛ የሆኑ ሰዎችን ያውቅ ነበር። ኩራተኛ የነበሩት የሃይማኖት መሪዎች በጣም የተማሩ ቢሆኑም ኢየሱስ ያስተማረውን መልእክት ማስተዋል አልቻሉም፤ ትሑት የሆኑ ዓሣ አጥማጆች ግን ይህን ማድረግ ችለዋል። (ማቴዎስ 4:18-22፤ 23:1-5፤ የሐዋርያት ሥራ 4:13) በሌላ በኩል ደግሞ እውነተኛ ትሕትና ያሳዩ አንዳንድ ሀብታምና የተማሩ ሰዎች የኢየሱስ ተከታዮች ሆነዋል።—ሉቃስ 19:1, 2, 8፤ የሐዋርያት ሥራ 22:1-3

በዚህ ርዕስ መግቢያ ላይ ወዳነሳነው ጥያቄ እንመለስ፤ ስለ አምላክ እውነቱን ማወቅ ትፈልጋለህ? ከሆነ በዓለማዊ ጥበብ ራሳቸውን ጥበበኛ አድርገው የሚቆጥሩ ሰዎችን አምላክ እንደማይቀበል ማወቅህ ያጽናናህ ይሆናል። ከዚህ በተለየ መልኩ አምላክ፣ በዓለም ጠቢባን የሚባሉ ሰዎች የሚንቋቸውን ግለሰቦች ከፍ አድርጎ ይመለከታቸዋል። ትሑት ልብ ኖሮህ የአምላክን ቃል የምታጠና ከሆነ አምላክ ውድ ስጦታ ከሚሰጣቸው ይኸውም ስለ እሱ እውነቱን እንዲያስተውሉ ከሚፈቅድላቸው ሰዎች አንዱ መሆን ትችላለህ። ይህንን እውነት ማወቅህ በአሁኑ ጊዜ ትርጉም ያለው ሕይወት ለመምራት ወደፊት ደግሞ “እውነተኛ የሆነውን ሕይወት” ይኸውም አምላክ ቃል በገባው መሠረት ጽድቅ በሚሰፍንበት አዲስ ዓለም ውስጥ ማለቂያ የሌለው ሕይወት ለማግኘት ያስችልሃል። *1 ጢሞቴዎስ 6:12, 19፤ 2 ጴጥሮስ 3:13

በጥር ወር የሚነበብ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል

ማቴዎስ 1-21

^ စာပိုဒ်၊ 7 የይሖዋ ምሥክሮች ስለ አምላክ እና ስለ ዓላማዎቹ እውነቱን ሊያስተምሩህ ፈቃደኞች ናቸው። ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተባለውን መጽሐፍ በመጠቀም ሰዎችን በነፃ መጽሐፍ ቅዱስን ያስተምራሉ።