በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የመሳፍንት መጽሐፍ ጎላ ያሉ ነጥቦች

የመሳፍንት መጽሐፍ ጎላ ያሉ ነጥቦች

የይሖዋ ቃል ሕያው ነው

የመሳፍንት መጽሐፍ ጎላ ያሉ ነጥቦች

ይሖዋ የገዛ ሕዝቦቹ ጀርባቸውን ሲሰጡትና የሐሰት አማልክትን ሲያመልኩ ምን ይሰማዋል? በተደጋጋሚ ጊዜያት ትእዛዙን ቢጥሱና በተጨነቁበት ወቅት ብቻ እንዲረዳቸው ቢጠይቁትስ? ይሖዋ በዚህ ጊዜም ቢሆን ከችግራቸው ማምለጫ መንገድ ያዘጋጅላቸዋል? የመሳፍንት መጽሐፍ ለእነዚህና ለሌሎች አንገብጋቢ ጥያቄዎች መልስ ይሰጣል። ይህ መጽሐፍ ከክርስቶስ ልደት በፊት በ1100 በነቢዩ ሳሙኤል ተጽፎ ያለቀ ሲሆን ኢያሱ ከሞተበት ጊዜ አንስቶ የመጀመሪያው የእስራኤል ንጉሥ ሥልጣን እስከያዘበት ጊዜ ድረስ ያሉትን የ330 ዓመታት ገደማ ታሪክ ይዟል።

የመሳፍንት መጽሐፍ ኃይለኛ ቃላት ወይም መልእክቶች የያዘው የአምላክ ቃል ክፍል እንደመሆኑ መጠን ለእኛም ትልቅ ጠቀሜታ አለው። (ዕብራውያን 4:12) በመጽሐፉ ውስጥ የሰፈሩት ስሜት ቀስቃሽ ዘገባዎች ስለ አምላክ ማንነት ጥልቅ ማስተዋል ይሰጡናል። ከዘገባዎቹ የምናገኘው ትምህርት እምነታችንን የሚያጠነክርልን ከመሆኑም በላይ “እውነተኛ የሆነውን ሕይወት” ማለትም አምላክ ቃል በገባልን አዲስ ዓለም ውስጥ የምናገኘውን የዘላለም ሕይወት አጥብቀን እንድንይዝ ይረዳናል። (1 ጢሞቴዎስ 6:12, 19፤ 2 ጴጥሮስ 3:13) ይሖዋ ሕዝቡን ለማዳን የፈጸማቸው ድርጊቶች በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት ወደፊት ለሚያከናውነው ታላቅ ነፃ የማውጣት ተግባር መቅድም ናቸው።

መሳፍንት ያስፈለጉት ለምን ነበር?

(መሳፍንት 1:1 እስከ 3:6)

የእስራኤል ነገዶች በኢያሱ መሪነት በከነዓን ምድር የነበሩትን ነገሥታት ድል ከመቱ በኋላ ርስታቸውን ተከፋፍለው በመያዝ ምድሪቱን ወረሱ። ነገር ግን እስራኤላውያን የምድሪቱን ነዋሪዎች አላባረሩም። ይህን አለማድረጋቸው ከባድ ወጥመድ ሆነባቸው።

ኢያሱ ከሞተ በኋላ “እግዚአብሔርንም ሆነ እርሱ ለእስራኤል ሕዝብ ያደረገውን ነገር የማያውቅ ሌላ ትውልድ ተነሣ።” (መሳፍንት 2:10) ከዚህም በላይ ሕዝቡ ከከነዓናውያን ጋር የጋብቻ ቃል ኪዳን አደረገ፤ እንዲሁም አማልክቶቻቸውን አመለከ። ስለዚህ ይሖዋ እስራኤላውያንን ለጠላቶቻቸው አሳልፎ ሰጣቸው። እስራኤላውያን የጭቆናው ቀንበር በከበዳቸው ጊዜ ግን እውነተኛው አምላክ እንዲረዳቸው ለመኑት። በዚህ ሃይማኖታዊ፣ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ሁኔታ ውስጥ ይሖዋ ሕዝቡን ከጠላቶቻቸው ለመታደግ ተራ በተራ መሳፍንትን እንዳስነሳ ተዘግቧል።

ቅዱስ ጽሑፋዊ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው:-

1:2, 4—ይሁዳ የተመደበለትን ርስት ከሌሎቹ ነገዶች ቀድሞ እንዲወስድ የተደረገው ለምንድን ነው? በልማዱ መሠረት ይህ መብት መጀመሪያ መሰጠት የነበረበት ለያዕቆብ የበኩር ልጅ ለሮቤል ነው። ነገር ግን ያዕቆብ በሞት አፋፍ ላይ በነበረበት ጊዜ ሮቤል የብኩርና መብቱን በማጣቱ ምክንያት እልቅና እንደማይኖረው ተንብዮ ነበር። ስምዖንና ሌዊ ደግሞ በጭካኔ ተግባራቸው ምክንያት በእስራኤል ተበታትነው ይኖራሉ። (ዘፍጥረት 49:3-5, 7) ስለዚህ ይህን መብት ማግኘት የሚችለው የያዕቆብ አራተኛ ልጅ ይሁዳ ነበር። የስምዖን ነገድ ከይሁዳ ጋር በመሄድ ሰፊ በሆነው የይሁዳ ርስት ውስጥ ተበታትነው የሚገኙ ስፋት የሌላቸው ጥቂት ቦታዎችን ወረሰ። aኢያሱ 19:9

1:6, 7—ድል የተመቱ ነገሥታት የእጃቸውና የእግራቸው አውራ ጣቶች የሚቆረጡባቸው ለምን ነበር? የእጆቹና የእግሮቹ አውራ ጣቶች የተቆረጡበት ሰው መዋጋት አይችልም። የእጁን አውራ ጣት ያጣ ሰው እንዴት ሰይፍና ጦር መያዝ ይችላል? የእግር አውራ ጣት የሌለው ሰው ደግሞ ሚዛኑን በአግባቡ መጠበቅ አይችልም።

ምን ትምህርት እናገኛለን?

2:10-12:- የይሖዋን ‘ውለታ እንዳንረሳ’ መጽሐፍ ቅዱስን የምናጠናበት ቋሚ ፕሮግራም ሊኖረን ይገባል። (መዝሙር 103:2) ወላጆች በልጆቻቸው ልብ ውስጥ የአምላክን ቃል እውነት መትከል ይገባቸዋል።—ዘዳግም 6:6-9

2:14, 21, 22:- ይሖዋ ታዛዥ ያልሆኑትን ሕዝቦቹን ለመቅጣት፣ ለማጥራትና ወደ እርሱ እንዲመለሱ ለማድረግ ሲል ክፉ ነገር እንዲደርስባቸው በዓላማ ይፈቅዳል።

ይሖዋ መሳፍንት አስነሳ

(መሳፍንት 3:7 እስከ 16:31)

ስለ መሳፍንት ጀብዱ የሚገልጸው አስደሳች ዘገባ፣ ጎቶንያል ለስምንት ዓመት እስራኤላውያንን በቁጥጥሩ ሥር አድርጎ የነበረውን የመስጴጦምያን ንጉሥ ድል እንዳደረገ በመግለጽ ይጀምራል። መስፍኑ ናዖድ ድፍረት የተሞላበት ዘዴ በመቀየስ ወፍራም የነበረውን የሞዓብ ንጉሥ ዔግሎንን ገደለ። ጀግናው ሰሜጋር ያለማንም እርዳታ 600 ፍልስጥኤማውያንን በበሬ መንጃ ገደለ። ነቢዪት በነበረችው ዲቦራ አበረታችነት እንዲሁም በይሖዋ ድጋፍ፣ ባርቅና የተሟላ ትጥቅ ያልነበራቸው አሥር ሺህ ወታደሮችን የያዘው ሠራዊቱ ኃያል የነበረውን የሲሣራን ሠራዊት ብትንትኑ እስኪወጣ ድረስ ድል አደረጉት። ይሖዋ ጌዴዎንን በማስነሳት ከ300 ወታደሮቹ ጋር ሆኖ ምድያማውያንን ድል እንዲያደርግ አስቻለው።

ይሖዋ በዮፍታሔ ተጠቅሞ እስራኤላውያንን ከአሞናውያን አገዛዝ ነፃ አወጣቸው። በእስራኤል ከተነሱት 12 መሳፍንት ውስጥ ቶላ፣ ኢያዕር፣ ኢብጻን፣ ኤሎምና ዓብዶን ይገኙበታል። ፍልስጥኤማውያንን ይዋጋ ከነበረው ከሳምሶን በኋላ የመሳፍንት ዘመን አበቃ።

ቅዱስ ጽሑፋዊ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው:-

4:8—ባርቅ ነቢዪቱ ዲቦራ አብራው ወደ ጦር ሜዳ እንድትሄድ አጥብቆ የጠየቃት ለምንድን ነው? ባርቅ ብቻውን ሆኖ የሲሣራን ሠራዊት ድል ለማድረግ እንደማይችል ሳይሰማው አልቀረም። ነቢዪቱ አብራው መሄዷ እርሱና ወታደሮቹ አምላክ እየመራቸው እንዳለ በእርግጠኝነት እንዲተማመኑና ልበ ሙሉ እንዲሆኑ ያስችላቸዋል። ስለዚህ ባርቅ ዲቦራ አብራው እንድትሄድ አጥብቆ መጠየቁ የደካማነት ምልክት ሳይሆን ጠንካራ እምነት እንደነበረው የሚያሳይ ነው።

5:20—ከዋክብት ከሰማይ ሆነው ለባርቅ የተዋጉለት እንዴት ነው? መጽሐፍ ቅዱስ ይህ ሁኔታ ባርቅ መላእክታዊ ድጋፍ እንዳገኘ ወይም የሲሣራ ጠቢባን እንዳሰቡት መጥፎ ገድን የሚያመለክት የተወርዋሪ አካላት ናዳ እንደነበረ አሊያም ሲሣራ የታመነባቸው የኮከብ ቆጠራ ትንበያዎች ከንቱ ሆነው እንደቀሩ እንደሚያመለክት በግልጽ አይነግረንም። ይሁን እንጂ አምላክ በሆነ መንገድ ጣልቃ ገብቶ እንደነበረ ምንም ጥርጥር የለውም።

7:1-3፤ 8:10—ይሖዋ ጌዴዎን የሚመራቸው 32,000 ሰዎች 135,000 ወታደሮችን ላቀፈው የጠላት ሠራዊት እንደሚበዙ የተናገረው ለምንድን ነው? ይህ የሆነበት ምክንያት ለጌዴዎንና ለሠራዊቱ ድል የሚሰጣቸው ይሖዋ በመሆኑ ነው። አምላክ ተዋጊዎቹ ምድያማውያንን ድል የመቱት በራሳቸው ኃይል እንደሆነ እንዲሰማቸው አልፈለገም ነበር።

11:30, 31—ዮፍታሔ በተሳለበት ወቅት የሰው መሥዋዕት የማቅረብ ሐሳብ ነበረው? ሕጉ ‘በመካከላቸው ወንድ ወይም ሴት ልጁን በእሳት የሚሠዋ ሰው እንዳይገኝ’ ስለሚያዝ ዮፍታሔ እንዲህ ያለ ሐሳብ ፈጽሞ አልነበረውም። (ዘዳግም 18:10) የሆነ ሆኖ ዮፍታሔ ለማቅረብ ያሰበው የሰው እንጂ የእንስሳ መሥዋዕት አይደለም። እስራኤላውያን መሥዋዕት ሆነው ለመቅረብ ተስማሚ የሆኑ እንስሳትን ቤት ውስጥ የማስቀመጥ ልማድ አልነበራቸውም። ደግሞም የእንስሳ መሥዋዕት ማቅረብ ያን ያህል ስእለት የሚያስፈልገው ልዩ ስጦታ አይደለም። ዮፍታሔ ልጁ ከቤት ወጥታ ልትቀበለው እንደምትችል ያውቅ ነበር። ቀድሞ የሚወጣው ሰው “የሚቃጠል መሥዋዕት” ይሆናል የሚለው አነጋገር በቤተ መቅደሱ ውስጥ ሙሉ ለሙሉ ለይሖዋ አገልግሎት ተወስኖ እንደሚኖር የሚያመለክት ነው።

ምን ትምህርት እናገኛለን?

3:10:- መንፈሳዊ ነገሮችን በመከታተል የሚገኘው ስኬት የተመካው በሰው ጥበብ ሳይሆን በይሖዋ መንፈስ እርዳታ ነው።—መዝሙር 127:1

3:21:- ናዖድ በሰይፍ የመጠቀም ጥሩ ችሎታና ድፍረት ነበረው። እኛም ‘የመንፈስ ሰይፍ’ የተባለውን “የእግዚአብሔር ቃል” በመጠቀም ረገድ ችሎታችንን ማዳበር ይገባናል። ይህም ስናገለግል ቅዱሳን ጽሑፎችን በድፍረት መጠቀም ይኖርብናል ማለት ነው።—ኤፌሶን 6:17፤ 2 ጢሞቴዎስ 2:15

6:11-15፤ 8:1-3, 22, 23:- ጌዴዎን ያሳየው ትሕትና ሦስት አስፈላጊ ነገሮችን ያስተምረናል:- (1) አንድ ዓይነት የአገልግሎት መብት ሲሰጠን የሚያስከትለውን ኃላፊነት ማስተዋል ይገባናል እንጂ ስለሚያስገኝልን ታዋቂነት ወይም ክብር ማሰብ የለብንም። (2) የጠበኝነት ዝንባሌ ካላቸው ሰዎች ጋር ስንነጋገር ትሕትና ማሳየት የጥበብ መንገድ ነው። (3) ትሕትና የሥልጣን ጥመኛ ከመሆን ይጠብቀናል።

6:17-22, 36-40:- እኛም ጥንቁቅ መሆን አለብን፤ እንዲሁም ‘መንፈስን ሁሉ ማመን’ አይገባንም። ከዚህ ይልቅ ‘መናፍስት ከእግዚአብሔር መሆናቸውን መመርመር’ ያስፈልገናል። (1 ዮሐንስ 4:1) አንድ አዲስ ክርስቲያን ሽማግሌ ሊሰጥ ያሰበው ምክር በአምላክ ቃል ላይ በጥብቅ የተመሠረተ መሆኑን ለማረጋገጥ ይበልጥ ልምድ ያካበተ ሽማግሌ ማማከሩ ጥበብ ነው።

6:25-27:- ጌዴዎን ሳያስፈልግ ተቃዋሚዎቹን ላለማስቆጣት ጥንቃቄ አድርጓል። እኛም ምሥራቹን በምንሰብክበት ጊዜ ሌሎችን በአነጋገራችን እንዳናስቀይም መጠንቀቅ ይገባናል።

7:6:- ይሖዋን በምናገለግልበት ጊዜ እንደ 300ዎቹ የጌዴዎን ወታደሮች ንቁና ጠንቃቃ መሆን አለብን።

9:8-15:- እብሪተኝነት እንዲሁም ለክብርና ለሥልጣን መቋመጥ ትልቅ ሞኝነት ነው!

11:35-37:- የዮፍታሔ መልካም ምሳሌነት ሴት ልጁ ጠንካራ እምነትና የራስን ጥቅም የመሠዋት መንፈስ እንድታዳብር በጣም እንደረዳት ምንም ጥርጥር የለውም። በዛሬውም ጊዜ ወላጆች ለልጆቻቸው ጥሩ ምሳሌ መሆን ይችላሉ።

11:40:- በይሖዋ አገልግሎት በፈቃደኝነት መንፈስ የሚካፈልን ሰው ማመስገን እንዲበረታታ ያደርገዋል።

13:8:- ወላጆች ልጆቻቸውን በሚያስተምሩበት ጊዜ የይሖዋን መመሪያ ለማግኘትና ሥርዓቱን ለመከተል ወደ እርሱ መጸለይ ይገባቸዋል።—2 ጢሞቴዎስ 3:16

14:16, 17፤ 16:16:- በማልቀስና በመነዝነዝ አንድን ሰው ማስጨነቅ መልካም ግንኙነት እንዲበላሽ ሊያደርግ ይችላል።—ምሳሌ 19:13፤ 21:19

በእስራኤል የተፈጸሙ ሌሎች በደሎች

(መሳፍንት 17:1 እስከ 21:25)

የመሳፍንት መጽሐፍ የመጨረሻ ክፍል ሁለት ለየት ያሉ ዘገባዎችን ይዟል። የመጀመሪያው ዘገባ በቤቱ ውስጥ ጣዖት ስላቆመና ካህን ሆኖ እንዲያገለግለው ሌዋዊ ስለቀጠረ ሚካ የተባለ ሰው ይተርካል። የዳን ዘሮች ላይሽ ወይም ሌሼም የተባለችውን ከተማ ካጠፉ በኋላ እንደገና የራሳቸውን ከተማ ገንብተው ዳን ብለው ሰየሟት። ሚካ የሠራውን ጣዖትና የቀጠረውን ካህን በመጠቀም ዳን ውስጥ ሌላ ዓይነት አምልኮ አቋቋሙ። ከሁኔታው መረዳት እንደሚቻለው ላይሽ ድል የተደረገችው ኢያሱ ከመሞቱ በፊት ነበር።—ኢያሱ 19:47

ሁለተኛው ክንውን የተፈጸመው ኢያሱ ከሞተ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ነበር። በጊብዓ ጥቂት ብንያማውያን ወንዶች በቡድን ሆነው በፈጸሙት የጾታ ብልግና ወንጀል ምክንያት የብንያም ነገድ ሙሉ ለሙሉ ሊጠፋ ተቃርቦ ነበር፤ የተረፉት 600 የሚያህሉ ወንዶች ብቻ ነበሩ። ሆኖም አንድ ጠቃሚ ዝግጅት ተደርጎላቸው ሚስቶች ያገኙ ሲሆን በዳዊት የግዛት ዘመን ቁጥራቸው አድጎ ወደ 60,000 የሚጠጉ ተዋጊዎች ሊገኙ ችለዋል።—1 ዜና መዋዕል 7:6-11

ቅዱስ ጽሑፋዊ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው:-

17:6፤ 21:25—‘እያንዳንዱ ሰው ለራሱ መልካም መስሎ የታየውን ማድረጉ’ ሥርዓት አልበኝነት እንዲነግሥ አላደረገም? ይሖዋ ሕዝቡን ለመምራት በቂ ዝግጅት አድርጎ ስለነበር እንደዚያ ማለት አይቻልም። መንገዱን መማር እንዲችሉ ሕግ ሰጥቷቸውና የካህናት ሥርዓት አቋቁሞላቸው ነበር። ሊቀ ካህናቱ በኡሪምና በቱሚም አማካኝነት አስፈላጊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ የአምላክን መመሪያ መጠየቅ ይችል ነበር። (ዘፀአት 28:30) በእያንዳንዱ ከተማ ደግሞ አስተማማኝ ምክር ሊሰጡ የሚችሉ ሽማግሌዎች ነበሩ። አንድ እስራኤላዊ በእነዚህ ዝግጅቶች በአግባቡ ከተጠቀመ ሕሊናውን ለማሠልጠን የሚረዳ ጥሩ መመሪያ ያገኛል። በእነዚህ ዝግጅቶች ተጠቅሞ “እያንዳንዱ ሰው ለራሱ መልካም መስሎ የታየውን” የሚያደርግ ከሆነ ጥሩ ውጤት ያገኛል። በሌላ በኩል ደግሞ አንድ ሰው ሕጉን ችላ ብሎ አኗኗርንና አምልኮን በተመለከተ የራሱን ውሳኔ ቢያደርግ ውጤቱ አስከፊ ይሆናል።

20:17-48—መቀጣት የነበረባቸው እነርሱ ሆነው ሳለ ይሖዋ ብንያማውያን ሌሎቹን ነገዶች ሁለት ጊዜ ድል እንዲያደርጓቸው የፈቀደው ለምንድን ነው? ይሖዋ ታማኞቹ ነገዶች ክፉ የሆነውን ነገር ከእስራኤል ለማጥፋት ያላቸውን ቁርጠኝነት ለመፈተን ሲል መጀመሪያ ላይ ከአንዴም ሁለቴ ትልቅ ሽንፈት እንዲደርስባቸው ፈቅዷል።

ምን ትምህርት እናገኛለን?

19:14, 15:- የጊብዓ ነዋሪዎች እንግዳ ተቀባይ አለመሆናቸው ግብረ ገብነት እንደሚጎድላቸው የሚያሳይ ነበር። ክርስቲያኖች “እንግዶችን ተቀበሉ” ተብለው ተመክረዋል።—ሮሜ 12:13

በቅርቡ ነፃ እንወጣለን

በቅርቡ የአምላክ መንግሥት በክርስቶስ ኢየሱስ አማካኝነት ክፉውን ዓለም በማጥፋት ቅኖችንና ነቀፋ የሌለባቸውን ሰዎች ነፃ ያወጣቸዋል። (ምሳሌ 2:21, 22፤ ዳንኤል 2:44) በዚያን ጊዜ ‘የእግዚአብሔር ጠላቶች ሁሉ ይጠፋሉ፤ እርሱን የሚወዱ ግን የንጋት ፀሐይ በኀይል እንደሚወጣ እንዲያ ይሆናሉ።’ (መሳፍንት 5:31) ከመሳፍንት መጽሐፍ ያገኘነውን ትምህርት በሥራ በማዋል ይሖዋን ከሚወዱት መካከል መሆናችንን እናረጋግጥ።

የመሳፍንት መጽሐፍ በያዘው ዘገባ ላይ በተደጋጋሚ የጎላው መሠረታዊ እውነት እንደሚያሳየው ይሖዋን መታዘዝ የተትረፈረፈ በረከት ያስገኛል፤ አለመታዘዝ ደግሞ አደገኛ መዘዝ ያስከትላል። (ዘዳግም 11:26-28) ለአምላክ ፈቃድ ‘በሙሉ ልብ መታዘዝ’ እንዴት አስፈላጊ ነው!—ሮሜ 6:17፤ 1 ዮሐንስ 2:17

[የግርጌ ማስታወሻ]

a ሌዋውያን በተስፋይቱ ምድር ውስጥ ርስት ባይሰጣቸውም በመላው እስራኤል ተበታትነው የሚገኙ 48 ከተሞች ተሰጥተዋቸው ነበር።

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ካርታ]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

“እግዚአብሔርም ከእነዚህ ወራሪዎች የሚያድኗቸውን መሳፍንት አስነሣ።”—መሳፍንት 2:16

መሳፍንት

1. ጎቶንያል (የምናሴ ነገድ)

2. ናዖድ (የይሁዳ ነገድ)

3. ሰሜጋር (የይሁዳ ነገድ)

4. ባርቅ (የንፍታሌም ነገድ)

5. ጌዴዎን (የይሳኮር ነገድ)

6. ቶላ (የምናሴ ነገድ)

7. ኢያዕር (የምናሴ ነገድ)

8. ዮፍታሔ (የጋድ ነገድ)

9. ኢብጻን የአሴር ነገድ

10. ኤሎም የዛብሎን ነገድ

11. ዓብዶን (የኤፍሬም ነገድ)

12. ሳምሶን (የይሁዳ ነገድ)

ዳን

ምናሴ

ንፍታሌም

አሴር

ዛብሎን

ይሳኮር

ምናሴ

ጋድ

ኤፍሬም

ዳን

ብንያም

ሮቤል

ይሁዳ

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ባርቅ ዲቦራን ወደ ጦር ሜዳ አብራው እንድትሄድ አጥብቆ እንደጠየቃት ከሚናገረው ዘገባ ምን ትምህርት አግኝተሃል?