በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

እርጅና “የክብር ዘውድ” ሲሆን

እርጅና “የክብር ዘውድ” ሲሆን

“ረዳቴ . . . ይሖዋ ነው።”

እርጅና “የክብር ዘውድ” ሲሆን

 “ከዚህ የተሻለ ሕይወት የለም።” እንዲህ ያሉት የ103 ዓመት አረጋዊቷ ሙርኤል ነበሩ። ቴኦዶሮስ የተባሉ የ70 ዓመት አረጋዊ ደግሞ “በእርግጥም ልዩ መብት ነው!” ይላሉ። የ73 ዓመቷ ማሪያም “በሕይወቴ ከሁሉ የተሻለውን ነገር እንዳደረግሁ ይሰማኛል” ብለዋል። ሦስቱም አብዛኛውን ሕይወታቸውን በይሖዋ አምላክ አገልግሎት ያሳለፉ ክርስቲያኖች ናቸው።

በዓለም ዙሪያ ባሉት ቀናተኛ የይሖዋ አምላኪዎች መካከል እንደነዚህ ያሉ አረጋውያን በብዛት ይገኛሉ። የዕድሜ መግፋት፣ የጤና እክሎችና ሌሎች አስቸጋሪ ሁኔታዎች ቢኖሩባቸውም አምላክን በሙሉ ነፍሳቸው ማገልገላቸውን አላቋረጡም። እንደነዚህ ያሉት ታማኝ አረጋውያን ለአምላክ ያደሩ በመሆናቸው በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ግሩም ምሳሌ ይሆናሉ። ምንም እንኳ ባሉባቸው የአቅም ገደቦች የተነሳ ሊያከናውኑ የሚችሉት ነገር ውስን ቢሆንም ይሖዋ አገልግሎታቸውን በአድናቆት ይመለከተዋል። a2 ቆሮንቶስ 8:12

የመዝሙር መጽሐፍ አረጋውያን የሆኑ ታማኝ የአምላክ አገልጋዮች በስተርጅናቸው የሚኖራቸውን ሕይወት ግሩም አድርጎ ይገልጸዋል። ረጅም ዕድሜ ቢኖርም ፍሬ ማፍራቱን በማያቋርጥ ግርማ ሞገስ ባለው ዛፍ ይመስላቸዋል። መዝሙራዊው ታማኝ አረጋውያንን በሚመለከት “ባረጁ ጊዜ እንኳ ያፈራሉ፤ እንደ ለመለሙና እንደ ጠነከሩም ይኖራሉ” በማለት ዘምሯል።—መዝሙር 92:14

አንዳንዶች በእርጅና ምክንያት አቅማቸው እየደከመ ሲሄድ ተፈላጊነታቸው እንደሚቀንስ ወይም ችላ እንደሚባሉ ሊሰማቸው ይችላል። ዳዊት “በእርጅናዬ ዘመን አትጣለኝ፤ ጒልበቴም ባለቀበት ጊዜ አትተወኝ” በማለት አምላክን ተማጽኖ ነበር። (መዝሙር 71:9) አንድ ሰው በስተርጅናው ጉልበቱ እየደከመ በመሄድ ፋንታ እንዲለመልም የሚረዳው ምንድን ነው? አምላካዊ ባሕርይ የሆነውን ጽድቅን መከተሉ ነው። መዝሙራዊው “ጻድቃን እንደ ዘንባባ ይንሰራፋሉ” በማለት ዘምሯል።—መዝሙር 92:12

ይሖዋን ለረጅም ዓመታት በታማኝነት ያገለገሉ ክርስቲያኖች በስተርጅናቸውም ፍሬ ማፍራታቸውን እንደሚቀጥሉ የታወቀ ነው። አንድ ዘር ተዘርቶ ካደገ በኋላ ብዙ ፍሬ እንደሚሰጥ ሁሉ እነዚህ አረጋውያንም በሕይወታቸው ውስጥ ራሳቸውንም ሆነ ሌሎችን ለመርዳት ካከናወኗቸው ነገሮች ውስጥ አብዛኞቹ ለመልካም ፍሬ በቅተዋል። (ገላትያ 6:7-10፤ ቆላስይስ 1:10) የአምላክን መንገዶች ችላ ብለው የራሳቸውን ጥቅም በማሳደድ ሕይወታቸውን ያባከኑ ሰዎች ግን ዕድሜያቸው እየገፋ ሲሄድ ያን ያህል አከናወንኩት የሚሉት ነገር አይኖራቸውም።

የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሆነው የምሳሌ መጽሐፍም የጽድቅ መንገድ መከተል በስተርጅና እንደሚያስከብር ጎላ አድርጎ ይገልጻል። “ሽበት የክብር ዘውድ ነው፤ የሚገኘውም በጽድቅ ሕይወት ነው” ይላል። (ምሳሌ 16:31) አዎን ጽድቅ የውስጣዊ ውበት መገለጫ ነው። የጽድቅ ጎዳና እየተከተሉ ረጅም ዕድሜ መኖር አክብሮት ያስገኛል። (ዘሌዋውያን 19:32) በእርጅና የሚመጣ ሽበት ከጥበብና ከጨዋነት ጋር ተዳምሮ በሌሎች ዘንድ ያስከብራል።—ኢዮብ 12:12

ይሖዋ በጽድቅ ጎዳና በመመላለስ ሕይወታቸውን በእርሱ አገልግሎት ያሳለፉ ሰዎችን ሲመለከት ይደሰታል። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል:- “እስከ ሽምግልናችሁ፣ እስከ ሽበትም፣ የምሸከማችሁ እኔ ነኝ፤ እኔው ነኝ። ሠርቻችኋለሁ፤ እሸከማችኋለሁ፤ እደግፋችኋለሁ፤ አድናችኋለሁ።” (ኢሳይያስ 46:4) በሰማይ ያለው አፍቃሪው አባታችን ታማኝ አገልጋዮቹን በስተርጅናቸው ሊደግፋቸውና የሚያስፈልጋቸውን ሊያሟላላቸው ቃል እንደገባ ማወቁ ምንኛ የሚያጽናና ነው!—መዝሙር 48:14

ይሖዋ ሕይወታቸውን በእርሱ አገልግሎት ያሳለፉትን ታማኝ አገልጋዮቹን በአድናቆት የሚመለከታቸው ከሆነ ሌሎችስ በአክብሮት ሊይዟቸው አይገባም? እኛም የአምላክን አስተሳሰብ በመኮረጅ አረጋዊ የሆኑ የእምነት ባልንጀሮቻችንን በአድናቆት ልንመለከታቸው ይገባል። (1 ጢሞቴዎስ 5:1, 2) እንግዲያው የሚያስፈልጓቸውን ነገሮች በማሟላት ክርስቲያናዊ ፍቅራችንን ማሳየት የምንችልባቸውን አጋጣሚዎች በንቃት እንከታተል።

ዕድሜያቸው ቢገፋም በጽድቅ ጎዳና መጓዝ የጀመሩ አረጋውያን

ሰሎሞን “በጽድቅ መንገድ ላይ ሕይወት አለ” በማለት ማረጋገጫ ሰጥቶናል። (ምሳሌ 12:28) አንድ ሰው ዕድሜው መግፋቱ በጽድቅ ጎዳና መመላለስ ከመጀመር አያግደውም። ለምሳሌ በሞልዶቫ አንድ የ99 ዓመት አረጋዊ ሰው የወጣትነት ሕይወታቸውን ያሳለፉት የኮሚኒዝምን አስተሳሰብ በማራመድ ነበር። እንደ ቭላድሚር ኤሊች ሌኒን ካሉ የታወቁ የኮሚኒስት መሪዎች ጋር በግል ተገናኝተው ለማውራት በመቻላቸው በጣም ይኩራሩ ነበር። ይሁን እንጂ የኮሚኒስት አገዛዝ ተንኮታኩቶ ሲወድቅ እኚህ አረጋዊ ሰው ሕይወት ዓላማ የለሽ ሆነባቸው። ሆኖም ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ተገናኝተው ለሰው ልጆች ችግሮች እውነተኛ መፍትሔ የሚያመጣው የአምላክ መንግሥት እንደሆነ ሲነግሯቸው የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ተቀብለው ቅዱሳን ጽሑፎችን በትጋት ማጥናት ጀመሩ። የሚያሳዝነው ግን ተጠምቀው የይሖዋ አገልጋይ ከመሆናቸው በፊት ሞት ቀደማቸው።

በሃንጋሪ የሚኖሩ አንዲት የ81 ዓመት አረጋዊት ስለ አምላክ የጽድቅ መሥፈርቶች ሲማሩ ለብዙ ዓመታት አብረዋቸው ይኖሩ ከነበሩት ሰውዬ ጋር በሕጋዊ መንገድ መጋባት እንደሚኖርባቸው ተገነዘቡ። ከዚያም እንደምንም ራሳቸውን አደፋፈሩና አብረዋቸው ለሚኖሩት ሰው በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተውን አቋማቸውን ነገሯቸው። የሚያስገርመው ሰውየው በሕግ ለመጋባት ተስማሙ። ሴትየዋ ትዳራቸውን ሕጋዊ ካደረጉ በኋላ ፈጣን መንፈሳዊ እድገት አደረጉ። መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት በጀመሩ በስምንት ወራቸው ያልተጠመቁ አስፋፊ የሆኑ ሲሆን ከዚያ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ተጠመቁ። ጽድቅ ለአረጋውያን እውነተኛ ውበት ያጎናጽፋቸዋል መባሉ ምንኛ ትክክል ነው!

አዎን ታማኝ አረጋውያን ክርስቲያኖች ይሖዋ እንደሚያስብላቸው እርግጠኞች መሆን ይችላሉ። ይሖዋ ለእርሱ ታማኝ የሆኑትን ፈጽሞ አይተዋቸውም። ከዚያ ይልቅ በእርጅና ዘመናቸው እንኳን ሊመራቸው፣ ሊደግፋቸውና የሚያስፈልጋቸውን ሊሰጣቸው ቃል ገብቷል። እነርሱም እንደ መዝሙራዊው “ረዳቴ . . . ይሖዋ ነው” የሚሉትን ቃላት ያስተጋባሉ።—መዝሙር 121:2 NW

[የግርጌ ማስታወሻ]

a የ2005 የይሖዋ ምሥክሮች የቀን መቁጠሪያ ጥር/የካቲት የሚለውን ተመልከት።

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

“ሽበት የክብር ዘውድ ነው፤ የሚገኘውም በጽድቅ ሕይወት ነው።”ምሳሌ 16:31

[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ይሖዋ በዕድሜ የገፉ አገልጋዮቹን ይንከባከባቸዋል

“ዕድሜው ለገፋ ተነሥለት፤ ሽማግሌውን አክብር።”—ዘሌዋውያን 19:32

“እስከ ሽምግልናችሁ፣ እስከ ሽበትም፣ የምሸከማችሁ እኔ ነኝ፤ እኔው ነኝ።”—ኢሳይያስ 46:4