በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 20

“ጥበበኛ ልብ አለው”—ግን ትሑት ነው

“ጥበበኛ ልብ አለው”—ግን ትሑት ነው

1-3. ይሖዋ ትሑት ነው ብለን በእርግጠኝነት ልንናገር የምንችለው ለምንድን ነው?

 አንድ አባት ለትንሽ ልጁ በጣም አስፈላጊ የሆነ ትምህርት ማስተማር ፈለገ እንበል። ልጁ ትምህርቱን ከልቡ ሊቀበል የሚችለው አባትየው በምን መንገድ ቢያነጋግረው ነው? ልጁን ቁልቁል እያየ ቢያፈጥበትና ቢጮኽበት ነው ወይስ በርከክ ብሎ በፍቅርና በለሰለሰ አንደበት ቢያነጋግረው? ጥበበኛና ትሑት የሆነ አባት ልጁን በደግነት ማነጋገር እንደሚመርጥ የታወቀ ነው።

2 ይሖዋ ምን ዓይነት አባት ነው? ትዕቢተኛና ኃይለኛ ነው ወይስ ትሑትና ገር? ይሖዋ ሁሉን የሚያውቅ ከመሆኑም በላይ ወደር የለሽ ጥበብ ያለው አምላክ ነው። ይሁን እንጂ እውቀትና ጥበብ በራሱ ሰዎች ትሑት እንዲሆኑ እንደማያደርግ አስተውለህ ይሆናል። መጽሐፍ ቅዱስ “እውቀት ያስታብያል” ሲል ይገልጻል። (1 ቆሮንቶስ 3:19፤ 8:1) ሆኖም “ጥበበኛ ልብ” ያለው ይሖዋ ትሑት ነው። (ኢዮብ 9:4) ይሖዋ ትሑት ነው የሚለው አባባል ቦታውን ወይም ታላቅነቱን ዝቅ የሚያደርግ ሳይሆን ፈጽሞ የትዕቢት ባሕርይ የሌለው መሆኑን የሚያሳይ ነው። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው?

3 ይሖዋ ቅዱስ ነው። ትዕቢት የሚያረክስ በመሆኑ ይሖዋ እንዲህ ዓይነት ባሕርይ ሊኖረው አይችልም። (ማርቆስ 7:20-22) በተጨማሪም ነቢዩ ኤርምያስ ይሖዋን አስመልክቶ ሲናገር “አንተ በእርግጥ ታስታውሳለህ፤ እኔን ለመርዳትም ታጎነብሳለህ” ብሏል። a (ሰቆቃወ ኤርምያስ 3:20) የአጽናፈ ዓለም ሉዓላዊ ጌታ የሆነው ይሖዋ ፍጽምና የጎደለውን ኤርምያስን ለመርዳት ሲል ወደ እሱ ‘ለማጎንበስ’ ወይም ዝቅ ለማለት ፈቃደኛ መሆኑ የሚያስገርም ነው! (መዝሙር 113:7) አዎን፣ ይሖዋ ትሑት ነው። ሆኖም አምላክ ትሑት ነው ሲባል ምን ማለት ነው? ትሕትና ከጥበብ ጋር ምን ዝምድና አለው? ይህስ ለእኛ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

ይሖዋ ትሑት መሆኑን የሚያሳየው እንዴት ነው?

4, 5. (ሀ) ትሕትና ምንድን ነው? በየትኞቹ ባሕርያትስ ይንጸባረቃል? የድክመት ወይም የፍርሃት ምልክት ተደርጎ ሊታይ የማይገባውስ ለምንድን ነው? (ለ) ይሖዋ ከዳዊት ጋር በነበረው ግንኙነት ትሕትናን ያሳየው እንዴት ነው? የይሖዋ ትሕትና ለእኛ ምን ያህል አስፈላጊ ነው?

4 ትሕትና ማለት ራስን ከፍ አድርጎ አለመመልከት እንዲሁም ከእብሪትና ከኩራት መራቅ ማለት ነው። ይህ ባሕርይ የውስጣዊ ማንነት መገለጫ ሲሆን እንደ ገርነት፣ ትዕግሥትና ምክንያታዊነት ባሉት ባሕርያት ይንጸባረቃል። (ገላትያ 5:22, 23) ይሁን እንጂ እነዚህ አምላካዊ ባሕርያት፣ የድክመት ወይም የፍርሃት ምልክት ተደርገው መታየት የለባቸውም። ይሖዋ እነዚህ ባሕርያት ስላሉት የጽድቅ ቁጣ አይቆጣም ወይም አስፈላጊ ሲሆን የማጥፋት ኃይሉን አይጠቀምም ማለት አይደለም። ከዚህ ይልቅ ትሕትናውና ገርነቱ፣ ራሱን ፍጹም በሆነ ሁኔታ መቆጣጠር እንደሚችልና ታላቅ ኃይሉን ምንጊዜም በትክክለኛው መንገድ እንደሚጠቀምበት የሚያሳይ ነው። (ኢሳይያስ 42:14) ይሖዋ ትሑት መሆኑ ጥበበኛ እንደሆነም የሚያሳይ ነው፤ እንዴት? ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ማብራሪያ የሚሰጥ አንድ የማመሣከሪያ ጽሑፍ “ትሕትና . . . ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ ባሕርይ ሲሆን የጥበብ ሁሉ መሠረት ነው” ሲል ገልጿል። እንግዲያው እውነተኛ ጥበብና ትሕትና የማይነጣጠሉ ነገሮች ናቸው። የይሖዋ ትሕትና የሚጠቅመን እንዴት ነው?

ጥበበኛ የሆነ አባት ልጆቹን የሚይዘው በትሕትናና በገርነት ነው

5 ንጉሥ ዳዊት “የመዳን ጋሻህን ትሰጠኛለህ፤ ቀኝ እጅህ ይደግፈኛል፤ ትሕትናህም ታላቅ ያደርገኛል” በማለት ለይሖዋ ዘምሯል። (መዝሙር 18:35) ይሖዋ ይህን ፍጽምና የጎደለው ሰው በየዕለቱ ለመንከባከብና ለመጠበቅ ሲል ራሱን ዝቅ ያደረገ ያህል ነበር። ዳዊት መዳን ማግኘት ብሎም ታላቅ ንጉሥ መሆን የሚችለው ይሖዋ በዚህ መንገድ ራሱን ዝቅ ለማድረግ ፈቃደኛ እስከሆነ ድረስ ብቻ እንደሆነ ተገንዝቧል። በእርግጥም ይሖዋ በትሕትና ራሱን ዝቅ አድርጎ እንደ አንድ አፍቃሪና ገር አባት ባይዘን ኖሮ የመዳን ተስፋ ይኖረን ነበር?

6, 7. (ሀ) በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ይሖዋ ልኩን የሚያውቅ አምላክ እንደሆነ የሚገልጽ ሐሳብ የማናገኘው ለምንድን ነው? (ለ) በገርነትና በጥበብ መካከል ምን ዝምድና አለ? በዚህ ረገድ ግሩም ምሳሌ የሚሆነንስ ማን ነው?

6 በትሕትናና ልክን በማወቅ መካከል ልዩነት እንዳለ ልብ ማለት ያስፈልጋል። ልክን ማወቅ፣ ታማኝ ሰዎች ሊያዳብሩት የሚገባ ግሩም ባሕርይ ነው። እንደ ትሕትና ሁሉ ይህ ባሕርይም ከጥበብ ጋር ዝምድና አለው። ምሳሌ 11:2 “ልካቸውን በሚያውቁ ዘንድ . . . ጥበብ ትገኛለች” በማለት ይገልጻል። ይሁን እንጂ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ይሖዋ ልኩን የሚያውቅ አምላክ እንደሆነ ተደርጎ የተገለጸበት ቦታ አናገኝም። ለምን? ልክን ማወቅ የሚለው አነጋገር በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተሠራበት አቅምንና ገደብን አምኖ መቀበልን ለማመልከት ነው። ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ የራሱን የጽድቅ መሥፈርቶች ለመጠበቅ ሲል በራሱ ላይ ገደብ ያበጃል እንጂ ምንም ዓይነት ገደብ የለበትም። (ማርቆስ 10:27፤ ቲቶ 1:2) ከዚህም በተጨማሪ ልዑል አምላክ እንደመሆኑ መጠን የማንም ተገዢ አይደለም። ስለዚህ ይሖዋ ልኩን የሚያውቅ አምላክ ነው ሊባል አይችልም።

7 ይሁን እንጂ ይሖዋ ትሑትና ገር ነው። አገልጋዮቹም ገርነት ለእውነተኛ ጥበብ ወሳኝ መሆኑን እንዲገነዘቡ ይፈልጋል። መጽሐፍ ቅዱስ ‘ከጥበብ የመነጨ ገርነት’ ስለማሳየት ይናገራል። b (ያዕቆብ 3:13) ይሖዋ በዚህ ረገድ የተወውን ግሩም ምሳሌ እስቲ እንመልከት።

ይሖዋ ለሌሎች ኃላፊነት ይሰጣል እንዲሁም ያዳምጣቸዋል

8-10. (ሀ) ይሖዋ ኃላፊነት ለመስጠትና ሌሎች የሚያቀርቡትን ሐሳብ ለመስማት ፈቃደኛ መሆኑ አስገራሚ የሆነው ለምንድን ነው? (ለ) ሁሉን ቻይ የሆነው ይሖዋ ከመላእክቱ ጋር ባለው ግንኙነት ትሕትናን ያሳየው እንዴት ነው?

8 ይሖዋ ኃላፊነት ለመስጠትና የሌሎችን ሐሳብ ለመስማት ፈቃደኛ መሆኑ ትሕትናውን የሚያሳይ ግሩም ማስረጃ ነው። እርዳታ ወይም ምክር የሚያስፈልገው አምላክ ባለመሆኑ ሌሎችን ለመስማት ፈቃደኛ መሆኑ በጣም የሚያስገርም ነው። (ኢሳይያስ 40:13, 14፤ ሮም 11:34, 35) መጽሐፍ ቅዱስ፣ ይሖዋ በዚህ መንገድ ትሑት መሆኑን ያሳየባቸውን በርካታ አጋጣሚዎች ይጠቅሳል።

9 ለምሳሌ ያህል፣ አብርሃም በአንድ ወቅት ያጋጠመውን አስገራሚ ሁኔታ ተመልከት። ሦስት እንግዶች ወደ ቤቱ መጥተው የነበረ ሲሆን አብርሃም ከእነዚህ መካከል አንዱን “ይሖዋ” ሲል ጠርቶታል። በእርግጥ እንግዶቹ መላእክት ነበሩ፤ ከመካከላቸው አንዱ ግን ይሖዋን ወክሎ በይሖዋ ስም የመጣ ነበር። በመሆኑም መልአኩ አብርሃምን ሲያነጋግረው ይሖዋ እያነጋገረው ያለ ያህል ነበር። በዚህ መልአክ አማካኝነት ይሖዋ “በሰዶምና በገሞራ ላይ የሚሰማው ጩኸት” ታላቅ እንደሆነ ለአብርሃም ገለጸለት። አክሎም “ድርጊታቸው እኔ ዘንድ እንደደረሰው ጩኸት መሆን አለመሆኑን ለማየት ወደዚያ እወርዳለሁ። ነገሩ እንደዚያ ካልሆነም ማወቅ እችላለሁ” አለው። (ዘፍጥረት 18:3, 20, 21) እንዲህ ሲባል ግን ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ ራሱ ‘ወርዶ’ በሰዶምና በገሞራ የነበረውን ሁኔታ ይመለከታል ማለት አይደለም። ከዚህ ይልቅ ሁኔታውን እንዲያጣሩ መላእክትን ልኳል። (ዘፍጥረት 19:1) ለምን? ሁሉን ማየት የሚችለው ይሖዋ በእነዚህ ከተሞች ያለውን ሁኔታ ራሱ “ማወቅ” አይችልም ነበር? እንደሚችል የታወቀ ነው። ሆኖም ይሖዋ ትሑት ስለሆነ እነዚህ መላእክት ሁኔታውን እንዲያጣሩና በሰዶም የነበረውን የሎጥ ቤተሰብ እንዲያነጋግሩ ተልእኮ ሰጥቷቸዋል።

10 በተጨማሪም ይሖዋ ሌሎች የሚሰጡትን ሐሳብ ይሰማል። በአንድ ወቅት፣ ክፉ የሆነውን ንጉሥ አክዓብን ለማጥፋት ባሰበ ጊዜ መላእክቱ ይህን ለማድረግ የሚያስችሉ የተለያዩ ሐሳቦችን እንዲያቀርቡ ጠይቋቸው ነበር። ይሖዋ የሌሎች ምክር እንደማያስፈልገው የታወቀ ነው። ሆኖም ይሖዋ አንድ መልአክ ያቀረበውን ሐሳብ በመቀበል ያንኑ ሐሳብ እንዲያስፈጽም ተልእኮ ሰጠው። (1 ነገሥት 22:19-22) ይህ ሁኔታ ይሖዋ ምን ያህል ትሑት እንደሆነ የሚያሳይ አይደለም?

11, 12. አብርሃም ይሖዋ ትሑት መሆኑን የተገነዘበው እንዴት ነው?

11 ይሖዋ ፍጽምና የሌላቸው ሰዎች እንኳ የሚያሳስባቸውን ነገር ሲገልጹ ለመስማት ፈቃደኛ ነው። ለምሳሌ ያህል፣ ይሖዋ ሰዶምንና ገሞራን ለማጥፋት እንዳሰበ በነገረው ጊዜ ታማኙ አብርሃም ግራ ተጋብቶ ነበር። አብርሃም “ይህ በአንተ ዘንድ ፈጽሞ የማይታሰብ ነገር ነው። የምድር ሁሉ ዳኛ ትክክል የሆነውን ነገር አያደርግም?” በማለት ተናገረ። ‘በከተሞቹ ውስጥ 50 ጻድቃን ቢገኙ ስፍራውን አትምርም?’ ሲል ይሖዋን ጠየቀው። ይሖዋም ይህ ቢሆን ከተሞቹን እንደማያጠፋቸው አረጋገጠለት። ሆኖም አብርሃም ቁጥሩን ወደ 45፣ ወደ 40 እና ከዚያም በታች ዝቅ በማድረግ መጠየቁን ቀጠለ። ይሖዋ በተደጋጋሚ ማረጋገጫ ቢሰጠውም አብርሃም ቁጥሩ አሥር እስኪደርስ ድረስ መጠየቁን አላቆመም። አብርሃም ይሖዋ ምን ያህል መሐሪ እንደሆነ ሙሉ በሙሉ አልተረዳ ይሆናል። ያም ሆነ ይህ ይሖዋ፣ ወዳጁና አገልጋዩ የሆነው አብርሃም ያሳሰበውን ጉዳይ ሲናገር በትዕግሥትና በትሕትና አዳምጦታል።—ዘፍጥረት 18:23-33

12 ከፍተኛ እውቀት ካላቸው ምሁራን መካከል ተራ ሰዎች የሚያቀርቡትን ሐሳብ በትዕግሥት ለመስማት ፈቃደኞች የሚሆኑት ስንቶቹ ናቸው? c አምላካችን ግን እንዲህ በማድረግ ትሑት መሆኑን አሳይቷል። አብርሃም ከአምላክ ጋር ባደረገው በዚህ ውይይት ይሖዋ “ለቁጣ የዘገየ” መሆኑንም ተገንዝቧል። (ዘፀአት 34:6) አብርሃም ልዑሉ አምላክ በሚወስደው እርምጃ ላይ ጥያቄ የማንሳት መብት እንደሌለው ተገንዝቦ ሳይሆን አይቀርም፣ “ይሖዋ እባክህ፣ አትቆጣ” ሲል ሁለት ጊዜ ተማጽኗል። (ዘፍጥረት 18:30, 32) በእርግጥ አብርሃም ባነሳው ጥያቄ ይሖዋ አልተቆጣም። ‘ከጥበብ የመነጨ ገርነት’ አንጸባርቋል።

ይሖዋ ምክንያታዊ ነው

13. በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው “ምክንያታዊ” የሚለው ቃል ምን ትርጉም አለው? ይህ ቃል ይሖዋን በሚገባ ይገልጸዋል የምንለውስ ለምንድን ነው?

13 ይሖዋ ትሑት መሆኑን የሚያሳየው ሌላው ግሩም ባሕርይ ምክንያታዊነቱ ነው። የሚያሳዝነው ግን ፍጽምና የሌላቸው የሰው ልጆች ይህ ባሕርይ ይጎድላቸዋል። ይሖዋ የማሰብ ችሎታ ያላቸው ፍጥረታቱ የሚያቀርቡትን ሐሳብ ለመስማት ብቻ ሳይሆን ከጽድቅ ሥርዓቶቹ ጋር የሚጋጭ እስካልሆነ ድረስ ሐሳባቸውን ለመቀበልም ፈቃደኛ ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው “ምክንያታዊ” የሚለው ቃል በቀጥታ ሲተረጎም “እሺ ብሎ መቀበል” ማለት ነው። ይህ ባሕርይም ቢሆን የመለኮታዊ ጥበብ መለያ ነው። ያዕቆብ 3:17 “ከሰማይ የሆነው ጥበብ . . . ምክንያታዊ” እንደሆነ ይገልጻል። ወደር የለሽ ጥበብ ያለው ይሖዋ ምክንያታዊ የሆነው በምን መንገድ ነው? በመጀመሪያ ደረጃ፣ ይሖዋ ሁኔታዎችን እንደ አመጣጣቸው የማስተናገድ ልዩ ችሎታ አለው። ስሙ ራሱ እንደሚጠቁመው ይሖዋ ዓላማውን ዳር ለማድረስ መሆን የሚያስፈልገውን ሁሉ ይሆናል። (ዘፀአት 3:14) ይህ ሁኔታ ይሖዋ የተለያዩ ክስተቶችን እንደ ሁኔታው የሚያስተናግድ ምክንያታዊ አምላክ መሆኑን የሚያሳይ አይደለም?

14, 15. ሕዝቅኤል የይሖዋን ሰማያዊ ሠረገላ በተመለከተ ያየው ራእይ ስለ ይሖዋ ድርጅት ሰማያዊ ክፍል ምን ያስተምረናል? ይህ ድርጅት ከሰብዓዊ ድርጅቶች የሚለየውስ እንዴት ነው?

14 ይሖዋ የተለያዩ ክስተቶችን እንደ ሁኔታው የሚያስተናግድ አምላክ መሆኑን እንድንገነዘብ የሚረዳ አንድ ግሩም የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ አለ። ነቢዩ ሕዝቅኤል መንፈሳዊ ፍጥረታትን ያቀፈውን የይሖዋ ድርጅት ሰማያዊ ክፍል የሚያሳይ አንድ ራእይ ተመልክቶ ነበር። በራእዩ ላይ እጅግ ግዙፍ የሆነ አስገራሚ ሠረገላ ማለትም ይሖዋ ምንጊዜም የሚቆጣጠረውን “ተሽከርካሪ” ተመለከተ። ይህ ሠረገላ የሚያደርገው እንቅስቃሴ እጅግ የሚያስደንቅ ነው። የሠረገላው ትላልቅ መንኮራኩሮች በአራቱም ጎን መሄድ የሚችሉና ዙሪያቸውን በዓይን የተሞሉ ናቸው፤ ስለዚህ በየትኛውም አቅጣጫ ማየት የሚችሉ ከመሆናቸውም በላይ መቆም ወይም መዞር ሳያስፈልጋቸው በቅጽበት አቅጣጫቸውን መቀየር ይችላሉ። በተጨማሪም ይህ ግዙፍ ሠረገላ ሰዎች እንደሚሠሯቸው ከባድ መኪኖች አይንቀራፈፍም። በመብረቅ ፍጥነት እየተጓዘም እንኳ ዘጠና ዲግሪ መታጠፍ ይችላል! (ሕዝቅኤል 1:1, 14-28) አዎን፣ ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ የተለያዩ ክስተቶችን እንደ ሁኔታው እንደሚያስተናግድ ሁሉ በእሱ ቁጥጥር ሥር ያለው ድርጅቱም በየጊዜው የሚፈጠሩትን አዳዲስ ሁኔታዎች እንደ አስፈላጊነቱ ማስተናገድ ይችላል።

15 የሰው ልጆች ይህን ልዩ የይሖዋ ችሎታ ሙሉ በሙሉ ሊኮርጁ አይችሉም። እንዲያውም በአብዛኛው ሲታይ የሰው ልጆችም ሆኑ ድርጅቶቻቸው ሁኔታዎችን እንደ አመጣጣቸው የማስተናገድ ችሎታ የላቸውም፤ እንዲሁም ምክንያታዊነትና እሺ ባይነት ይጎድላቸዋል። ለምሳሌ ያህል፣ አንድ ግዙፍ ነዳጅ ጫኝ መርከብ ወይም አንድ ዕቃ ጫኝ ባቡር ግዝፈታቸውና ጉልበታቸው በጣም ሊያስገርመን ይችላል። ሆኖም ድንገተኛ ለውጥ የሚጠይቅ ክስተት ቢፈጠር ሁኔታውን ለመወጣት ፈጣን እርምጃ መውሰድ ይችላሉ? ባቡሩ በሐዲዱ ላይ አንድ ዓይነት እንቅፋት ቢያጋጥመው አቅጣጫውን ሊቀይር እንደማይችል የታወቀ ነው። ወዲያውኑ ባቡሩን ማቆምም የማይቻል ነገር ነው። አንድ ግዙፍ ዕቃ ጫኝ ባቡር ፍሬኑ ከተያዘ በኋላ እንኳ ሁለት ኪሎ ሜትር ገደማ ሊሄድ ይችላል! በተመሳሳይም አንድ ግዙፍ ነዳጅ ጫኝ መርከብ ሞተሩ ከጠፋ በኋላ ስምንት ኪሎ ሜትር ሊጓዝ ይችላል። መርከቡ የኋላ ማርሽ ከገባለትም በኋላ እንኳ ሦስት ኪሎ ሜትር ያህል ወደ ፊት ሊሄድ ይችላል! በአብዛኛው ግትርነት የሚንጸባረቅባቸው ሰብዓዊ ድርጅቶች ሁኔታም ተመሳሳይ ነው። ብዙውን ጊዜ የሰው ልጆች ኩራት ስላለባቸው አስፈላጊውን ለውጥ በማድረግ ነገሮችን እንደ ሁኔታው ለማስተናገድ ፈቃደኞች አይሆኑም። እንዲህ ያለው ግትር አቋም የተለያዩ ድርጅቶችን ኪሳራ ላይ ከመጣሉም በላይ መንግሥታትን ለውድቀት ዳርጓል። (ምሳሌ 16:18) ይሖዋም ሆነ ድርጅቱ ከዚህ ፈጽሞ የተለዩ መሆናቸው እንዴት የሚያስደስት ነው!

ይሖዋ ምክንያታዊ መሆኑን የሚያሳየው እንዴት ነው?

16. ይሖዋ ሰዶምንና ገሞራን ከማጥፋቱ በፊት ለሎጥ ያደረገለት ነገር ምክንያታዊ አምላክ መሆኑን የሚያሳየው እንዴት ነው?

16 በሰዶምና በገሞራ ላይ ስለደረሰው ጥፋት እስቲ እንደገና እንመልከት። የይሖዋ መልአክ “ወደ ተራራማው አካባቢ ሽሽ!” የሚል ግልጽ መመሪያ ለሎጥና ለቤተሰቡ ሰጥቶ ነበር። ይሁን እንጂ ሎጥ ይህ መመሪያ ስለከበደው “እባክህ ይሖዋ፣ ወደዚያስ አልሂድ!” ሲል ለመነ። ሎጥ ወደ ተራራው ቢሸሽ ሊሞት እንደሚችል ስለተሰማው እሱና ቤተሰቡ በአቅራቢያቸው ወደምትገኝ ዞአር ወደምትባል ከተማ መሸሽ እንዲፈቀድላቸው ተማጸነ። ይሖዋ ይህችን ከተማ ለማጥፋት አስቦ ነበር። ሎጥም ቢሆን ‘እሞታለሁ’ ብሎ የሚፈራበት አጥጋቢ ምክንያት አልነበረውም። ሎጥ ወደ ተራራው ቢሸሽ ይሖዋ በዚያ ጥበቃ እንደሚያደርግለት የተረጋገጠ ነው! ያም ሆኖ ይሖዋ የሎጥን ልመና እሺ ብሎ ተቀበለ። መልአኩ ሎጥን “እሺ ይሁን፣ ያልካትን ከተማ ባለማጥፋት አሁንም አሳቢነት አሳይሃለሁ” አለው። (ዘፍጥረት 19:17-22) ይህ ሁኔታ ይሖዋ ምክንያታዊ አምላክ መሆኑን የሚያሳይ አይደለም?

17, 18. ስለ ነነዌ ሰዎች የሚገልጸው ዘገባ ይሖዋ ምክንያታዊ አምላክ መሆኑን የሚያሳየው እንዴት ነው?

17 በተጨማሪም ይሖዋ ከልብ ንስሐ ለሚገቡ ሰዎች ምንጊዜም ምሕረት በማሳየት ሊወስድ ባሰበው እርምጃ ላይ ተገቢውን ማስተካከያ ያደርጋል። ነቢዩ ዮናስ በክፋትና በግፍ ወደተሞላችው የነነዌ ከተማ በተላከ ጊዜ ምን ሁኔታ ተከስቶ እንደነበር አስታውስ። ዮናስ በነነዌ ጎዳናዎች እየተዘዋወረ ‘ታላቂቱ ከተማ በ40 ቀን ውስጥ ትጠፋለች’ በማለት ከአምላክ የተቀበለውን መልእክት አወጀ። ይሁን እንጂ ሁኔታዎቹ ድንገት ተለወጡ። የነነዌ ሰዎች ንስሐ ገቡ!—ዮናስ ምዕራፍ 3

18 በዚህ ጊዜ ይሖዋ ያደረገውን ነገር ዮናስ ከሰጠው ምላሽ ጋር ማነጻጸሩ ጠቃሚ ነው። ይሖዋ ሰዎቹ ንስሐ መግባታቸውን ሲያይ፣ “ኃያል ተዋጊ” በመሆን ሊወስደው የነበረውን እርምጃ በመተው ይቅር ባይ ሆነ። d (ዘፀአት 15:3) በአንጻሩ ግን ዮናስ ምሕረት ከማሳየት ይልቅ ግትር አቋም ይዞ ነበር። እንደ ይሖዋ ምክንያታዊ መሆን ሲገባው ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው መርከብ ወይም ባቡር አስፈላጊውን ማስተካከያ ለማድረግ ተቸግሮ ነበር። ጥፋት ይመጣል ብሎ አውጇል፣ ስለዚህ ጥፋት መምጣት አለበት! ይሁን እንጂ ይሖዋ በትዕግሥት ለዮናስ አንድ የማይረሳ ትምህርት ሰጠው፤ ዮናስን ምክንያታዊና መሐሪ መሆን እንደሚያስፈልገው አስገነዘበው።—ዮናስ ምዕራፍ 4

ይሖዋ ምክንያታዊ አምላክ በመሆኑ አቅማችንን ያውቃል

19. (ሀ) ይሖዋ ከእኛ በሚጠብቀው ነገር ረገድ ምክንያታዊ እንደሆነ እርግጠኞች መሆን የምንችለው ለምንድን ነው? (ለ) ምሳሌ 19:17 ይሖዋ “ጥሩና ምክንያታዊ” ጌታ እንዲሁም ትሑት እንደሆነ የሚያሳየው እንዴት ነው?

19 ይሖዋ ከእኛ በሚጠብቀው ነገርም ምክንያታዊ ነው። ንጉሥ ዳዊት “እሱ እንዴት እንደተሠራን በሚገባ ያውቃልና፤ አፈር መሆናችንን ያስታውሳል” ሲል ተናግሯል። (መዝሙር 103:14) ይሖዋ አቅማችንንና ያለብንን ጉድለት ከእኛ በተሻለ ሁኔታ ያውቃል። ከአቅማችን በላይ አይጠብቅብንም። መጽሐፍ ቅዱስ “ጥሩና ምክንያታዊ” የሆኑ ሰብዓዊ ጌቶችን ‘በቀላሉ ከማይደሰቱ’ ጌቶች ጋር ያነጻጽራል። (1 ጴጥሮስ 2:18) ይሖዋ ምን ዓይነት ጌታ ነው? ምሳሌ 19:17 “ለችግረኛ ሞገስ የሚያሳይ ለይሖዋ ያበድራል” በማለት ይገልጻል። በመሆኑም ይሖዋ አገልጋዮቹ ለችግረኞች የሚያደርጉትን እያንዳንዱን መልካም ነገር የሚያስተውል ጥሩና ምክንያታዊ ጌታ ነው። የሚያስገርመው ደግሞ የአጽናፈ ዓለሙ ፈጣሪ፣ እንዲህ ያለውን ቸርነት የሚያደርጉ ሰዎች ለእሱ እንዳበደሩት አድርጎ የሚቆጥር መሆኑ ነው! ይህም ይሖዋ ምን ያህል ትሑት እንደሆነ የሚያሳይ ነው።

20. ይሖዋ ጸሎታችንን እንደሚሰማና መልስ እንደሚሰጠን እርግጠኞች መሆን የምንችለው ለምንድን ነው?

20 ይሖዋ በዛሬው ጊዜ ካሉት አገልጋዮቹ ጋር ባለው ግንኙነትም ገርና ምክንያታዊ ነው። በእምነት የምናቀርበውን ጸሎት ይሰማል። መላእክትን ልኮ እንዲያነጋግሩን ባያደርግም እንኳ ለጸሎታችን መልስ እንደማይሰጥ አድርገን ማሰብ አይኖርብንም። ሐዋርያው ጳውሎስ የእምነት ባልንጀሮቹ ከእስር እንዲፈታ ‘መጸለያቸውን እንዲቀጥሉ’ በጠየቀበት ወቅት “ወደ እናንተ በፍጥነት ተመልሼ እንድመጣ” ብሏቸው እንደነበር አስታውስ። (ዕብራውያን 13:18, 19) ስለዚህ ይሖዋ ባንጸልይ ኖሮ የማያደርገውን ነገር ስለጸለይን ብቻ ለማድረግ ሊነሳሳ ይችላል።—ያዕቆብ 5:16

21. የይሖዋን ትሕትና በተመለከተ ምን መደምደሚያ ላይ ልንደርስ አይገባም? ስለ ይሖዋ ትሕትና ምን ይሰማሃል?

21 እርግጥ ነው፣ ይሖዋ ገር፣ ታጋሽና ምክንያታዊ በመሆን እንዲሁም ሌሎች የሚያቀርቡትን ሐሳብ በመስማት ትሕትና ያሳያል ሲባል ከጽድቅ መሠረታዊ ሥርዓቶቹ ጋር የሚጋጭ ነገር ያደርጋል ማለት አይደለም። የሕዝበ ክርስትና ቀሳውስት የይሖዋን የሥነ ምግባር ሕግጋት በማላላት የመንጎቻቸውን ጆሮ የሚኮረኩረውን ነገር ሲያስተምሩ ምክንያታዊነት እያሳዩ እንደሆነ ይሰማቸው ይሆናል። (2 ጢሞቴዎስ 4:3) ይሁን እንጂ ሰዎች ከራሳቸው ፍላጎት ጋር የሚጣጣም ነገር ለማድረግ ሲሉ የአምላክን ሕግጋት ለማላላት የሚያደርጉት ጥረት አምላክ ከሚያሳየው ምክንያታዊነት ጋር ፈጽሞ ሊወዳደር አይችልም። ይሖዋ ቅዱስ አምላክ ስለሆነ የጽድቅ መሥፈርቶቹን በምንም መንገድ አያላላም። (ዘሌዋውያን 11:44) እንግዲያው የይሖዋ ምክንያታዊነት ትሕትናውን የሚያሳይ በመሆኑ ልናደንቀው ይገባል። በጽንፈ ዓለሙ ውስጥ ከሁሉ ይበልጥ ጥበበኛ የሆነው አምላክ ትሑት መሆኑን ማወቅህ እጅግ አያስደስትህም? ይሖዋ አስፈሪ ግርማ ያለው ቢሆንም ገር፣ ታጋሽና ምክንያታዊ አምላክ ነው። እንዲህ ወዳለው አምላክ መቅረብ ምንኛ የሚያስደስት ነው!

a የጥንት ገልባጮች (ሶፌሪም) ይህን ጥቅስ ሲገለብጡ ወደ ታች ያጎነበሰው ይሖዋ ሳይሆን ኤርምያስ እንደሆነ አድርገው ጽፈዋል። በዚህ መንገድ የጻፉት አምላክ እንዲህ ያለውን ትሕትና የሚጠይቅ ድርጊት ይፈጽማል ብለው መጻፍ ተገቢ እንደሆነ ስላልተሰማቸው መሆን አለበት። በዚህም የተነሳ ይህ ግሩም ጥቅስ በብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ላይ በትክክል ሳይተረጎም ቀርቷል። ይሁን እንጂ ዘ ኒው ኢንግሊሽ ባይብል ኤርምያስ “አስበኝ፣ አቤቱ አስበኝ፣ ወደ እኔም ጎንበስ በል” ሲል አምላክን እንደተማጸነ በመግለጽ ይህን ጥቅስ በትክክል ተርጉሞታል።

b አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ይህን ጥቅስ “ከጥበብ የሚመነጭ ትሕትና” እና “የጥበብ መለያ የሆነው ገርነት” በማለት ተርጉመውታል።

c መጽሐፍ ቅዱስ ትዕግሥትን ከትዕቢት ጋር ያነጻጽራል። (መክብብ 7:8) የይሖዋ ትዕግሥት፣ ትሑት መሆኑን የሚያሳይ ተጨማሪ ማስረጃ ነው።—2 ጴጥሮስ 3:9

d መዝሙር 86:5 ላይ ይሖዋ “ጥሩ . . . ይቅር ለማለትም ዝግጁ ነህ” ተብሏል። ይህ መዝሙር ወደ ግሪክኛ ሲተረጎም ‘ይቅር ለማለት ዝግጁ’ የሚለው ሐረግ ኤፒኢኪስ ወይም “ምክንያታዊ” ተብሎ ተተርጉሟል።