ሕዝቅኤል 1:1-28

 • ሕዝቅኤል በባቢሎን ሆኖ የአምላክን ራእዮች ተመለከተ (1-3)

 • የይሖዋ ሰማያዊ ሠረገላ ራእይ (4-28)

  • አውሎ ነፋስ፣ ደመናና እሳት (4)

  • አራት ሕያዋን ፍጥረታት (5-14)

  • አራት መንኮራኩሮች (15-21)

  • እንደ በረዶ የሚያብረቀርቅ ጠፈር (22-24)

  • የይሖዋ ዙፋን (25-28)

1  በ30ኛው ዓመት፣ በአራተኛው ወር፣ ከወሩም በአምስተኛው ቀን፣ በኬባር ወንዝ+ አጠገብ በግዞት በተወሰደው ሕዝብ+ መካከል ሳለሁ ሰማያት ተከፍተው አምላክ የገለጠልኝን ራእዮች ማየት ጀመርኩ።  ከወሩ በአምስተኛው ቀን ይኸውም ንጉሥ ዮአኪን+ በግዞት በተወሰደ በአምስተኛው ዓመት፣  በከለዳውያን+ ምድር በኬባር ወንዝ አጠገብ የይሖዋ ቃል የካህኑ የቡዚ ልጅ ወደሆነው ወደ ሕዝቅኤል* መጣ። በዚያም የይሖዋ ኃይል* በእሱ ላይ ወረደ።+  እኔም በማየት ላይ ሳለሁ ከሰሜን ኃይለኛ አውሎ ነፋስ+ ሲመጣ ተመለከትኩ፤ በዚያም ታላቅ ደመናና በደማቅ ብርሃን የተከበበ የእሳት+ ብልጭታ* ነበር፤ ከእሳቱም መካከል የሚያብረቀርቅ ብረት*+ የሚመስል ነገር ይወጣ ነበር።  በመካከሉም የአራት ሕያዋን ፍጥረታት+ አምሳያ ነበር፤ የእያንዳንዳቸውም መልክ እንደ ሰው መልክ ነበር።  እያንዳንዳቸው አራት አራት ፊትና አራት አራት ክንፍ ነበራቸው።+  እግሮቻቸው ቀጥ ያሉ ነበሩ፤ የእግራቸውም ኮቴ የጥጃ ኮቴ ይመስል ነበር፤ እግሮቻቸውም እንደተወለወለ መዳብ ያብረቀርቃሉ።+  በአራቱም ጎኖቻቸው ከክንፎቻቸው ሥር የሰው እጆች ነበሯቸው፤ አራቱም ፊቶችና ክንፎች ነበሯቸው።  ክንፎቻቸውም እርስ በርሳቸው ይነካኩ ነበር። በሚሄዱበት ጊዜ አይዞሩም፤ እያንዳንዳቸውም ቀጥ ብለው ወደ ፊት ይሄዱ ነበር።+ 10  የፊታቸው መልክ ይህን ይመስል ነበር፦ አራቱም የሰው ፊት ነበራቸው፤ በስተ ቀኝ የአንበሳ+ ፊት፣ በስተ ግራ የበሬ+ ፊት ነበራቸው፤ ደግሞም አራቱም የንስር+ ፊት ነበራቸው።+ 11  ፊታቸው ይህን ይመስላል። ክንፎቻቸው ከእነሱ በላይ ተዘርግተዋል። እያንዳንዳቸው እርስ በርሳቸው የሚነካኩ ሁለት ክንፎች ነበሯቸው፤ ሁለቱ ክንፎቻቸው ደግሞ ሰውነታቸውን ይሸፍኑ ነበር።+ 12  እያንዳንዳቸው መንፈሱ ወደመራቸው አቅጣጫ ሁሉ ቀጥ ብለው ወደ ፊት ይሄዱ ነበር።+ በሚሄዱበት ጊዜ አይዞሩም። 13  የሕያዋን ፍጥረታቱ መልክ የሚነድ የከሰል ፍም ይመስላል፤ በሕያዋን ፍጥረታቱም መካከል እየነደደ ያለ ችቦ የሚመስል ነገር ወዲያና ወዲህ ይል ነበር፤ ከእሳቱም+ መካከል መብረቅ ይወጣ ነበር። 14  ሕያዋን ፍጥረታቱም ወዲያና ወዲህ ሲሄዱ እንቅስቃሴያቸው የመብረቅ ብልጭታ ይመስል ነበር። 15  እኔም ሕያዋን ፍጥረታቱን ስመለከት አራት ፊቶች ባሉት በእያንዳንዱ ሕያው ፍጡር አጠገብ በምድር ላይ አንድ አንድ መንኮራኩር* አየሁ።+ 16  መንኮራኩሮቹ በአጠቃላይ ሲታዩ እንደ ክርስቲሎቤ የሚያብረቀርቅ መልክ ነበራቸው፤ አራቱም ይመሳሰላሉ። መልካቸውና አሠራራቸው ሲታይ በአንድ መንኮራኩር ውስጥ በጎን በኩል ሌላ መንኮራኩር የተሰካ ይመስላል። 17  በሚንቀሳቀሱበት ጊዜ መዞር ሳያስፈልጋቸው በአራቱም ጎን በፈለጉበት አቅጣጫ መሄድ ይችላሉ። 18  የመንኮራኩሮቹም ጠርዝ እጅግ ረጅም ከመሆኑ የተነሳ የሚያስፈራ ነበር፤ የአራቱም መንኮራኩሮች ጠርዝ ዙሪያውን በዓይኖች የተሞላ ነበር።+ 19  ሕያዋን ፍጥረታቱ በተንቀሳቀሱ ቁጥር፣ መንኮራኩሮቹም ከእነሱ ጋር አብረው ይንቀሳቀሳሉ፤ ሕያዋን ፍጥረታቱ ከምድር ከፍ ከፍ ሲሉ መንኮራኩሮቹም ከፍ ከፍ ይላሉ።+ 20  መንፈሱ ወደመራቸው አቅጣጫ፣ መንፈሱ ወደሚሄድበት ቦታ ሁሉ ይሄዳሉ። መንኮራኩሮቹ ከእነሱ ጋር አብረው ከፍ ከፍ ይሉ ነበር፤ በሕያዋን ፍጥረታቱ ላይ የሚሠራው መንፈስ* በመንኮራኩሮቹም ውስጥ ነበርና። 21  ሕያዋን ፍጥረታቱ ሲንቀሳቀሱ እነሱም ይንቀሳቀሳሉ፤ ሕያዋን ፍጥረታቱ ሲቆሙ እነሱም ይቆማሉ፤ ከምድር ከፍ ከፍ ሲሉ መንኮራኩሮቹም ከእነሱ ጋር አብረው ከፍ ከፍ ይሉ ነበር፤ በሕያዋን ፍጥረታቱ ላይ የሚሠራው መንፈስ በመንኮራኩሮቹም ውስጥ ነበርና። 22  ከሕያዋን ፍጥረታቱ ራስ በላይ እጅግ አስደናቂ እንደሆነ በረዶ የሚያብረቀርቅ ጠፈር የሚመስል ነገር ነበር፤ ይህም ከራሳቸው በላይ ተዘርግቶ ነበር።+ 23  ከጠፈሩ በታች ክንፎቻቸው አንዳቸው ወደ ሌላው ቀጥ ብለው ነበር።* እያንዳንዳቸውም በዚህ ጎንና በዚያኛው ጎን ሰውነታቸውን የሚሸፍኑባቸው ሁለት ሁለት ክንፎች ነበሯቸው። 24  የክንፎቻቸውን ድምፅ ስሰማ እንደሚጎርፍ ውኃ ድምፅ፣ ደግሞም ሁሉን እንደሚችል አምላክ ድምፅ ነበር።+ በሚንቀሳቀሱበት ጊዜ ድምፁ እንደ ሠራዊት ድምፅ ነበር። በሚቆሙበት ጊዜ ክንፎቻቸውን ወደ ታች ያደርጋሉ። 25  ከራሳቸው በላይ ካለው ጠፈር በላይ አንድ ድምፅ ይሰማ ነበር። (በሚቆሙበት ጊዜ ክንፎቻቸውን ወደ ታች ያደርጉ ነበር።) 26  ከራሳቸው በላይ ካለው ጠፈር በላይ የሰንፔር ድንጋይ+ የመሰለ እንደ ዙፋን ያለ ነገር ነበር።+ ከላይ በኩል ባለው በዙፋኑ ላይ መልኩ የሰው መልክ የሚመስል ተቀምጦ ነበር።+ 27  ወገቡ ከሚመስለው ነገር ጀምሮ ወደ ላይ፣ እሳት የሚመስል እንደ ብረት የሚያብረቀርቅ ነገር+ ሲወጣ አየሁ፤ ደግሞም ከወገቡ ጀምሮ ወደ ታች፣ እሳት የሚመስል ነገር አየሁ።+ በዙሪያውም ደማቅ ብርሃን ነበር፤ 28  ይህም ዝናባማ በሆነ ቀን በደመና ውስጥ እንደሚታይ ቀስተ ደመና ነበር።+ በዙሪያው ያለው ደማቅ ብርሃን ይህን ይመስላል። ደግሞም የይሖዋን ክብር ይመስል ነበር።+ እኔም ባየሁት ጊዜ በግንባሬ ተደፋሁ፤ ከዚያም አንዱ ሲናገር ድምፅ ሰማሁ።

የግርጌ ማስታወሻዎች

“አምላክ ያበረታል” የሚል ትርጉም አለው።
ቃል በቃል “እጅ።”
የሚያብረቀርቅ የወርቅና የብር ቅይጥ።
ወይም “መብረቅ።”
የሠረገላ ተሽከርካሪ እግር።
ቃል በቃል “የሕያው ፍጡሩ መንፈስ።”
“ቀጥ ብለው ተዘርግተው ነበር” ማለትም ሊሆን ይችላል።