ዮናስ 3:1-10

  • ዮናስ አምላክን በመታዘዝ ወደ ነነዌ ሄደ (1-4)

  • የነነዌ ሰዎች የዮናስን መልእክት ሰምተው ንስሐ ገቡ (5-9)

  • አምላክ ነነዌን ላለማጥፋት ወሰነ (10)

3  ከዚያም የይሖዋ ቃል ለሁለተኛ ጊዜ እንዲህ ሲል ወደ ዮናስ መጣ፦+  “ተነስተህ ወደ ታላቂቱ ከተማ ወደ ነነዌ+ ሂድ፤ የምነግርህንም መልእክት በመካከሏ አውጅ።”  ዮናስም የይሖዋን ቃል በመታዘዝ ተነስቶ ወደ ነነዌ+ ሄደ።+ ነነዌ እጅግ ታላቅ ከተማ የነበረች ስትሆን* በእግር የሦስት ቀን ያህል መንገድ ታስኬድ ነበር።  ዮናስም ወደ ከተማዋ ገብቶ የአንድ ቀን መንገድ ከተጓዘ በኋላ “ነነዌ በ40 ቀን ውስጥ ትደመሰሳለች” ብሎ አወጀ።  የነነዌም ሰዎች በአምላክ አመኑ፤+ ከትልቁም አንስቶ እስከ ትንሹ ድረስ ጾም አወጁ፤ ማቅም ለበሱ።  የነነዌ ንጉሥ መልእክቱን በሰማ ጊዜ ከዙፋኑ ተነስቶ ልብሰ መንግሥቱን አወለቀ፤ ማቅም ለብሶ አመድ ላይ ተቀመጠ።  በተጨማሪም በመላው ነነዌ አዋጅ አስነገረ፤“ንጉሡና መኳንንቱ ያወጡት ድንጋጌ፦ ሰውም ሆነ እንስሳ፣ ከብትም ሆነ መንጋ ምንም ነገር አይቅመስ። ምግብ አይብሉ፤ ውኃም አይጠጡ።  ሰውም ሆነ እንስሳ ማቅ ይልበስ፤ ሁሉም አጥብቆ ወደ አምላክ ይጩኽ፤ ክፉ መንገዳቸውንና የሚፈጽሙትን ግፍ ይተዉ።  እኛ እንዳንጠፋ፣ እውነተኛው አምላክ ሊያመጣው ያሰበውን ነገር እንደገና በማጤን* ከሚነደው ቁጣው ይመለስ እንደሆነ ማን ያውቃል?” 10  እውነተኛው አምላክ ያደረጉትን ነገር ይኸውም ከክፉ መንገዳቸው እንዴት እንደተመለሱ አየ፤+ በእነሱም ላይ አመጣዋለሁ ያለውን ነገር መልሶ በማጤን* ጥፋቱን ከማምጣት ተቆጠበ።+

የግርጌ ማስታወሻዎች

ቃል በቃል “ለአምላክ ታላቅ ከተማ ነበረች።”
ወይም “ሊያመጣ ባሰበው ነገር ተጸጽቶ።”
ወይም “አመጣዋለሁ ባለው ነገር ተጸጽቶ።”