ምዕራፍ 2
በእርግጥ ‘ወደ አምላክ መቅረብ’ ትችላለህ?
1, 2. (ሀ) ብዙዎች የአምላክ ወዳጅ መሆንን በተመለከተ ምን ሊሰማቸው ይችላል? ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? (ለ) አብርሃም ምን መብት አግኝቷል? ለምንስ?
የሰማይና የምድር ፈጣሪ “ወዳጄ” ብሎ ቢጠራህ ምን ይሰማሃል? ብዙዎች ይህ ጨርሶ የማይታሰብ ነገር እንደሆነ ሊሰማቸው ይችላል። ደግሞስ ሰው እንደ ይሖዋ ካለ ታላቅ አምላክ ጋር እንዴት ወዳጅነት ሊመሠርት ይችላል? ይሁንና መጽሐፍ ቅዱስ ወደ አምላክ መቅረብ እንደምንችል ይገልጻል።
2 በጥንት ዘመን የኖረው አብርሃም ከአምላክ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት ነበረው። ይሖዋ ይህን የዕብራውያን አባት “ወዳጄ” ሲል ጠርቶታል። (ኢሳይያስ 41:8) አዎን፣ ይሖዋ አብርሃምን የቅርብ ወዳጁ አድርጎ ተመልክቶታል። አብርሃም የአምላክ የቅርብ ወዳጅ የመሆን መብት ሊያገኝ የቻለው ‘በይሖዋ ስላመነ’ ነው። (ያዕቆብ 2:23) በዛሬው ጊዜም ይሖዋ ከአገልጋዮቹ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት መመሥረት እንዲሁም ለእነሱ ‘ፍቅሩን መግለጽ’ ይፈልጋል። (ዘዳግም 10:15) የአምላክ ቃል “ወደ አምላክ ቅረቡ፤ እሱም ወደ እናንተ ይቀርባል” የሚል ማበረታቻ ይሰጠናል። (ያዕቆብ 4:8) ይህ ጥቅስ ይሖዋ ግብዣ እንዳቀረበልንና ቃል እንደገባልን የሚያሳይ ነው።
3. ይሖዋ ምን ግብዣ አቅርቦልናል? ከዚህስ ጋር በተያያዘ ምን ቃል ገብቷል?
3 ይሖዋ ወደ እሱ እንድንቀርብ ይጋብዘናል። ከእኛ ጋር ወዳጅነት ለመመሥረት ፈቃደኛና ዝግጁ ነው። ከዚህም በተጨማሪ ወደ እሱ ከቀረብን እሱም ተመሳሳይ እርምጃ በመውሰድ ወደ እኛ እንደሚቀርብ ቃል ገብቷል። በዚህ መንገድ “ከይሖዋ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት” የመመሥረት ውድ መብት ልናገኝ እንችላለን። (መዝሙር 25:14) “የጠበቀ ወዳጅነት” የሚለው ሐረግ የልብ ወዳጅ ለሆነ ሰው ሚስጥር ማካፈልን ያመለክታል።
4. የልብ ወዳጅ የሚባለው እንዴት ያለ ሰው ነው? ይሖዋ ወደ እሱ ለሚቀርቡት ሰዎች እንዲህ ያለ ወዳጅ የሚሆነው በምን መንገድ ነው?
4 ሚስጥርህን የምታካፍለው የልብ ወዳጅ አለህ? እንዲህ ዓይነቱ ወዳጅ ከልቡ ያስብልሃል። ታማኝነቱን በተግባር ያስመሠከረ በመሆኑ ታምነዋለህ። ደስታህን ለእሱ ለማካፈል ትጓጓለህ። ሐዘንህን ስታካፍለው ቀለል ይልሃል። ስሜትህን ማንም ሰው ባይረዳልህ እንኳ እሱ ይረዳልሃል። ይሖዋም ስትቀርበው እንዲህ ያለ የልብ ወዳጅ ይሆንልሃል፤ ከልብ ያስብልሃል እንዲሁም ስሜትህን ይረዳልሃል። (መዝሙር 103:14፤ 1 ጴጥሮስ 5:7) ይሖዋ ታማኝ ለሆኑ አገልጋዮቹ ታማኝ እንደሆነ ስለምታውቅ ለእሱ የልብህን አውጥተህ ለመናገር አትፈራም። (መዝሙር 18:25) ይሁን እንጂ ከአምላክ ጋር እንዲህ ያለ የጠበቀ ወዳጅነት የመመሥረት መብት ያገኘነው ይሖዋ ራሱ አጋጣሚውን ስለከፈተልን ብቻ ነው።
ይሖዋ አጋጣሚውን ከፍቶልናል
5. ይሖዋ ወደ እሱ መቅረብ እንድንችል ምን አድርጓል?
5 ኃጢአተኞች ስለሆንን በራሳችን ጥረት ብቻ ወደ አምላክ ልንቀርብ አንችልም። (መዝሙር 5:4) ሐዋርያው ጳውሎስ “ሆኖም አምላክ ገና ኃጢአተኞች ሳለን ክርስቶስ እንዲሞትልን በማድረግ ለእኛ ያለውን የራሱን ፍቅር አሳይቷል” ሲል ጽፏል። (ሮም 5:8) አዎን፣ ይሖዋ “በብዙ ሰዎች ምትክ ሕይወቱን ቤዛ አድርጎ [እንዲሰጥ]” ልጁን ወደ ምድር ልኮታል። (ማቴዎስ 20:28) በዚህ ቤዛዊ መሥዋዕት ካመንን ወደ አምላክ መቅረብ እንችላለን። አምላክ “አስቀድሞ ስለወደደን” ከእሱ ጋር መወዳጀት የምንችልበትን መሠረት ጥሎልናል።—1 ዮሐንስ 4:19
6, 7. (ሀ) ይሖዋ ሊታወቅ የማይችል ሚስጥራዊ አምላክ እንዳልሆነ እንዴት እናውቃለን? (ለ) ይሖዋ ራሱን የገለጠው በምን መንገዶች ነው?
6 ይሖዋ ወደ እሱ መቅረብ የምንችልበትን ሌላም ዝግጅት አድርጓል፦ ራሱን ለእኛ ገልጧል። ከአንድ ሰው ጋር የጠበቀ ወዳጅነት መመሥረት የምንችለው ግለሰቡን በሚገባ ስናውቀውና ባሕርያቱን ስናደንቅ ነው። በመሆኑም ይሖዋ ፈጽሞ ሊታወቅ የማይችል ሚስጥራዊ አምላክ ቢሆን ኖሮ ወደ እሱ ልንቀርብ አንችልም ነበር። ይሁንና አምላክ ራሱን ከመሰወር ይልቅ እንድናውቀው ይፈልጋል። (ኢሳይያስ 45:19) ከዚህም በተጨማሪ ይሖዋ ራሱን የገለጠው ለሁሉም ሰው ማለትም ዓለም እንደ ተራ ለሚመለከተን ሰዎች ጭምር ነው።—ማቴዎስ 11:25
7 ይሖዋ ራሱን የገለጠልን እንዴት ነው? የፍጥረት ሥራዎቹ አንዳንድ ባሕርያቱን ይኸውም የኃይሉን ታላቅነት፣ የጥበቡን ጥልቀትና የፍቅሩን ስፋት ያንጸባርቃሉ። (ሮም 1:20) ይሁን እንጂ ይሖዋ ራሱን የገለጠልን በፈጠራቸው ነገሮች ብቻ አይደለም። ለሌሎች እንዴት እውቀት መስጠት እንደሚቻል ከማንም በላይ የሚያውቅ አምላክ ስለሆነ በቃሉ ማለትም በመጽሐፍ ቅዱስ አማካኝነት ራሱን ገልጦልናል።
ይሖዋ በቃሉ አማካኝነት ራሱን የገለጠው እንዴት ነው?
8. መጽሐፍ ቅዱስ ራሱ፣ ይሖዋ እንደሚወደን የሚያሳይ ጥሩ ማስረጃ ነው ሊባል የሚችለው ለምንድን ነው?
8 መጽሐፍ ቅዱስ ራሱ፣ ይሖዋ እንደሚወደን የሚያሳይ ጥሩ ማስረጃ ነው። በቃሉ ውስጥ ራሱን የገለጠልን በቀላሉ ልንረዳው በምንችለው መንገድ ነው፤ ይህም እንደሚወደን ብቻ ሳይሆን እንድናውቀውና እንድንወደው እንደሚፈልግ የሚያሳይ ነው። በዚህ ድንቅ መጽሐፍ ውስጥ የሰፈረውን ሐሳብ ማንበብ ወደ ይሖዋ ለመቅረብ ያስችለናል። (መዝሙር 1:1-3) ይሖዋ በቃሉ ውስጥ ራሱን የገለጠባቸውን አንዳንድ ልብ የሚነኩ ሐሳቦች እስቲ እንመልከት።
9. የአምላክን ባሕርያት በቀጥታ የሚገልጹ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙ አንዳንድ ጥቅሶች የትኞቹ ናቸው?
9 የአምላክ ባሕርያት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በብዙ ቦታዎች ላይ በቀጥታ ተገልጸዋል። አንዳንድ ምሳሌዎችን ተመልከት። “ይሖዋ ፍትሕን ይወዳል።” (መዝሙር 37:28) “[አምላክ] ኃይሉ ታላቅ ነው።” (ኢዮብ 37:23) “‘እኔ ታማኝ [ነኝ]’ ይላል ይሖዋ።” (ኤርምያስ 3:12) “እሱ ጥበበኛ ልብ አለው።” (ኢዮብ 9:4) “መሐሪና ሩኅሩኅ . . . ለቁጣ የዘገየ፣ ታማኝ ፍቅሩና እውነቱ እጅግ ብዙ የሆነ” አምላክ ነው። (ዘፀአት 34:6) “ይሖዋ ሆይ፣ አንተ ጥሩ ነህና፤ ይቅር ለማለትም ዝግጁ ነህ።” (መዝሙር 86:5) ከዚህም በተጨማሪ በመጀመሪያው ምዕራፍ ላይ እንደተገለጸው ይሖዋ ከሁሉ ይበልጥ ጎልቶ የሚታይ አንድ ባሕርይ አለው፤ “አምላክ ፍቅር ነው።” (1 ዮሐንስ 4:8) በእነዚህ ግሩም ባሕርያት ላይ ስታሰላስል አቻ ወደማይገኝለት ወደዚህ አምላክ ለመቅረብ አትገፋፋም?
10, 11. (ሀ) ይሖዋ ባሕርያቱ ይበልጥ ግልጽ ሆነው እንዲታዩን በቃሉ ውስጥ ምን አስፍሮልናል? (ለ) አምላክ ኃይሉን እንዴት እንደሚጠቀምበት በዓይነ ሕሊናችን ለማየት የሚረዳን የትኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ ነው?
10 ይሖዋ ባሕርያቱን ከመግለጹም በተጨማሪ እነዚህን ባሕርያት እንዴት እንዳንጸባረቀ የሚያሳዩ ሕያው የሆኑ ምሳሌዎችን በቃሉ ውስጥ አስፍሮልናል። እነዚህ ዘገባዎች ይሖዋ ያደረገውን ነገር በዓይነ ሕሊናችን ለመሳል ይረዱናል፤ ይህም ስለ ይሖዋ ባሕርያት የተሻለ ግንዛቤ እንዲኖረን ስለሚያደርግ ወደ እሱ እንድንቀርብ ያነሳሳናል። እስቲ አንድ ምሳሌ ተመልከት።
መጽሐፍ ቅዱስ ወደ ይሖዋ እንድንቀርብ ይረዳናል
11 አምላክ ‘የሚያስደምም ኃይል’ እንዳለው ማንበብ አንድ ነገር ነው። (ኢሳይያስ 40:26) ሆኖም እስራኤላውያንን ነፃ በማውጣት ቀይ ባሕርን እንዴት እንዳሻገራቸውና ለ40 ዓመታት በምድረ በዳ ምን ያህል እንደተንከባከባቸው ማንበብ ፈጽሞ የተለየ ነገር ነው። ባሕሩ ለሁለት ከተከፈለ በኋላ እንደ ግድግዳ በቆመው ውኃ መካከል 3,000,000 ገደማ የሚሆነው የእስራኤል ሕዝብ በደረቅ ምድር ሲሻገር በዓይነ ሕሊናህ ልትመለከት ትችላለህ። (ዘፀአት 14:21፤ 15:8) አምላክ እስራኤላውያንን በምድረ በዳ ምን ያህል እንደተንከባከባቸውም በምናብህ ለማየት ሞክር። ከዓለት ውስጥ ውኃ አፈለቀላቸው። ነጭ የድንብላል ዘር የሚመስል ምግብ መሬት ላይ አዘነበላቸው። (ዘፀአት 16:31፤ ዘኁልቁ 20:11) ይህ ዘገባ ይሖዋ ኃይል እንዳለው ብቻ ሳይሆን ኃይሉን ሕዝቦቹን ለመንከባከብና ለመጠበቅ እንደሚጠቀምበት ያሳያል። የምንጸልየው “መጠጊያችንና ብርታታችን፣ በጭንቅ ጊዜ ፈጥኖ የሚደርስልን ረዳታችን” ወደሆነ ኃያል አምላክ መሆኑን ማወቃችን የሚያጽናና አይደለም?—መዝሙር 46:1
12. ይሖዋ እኛ በቀላሉ ልንረዳው በምንችል መንገድ ራሱን የገለጸልን እንዴት ነው?
12 መንፈስ የሆነው ይሖዋ እሱን ማወቅ እንድንችል ሌላም ያደረገው ነገር አለ። ሰዎች እንደመሆናችን መጠን ማየት የምንችለው በሰብዓዊ ዓይን ሊታይ የሚችለውን ነገር ብቻ ነው። በመንፈሳዊው ዓለም ያለውን ነገር የማየት ችሎታ የለንም። አምላክ በመንፈሳዊው ዓለም ያሉ ሌሎች ፍጥረታቱን በሚያነጋግርበት ቋንቋ ራሱን ቢገልጽልን ኖሮ ምን ያህል እንረዳው ነበር? ይህ ሲወለድ ጀምሮ ማየት ለተሳነው ሰው መልካችንን ለማስረዳት እንደመሞከር ያህል ይሆን ነበር። ከዚህ ይልቅ ይሖዋ በቀላሉ ሊገባን በሚችል መንገድ ራሱን ገልጾልናል። አንዳንድ ጊዜ ዘይቤያዊ አገላለጾችን በመጠቀም ራሱን፣ እኛ ከምናውቃቸው ነገሮች ጋር እያመሳሰለ ይገልጻል። ሌላው ቀርቶ አንዳንድ ሰብዓዊ ገጽታዎች እንዳሉት አድርጎ የገለጸባቸው ጊዜያትም አሉ። a
13. ኢሳይያስ 40:11 ይሖዋን እንዴት አድርጎ ይገልጸዋል? ይህስ ምን እንዲሰማህ ያደርጋል?
13 በኢሳይያስ 40:11 ላይ ስለ ይሖዋ የተሰጠውን መግለጫ ተመልከት፦ “መንጋውን እንደ እረኛ ይንከባከባል። ግልገሎቹን በክንዱ ይሰበስባል፤ በእቅፉም ይሸከማቸዋል።” እዚህ ላይ ይሖዋ ግልገሎቹን “በክንዱ” እንደሚያቅፍ እረኛ ተደርጎ ተገልጿል። ይህም አምላክ፣ አቅም የሌላቸውን ጨምሮ ሕዝቦቹን ሁሉ የመጠበቅና የመደገፍ ችሎታ እንዳለው ያመለክታል። ለእሱ ታማኞች እስከሆንን ድረስ ፈጽሞ ስለማይተወን ኃያል በሆኑት ክንዶቹ ሥር ያለስጋት ተረጋግተን መኖር እንችላለን። (ሮም 8:38, 39) ታላቁ እረኛ ግልገሎቹን “በእቅፉ” እንደሚሸከማቸው የሚገልጸው አነጋገር አንድ እረኛ መጎናጸፊያውን ወደ ላይ አጥፎ ገና የተወለደን ግልገል በእቅፉ እንደሚይዝ የሚያመለክት ነው። ይህም ይሖዋ እንደሚሳሳልንና በፍቅር እንደሚንከባከበን እርግጠኞች እንድንሆን ያደርገናል። ወደ እሱ ለመቅረብ ብንነሳሳ ምንም አያስደንቅም።
‘ወልድ አብን ሊገልጥልን ፈቃደኛ ነው’
14. ይሖዋ ከሁሉ በተሻለ መንገድ ራሱን የገለጠው በኢየሱስ በኩል ነው ሊባል የሚችለው ለምንድን ነው?
14 ይሖዋ ራሱን ከሁሉ በተሻለ መንገድ የገለጠው በተወዳጅ ልጁ በኢየሱስ በኩል ነው። ከኢየሱስ በተሻለ ሁኔታ የአምላክን አስተሳሰብና ስሜት ሊያንጸባርቅ ወይም አምላክን ቁልጭ ባለ መንገድ ሊገልጽ የሚችል አንድም አካል የለም። ደግሞም የአምላክ የበኩር ልጅ የሆነው ኢየሱስ ከአባቱ ጋር መኖር የጀመረው ሌሎች መንፈሳዊ ፍጥረታት ከመፈጠራቸውም ሆነ ግዑዙ ጽንፈ ዓለም ወደ ሕልውና ከመምጣቱ በፊት ነው። (ቆላስይስ 1:15) ኢየሱስ ይሖዋን በቅርብ ያውቀዋል። “ከአብ በስተቀር ወልድ ማን እንደሆነ የሚያውቅ የለም፤ እንዲሁም ከወልድና ወልድ ሊገልጥለት ከሚፈቅድ በስተቀር አብ ማን እንደሆነ የሚያውቅ የለም” ብሎ ሊናገር የቻለው ለዚህ ነው። (ሉቃስ 10:22) ኢየሱስ ሰው ሆኖ በምድር ላይ በኖረበት ዘመን አባቱን በሁለት ዋና ዋና መንገዶች ገልጦታል።
15, 16. ኢየሱስ አባቱን የገለጠው በየትኞቹ ሁለት መንገዶች ነው?
15 በመጀመሪያ ደረጃ፣ ኢየሱስ ያስተማራቸው ትምህርቶች አባቱን እንድናውቅ ይረዱናል። ኢየሱስ ይሖዋን የገለጸበት መንገድ ልብ የሚነካ ነው። ለምሳሌ ያህል፣ ኢየሱስ ንስሐ የሚገቡ ኃጢአተኞችን እጁን ዘርግቶ የሚቀበለውን መሐሪ አምላክ፣ በአንድ ይቅር ባይ አባት መስሎታል። በምሳሌው ላይ የተጠቀሰው አባት፣ አባካኝ የነበረው ልጁ ወደ ቤቱ ሲመለስ ከሩቅ አይቶ አንጀቱ እንደተላወሰ እንዲሁም ሮጦ አንገቱ ላይ በመጠምጠም አቅፎ እንደሳመው ተገልጿል። (ሉቃስ 15:11-24) በተጨማሪም ይሖዋ ቅን ልብ ያላቸውን ሰዎች በግለሰብ ደረጃ ስለሚወዳቸው ወደ ራሱ ‘እንደሚስባቸው’ ኢየሱስ ገልጿል። (ዮሐንስ 6:44) ሌላው ቀርቶ ይሖዋ አንዲት ድንቢጥ እንኳ መሬት ላይ ስትወድቅ ያውቃል። ኢየሱስ “አትፍሩ፤ እናንተ ከብዙ ድንቢጦች የላቀ ዋጋ አላችሁ” ሲል ተናግሯል። (ማቴዎስ 10:29, 31) እንዲህ ወዳለው አምላክ ለመቅረብ እንደምንገፋፋ ምንም ጥርጥር የለውም።
16 በሁለተኛ ደረጃ፣ የኢየሱስ መላ ሕይወት ይሖዋ ምን ዓይነት አምላክ እንደሆነ እንድንገነዘብ ያደርገናል። ኢየሱስ የአባቱ ፍጹም ነጸብራቅ በመሆኑ “እኔን ያየ ሁሉ አብንም አይቷል” ማለት ችሏል። (ዮሐንስ 14:9) በመሆኑም ኢየሱስ ምን እንደተሰማው እንዲሁም ሰዎችን እንዴት እንደያዘ የሚገልጹ የወንጌል ዘገባዎችን ስናነብ አባቱን የማየት ያህል ይሆንልናል። ይሖዋ ባሕርያቱን ከዚህ በተሻለ መንገድ ሊገልጥልን አይችልም። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው?
17. ይሖዋ ምን ዓይነት አምላክ እንደሆነ ለእኛ ግልጽ ለማድረግ ምን ዘዴ እንደተጠቀመ በምሳሌ አስረዳ።
17 ለምሳሌ ያህል፣ ደግነት ምን ማለት እንደሆነ ለማስረዳት ፈለግህ እንበል። ትርጉሙን እንዲሁ በቃልህ ታስረዳ ይሆናል። ይሁን እንጂ አንድ ሰው ያከናወነውን የደግነት ድርጊት ምሳሌ አድርገህ ብትጠቅስ “ደግነት” የሚለው ቃል ይበልጥ ግልጽ ሊሆን ይችላል። ይሖዋም ምን ዓይነት አምላክ እንደሆነ ለመግለጽ ተመሳሳይ የሆነ ዘዴ ተጠቅሟል። ባሕርያቱን እንዲሁ በቃላት ከመግለጽ በተጨማሪ ልጁን ሕያው ምሳሌ አድርጎ ተጠቅሞበታል። ኢየሱስ የአምላክን ባሕርያት በተግባር አሳይቶናል። ይሖዋ ስለ ኢየሱስ በሚተርኩት የወንጌል ዘገባዎች አማካኝነት፣ ‘እኔ እንዲህ ዓይነት አምላክ ነኝ’ እያለን እንዳለ አድርገን ልናስብ እንችላለን። ታዲያ በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈው ዘገባ ስለ ኢየሱስ ምድራዊ ሕይወት ምን ይላል?
18. ኢየሱስ ኃይልን፣ ፍትሕንና ጥበብን ያንጸባረቀው እንዴት ነው?
18 አራቱ የአምላክ ዋና ዋና ባሕርያት በኢየሱስ ምድራዊ ሕይወት ላይ ግሩም በሆነ መንገድ ተንጸባርቀዋል። ኢየሱስ በበሽታ፣ በረሃብና አልፎ ተርፎም በሞት ላይ የነበረው ሥልጣን ኃይሉን የሚያሳይ ነው። ሆኖም ኢየሱስ ሥልጣናቸውን አላግባብ እንደሚጠቀሙ ራስ ወዳድ ሰዎች ኃይሉን የግል ጥቅሙን ለማራመድ ወይም ደግሞ ሌሎችን ለመጉዳት አልተጠቀመበትም። (ማቴዎስ 4:2-4) ፍትሕን ይወድ ነበር። ስግብግብ የሆኑ ነጋዴዎች ሕዝቡን አላግባብ ሲበዘብዙ ሲያይ ልቡ በጽድቅ ቁጣ ተሞልቶ ነበር። (ማቴዎስ 21:12, 13) ድሆችንና የተጨቆኑትን ከአድልዎ ነፃ በሆነ መንገድ በመያዝ “እረፍት” እንዲያገኙ ረድቷቸዋል። (ማቴዎስ 11:4, 5, 28-30) ‘ከሰለሞን የሚበልጠው’ ኢየሱስ ያስተማራቸው ትምህርቶች ወደር የለሽ ጥበብ የተንጸባረቀባቸው ናቸው። (ማቴዎስ 12:42) ይሁን እንጂ ኢየሱስ ጥበቡን በሌሎች ዘንድ አድናቆት ለማትረፍ አልተጠቀመበትም። ትምህርቶቹ ግልጽ፣ ቀላልና በተግባር ሊተረጎሙ የሚችሉ ስለነበሩ የተናገራቸው ቃላት የተራውን ሕዝብ ልብ በእጅጉ ነክተዋል።
19, 20. (ሀ) ኢየሱስ የላቀ የፍቅር ምሳሌ የሆነው በምን መንገድ ነው? (ለ) የኢየሱስን ታሪክ ስናነብና ስናሰላስልበት ልንዘነጋው የማይገባው ነገር ምንድን ነው?
19 ኢየሱስ የላቀ የፍቅር ምሳሌ ነው። አገልግሎቱን ባከናወነበት ወቅት የሌሎችን ችግር መረዳትንና ርኅራኄ ማሳየትን ጨምሮ በርካታ የፍቅር ገጽታዎችን አንጸባርቋል። ሰዎች መከራ ሲደርስባቸው ሲያይ አያስችለውም። በተደጋጋሚ ጊዜያት እንዲህ ያሉ ሰዎችን ለመርዳት አስፈላጊውን እርምጃ ወስዷል። (ማቴዎስ 14:14) ኢየሱስ የታመሙትን በመፈወስና የተራቡትን በመመገብ ብቻ ሳይሆን ይበልጥ አስፈላጊ በሆነ ሌላ መንገድም ሩኅሩኅ መሆኑን አሳይቷል። ሰዎች ዘላቂ በረከት ስለሚያመጣው የአምላክ መንግሥት የሚናገረውን እውነት እንዲያውቁና እንዲቀበሉ እንዲሁም ለዚህ እውነት ከፍተኛ አድናቆት እንዲያድርባቸው ረድቷል። (ማርቆስ 6:34፤ ሉቃስ 4:43) ከሁሉ በላይ ደግሞ ሕይወቱን በፈቃደኝነት ለሌሎች አሳልፎ በመስጠት የራስን ጥቅም መሥዋዕት የማድረግ መንፈስ የተንጸባረቀበት ፍቅር አሳይቷል።—ዮሐንስ 15:13
20 ታዲያ በሁሉም የኑሮ ደረጃና ዕድሜ ላይ የሚገኙ ሰዎች ወደዚህ አፍቃሪና አሳቢ ሰው መቅረባቸው ሊያስደንቀን ይገባል? (ማርቆስ 10:13-16) ይሁን እንጂ የኢየሱስን ታሪክ ስናነብና ስናሰላስልበት የአባቱን ጥርት ያለ ነጸብራቅ በልጁ ላይ እየተመለከትን መሆኑን ፈጽሞ መዘንጋት አይኖርብንም።—ዕብራውያን 1:3
እኛን ለመርዳት የተዘጋጀ መጽሐፍ
21, 22. ይሖዋን መፈለግ ምን ማድረግ ይጠይቃል? ይህ መጽሐፍ በዚህ ረገድ እኛን ሊረዳ የሚችል ምን ነገር ይዟል?
21 ይሖዋ ራሱን በቃሉ ውስጥ ቁልጭ ባለ መንገድ በመግለጽ ወደ እሱ እንድንቀርብ እንደሚፈልግ በማያሻማ መንገድ አሳይቷል። ይሁንና ወደ እሱ እንድንቀርብ አያስገድደንም። ይሖዋን “በሚገኝበት ጊዜ [መፈለግ]” የእያንዳንዳችን ኃላፊነት ነው። (ኢሳይያስ 55:6) ይሖዋን መፈለግ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተገለጹትን ባሕርያቱንና የተለያዩ ነገሮችን የሚያከናውንበትን መንገድ ማወቅ ይጠይቃል። ይህ የምታነበው መጽሐፍ በዚህ ረገድ አንተን ለመርዳት ታስቦ የተዘጋጀ ነው።
22 ይህ መጽሐፍ በይሖዋ ዋና ዋና ባሕርያት ማለትም በኃይሉ፣ በፍትሑ፣ በጥበቡና በፍቅሩ ላይ የተመሠረቱ አራት ክፍሎችን የያዘ ነው። እያንዳንዱ ክፍል፣ ስለሚብራራው የይሖዋ ባሕርይ ጠቅለል ያለ ሐሳብ የያዘ መግቢያ አለው። ቀጣዮቹ ምዕራፎች ይሖዋ የተጠቀሰውን ባሕርይ በተለያዩ መንገዶች እንዴት እንዳንጸባረቀ ያብራራሉ። ከዚህም በተጨማሪ እያንዳንዱ ክፍል ኢየሱስ ያንን ባሕርይ እንዴት እንዳንጸባረቀ የሚገልጽ ምዕራፍ ያለው ከመሆኑም በላይ እኛም ያንኑ ባሕርይ በሕይወታችን ውስጥ እንዴት ማንጸባረቅ እንደምንችል የሚያብራራ ምዕራፍ ይዟል።
23, 24. (ሀ) “ለማሰላሰል የሚረዱ ጥያቄዎች” የሚለው ሣጥን የተዘጋጀበትን ዓላማ ግለጽ። (ለ) ማሰላሰል ወደ አምላክ ይበልጥ እንድንቀርብ የሚረዳን እንዴት ነው?
23 ከዚህኛው አንስቶ በሁሉም ምዕራፎች ውስጥ “ለማሰላሰል የሚረዱ ጥያቄዎች” የሚል ርዕስ ያለው ሣጥን ይገኛል። ለምሳሌ ያህል ገጽ 24 ላይ የሚገኘውን ሣጥን ተመልከት። ጥቅሶቹም ሆኑ ጥያቄዎቹ የተዘጋጁት ምዕራፉን ለመከለስ አይደለም። ከዚህ ይልቅ ከርዕሰ ጉዳዩ ጋር ግንኙነት ባላቸው ሌሎች አስፈላጊ ነጥቦች ላይ ማሰላሰል እንድትችል ለማገዝ ነው። ይህን ሣጥን ጥሩ አድርገህ ልትጠቀምበት የምትችለው እንዴት ነው? እያንዳንዱን ጥቅስ አውጥተህ በጥሞና አንብበው። ከዚያም ከጥቅሱ ጋር ተያይዞ የቀረበውን ጥያቄ ተመልከት። መልሱን ቆም ብለህ አስብ። ካስፈለገም ምርምር ልታደርግ ትችላለህ። በተጨማሪም ‘ይህ ሐሳብ ስለ ይሖዋ ምን ያስተምረኛል? ሕይወቴን ሊነካ የሚችለው እንዴት ነው? ሌሎችን ለመርዳት እንዴት ልጠቀምበት እችላለሁ?’ እያልክ ራስህን ጠይቅ።
24 በዚህ መንገድ ማሰላሰላችን ወደ ይሖዋ ይበልጥ እንድንቀርብ ሊረዳን ይችላል። ለምን? መጽሐፍ ቅዱስ፣ ማሰላሰልን ከልብ ጋር አዛምዶ ይገልጸዋል። (መዝሙር 19:14) ስለ አምላክ በተማርነው ነገር ላይ ከልብ በመነጨ የአድናቆት ስሜት ስናሰላስል ትምህርቱ ወደ ምሳሌያዊው ልባችን ዘልቆ ይገባል፤ ይህም አስተሳሰባችን እንዲለወጥ፣ ስሜታችን እንዲነካ ብሎም ለተግባር እንድንነሳሳ ያደርጋል። ከዚህም በተጨማሪ ለአምላክ ያለን ፍቅር ይጠነክራል፤ ይህ ፍቅር ደግሞ ይሖዋን ከማንም የበለጠ የቅርብ ወዳጃችን እንደሆነ አድርገን በማየት እሱን ለማስደሰት እንድንጥር ይገፋፋናል። (1 ዮሐንስ 5:3) እንዲህ ያለ ዝምድና ለመመሥረት የይሖዋን ባሕርያትና የተለያዩ ነገሮችን የሚያከናውንበትን መንገድ ማወቅ ያስፈልገናል። በቅድሚያ ግን ወደ አምላክ እንድንቀርብ የሚገፋፋንን አንድ የይሖዋ ባሕርይ ይኸውም ቅድስናውን እንመርምር።
a ለምሳሌ ያህል መጽሐፍ ቅዱስ ስለ አምላክ ፊት፣ ዓይን፣ ጆሮ፣ አፍንጫ፣ አፍ፣ ክንድና እግር ይናገራል። (መዝሙር 18:15፤ 27:8፤ 44:3፤ ኢሳይያስ 60:13፤ ማቴዎስ 4:4፤ 1 ጴጥሮስ 3:12) ለይሖዋ የተሰጡትን “ዓለት” ወይም “ጋሻ” እንደሚሉት ያሉ መግለጫዎችን ቃል በቃል እንደማንረዳቸው ሁሉ እነዚህ ምሳሌያዊ አገላለጾችም ቃል በቃል ሊወሰዱ አይገባም።—ዘዳግም 32:4፤ መዝሙር 84:11