በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችና ማብራሪያቸው

ራእይ 21:1—“አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር”

ራእይ 21:1—“አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር”

 “እኔም አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር አየሁ፤ የቀድሞው ሰማይና የቀድሞው ምድር አልፈዋልና፤ ባሕሩም ከእንግዲህ ወዲህ የለም።”—ራእይ 21:1 አዲስ ዓለም ትርጉም

 “ከዚህ በኋላ አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር አየሁ፤ የመጀመሪያው ሰማይና የመጀመሪያዪቱ ምድር ዐልፈዋልና፤ ባሕርም ከእንግዲህ ወዲህ አይኖርም።”—ራእይ 21:1 አዲሱ መደበኛ ትርጉም

የራእይ 21:1 ትርጉም

 ይህ ጥቅስ ዘይቤያዊ አገላለጽ በመጠቀም፣ በሰማይ ላይ ያለው የአምላክ መንግሥት የሰዎችን መንግሥታት በሙሉ እንደሚተካ ይገልጻል። የአምላክ መንግሥት ክፉዎችን ካጠፋ በኋላ በፈቃደኝነት በሚገዙለት ሰዎች በተዋቀረው አዲስ ኅብረተሰብ ላይ ይገዛል።

 የራእይ መጽሐፍ የተጻፈው “በምልክቶች” ነው። (ራእይ 1:1) በመሆኑም በዚህ ጥቅስ ላይ የሚገኘው ሰማይና ምድር ቃል በቃል ሰማይንና ምድርን የሚያመለክት ሳይሆን ምሳሌያዊ ነው ብሎ መደምደም ምክንያታዊ ነው። “አዲስ ሰማያትና አዲስ ምድር” የሚለው አገላለጽ በሌሎች ጥቅሶች ላይም ምሳሌያዊ በሆነ መንገድ ተሠርቶበታል። (ኢሳይያስ 65:17፤ 66:22፤ 2 ጴጥሮስ 3:13) እነዚህንና ሌሎች ጥቅሶችን መመርመራችን ሰማይና ምድር የሚሉት ቃላት ያላቸውን ትርጉም ለማወቅ ይረዳናል።

 “አዲስ ሰማይ።” መጽሐፍ ቅዱስ አንዳንድ ጊዜ “ሰማይ” የሚለውን ቃል አገዛዝን ወይም መንግሥትን ለማመልከት ይጠቀምበታል። (ኢሳይያስ 14:12-14፤ ዳንኤል 4:25, 26) አንድ የማመሣከሪያ ጽሑፍ በትንቢታዊ ራእዮች ላይ “ሰማይ ገዢን ወይም መንግሥትን በምሳሌያዊ ሁኔታ” እንደሚያመለክት ገልጿል። a በራእይ 21:1 ላይ የተጠቀሰው “አዲስ ሰማይ” የአምላክን መንግሥት ያመለክታል። “መንግሥተ ሰማያት” ተብሎም የሚጠራው በሰማይ ያለው ይህ መንግሥት በራእይ መጽሐፍና በሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት ላይ በተደጋጋሚ ተጠቅሷል። (ማቴዎስ 4:17፤ የሐዋርያት ሥራ 19:8፤ 2 ጢሞቴዎስ 4:18፤ ራእይ 1:9፤ 5:10፤ 11:15፤ 12:10) ኢየሱስ ንጉሥ ሆኖ የሚያስተዳድረው የአምላክ መንግሥት ወደፊት ‘የቀድሞውን ሰማይ’ ማለትም የሰዎችን መንግሥታት በሙሉ ይተካል።—ዳንኤል 2:44፤ ሉቃስ 1:31-33፤ ራእይ 19:11-18

 “አዲስ ምድር።” መጽሐፍ ቅዱስ ፕላኔቷ ምድር ፈጽሞ እንደማትጠፋ ወይም በሌላ እንደማትተካ ይናገራል። (መዝሙር 104:5፤ መክብብ 1:4) ታዲያ ምሳሌያዊው ምድር ምንድን ነው? መጽሐፍ ቅዱስ “ምድር” የሚለውን ቃል የሰው ልጆችን ለማመልከት ብዙ ጊዜ ይጠቀምበታል። (ዘፍጥረት 11:1፤ 1 ዜና መዋዕል 16:31፤ መዝሙር 66:4፤ 96:1) ስለዚህ “አዲስ ምድር” የሚለው አገላለጽ በሰማይ ላለው የአምላክ መንግሥት በፈቃደኝነት በሚገዙ ሰዎች የተዋቀረን አዲስ ኅብረተሰብ የሚያመለክት መሆን አለበት። “የቀድሞው ምድር” ማለትም የአምላክን መንግሥት የሚቃወሙ ሰዎች ያልፋሉ።

 “ባሕሩም ከእንግዲህ ወዲህ የለም።” በራእይ 21:1 ላይ እንደሚገኙት ሌሎች አገላለጾች ሁሉ ‘ባሕር’ የሚለው ቃልም ምሳሌያዊ ነው። በቀላሉ የሚናወጠው ባሕር ብዙ ችግርና ነውጥ የሚፈጥሩትን ከአምላክ የራቁ ሰዎች የሚያመለክት ጥሩ ምሳሌ ነው። (ኢሳይያስ 17:12, 13፤ 57:20፤ ራእይ 17:1, 15) እንዲህ ያሉ ሰዎችም ይጠፋሉ። መዝሙር 37:10 እንዲህ ይላል፦ “ለጥቂት ጊዜ ነው እንጂ ክፉዎች አይኖሩም፤ በቀድሞ ቦታቸው ትፈልጋቸዋለህ፤ እነሱ ግን በዚያ አይገኙም።”

የራእይ 21:1 አውድ

 የራእይ መጽሐፍ ‘በጌታ ቀን’ ስለሚከናወኑት ነገሮች ይናገራል። (ራእይ 1:10) በመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት መሠረት ይህ ቀን የጀመረው ኢየሱስ የአምላክ መንግሥት ንጉሥ ሆኖ መግዛት በጀመረበት በ1914 ነው። b ሆኖም ኢየሱስ ሥልጣን እንደያዘ መላዋን ምድር አይቆጣጠርም። እንዲያውም ሌሎች ትንቢቶች እንደሚገልጹት ‘በጌታ ቀን’ የመጀመሪያ ክፍል ላይ በዓለም ላይ ያለው ሁኔታ እየተባባሰ ይሄዳል። ይህ ወቅት ‘የመጨረሻዎቹ ቀናት’ ተብሎ ይጠራል። (2 ጢሞቴዎስ 3:1-5, 13፤ ማቴዎስ 24:3, 7፤ ራእይ 6:1-8፤ 12:12) በመከራ የተሞላው ይህ አስጨናቂ ወቅት ሲያበቃ የአምላክ መንግሥት አሮጌውን ምሳሌያዊ ሰማይና ምድር አስወግዶ ሰላምና ፍቅር የሰፈነበት አዲስ ዓለም ያመጣል። ከዚያም ‘አዲሱ ምድር’ ማለትም የአምላክ መንግሥት ተገዢዎች በተመቻቸ ሁኔታ ውስጥ ፍጹም ጤንነት አግኝተው ይኖራሉ።—ራእይ 21:3, 4

 የራእይ መጽሐፍን አጠቃላይ ይዘት ለማየት ይህን አጭር ቪዲዮ ተመልከት።

a በማክሊንቶክ እና ስትሮንግ የተዘጋጀው ሳይክሎፒዲያ (1891) ጥራዝ 4 ገጽ 122።