ለዮሐንስ የተገለጠለት ራእይ 6:1-17

  • በጉ የመጀመሪያዎቹን ስድስት ማኅተሞች ከፈተ (1-17)

    • በነጭ ፈረስ ላይ የተቀመጠ ድል አድራጊ (1, 2)

    • ከምድር ላይ ሰላምን የሚወስድ ደማቅ ቀይ ቀለም ያለው ፈረስ ጋላቢ (3, 4)

    • ረሃብ የሚያመጣው የጥቁሩ ፈረስ ጋላቢ (5, 6)

    • ሞት የተባለው የግራጫው ፈረስ ጋላቢ (7, 8)

    • የታረዱ ሰዎች ነፍሳት ከመሠዊያው በታች ታዩ (9-11)

    • ታላቅ የምድር ነውጥ (12-17)

6  እኔም በጉ+ ከሰባቱ ማኅተሞች አንዱን ሲከፍት አየሁ፤+ ከአራቱ ሕያዋን ፍጥረታትም+ አንዱ እንደ ነጎድጓድ ባለ ድምፅ “ና!” ሲል ሰማሁ። 2  እኔም አየሁ፣ እነሆ ነጭ ፈረስ ነበር፤+ በእሱም ላይ የተቀመጠው ቀስት ነበረው፤ አክሊልም ተሰጠው፤+ እሱም ድል እያደረገ ወጣ፤ ድሉንም ለማጠናቀቅ ወደ ፊት ገሰገሰ።+ 3  ሁለተኛውን ማኅተም በከፈተ ጊዜ ሁለተኛው ሕያው ፍጡር+ “ና!” ሲል ሰማሁ። 4  ደማቅ ቀይ ቀለም ያለው ሌላ ፈረስ ወጣ፤ በእሱም ላይ ለተቀመጠው ሰዎች እርስ በርሳቸው ይተራረዱ ዘንድ ሰላምን ከምድር እንዲወስድ ተፈቀደለት፤ እንዲሁም ትልቅ ሰይፍ ተሰጠው።+ 5  ሦስተኛውን ማኅተም በከፈተ ጊዜ+ ሦስተኛው ሕያው ፍጡር+ “ና!” ሲል ሰማሁ። እኔም አየሁ፣ እነሆ ጥቁር ፈረስ ነበር፤ በእሱም ላይ የተቀመጠው በእጁ ሚዛን ይዞ ነበር። 6  ከአራቱ ሕያዋን ፍጥረታት መካከል እንደ ድምፅ ያለ ነገር “አንድ እርቦ* ስንዴ በዲናር፣*+ ሦስት እርቦ ገብስም በዲናር፤ ደግሞም የወይራ ዘይቱንና የወይን ጠጁን አትጉዳ” ሲል ሰማሁ።+ 7  አራተኛውን ማኅተም በከፈተ ጊዜ አራተኛው ሕያው ፍጡር+ “ና!” ሲል ሰማሁ። 8  እኔም አየሁ፣ እነሆ ግራጫ ፈረስ ነበር፤ በእሱም ላይ የተቀመጠው ስሙ ሞት ነበር። መቃብርም* በቅርብ ይከተለው ነበር። ሞትና መቃብርም በረጅም ሰይፍ፣ በምግብ እጥረት፣+ በገዳይ መቅሰፍትና በምድር አራዊት እንዲገድሉ በምድር አንድ አራተኛ ላይ ሥልጣን ተሰጣቸው።+ 9  አምስተኛውን ማኅተም በከፈተ ጊዜ በአምላክ ቃል የተነሳና በሰጡት ምሥክርነት የተነሳ የታረዱትን ሰዎች ነፍሳት*+ ከመሠዊያው በታች+ አየሁ።+ 10  እነሱም “ቅዱስና እውነተኛ የሆንከው ሉዓላዊ ጌታ ሆይ፣+ በምድር በሚኖሩት ላይ የማትፈርደውና ደማችንን የማትበቀለው እስከ መቼ ነው?”+ ብለው በታላቅ ድምፅ ጮኹ። 11  ለእያንዳንዳቸውም ነጭ ልብስ ተሰጣቸው፤+ እንዲሁም ወደፊት እንደ እነሱ የሚገደሉት ባልንጀሮቻቸው የሆኑ ባሪያዎችና የወንድሞቻቸው ቁጥር እስኪሞላ ድረስ ለጥቂት ጊዜ እንዲጠብቁ ተነገራቸው።+ 12  ስድስተኛውንም ማኅተም ሲከፍት አየሁ፤ ታላቅ የምድር ነውጥም ተከሰተ፤ ፀሐይም ከፀጉር* እንደተሠራ ማቅ ጠቆረች፤ ጨረቃም ሙሉ በሙሉ ደም መሰለች፤+ 13  ኃይለኛ ነፋስ የበለስን ዛፍ ሲያወዛውዝ ያልበሰሉት ፍሬዎች ከዛፉ ላይ እንደሚረግፉ፣ የሰማይ ከዋክብትም ወደ ምድር ወደቁ። 14  ሰማይም እየተጠቀለለ እንዳለ የመጽሐፍ ጥቅልል ከቦታው ተነሳ፤+ እንዲሁም ተራሮች ሁሉና ደሴቶች ሁሉ ከቦታቸው ተወገዱ።+ 15  ከዚያም የምድር ነገሥታት፣ ከፍተኛ ባለሥልጣናት፣ የጦር አዛዦች፣ ሀብታሞች፣ ብርቱዎች፣ ባሪያዎች ሁሉና ነፃ ሰዎች ሁሉ በዋሻዎች ውስጥና ተራራ ላይ ባሉ ዓለቶች መካከል ተደበቁ።+ 16  ተራሮቹንና ዓለቶቹንም እንዲህ እያሉ ተማጸኑ፦ “በላያችን ውደቁና+ በዙፋኑ ላይ ከተቀመጠው+ ፊትና ከበጉ+ ቁጣ ሰውሩን፤ 17  ምክንያቱም ቁጣቸውን የሚገልጹበት ታላቁ ቀን መጥቷል፤+ ማንስ ሊቆም ይችላል?”+

የግርጌ ማስታወሻዎች

^ አንድ እርቦ ስንዴ 0.7 ኪሎ ግራም ገደማ ይመዝናል። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።
^ የሮም የብር ሳንቲም ሲሆን አንድ ሠራተኛ ከሚከፈለው የቀን ደሞዝ ጋር እኩል ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።
^ ወይም “ሐዲስም።” የሰው ልጆችን ሁሉ መቃብር ያመለክታል። የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
^ መሠዊያው ላይ የፈሰሰውን ለሕይወታቸው ወሳኝ የሆነውን ደማቸውን እንደሚያመለክት ግልጽ ነው። የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
^ የፍየል ፀጉር ሳይሆን አይቀርም።