በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ድንግል ማርያም—መጽሐፍ ቅዱስ ስለ እሷ ምን ይላል?

ድንግል ማርያም—መጽሐፍ ቅዱስ ስለ እሷ ምን ይላል?

 መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

 መጽሐፍ ቅዱስ የኢየሱስ እናት የሆነችው ማርያም፣ ድንግል ሆና እያለ ኢየሱስን የመውለድ ልዩ መብት እንዳገኘች ይናገራል። መጽሐፍ ቅዱስ በኢሳይያስ መጽሐፍ ላይ ስለዚህ ተአምር አስቀድሞ የተናገረ ሲሆን በማቴዎስና በሉቃስ ወንጌል ላይ ደግሞ ይህ ተአምር ፍጻሜውን ያገኘው እንዴት እንደሆነ ገልጿል።

 ኢሳይያስ ስለ መሲሑ መገለጥ በተናገረው ትንቢት ላይ “እነሆ፣ ወጣቷ ትፀንሳለች፤ ወንድ ልጅም ትወልዳለች” ብሏል። (ኢሳይያስ 7:14) የወንጌል ጸሐፊው ማቴዎስ፣ ኢሳይያስ የተናገረው ትንቢት ማርያም ኢየሱስን በፀነሰችበት ጊዜ ፍጻሜውን እንዳገኘ በመንፈስ መሪነት ጽፏል። ማቴዎስ፣ ማርያም ተአምራዊ በሆነ መንገድ እንደፀነሰች ከገለጸ በኋላ እንዲህ ብሏል፦ “ይህ ሁሉ የሆነው ይሖዋ በነቢዩ በኩል እንዲህ ሲል የተናገረው ይፈጸም ዘንድ ነው፦ ‘እነሆ! ድንግል a ትፀንሳለች፤ ወንድ ልጅም ትወልዳለች፤ ስሙንም አማኑኤል ይሉታል’፤ ትርጉሙም ‘አምላክ ከእኛ ጋር ነው’ ማለት ነው።”—ማቴዎስ 1:22, 23

 የወንጌል ጸሐፊው ሉቃስም ማርያም ተአምራዊ በሆነ መንገድ እንደፀነሰች ዘግቧል። ሉቃስ፣ “አምላክ መልአኩ ገብርኤልን . . . ከዳዊት ቤት ለሆነ ዮሴፍ ለሚባል ሰው ወደታጨች አንዲት ድንግል [እንደላከው]” እንዲሁም “የድንግሊቱ ስም ማርያም” እንደሆነ ጽፏል። (ሉቃስ 1:26, 27) ማርያም ራሷም ብትሆን ድንግል እንደሆነች ተናግራለች። የመሲሑ የኢየሱስ እናት እንደምትሆን ስትሰማ “እኔ ከወንድ ጋር ግንኙነት ፈጽሜ ስለማላውቅ ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል?” በማለት ጠይቃለች።—ሉቃስ 1:34

 ማርያም ድንግል ሆና ሳለ ልትፀንስ የቻለችው እንዴት ነው?

 ማርያም የፀነሰችው በመንፈስ ቅዱስ ይኸውም በሥራ ላይ ባለው የአምላክ ኃይል አማካኝነት ነው። (ማቴዎስ 1:18) ማርያም እንዲህ ተብሎ ተነግሯታል፦ “መንፈስ ቅዱስ በአንቺ ላይ ይመጣል፤ የልዑሉም ኃይል በአንቺ ላይ ያርፋል። ስለሆነም የሚወለደው ልጅ ቅዱስና የአምላክ ልጅ ይባላል።” b (ሉቃስ 1:35) አምላክ ተአምራዊ በሆነ መንገድ የልጁን ሕይወት ወደ ማርያም ማህፀን በማዛወር ማርያም እንድትፀንስ አድርጓል።

 ኢየሱስ ከድንግል መወለድ ያስፈለገው ለምንድን ነው?

 ኢየሱስ ፍጽምና ከጎደለው አባት አልተወለደም። ከዚህ ይልቅ አምላክ ራሱ የኢየሱስን ሕይወት ወደ ድንግል ማርያም ማህፀን አዛውሮታል። በመሆኑም ኢየሱስ ፍጹም የሆነ ሰብዓዊ አካል ሊኖረው እንዲሁም የሰው ልጆችን ከኃጢአትና ከሞት ሊያድን ችሏል። (ዮሐንስ 3:16፤ ዕብራውያን 10:5) ከሁኔታዎች መረዳት እንደሚቻለው፣ ኢየሱስ ፅንስ ሆኖ በማርያም ማህፀን ውስጥ ሳለ ኃጢአትን እንዳይወርስ የአምላክ ቅዱስ መንፈስ ጥበቃ አድርጎለታል።—ሉቃስ 1:35

 በመሆኑም ኢየሱስ ፍጹም ሰው ሆኖ ሊወለድ ማለትም አዳም ኃጢአት ከመሥራቱ በፊት የነበረው ዓይነት ሕይወት ሊኖረው ችሏል። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ኢየሱስ ሲናገር “እሱ ምንም ኃጢአት አልሠራም” ይላል። (1 ጴጥሮስ 2:22) ፍጹም ሰው የነበረው ኢየሱስ፣ የሰው ልጆችን ከኃጢአትና ከሞት ለመዋጀት የሚያስፈልገውን ቤዛ መክፈል ችሏል።—1 ቆሮንቶስ 15:21, 22፤ 1 ጢሞቴዎስ 2:5, 6

 ማርያም እስከ መጨረሻው ድንግል ሆና ቀጥላለች?

 መጽሐፍ ቅዱስ ማርያም ሕይወቷን ሁሉ ድንግል ሆና እንደኖረች አይናገርም። ከዚህ ይልቅ ማርያም ሌሎች ልጆች እንደነበሯት ይገልጻል።—ማቴዎስ 12:46፤ ማርቆስ 6:3፤ ሉቃስ 2:7፤ ዮሐንስ 7:5

መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስ ወንድሞችና እህቶች እንደነበሩት ይናገራል

 መጽሐፍ ቅዱስ “ማርያም ስትፀነስ ጀምሮ ከኃጢአት ነፃ ነበረች” የሚለውን መሠረተ ትምህርት ይደግፋል?

 አይደግፍም። ኒው ካቶሊክ ኢንሳይክሎፒዲያ እንደገለጸው ይህ መሠረተ ትምህርት “ድንግል ማርያም ከሕይወቷ መጀመሪያ ማለትም ከተፀነሰችበት ጊዜ አንስቶ ከመጀመሪያው ኃጢአት ነፃ እንደሆነች ያስተምራል። ሌላው የሰው ዘር በሙሉ በኃጢአት ተበክሎ ይወለዳል . . . ማርያም ግን ለየት ባለ ጸጋ አማካኝነት የመጀመሪያውን ኃጢአት እንዳትወርስ ጥበቃ ተደርጎላታል።” c

 ከዚህ በተቃራኒ፣ መጽሐፍ ቅዱስ ማርያም ከመጀመሪያው ኃጢአት ነፃ እንደሆነች አንድም ቦታ ላይ አያስተምርም። (መዝሙር 51:5፤ ሮም 5:12) እንዲያውም ማርያም፣ የሙሴ ሕግ እናቶች እንዲያቀርቡ የሚያዝዘውን የኃጢአት ማስተሰረያ መሥዋዕት ያቀረበች ሲሆን ይህም ኃጢአት እንደነበረባት በግልጽ ያሳያል። (ዘሌዋውያን 12:2-8፤ ሉቃስ 2:21-24) ኒው ካቶሊክ ኢንሳይክሎፒዲያ እንዲህ ይላል፦ “‘ማርያም ስትፀነስ ጀምሮ ከኃጢአት ነፃ ነበረች’ የሚለው መሠረተ ትምህርት በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ በግልጽ አይገኝም . . . [ይህ ትምህርት] ቤተ ክርስቲያኗ የደረሰችበት ድምዳሜ ነው።”

 ለማርያም ምን አመለካከት ሊኖረን ይገባል?

 ማርያም በእምነት፣ በታዛዥነት፣ በትሕትናና መንፈሳዊ ሰው በመሆን ረገድ ግሩም ምሳሌ ትታልናለች። በመሆኑም ምሳሌያቸውን ልንከተላቸው ከሚገባን ታማኝ የአምላክ አገልጋዮች መካከል አንዷ ናት።—ዕብራውያን 6:12

 ማርያም የኢየሱስ እናት በመሆን ልዩ ሚና የተጫወተች ቢሆንም መጽሐፍ ቅዱስ ማርያምን ልናመልክ ወይም ወደ እሷ ልንጸልይ እንደሚገባ አያስተምርም። ኢየሱስ ለእናቱ ለየት ያለ ክብር አልሰጠም፤ ተከታዮቹንም እንዲህ እንዲያደርጉ አልነገራቸውም። እንዲያውም ከወንጌል ዘገባዎችና አንድ ጊዜ ብቻ ከተጠቀሰችበት ከሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ በቀር አዲስ ኪዳን ተብለው በተለምዶ በሚጠሩት በቀሪዎቹ 22 መጻሕፍት ውስጥ ስለ ማርያም የሚናገር ሐሳብ አናገኝም።—የሐዋርያት ሥራ 1:14

 በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ ክርስቲያኖች ማርያምን ማምለክ ቀርቶ ለየት ያለ ትኩረት እንደሰጧት እንኳ የሚገልጽ አንዳች ማስረጃ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አናገኝም። ከዚህ ይልቅ መጽሐፍ ቅዱስ ክርስቲያኖች አምላክን ብቻ ሊያመልኩ እንደሚገባ ያስተምራል።—ማቴዎስ 4:10

a በኢሳይያስ ትንቢት ላይ “ወጣቷ” ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጥ ቃል አልማ የሚለው ሲሆን ቃሉ ድንግል የሆነችን ወይም ያልሆነችን ሴት ሊያመለክት ይችላል። ማቴዎስ ግን በአምላክ መንፈስ መሪነት፣ ድንግል የሆነችን ሴት ብቻ የሚያመለክተውን ፓርቴኖስ የሚለውን የግሪክኛ ቃል ተጠቅሟል።

b አንዳንዶች “የአምላክ ልጅ” የሚለው አገላለጽ አምላክ ከሴት ጋር ግንኙነት እንደፈጸመ የሚያመለክት እንደሆነ ስለሚሰማቸው ይህን አገላለጽ መጠቀም ተገቢ እንዳልሆነ ይናገራሉ። ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ አይልም። እንዲያውም ኢየሱስ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ “የአምላክ ልጅ” እንዲሁም “የፍጥረት ሁሉ በኩር” ተብሎ ተጠርቷል፤ ይህ መጠሪያ የተሰጠው በቀጥታ በአምላክ የተፈጠረው የመጀመሪያውና ብቸኛው አካል እሱ ስለሆነ ነው። (ቆላስይስ 1:13-15) በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ የመጀመሪያውን ሰው አዳምን “የአምላክ ልጅ” በማለት ይጠራዋል። (ሉቃስ 3:38) አዳም እንዲህ ተብሎ የተጠራው በአምላክ ስለተፈጠረ ነው።

c ሁለተኛው እትም፣ ጥራዝ 7 ገጽ 331