ማርያም የአምላክ እናት ናት?
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?
አይደለችም። መጽሐፍ ቅዱስ ማርያም የአምላክ እናት እንደሆነች አያስተምርም፤ በተጨማሪም ክርስቲያኖች ማርያምን ሊያመልኳት ወይም እንደ ቅዱስ አድርገው ሊመለከቷት እንደሚገባ አይናገርም። a እስቲ የሚከተለውን አስብ፦
ማርያም የአምላክ እናት እንደሆነች ፈጽሞ ተናግራ አታውቅም። መጽሐፍ ቅዱስ ማርያም አምላክን ሳይሆን ‘የአምላክን ልጅ’ እንደወለደች ይናገራል።—ማርቆስ 1:1፤ ሉቃስ 1:32
ኢየሱስ ክርስቶስ ማርያም የአምላክ እናት እንደሆነች አንድም ቦታ አልተናገረም፤ የተለየ ክብር ሊሰጣት እንደሚገባም አልጠቀሰም። በአንድ ወቅት አንዲት ሴት፣ ማርያም የእሱ እናት የመሆን አስደሳች መብት በማግኘቷ ምክንያት ለየት ያለ ትኩረት ልትሰጣት ፈልጋ ነበር፤ ኢየሱስ ግን “ደስተኞችስ የአምላክን ቃል ሰምተው የሚጠብቁት ናቸው!” በማለት አርሟታል።—ሉቃስ 11:27, 28
“የአምላክ እናት” እንዲሁም “ቲኦቶኮስ” (ወላዲተ አምላክ) የሚሉት ሐረጎች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አይገኙም።
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ‘የሰማይ ንግሥት’ ተብላ የተጠራችው ማርያም ሳትሆን ከሃዲ የሆኑ እስራኤላውያን ያመልኳት የነበረችው የሐሰት አምላክ ናት። (ኤርምያስ 44:15-19) ‘የሰማይ ንግሥት’ ተብላ የተጠራችው የባቢሎናውያን አምላክ የሆነችው ኢሽታር (አስታርቴ) ሳትሆን አትቀርም።
ጥንት የነበሩ ክርስቲያኖች ማርያምን አላመለኩም፤ የተለየ ክብርም አልሰጧትም። አንድ የታሪክ ምሁር እንደገለጹት የጥንቶቹ ክርስቲያኖች “ኑፋቄዎችን ይቃወሙ የነበረ ከመሆኑም ሌላ ለማርያም ተገቢ ያልሆነ ትኩረት መስጠት ‘እንስት አምላክን ያመልካሉ የሚል ጥርጣሬ ያስነሳል’ የሚል ስጋት ሳይፈጥርባቸው አይቀርም።”—ኢን ኩዌስት ኦቭ ዘ ጂዊሽ ሜሪ
መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ ምንጊዜም እንዳለ ይናገራል። (መዝሙር 90:1, 2፤ ኢሳይያስ 40:28) አምላክ መጀመሪያ ስለሌለው እናት ልትኖረው አትችልም። በተጨማሪም ማርያም አምላክን በማህፀኗ መያዝ አትችልም፤ ምክንያቱም አምላክን ሰማያት እንኳ ሊይዙት እንደማይችሉ መጽሐፍ ቅዱስ ይገልጻል።—1 ነገሥት 8:27
ማርያም—የኢየሱስ እንጂ “የአምላክ እናት” አይደለችም
ማርያም አይሁዳዊ ስትሆን የዘር ሐረጓም በንጉሥ ዳዊት በኩል የሚመጣ ነው። (ሉቃስ 3:23-31) ማርያም እምነት ያላትና ለአምላክ ያደረች ሰው ስለነበረች አምላክ በእጅጉ ባርኳታል። (ሉቃስ 1:28) አምላክ የኢየሱስ እናት እንድትሆን መርጧታል። (ሉቃስ 1:31, 35) ማርያምና ባሏ ዮሴፍ ሌሎች ልጆችም ነበሯቸው።—ማርቆስ 6:3
መጽሐፍ ቅዱስ፣ ማርያም የኢየሱስ ደቀ መዝሙር ሆና እንደነበር ቢናገርም ከዚያ ሌላ ስለ እሷ ተጨማሪ መረጃ አይሰጥም።—የሐዋርያት ሥራ 1:14
a በርካታ ሃይማኖቶች ማርያም የአምላክ እናት እንደሆነች ያስተምራሉ። ማርያምን “የሰማይ ንግሥት” ወይም ቲኦቶኮስ (በግሪክኛ “ወላዲተ አምላክ” ማለት ነው) ብለው ይጠሯታል።