በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ኢየሱስ ትዳር መሥርቶ ነበር? ኢየሱስ ወንድሞችና እህቶች ነበሩት?

ኢየሱስ ትዳር መሥርቶ ነበር? ኢየሱስ ወንድሞችና እህቶች ነበሩት?

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

 መጽሐፍ ቅዱስ፣ ኢየሱስ ትዳር ስለ መመሥረት አለመመሥረቱ በይፋ የሚናገረው ነገር የለም፤ ትዳር እንዳልመሠረተ በግልጽ የሚጠቁም ሐሳብ ግን እናገኛለን። a እስቲ የሚከተሉትን ሐሳቦች ተመልከት፦

  1.   መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ኢየሱስ ቤተሰብ እንዲሁም በሚያገለግልበት ጊዜም ሆነ በተሰቀለበት ወቅት ከጎኑ ስለነበሩ ሴቶች በተደጋጋሚ ጊዜ ይናገራል፤ ሚስት እንዳለው የተገለጸበት ቦታ ግን የለም። (ማቴዎስ 12:46, 47፤ ማርቆስ 3:31, 32፤ 15:40፤ ሉቃስ 8:2, 3, 19, 20፤ ዮሐንስ 19:25) መጽሐፍ ቅዱስ ስለዚህ ጉዳይ የማይናገርበት ዋነኛው ምክንያት ኢየሱስ ትዳር መሥርቶ የማያውቅ መሆኑ ነው።

  2.   ኢየሱስ፣ አምላክን ይበልጥ ለማገልገል ሲሉ ሳያገቡ የሚኖሩ ሰዎችን አስመልክቶ ሲናገር “ይህን [ማለትም ነጠላነትን] ሊቀበለው የሚችል ይቀበለው” ብሏል። (ማቴዎስ 19:10-12) ራሳቸውን ሙሉ በሙሉ ለአምላክ ለመስጠት ሲሉ ትዳር ላለመመሥረት ለሚወስኑ ሁሉ ጥሩ አርዓያ ሆኗል።—ዮሐንስ 13:15፤ 1 ቆሮንቶስ 7:32-38

  3.   ኢየሱስ ሊሞት ሲል እናቱ እንክብካቤ ማግኘት የምትችልበትን መንገድ አመቻችቶ ነበር። (ዮሐንስ 19:25-27) ኢየሱስ ትዳር መሥርቶ ወይም ልጆች ኖረውት ቢሆን ኖሮ እነሱም ተመሳሳይ እንክብካቤ የሚያገኙበትን መንገድ ያመቻች እንደነበር ምንም ጥያቄ የለውም።

  4.   መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስ ለባሎች ምሳሌ እንደሆነ ይናገራል፤ ይሁን እንጂ ሚስቱን እንዴት ይንከባከብ እንደነበረ የሚገልጽ ሐሳብ አናገኝም። ከዚህ ይልቅ እንዲህ ይላል፦ “ባሎች ሆይ፣ ክርስቶስ ጉባኤውን እንደወደደና ለእሱ ራሱን አሳልፎ እንደሰጠ ሁሉ እናንተም ሚስቶቻችሁን መውደዳችሁን ቀጥሉ።” (ኤፌሶን 5:25) ኢየሱስ ምድር ሳለ ትዳር መሥርቶ ቢሆን ኖሮ በዚህ ጥቅስ ላይ ባልነቱን ምሳሌያዊ በሆነ መንገድ ከመግለጽ ይልቅ ቃል በቃል የአንዲት ሴት ባል ሆኖ የተወውን ፍጹም ምሳሌ መጥቀሱ ይበልጥ ተስማሚ አይሆንም ነበር?

ኢየሱስ ወንድሞችና እህቶች ነበሩት?

 አዎ፣ ኢየሱስ ቢያንስ ስድስት ወንድሞችና እህቶች ነበሩት። ከወንድሞቹ መካከል ያዕቆብ፣ ዮሴፍ፣ ስምዖን እና ይሁዳ ይገኙበታል፤ እንዲሁም ቢያንስ ሁለት እህቶች ነበሩት። (ማቴዎስ 13:54-56፤ ማርቆስ 6:3) እነዚህ ልጆች የኢየሱስ እናት ማርያም ከባሏ ከዮሴፍ የወለደቻቸው ናቸው። (ማቴዎስ 1:25) ኢየሱስ የማርያም ‘የበኩር ልጅ’ እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል፤ ይህም ሌሎች ልጆች እንዳሏት ይጠቁማል።—ሉቃስ 2:7

የኢየሱስ ወንድሞችን አስመልክቶ የሚነገሩ የተሳሳቱ አመለካከቶች

 አንዳንዶች ማርያም ዕድሜዋን ሙሉ ድንግል ሆና ኖራለች የሚለውን ሐሳብ ለመደገፍ ሲሉ “ወንድሞች” የሚለው ቃል የተለየ ትርጉም እንዳለው ይናገራሉ። ለምሳሌ የኢየሱስ ወንድሞች የተባሉት ዮሴፍ ከቀድሞ ሚስቱ የወለዳቸው ልጆች እንደሆኑ የሚሰማቸው ሰዎች አሉ። ይሁንና ኢየሱስ ለዳዊት ቃል የተገባለትን ንግሥና እንደወረሰ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (2 ሳሙኤል 7:12, 13፤ ሉቃስ 1:32) ዮሴፍ ከኢየሱስ በዕድሜ የሚበልጡ ልጆች ቢኖሩት ኖሮ ወራሽ የሚሆነው ትልቁ የዮሴፍ ልጅ ነበር።

 ወንድሞች የሚለው ቃል የኢየሱስን ደቀ መዛሙርት ወይም መንፈሳዊ ወንድሞች የሚያመለክት ሊሆን ይችላል? ይህ ሐሳብ “ወንድሞቹም ቢሆኑ አላመኑበትም ነበር” ከሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ ሐሳብ ጋር የሚጋጭ ነው። (ዮሐንስ 7:5) እንዲያውም የኢየሱስ ወንድሞችና ደቀ መዛሙርቱ አንድ ቦታ ላይ ተነጣጥለው የተጠቀሱበት ጊዜ አለ።—ዮሐንስ 2:12

 ሌላው መላምት ደግሞ የኢየሱስ ወንድሞች የተባሉት የአጎቱ ወይም የአክስቱ ልጆች ናቸው የሚለው ነው። ይሁን እንጂ በግሪክኛ የተጻፉት የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች “ወንድምን፣” “ዘመድን” እና “የአጎት ልጅን” ለማመልከት የሚጠቀሙባቸው ቃላት የተለያዩ ናቸው። (ሉቃስ 21:16፤ ቆላስይስ 4:10) ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁራን የኢየሱስ ወንድሞችና እህቶች የተባሉት የእውነት ወንድሞቹና እህቶቹ እንደሆኑ ይስማማሉ። ለምሳሌ ዚ ኤክሲፖዚተርስ ባይብል ኮሜንታሪ እንዲህ ብሏል፦ “[የኢየሱስ] ‘ወንድሞች’ . . . የሚለው አገላለጽ የማርያምንና የዮሴፍን ልጆች ማለትም በእናቱ በኩል ያሉትን የኢየሱስ የሥጋ ወንድሞች የሚያመለክት መሆን አለበት።” b

a መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስ ሙሽራ እንደሆነ አድርጎ የሚገልጽበት ቦታ አለ፤ ይሁንና በጥቅሱ ዙሪያ ያለውን ሐሳብ ስንመለከት ይህ አገላለጽ ምሳሌያዊ እንደሆነ እንረዳለን።—ዮሐንስ 3:28, 29፤ 2 ቆሮንቶስ 11:2

b በተጨማሪም እነዚህን መጻሕፍት ተመልከት፦ The Gospel According to St. Mark, Second Edition, by Vincent Taylor, page 249, and A Marginal Jew—Rethinking the Historical Jesus, by John P. Meier, Volume 1, pages 331-332