ዘሌዋውያን 12:1-8

  • ከወሊድ በኋላ የሚከናወን የመንጻት ሥርዓት (1-8)

12  ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦ 2  “እስራኤላውያንን እንዲህ በላቸው፦ ‘አንዲት ሴት ብታረግዝና* ወንድ ልጅ ብትወልድ በወር አበባዋ ወቅት እንደምትረክሰው ሁሉ ለሰባት ቀን ትረክሳለች።+ 3  ሕፃኑም በስምንተኛው ቀን ይገረዛል።+ 4  እሷም ከደም ራሷን ለማንጻት ለቀጣዮቹ 33 ቀናት ትቆያለች። የምትነጻባቸው ቀናት እስኪያበቁ ድረስ ምንም ዓይነት ቅዱስ ነገር መንካትም ሆነ ወደ ቅዱሱ ስፍራ መግባት የለባትም። 5  “‘ሴት ልጅ ከወለደች ደግሞ በወር አበባዋ ወቅት እንደምትረክሰው ሁሉ ለ14 ቀን ትረክሳለች። ከደም ራሷን ለማንጻትም ለቀጣዮቹ 66 ቀናት ትቆያለች። 6  ሴትየዋ ወንድ ልጅ ወይም ሴት ልጅ ወልዳ የመንጻቷ ጊዜ ሲያበቃ ለሚቃጠል መባ እንዲሆን አንድ ዓመት ገደማ የሆነው የበግ ጠቦት፣+ ለኃጢአት መባ እንዲሆን ደግሞ አንድ የርግብ ጫጩት ወይም አንድ ዋኖስ ወደ መገናኛ ድንኳኑ መግቢያ ወደ ካህኑ ታመጣለች። 7  እሱም መባዎቹን በይሖዋ ፊት በማቅረብ ያስተሰርይላታል፤ እሷም ከሚፈሳት ደም ትነጻለች። ወንድ ልጅም ሆነ ሴት ልጅ ለወለደች ሴት የሚሠራው ሕግ ይህ ነው። 8  ሆኖም ሴትየዋ በግ ለማቅረብ አቅሟ የማይፈቅድላት ከሆነ ሁለት ዋኖሶች ወይም ሁለት የርግብ ጫጩቶች ታምጣ፤+ አንዱ ለሚቃጠል መባ ሌላው ደግሞ ለኃጢአት መባ ይሆናል። ካህኑም ያስተሰርይላታል፤ እሷም ንጹሕ ትሆናለች።’”

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “ዘር ብትፀንስና።”