በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አምላክን ፈልገን ማግኘት እንችላለን?

አምላክን ፈልገን ማግኘት እንችላለን?

“አምላክ ከሰው የመረዳት ችሎታ በላይ ነው።”—የእስክንድርያው ፋይሎ፣ የመጀመሪያው መቶ ዘመን ፈላስፋ

‘አምላክ ከእያንዳንዳችን የራቀ አይደለም።’—የጠርሴሱ ሳውል፣ በመጀመሪያው መቶ ዘመን አቴንስ ውስጥ ለነበሩ ፈላስፎች የተናገረው

ከላይ ከሰፈሩት ሁለት ሐሳቦች መካከል የአንተን አመለካከት የሚገልጸው የትኛው ነው? ብዙ ሰዎች የጠርሴሱ ሳውል (ሐዋርያው ጳውሎስ ተብሎም ይጠራል) የተናገረውን ሐሳብ የሚያበረታታና የሚያጽናና ሆነው አግኝተውታል። (የሐዋርያት ሥራ 17:26, 27) መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ የመሰሉ ሌሎች ሐሳቦችንም ይዟል። ለምሳሌ ያህል፣ ኢየሱስ ባቀረበው ጸሎት ላይ ተከታዮቹ አምላክን ማወቅና ከእሱ ዘንድ በረከት ማግኘት እንደሚችሉ በእርግጠኝነት ጠቅሶ ነበር።—ዮሐንስ 17:3

ይሁን እንጂ እንደ ፋይሎ ያሉ ፈላስፎች ከዚህ የተለየ አመለካከት ነበራቸው። አምላክ ከሰው የመረዳት ችሎታ በላይ ስለሆነ ፈጽሞ ልናውቀው እንደማንችል የሚጠቁም ሐሳብ ሰንዝረዋል። ይሁንና ሐቁ ምንድን ነው?

ሰዎች አምላክን በተመለከተ ለመረዳት የሚከብዷቸው አንዳንድ ነገሮች እንዳሉ መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ ይናገራል። ለምሳሌ ያህል፣ ፈጣሪ ምን ያህል ዘመን እንደኖረ እንዲሁም የአእምሮውን ችሎታና የጥበቡን ጥልቀት መለካት፣ በቁጥር ማስላት ወይም መረዳት አይቻልም። በአጭሩ እነዚህ ነገሮች ከሰው የመረዳት ችሎታ በላይ ናቸው። ይሁን እንጂ አምላክን በተመለከተ የተገለጹት እነዚህ ነገሮች እሱን ለማወቅ እንቅፋት አይሆኑብንም። እንዲያውም በእነዚህ ጉዳዮች ላይ ማሰላሰላችን ‘ወደ አምላክ እንድንቀርብ’ ሊረዳን ይችላል። (ያዕቆብ 4:8) እስቲ ከሰው የመረዳት ችሎታ በላይ ከሆኑ ነገሮች መካከል ጥቂት ምሳሌዎችን እንመልከት። ከዚያም አምላክን በተመለከተ ያለ ምንም ችግር መረዳት የምንችላቸውን አንዳንድ ነገሮች እንመረምራለን።

ከመረዳት አቅም በላይ የሆኑት ነገሮች የትኞቹ ናቸው?

የአምላክ ዘላለማዊ ሕልውና፦ መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ “ከዘላለም እስከ ዘላለም” እንደሚኖር ይናገራል። (መዝሙር 90:2) በሌላ አባባል አምላክ መጀመሪያ አልነበረውም፣ መጨረሻም የለውም። ከሰው አመለካከት አንጻር ሲታይ ‘የዘመኑ ቁጥር ከመረዳት ችሎታ በላይ ነው።’—ኢዮብ 36:26

ይህን ማወቅህ እንዴት ይጠቅምሃል? አምላክ፣ እሱን በሚገባ ካወቅከው የዘላለም ሕይወት እንደምታገኝ ቃል ገብቶልሃል። (ዮሐንስ 17:3) አምላክ ራሱ ለዘላለም የሚኖር ባይሆን ኖሮ ይህ ተስፋ ምን ያህል ተአማኒነት ይኖረው ነበር? እንዲህ ዓይነቱን ተስፋ መፈጸም የሚችለው ‘የዘላለሙ ንጉሥ’ ብቻ ነው።—1 ጢሞቴዎስ 1:17

የአምላክ አእምሮ፦ መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ ሐሳብ ከእኛ ሐሳብ እጅግ ከፍ ያለ በመሆኑ “ማስተዋሉ አይመረመርም” በማለት ይናገራል። (ኢሳይያስ 40:28፤ 55:9) መጽሐፍ ቅዱስ “ያስተምረው ዘንድ የይሖዋን አስተሳሰብ ያወቀ ማን ነው?” በማለት መልስ የማያሻው ጥያቄ ማንሳቱ ተገቢ ነው።—1 ቆሮንቶስ 2:16

ይህን ማወቅህ እንዴት ይጠቅምሃል? አምላክ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በተመሳሳይ ጊዜ የሚያቀርቧቸውን ጸሎቶች መስማት ይችላል። (መዝሙር 65:2) ሌላው ቀርቶ መሬት ላይ የምትወድቀውን እያንዳንዷን ድንቢጥ ያያል። ለመሆኑ አምላክ ሐሳብ በዝቶበት ለአንተ ትኩረት መስጠትና የምታቀርባቸውን ጸሎቶች መስማት ይሳነው ይሆን? በጭራሽ፣ ምክንያቱም የአእምሮ ችሎታው ውስን አይደለም። ከዚህም በላይ ሰዎች ‘ከብዙ ድንቢጦች የላቀ ዋጋ አላቸው።’—ማቴዎስ 10:29, 31

አምላክ ነገሮችን የሚያከናውንበት መንገድ፦ መጽሐፍ ቅዱስ ሰዎች “እውነተኛው አምላክ ከመጀመሪያው አንስቶ እስከ መጨረሻው ድረስ ያከናወነውን ሥራ በምንም ዓይነት መርምረው ሊደርሱበት አይችሉም” ይላል። (መክብብ 3:11) በመሆኑም ስለ አምላክ ሁሉንም ነገር አውቀን መጨረስ አንችልም። አምላክ ባከናወናቸው ነገሮች ላይ የሚንጸባረቀው ጥበብ “የማይደረስበት ነው!” (ሮም 11:33) ይሁን እንጂ አምላክ እሱን ደስ ማሰኘት ለሚፈልጉ ሰዎች መንገዶቹን ለመግለጥ ፈቃደኛ ነው።—አሞጽ 3:7

ፈጣሪ ምን ያህል ዘመን እንደኖረ እንዲሁም የአእምሮውን ችሎታና የጥበቡን ጥልቀት መለካት፣ በቁጥር ማስላት ወይም መረዳት አይቻልም

ይህን ማወቅህ እንዴት ይጠቅምሃል? መጽሐፍ ቅዱስን የምታነብና የምታጠና ከሆነ ስለ አምላክና ስለ መንገዶቹ ምንጊዜም አዳዲስ ነገሮችን ትማራለህ። በመሆኑም ለዘላለም ስንኖር ወደ ሰማዩ አባታችን ይበልጥ እየቀረብን መሄድ እንችላለን።

በቀላሉ መረዳት የምንችላቸው ነገሮች

ስለ አምላክ ሙሉ በሙሉ መረዳት የማንችላቸው አንዳንድ ነገሮች ስላሉ ብቻ አምላክን በጭራሽ ማወቅ አንችልም ማለት አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስ አምላክን በተሻለ ሁኔታ ማወቅ እንድንችል የሚረዱ ብዙ መረጃዎች ይዟል። እስቲ አንዳንድ ምሳሌዎችን እንመልከት፦

የአምላክ ስም፦ መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ ለራሱ ያወጣው አንድ ስም እንዳለው ይናገራል። “እኔ ይሖዋ ነኝ። ስሜ ይህ ነው” ብሏል። የአምላክ ስም መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ 7,000 ጊዜ ያህል ይገኛል፤ እንደዚህ ብዙ ጊዜ የተጠቀሰ ሌላ ስም የለም።—ኢሳይያስ 42:8

ይህን ማወቅህ እንዴት ይጠቅምሃል? ኢየሱስ በጸሎት ናሙናው ላይ “በሰማያት የምትኖር አባታችን ሆይ፣ ስምህ ይቀደስ” ብሏል። (ማቴዎስ 6:9) አንተስ ስትጸልይ በአምላክ ስም ለመጠቀም ትፈልጋለህ? ይሖዋ ለስሙ ተገቢውን አክብሮት የሚያሳዩ ሰዎችን በሙሉ ለማዳን ፈቃደኛ ነው።—ሮም 10:13

የአምላክ መኖሪያ፦ መጽሐፍ ቅዱስ ሁለት የመኖሪያ ቦታዎች ይኸውም መንፈሳዊ ፍጥረታት የሚኖሩበት መንፈሳዊ ዓለም እንዲሁም ምድራችንንና ጽንፈ ዓለምን የሚያጠቃልለው ግዑዝ ዓለም እንዳሉ ይናገራል። (ዮሐንስ 8:23፤ 1 ቆሮንቶስ 15:44) መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “ሰማያት” የሚለው ቃል ብዙውን ጊዜ የሚያመለክተው መንፈሳዊውን ዓለም ነው። የፈጣሪ “መኖሪያ ቦታ” የሚገኘው በእነዚያ “ሰማያት” ውስጥ ነው።—1 ነገሥት 8:43

ይህን ማወቅህ እንዴት ይጠቅምሃል? ስለ አምላክ ይበልጥ ግልጽ የሆነ ግንዛቤ ታገኛለህ። ፈጣሪ በሁሉም ቦታና በሁሉም ነገር ውስጥ የሚገኝ ኃይል አይደለም። ይሖዋ በአንድ የተወሰነ ቦታ ላይ የሚኖር እውን አካል ነው። ይሁንና “ከአምላክ እይታ የተሰወረ አንድም ፍጥረት የለም።”—ዕብራውያን 4:13

የአምላክ ባሕርይ፦ መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋ ያሉትን ተወዳጅ ባሕርያት ይገልጻል። “አምላክ ፍቅር ነው።” (1 ዮሐንስ 4:8) ደግሞም በፍጹም አይዋሽም። (ቲቶ 1:2) በተጨማሪም የማያዳላ፣ መሐሪ፣ ሩኅሩኅና ለቁጣ የዘገየ ነው። (ዘፀአት 34:6፤ የሐዋርያት ሥራ 10:34) ለብዙዎች አስገራሚ ሊሆን ቢችልም ፈጣሪ ከሚያከብሩት ሰዎች ጋር “የጠበቀ ወዳጅነት” እንዲኖረው ይፈልጋል።—መዝሙር 25:14

ይህን ማወቅህ እንዴት ይጠቅምሃል? አንተም የይሖዋ ወዳጅ መሆን ትችላለህ። (ያዕቆብ 2:23) ከዚያም የይሖዋን ባሕርያት ስታውቅ የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎች ይበልጥ ግልጽ ይሆኑልሃል።

‘እሱን ፈልገው’

መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ይሖዋ አምላክ ማንነት ግልጽ የሆነ መረጃ ይሰጠናል። ፈጣሪ ከሰው የመረዳት ችሎታ በላይ አይደለም። እንዲያውም እንድታውቀው ይፈልጋል። የአምላክ ቃል የሆነው መጽሐፍ ቅዱስ “ብትፈልገው ይገኝልሃል” የሚል ማረጋገጫ ይሰጠናል። (1 ዜና መዋዕል 28:9) ታዲያ የመጽሐፍ ቅዱስን ዘገባዎች በማንበብና በዚያ ላይ በማሰላሰል ለምን አምላክን ለማወቅ ጥረት አታደርግም? እንዲህ የምታደርግ ከሆነ ‘አምላክ ወደ አንተ እንደሚቀርብ’ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል።—ያዕቆብ 4:8

መጽሐፍ ቅዱስን የምታነብና የምታጠና ከሆነ ስለ አምላክና ስለ መንገዶቹ ምንጊዜም አዳዲስ ነገሮችን ትማራለህ

‘ስለ ፈጣሪ ሁሉንም ነገር መረዳት ስለማልችል እንዴት የእሱ ወዳጅ መሆን እችላለሁ?’ ብለህ ታስብ ይሆናል። እስቲ የሚከተለውን አስብ፦ የአንድ ቀዶ ሕክምና ዶክተር የቅርብ ወዳጅ መሆን የሚፈልግ ሰው የሕክምና ዲግሪ መያዝ ያስፈልገዋል? በጭራሽ! የዶክተሩ ወዳጅ ፈጽሞ የተለየ ሙያ ሊኖረው ይችላል። ያም ሆኖ ሁለቱ ሰዎች የቅርብ ወዳጆች ሊሆኑ ይችላሉ። ቁም ነገሩ ያለው የዶክተሩ ወዳጅ፣ የጓደኛውን ባሕርይ እንዲሁም የሚወደውንና የሚጠላውን ነገር ማወቁ ላይ ነው። በተመሳሳይ አንተም ይሖዋ ምን ዓይነት አምላክ እንደሆነ ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ መማር ይኖርብሃል፤ እንዲህ ካደረግክ ከእሱ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት መመሥረት ትችላለህ።

መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ፈጣሪ የሚገልጸው ሐሳብ የተድበሰበሰ አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ አምላክን ማወቅ እንድንችል የሚያስፈልገንን በቂ መረጃ ይዟል። ታዲያ ስለ ይሖዋ አምላክ ይበልጥ ማወቅ ትፈልጋለህ? የይሖዋ ምሥክሮች ሰዎችን በነፃ መጽሐፍ ቅዱስ ያስተምራሉበአካባቢህ ያሉትን የይሖዋ ምሥክሮች እንድታገኛቸው ወይም www.jw.org/am የተባለውን ድረ ገጻችንን እንድትመለከት እናበረታታሃለን።