በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ንዑስ መምረጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

አማርኛ

ሃሎዊን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ድጋፍ አለው?

ሃሎዊን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ድጋፍ አለው?

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

ሃሎዊን የሚለው ቃል መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አይገኝም። ያም ቢሆን የሃሎዊን ጥንታዊ አመጣጥም ሆነ በበዓሉ ላይ የሚደረጉት አንዳንድ ልማዶች እንደሚያሳዩት ለዚህ በዓል መሠረት የሆነው ነገር ሰዎች ስለ ሙታንና ስለ መናፍስት ወይም ስለ አጋንንት ያላቸው የተሳሳተ አመለካከት ነው።—“የሃሎዊን ታሪክና ልማዶች” የሚለውን ተመልከት።

መጽሐፍ ቅዱስ “መናፍስት ጠሪ ወይም ሙት አነጋጋሪ በመካከልህ ከቶ አይገኝ” የሚል ማስጠንቀቂያ ይሰጣል። (ዘዳግም 18:10-12) አንዳንድ ሰዎች ሃሎዊንን ምንም ጉዳት እንደሌለው በዓል አድርገው ቢመለከቱትም በበዓሉ ወቅት የሚደረጉት አንዳንድ ነገሮች ጎጂ እንደሆኑ መጽሐፍ ቅዱስ ይጠቁማል። መጽሐፍ ቅዱስ በ1 ቆሮንቶስ 10:20, 21 ላይ እንዲህ ይላል፦ “ከአጋንንት ጋር እንድትተባበሩም አልሻም። የጌታን ጽዋና፣ የአጋንንትን ጽዋ በአንድ ላይ መጠጣት አትችሉም።”አዲሱ መደበኛ ትርጉም

የሃሎዊን ታሪክና ልማዶች

  1. ሳወን፦ ዘ ወርልድ ቡክ ኢንሳይክሎፒዲያ እንደገለጸው ሃሎዊን የመጣው “ከ2,000 ዓመታት በፊት የኬልት ሕዝቦች ያከብሩት ከነበረው አረማዊ የሆነ ጥንታዊ ክብረ በዓል ነው።” አክሎም እንዲህ ብሏል፦ “ኬልቶች በዚህ ወቅት ሙታን በሕያዋን መካከል እንደሚንቀሳቀሱ ያምኑ ነበር። በሳወን ወቅት ሕያዋን ሙታንን ማግኘት ይችላሉ።” ያም ቢሆን መጽሐፍ ቅዱስ “ሙታን . . . ምንም አያውቁም” በማለት በግልጽ ያስተምራል። (መክብብ 9:5) በመሆኑም በሕይወት ካሉ ሰዎች ጋር ሊገናኙ አይችሉም።

  2. የሃሎዊን አልባሳት፣ ከረሜላ እንዲሁም የሃሎዊን ማታለያ ወይም ማባበያ፦ ሃሎዊንአን አሜሪካን ሆሊዴይ፣ አን አሜሪካን ሂስትሪ የተባለው መጽሐፍ እንደሚናገረው ከሆነ አንዳንድ ኬልቶች፣ መናፍስት ከእነሱ ወገን እንደሆኑ በመቁጠር እንዲርቋቸው ለማድረግ ሲሉ የሚያስፈሩ አልባሳትን ይለብሳሉ። ሌሎች ደግሞ መናፍስቱን ለመደለል ጣፋጮች ያቀርባሉ። በመካከለኛው ዘመን በአውሮፓ የካቶሊክ ቀሳውስት እነዚህን አረማዊ ልማዶች ተቀበሉ፤ እንዲሁም ምዕመኖቻቸው ለየት ያሉ አልባሳትን ለብሰው ከቤት ወደ ቤት እየሄዱ ትናንሽ ስጦታዎች እንዲጠይቁ ማድረግ ጀመሩ። በሌላ በኩል ግን መጽሐፍ ቅዱስ የሐሰት ሃይማኖት ልማዶች ከእውነተኛው አምልኮ ጋር እንዲቀላቀሉ አይፈቅድም።2 ቆሮንቶስ 6:17

  3. ጣረ ሞቶች፣ ቫምፓየሮች፣ ዌርዉልቮች፣ ጠንቋዮች፣ ዞምቢዎች፦ እነዚህ ነገሮች ከረጅም ጊዜ ጀምሮ የሚጠቀሱት ከክፉ መናፍስት ዓለም ጋር ተያይዘው ነው። (ሃሎዊን ትሪቪያ) መጽሐፍ ቅዱስ ክፉ መናፍስትን ማድነቅ ሳይሆን መቃወም እንዳለብን በግልጽ ይናገራል።ኤፌሶን 6:12

  4. የሃሎዊን ዱባ፦ በመካከለኛው ዘመን በብሪታንያ “ተመጽዋቾች ከቤት ወደ ቤት እየሄዱ ምግብ የሚጠይቁ ሲሆን በምላሹም ለሙታን ጸሎት ያቀርባሉ።” በተጨማሪም እነዚህ ተመጽዋቾች “ሻማ የተቀመጠበት የተቦረቦረ ቀይ ሥር መሰል አትክልት ይዘው ይዞሩ ነበር፤ ሻማው መንጽሔ ውስጥ የተያዘችን ነፍስ እንደሚወክል ይሰማቸዋል።” (ሃሎዊንፍሮም ፓጋን ሪችዋል ቱ ፓርቲ ናይት) ሌሎች ደግሞ እነዚህ ሻማዎች ጥቅም ላይ ይውሉ የነበረው ክፉ መናፍስትን ለማባረር እንደሆነ ይናገራሉ። በ1800ዎቹ በሰሜን አሜሪካ፣ ቀይ ሥር መሰል በሆነው አትክልት ፋንታ ዱባ መጠቀም ጀመሩ፤ ምክንያቱም በዚህ አካባቢ ዱባ በብዛት የሚገኝ ከመሆኑም በላይ ውስጡን ለመቦርቦር ቀላል ነው። በዚህ ልማድ ላይ የሚንጸባረቁት ነገሮች ማለትም የነፍስ አለመሞት፣ መንጽሔ እንዲሁም ለሙታን የሚቀርቡ ጸሎቶች በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ አይደሉም።ሕዝቅኤል 18:4