በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከወፍ አዳኙ ወጥመዶች መዳን

ከወፍ አዳኙ ወጥመዶች መዳን

ከወፍ አዳኙ ወጥመዶች መዳን

“[ይሖዋ] ከወፍ አዳኝ ወጥመድ ያድንሃል።”—መዝሙር 91:3 NW

1. “ወፍ አዳኝ” የተባለው ማን ነው? አደገኛ የሆነውስ ለምንድን ነው?

 ሁሉም እውነተኛ ክርስቲያኖች ከሰው ልጆች የበለጠ ብልህና አታላይ የሆነ ጠላት ጥቃት ይሰነዝርባቸዋል። ይህ አካል በመዝሙር 91:3 ላይ “ወፍ አዳኝ” ተብሎ ተጠርቷል። ይህ ጠላት ማን ነው? ይህ መጽሔት ከሰኔ 1, 1883 እትሙ ጀምሮ ይህ ጠላት ከሰይጣን ዲያብሎስ ሌላ ማንም ሊሆን እንደማይችል ሲገልጽ ቆይቷል። ይህ ኃያልና ብልህ ጠላት አንድን ወፍ ለማጥመድ እንደሚሞክር አዳኝ የይሖዋን ሕዝቦች ለማታለልና ለማጥመድ ይጥራል።

2. ሰይጣን ከወፍ አዳኝ ጋር የተመሳሰለው ለምንድን ነው?

2 በጥንት ጊዜያት ወፎች ማራኪ ለሆነው ዝማሬያቸው፣ በቀለማት ላሸበረቀው ላባቸው፣ ለምግብነት እንዲሁም መሥዋዕት እንዲሆኑ ሲባል ይያዙ ነበር። ይሁን እንጂ ወፎች በተፈጥሯቸው ጥንቁቅና ድንጉጥ ስለሆኑ በቀላሉ አይያዙም። በመሆኑም በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን የነበረ ወፍ አዳኝ ሊይዘው የሚፈልገውን የወፍ ዝርያ ባሕርይና ልማድ በጥንቃቄ ያጠናል። ከዚያም ይህንን ወፍ ለመያዝ ዘዴ ይፈልጋል። መጽሐፍ ቅዱስ ሰይጣንን ከወፍ አዳኝ ጋር በማመሳሰል ዘዴዎቹን እንድናውቅ ይረዳናል። ዲያብሎስ በግለሰብ ደረጃ የሚያጠናን ሲሆን ባሕርያችንንና ልማዳችንን በመመልከት እኛን ለመያዝ የሚያስችሉት ስውር ወጥመዶች ያዘጋጃል። (2 ጢሞቴዎስ 2:26) በሰይጣን ወጥመድ ከተያዝን ደግሞ ከአምላክ ጋር ያለን ግንኙነት የሚበላሽ ከመሆኑም በላይ ውሎ አድሮ ለጥፋት እንዳረጋለን። በመሆኑም ‘የወፍ አዳኙን’ የተለያዩ ዘዴዎች ማወቃችን ጥበቃ ይሆንልናል።

3, 4. ሰይጣን ዲያብሎስ፣ አንበሳና እፉኝት ከሚጠቀሙባቸው ዘዴዎች ጋር የሚመሳሰሉ ብልሃቶችን የሚጠቀመው እንዴት ነው?

3 መዝሙራዊው፣ የሰይጣንን ዘዴዎች ደቦል አንበሳና እፉኝት ከሚጠቀሙባቸው ዘዴዎች ጋር በማመሳሰል ነጥቡን በአእምሯችን ለመሳል በሚያስችል መንገድ አስቀምጦታል። (መዝሙር 91:13) አንዳንድ ጊዜ ሰይጣን በይሖዋ ሕዝቦች ላይ ስደት በማስነሳት ወይም በሕግ እንዲታገዱ በማድረግ እንደ አንበሳ ቀጥተኛ ጥቃት ይሰነዝራል። (መዝሙር 94:20) እንዲህ ያለው አስፈሪ ጥቃት አንዳንዶች ይሖዋን ማምለካቸውን እንዲተዉ ሊያደርጋቸው ይችላል። አብዛኛውን ጊዜ ግን ይህ ዓይነቱ ቀጥተኛ ጥቃት የሰይጣንን ዓላማ ከማሳካት ይልቅ የአምላክ ሕዝቦች አንድነት እንዲጠናከር ያደርጋል። ሰይጣን እንደ እፉኝት ስለሚሰነዝራቸው ስውር ጥቃቶችስ ምን ማለት ይቻላል?

4 ዲያብሎስ፣ ከሰው ልጆች የበለጠ ብልህ በመሆኑ አድብቶ ጥቃት እንደሚሰነዝር መርዛማ እፉኝት ሰዎችን በማታለል አደገኛ ጥቃት ይሰነዝራል። በዚህ መንገድ ተጠቅሞ አንዳንድ የአምላክ ሕዝቦችን አእምሮ በመመረዝ ከይሖዋ ፈቃድ ይልቅ የእሱን ፈቃድ እንዲያደርጉ ማታለል የቻለ ሲሆን ይህም አሳዛኝ ውጤት አስከትሏል። ጥሩነቱ ግን የሰይጣንን ዘዴዎች እናውቃቸዋለን። (2 ቆሮንቶስ 2:11) እስቲ ‘ወፍ አዳኙ’ የሚጠቀምባቸውን አራት አደገኛ ወጥመዶች እንመልከት።

ሰውን መፍራት

5. ክርስቲያኖች “ሰውን መፍራት” ወጥመድ እንዲሆንባቸው በማድረግ ረገድ ሰይጣን ውጤታማ የሆነው ለምንድን ነው?

5 ሰዎች በተፈጥሯቸው በሌሎች ዘንድ ተቀባይነት ለማግኘትና ለመወደድ እንደሚፈልጉ ‘ወፍ አዳኙ’ ያውቃል። ክርስቲያኖች በአካባቢያቸው ስላሉ ሰዎች አመለካከትና ስሜት የማያስቡና ግዴለሾች አይደሉም። የአምላክ አገልጋዮች፣ ሰዎች ስለ እነሱ ያላቸው አመለካከት እንደሚያሳስባቸው ዲያብሎስ ስለሚያውቅ በዚህ ተጠቅሞ ሊያጠምዳቸው ይሞክራል። ለምሳሌ፣ አንዳንድ የአምላክ ሕዝቦች “ሰውን መፍራት” ወጥመድ እንዲሆንባቸው ያደርጋል። (ምሳሌ 29:25) የአምላክ አገልጋዮች፣ ሰውን በመፍራት ይሖዋ የሚያወግዘውን ከሚያደርጉ ግለሰቦች ጋር የሚተባበሩ ወይም የአምላክ ቃል የሚያዘውን የማይፈጽሙ ከሆነ ‘በወፍ አዳኙ’ ወጥመድ ተይዘዋል ማለት ነው።—ሕዝቅኤል 33:8፤ ያዕቆብ 4:17

6. አንድ ወጣት ‘በወፍ አዳኙ’ ወጥመድ እንዴት ሊያዝ እንደሚችል የሚያሳይ ምሳሌ ተናገር።

6 ለአብነት ያህል፣ አንድ ወጣት አብረውት በሚማሩ ልጆች ተጽዕኖ ተሸንፎ ሲጋራ ሊያጨስ ይችላል። ይህ ወጣት የዚያን ቀን ወደ ትምህርት ቤት ሲሄድ ሲጋራ አጨሳለሁ ብሎ ፈጽሞ አላሰበ ይሆናል። ብዙም ሳይቆይ ግን ጤንነቱን የሚጎዳና አምላክን የሚያሳዝን ድርጊት ፈጸመ። (2 ቆሮንቶስ 7:1) ይህ ወጣት ሊታለል የቻለው እንዴት ነው? ምናልባት ከመጥፎ ጓደኞች ጋር ገጥሞ በእነሱ ዘንድ ተቀባይነት ላለማጣት ፈርቶ ሊሆን ይችላል። እናንት ወጣቶች፣ ‘ወፍ አዳኙ’ አታልሎ በወጥመዱ እንዲይዛችሁ አትፍቀዱ! ሰይጣን በወጥመዱ እንዳይዛችሁ ጥቃቅን በሆኑ ጉዳዮች እንኳ ሳይቀር አቋማችሁን ላለማላላት ተጠንቀቁ። ከመጥፎ ጓደኝነት እንድትርቁ የሚያሳስበውን የመጽሐፍ ቅዱስ ማስጠንቀቂያ ተግባራዊ አድርጉ።—1 ቆሮንቶስ 15:33

7. ሰይጣን፣ አንዳንድ ወላጆች መንፈሳዊ ሚዛናቸውን እንዲስቱ የሚያደርጋቸው እንዴት ሊሆን ይችላል?

7 ትጉህ የሆኑ ክርስቲያን ወላጆች ለቤተሰባቸው የሚያስፈልጉትን ቁሳዊ ነገሮች በማቅረብ ረገድ ያለባቸውን ቅዱስ ጽሑፋዊ ኃላፊነት በቁም ነገር ይመለከቱታል። (1 ጢሞቴዎስ 5:8) ይሁን እንጂ ሰይጣን፣ ክርስቲያኖች በዚህ ረገድ ሚዛናቸውን እንዲስቱ ማድረግ ይፈልጋል። አንዳንድ ክርስቲያኖች አሠሪያቸው ተጨማሪ ሰዓት እንዲሠሩ በሚያደርግባቸው ተጽዕኖ ተሸንፈው ከስብሰባዎች የመቅረት ልማድ ይኖራቸው ይሆናል። እነዚህ ክርስቲያኖች በአውራጃ ስብሰባ ላይ በሁሉም ቀናት ተገኝተው ከወንድሞቻቸው ጋር ይሖዋን ለማምለክ እንዲችሉ አሠሪያቸው ፈቃድ እንዲሰጣቸው መጠየቅ ይፈሩ ይሆናል። በዚህ ወጥመድ ላለመያዝ መፍትሔው ‘በይሖዋ መታመን’ ነው። (ምሳሌ 3:5, 6) ከዚህም በላይ ሁላችንም የይሖዋ ቤተሰብ አባላት እንደሆንንና እሱም እኛን የመንከባከብ ኃላፊነት እንዳለበት እንደሚሰማው ማስታወሳችን ሚዛናችንን ጠብቀን ለመኖር ይረዳናል። ወላጆች፣ የይሖዋን ፈቃድ የምትፈጽሙ ከሆነ እሱ በሆነ መንገድ እናንተንም ሆነ ቤተሰባችሁን እንደሚንከባከባችሁ ትተማመኑበታላችሁ? ወይስ ሰውን በመፍራታችሁ ዲያብሎስ በወጥመዱ ይዞ የእሱን ፈቃድ እንድትፈጽሙ ያደርጋችኋል? እነዚህን ጥያቄዎች በጸሎት እንድታስቡባቸው እናበረታታችኋለን።

የፍቅረ ንዋይ ወጥመድ

8. ሰይጣን በፍቅረ ንዋይ ተጠቅሞ ሊያጠምደን የሚሞክረው እንዴት ነው?

8 ሰይጣን በፍቅረ ንዋይ ተጠቅሞም ወጥመዱ ውስጥ ሊያስገባን ይሞክራል። የዚህ ዓለም የንግድ ሥርዓት፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ ሀብታም ለመሆን ያስችላሉ የሚባሉ ዘዴዎችን የሚያስፋፋ ሲሆን አንዳንድ የአምላክ ሕዝቦችም እንኳ በዚህ ዘዴ ሊታለሉ ይችላሉ። አንዳንድ ጊዜ ሰዎች እንዲህ የሚል ሐሳብ ይሰነዝሩ ይሆናል:- “ጠንክረህ ሥራ። የተደላደለ ኑሮ መምራት ስትጀምር ያን ጊዜ ዘና ማለትና ሕይወትን ማጣጣም ትችላለህ። እንዲያውም አቅኚ መሆን ትችላለህ።” እንደዚህ ዓይነት ሐሳብ የሚያቀርቡት በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ የሚገኙ ወንድሞቻቸውንና እህቶቻቸውን መጠቀሚያ በማድረግ ገንዘብ ለማካበት የሚፈልጉ ሚዛናቸውን የሳቱ ክርስቲያኖች ሊሆኑ ይችላሉ። ከጊዜ በኋላ የተደላደለ ኑሮ ለመምራት ስትል ሀብት እንድታካብት የሚቀርቡልህን ሐሳቦች እስቲ በጥሞና አስብባቸው። እንዲህ ዓይነቱ አመለካከት በኢየሱስ ምሳሌ ላይ “ሞኝ” የተባለውን ሀብታም ሰው አስተሳሰብ የሚያንጸባርቅ አይመስልህም?—ሉቃስ 12:16-21

9. አንዳንድ ክርስቲያኖች ለተለያዩ ነገሮች ያላቸው ምኞት ወጥመድ የሚሆንባቸው ለምን ሊሆን ይችላል?

9 ሰይጣን እሱ በሚቆጣጠረው ክፉ ሥርዓት በመጠቀም ሰዎች የተለያዩ ነገሮችን እንዲመኙ ተጽዕኖ ያደርግባቸዋል። ይህ ዓይነቱ ምኞት በአንድ ክርስቲያን ሕይወትም ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድርና ቃሉን አንቆ “ፍሬ እንዳያፈራ” ሊያደርገው ይችላል። (ማርቆስ 4:19) መጽሐፍ ቅዱስ፣ ምግብና ልብስ ካለን በዚህ ረክተን እንድንኖር ያበረታታናል። (1 ጢሞቴዎስ 6:8) ይሁን እንጂ ብዙዎች ይህንን ምክር በሕይወታቸው ውስጥ ተግባራዊ ስለማያደርጉት ‘በወፍ አዳኙ’ ወጥመድ ውስጥ ወድቀዋል። እነዚህ ሰዎች አንድ ዓይነት የኑሮ ደረጃ እንዲኖራቸው የሚጥሩት ለራሳቸው ከልክ ያለፈ ግምት ስላላቸው ይሆን? እኛስ በግለሰብ ደረጃ እንዴት ነን? አንዳንድ ነገሮችን ለማግኘት ያለን ፍላጎት ከእውነተኛው አምልኮ ጋር ለተያያዙ ጉዳዮች ሁለተኛ ቦታ እንድንሰጥ ያደርገን ይሆን? (ሐጌ 1:2-8) አንዳንዶች ኑሮ በሚወደድበት ጊዜ፣ የለመዱትን አኗኗር ላለመተው ሲሉ መንፈሳዊነታቸውን መሥዋዕት እስከ ማድረግ መድረሳቸው የሚያሳዝን ነው። እንዲህ ያለው ፍቅረ ንዋይ የሚንጸባረቅበት አመለካከት ‘ወፍ አዳኙን’ ያስደስተዋል።

ጎጂ የሆነ መዝናኛ

10. እያንዳንዱ ክርስቲያን በምን ረገድ ራሱን መመርመር ይገባዋል?

10 ‘ወፍ አዳኙ’ የሚጠቀምበት ሌላው ዘዴ ደግሞ ሰዎች በተፈጥሯቸው መልካምና መጥፎ ስለሆኑት ነገሮች ያላቸው አመለካከት የተዛባ እንዲሆን ማድረግ ነው። በዛሬው ጊዜ በሚገኘው በአብዛኛው የመዝናኛ ኢንዱስትሪ ላይ የሰዶምና የገሞራ ነዋሪዎች የነበራቸው ዓይነት አመለካከት ይንጸባረቃል። በቴሌቪዥንና በመጽሔቶች ላይ የሚቀርቡ የዜና ዘገባዎችም እንኳ ዓመጽንና ልቅ የጾታ ብልግናን የያዙ ናቸው። መዝናኛ ተብለው በመገናኛ ብዙኃን የሚቀርቡት አብዛኞቹ ነገሮች ሰዎች “መልካሙን ከክፉው ለመለየት” እንዳይችሉ የሚያደርጉ ናቸው። (ዕብራውያን 5:14) ሆኖም ይሖዋ “ክፉውን መልካም፣ መልካሙን ክፉ ለሚሉ . . . ወዮላቸው!” በማለት በነቢዩ ኢሳይያስ አማካኝነት የተናገረውን ማስጠንቀቂያ አስታውሱ። (ኢሳይያስ 5:20) ‘ወፍ አዳኙ’ እንዲህ ባሉ ጎጂ መዝናኛዎች በመጠቀም ሳታውቁት በአስተሳሰባችሁ ላይ ተጽዕኖ አሳድሮ ይሆን? በዚህ ረገድ ራሳችንን መመርመሩ አስፈላጊ ነው።—2 ቆሮንቶስ 13:5

11. በቴሌቪዥን የሚቀርቡ ተከታታይ ፊልሞችን በተመለከተ በዚህ መጽሔት ላይ ምን ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶ ነበር?

11 ከ25 ዓመታት ገደማ በፊት የመጠበቂያ ግንብ መጽሔት በቴሌቪዥን ስለሚቀርቡ ተከታታይ ፕሮግራሞች አስመልክቶ ለእውነተኛ የይሖዋ አምላኪዎች ፍቅራዊ ማስጠንቀቂያ ሰጥቶ ነበር። a ታዋቂ የሆኑ ተከታታይ ፊልሞች በረቀቀ መንገድ ስለሚያሳድሩት ጎጂ ተጽዕኖ በመጠበቂያ ግንብ ላይ የሚከተለው ሐሳብ ቀርቦ ነበር:- “ለፍቅር ሲባል ማንኛውንም ነገር ማድረግ ተቀባይነት እንዳለው ተደርጎ ይገለጻል። ለምሳሌ፣ አንዲት ሳታገባ ያረገዘች ወጣት ለጓደኛዋ እንዲህ ትላታለች:- ‘ግን እኮ ቪክቶርን እወደዋለሁ። [ለእሱ ስል ምንም ነገር ባደርግ] ግድ የለኝም። . . . ከእሱ መውለድ ለእኔ በጣም ትልቅ ነገር ነው!’ ይህን ስትል ከኋላ የሚሰማው ለስለስ ያለ ሙዚቃ ይህች ሴት የፈጸመችውን ድርጊት ያን ያህል መጥፎ አድርገን እንዳንመለከተው የሚያደርግ ነው። እናንተም ቪክቶርን ትወዱታላችሁ። ለልጅቷም ታዝኑላታላችሁ። ስሜቷን ‘ትረዱላታላችሁ።’ ተከታታይ ፊልሞችን የመመልከት ልማድ የነበራትና በኋላ ላይ ወደ ልቧ የተመለሰች አንዲት ሴት እንዲህ ብላለች:- ‘አስተሳሰብህ ትክክል እንደሆነ ለማስመሰል ለራስህ የምታቀርበው ምክንያት ያስገርማል። የሥነ ምግባር ብልግና መጥፎ እንደሆነ እናውቃለን። . . . ሆኖም በውስጤ የእነዚህን ሰዎች ስሜት እጋራ ነበር።’”

12. አንዳንድ የቴሌቪዥን ፕሮግራሞችን በተመለከተ በአሁኑ ጊዜ ማስጠንቀቂያ መሰጠቱ ተገቢ መሆኑን የሚያሳዩት የትኞቹ እውነታዎች ናቸው?

12 እነዚህ ሐሳቦች ከወጡ ወዲህ ደግሞ እንደነዚህ ዓይነቶቹ ልባችንን የሚያረክሱ ፕሮግራሞች ይበልጥ እየተስፋፉ መጥተዋል። በብዙ ቦታዎች እንዲህ ዓይነት ፕሮግራሞች ለ24 ሰዓት ይተላለፋሉ። ወንዶች፣ ሴቶችና በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ የሚገኙ በርካታ ወጣቶች በእንዲህ ዓይነቱ መዝናኛ አእምሯቸውንና ልባቸውን ይሞሉታል። እኛ ግን የተሳሳተ ሰበብ በማቅረብ ራሳችንን ማታለል የለብንም። ወራዳ የሆነ መዝናኛ በገሃዱ ዓለም ከሚታየው ነገር የከፋ ሊሆን አይችልም ብሎ ማሰብ ስህተት ነው። አንድ ክርስቲያን ቤቱ ለመጋበዝ ፈጽሞ የማያስባቸው ሰዎች በሚያቀርቡት መዝናኛ ለመዝናናት ቢመርጥ ለዚህ ምን አሳማኝ ምክንያት ሊያቀርብ ይችላል?

13, 14. አንዳንዶች ቴሌቪዥንን አስመልክቶ ከተሰጡት ማስጠንቀቂያዎች ያገኙትን ጥቅም የገለጹት እንዴት ነበር?

13 ብዙዎች “ታማኝና ልባም ባሪያ” የሰጠውን ማስጠንቀቂያ ሰምተው ተግባራዊ በማድረጋቸው ተጠቅመዋል። (ማቴዎስ 24:45-47 የ1954 ትርጉም) አንዳንዶች በዚህ መጽሔት ላይ የወጣውን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ግልጽ ምክር ካነበቡ በኋላ እነዚህ ርዕሶች በግለሰብ ደረጃ ምን ተጽዕኖ እንዳሳደሩባቸው ለመጠበቂያ ግንብ አዘጋጆች ጽፈዋል። b አንዲት ሴት እንዲህ ብላለች:- “ለ13 ዓመታት ያህል ተከታታይ ፊልሞችን የማየት ሱስ ነበረብኝ። በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ በመገኘትና አልፎ አልፎ በአገልግሎት በመካፈል ብቻ መንፈሳዊነቴን ጠብቄ መኖር የምችል መስሎኝ ነበር። ሆኖም በእነዚህ ተከታታይ ፊልሞች ላይ የሚታየውን የዓለም አመለካከት ማንጸባረቅ ጀመርኩ። አንዲት ሴት ባለቤቷ የሚበድላት ከሆነ ወይም እንደማይወዳት ከተሰማት ምንዝር ብትፈጽም ምንም ስህተት እንደሌለውና የራሱ ጥፋት እንደሆነ ማሰብ ጀመርኩ። በመሆኑም ምንዝር ለመፈጸም ‘በቂ ምክንያት እንዳለኝ’ ሲሰማኝ ይህን መጥፎ ጎዳና በመከተል በይሖዋና በትዳር ጓደኛዬ ላይ ኃጢአት ፈጸምኩ።” በዚህም የተነሳ ይህች ሴት ተወገደች። ከጊዜ በኋላ ግን ወደ ልቦናዋ ተመልሳ ንስሐ ስትገባ ውገዳው ተነሳላት። በቴሌቪዥን የሚቀርቡ ተከታታይ ፊልሞችን በተመለከተ ማስጠንቀቂያ ይዘው የወጡት ርዕሶች ይህች እህት ይሖዋ በሚጠላቸው ነገሮች መዝናናቷን ለማቆም የሚያስፈልጋትን ጥንካሬ ሰጥተዋታል።—አሞጽ 5:14, 15

14 አንዲት ሌላ ሴት እንዲህ ብላለች:- “እነዚህን ርዕሶች ሳነብ ይሖዋን በሙሉ ልቤ እያመለክሁት እንዳልሆነ ስለተገነዘብኩ አለቀስኩ። ከአሁን በኋላ ለእነዚህ ተከታታይ ፊልሞች ባሪያ ላለመሆን ለአምላኬ ቃል ገብቻለሁ።” አንዲት ክርስቲያን ደግሞ በመጠበቂያ ግንብ ላይ ለወጡት ለእነዚህ ርዕሶች ምስጋናዋን ከገለጸች በኋላ ተከታታይ ፊልሞችን የመመልከት ሱስ እንደነበረባት ስትናገር እንዲህ ብላለች:- “ከይሖዋ ጋር ያለኝን ዝምድና ሊነካብኝ እንደሚችል . . . አሰብኩ። በተከታታይ ፊልሞች ላይ የሚታዩት ገጸ ባሕርያት ጓደኛ ሆኜ እያለ እንዴት የይሖዋ ወዳጅ መሆን እችላለሁ?” እንደነዚህ ያሉት የቴሌቪዥን ፕሮግራሞች ከ25 ዓመታት በፊት የሰዎችን አስተሳሰብ ይበክሉ ከነበረ በዛሬው ጊዜማ ምን ያህል ጎጂ ተጽዕኖ ያሳድሩ ይሆን? (2 ጢሞቴዎስ 3:13) ሰይጣን ጎጂ የሆኑ መዝናኛዎችን እንደ ወጥመድ ሊጠቀምባቸው እንደሚችል መገንዘብ ይኖርብናል። እንደነዚህ ያሉት መዝናኛዎች በተለያዩ መንገዶች ይኸውም በቴሌቪዥን በሚተላለፉ ተከታታይ ፊልሞችም ሆነ ዓመጽ በሞላባቸው የቪዲዮ ጨዋታዎች ወይም የሥነ ምግባር ብልግና በሚንጸባረቅባቸው የሙዚቃ ቪዲዮዎች አማካኝነት ሊቀርቡ ይችላሉ።

አለመግባባቶች

15. አንዳንዶች በዲያብሎስ ወጥመድ የተያዙት እንዴት ነው?

15 ሰይጣን በይሖዋ ሕዝቦች መካከል መከፋፈል ለመፍጠር አለመግባባቶችን እንደ ወጥመድ ይጠቀምበታል። ምንም ዓይነት የአገልግሎት መብት ቢኖረን በዚህ ወጥመድ ልንያዝ እንችላለን። አንዳንዶች፣ ይሖዋ በሕዝቦቹ መካከል እንዲኖር ያደረገውን ግሩም መንፈሳዊ ሁኔታ እንዲሁም የጉባኤውን ሰላምና አንድነት አለመግባባቶች እንዲያደፈርሱት በመፍቀዳቸው በዲያብሎስ ወጥመድ ተይዘዋል።—መዝሙር 133:1-3

16. ሰይጣን አንድነታችንን ለማደፍረስ በተንኮል እያደባ ያለው እንዴት ነው?

16 ሰይጣን፣ በአንደኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ቀጥተኛ ጥቃት በመሰንዘር የይሖዋን ድርጅት ምድራዊ ክፍል ለማጥፋት ሞክሮ የነበረ ቢሆንም አልተሳካለትም። (ራእይ 11:7-13) ከዚያን ጊዜ ጀምሮ አንድነታችንን ለማደፍረስ በተንኮል እያደባ ነው። በአለመግባባቶች ምክንያት አንድነታችን እንዲደፈርስ ከፈቀድን ‘ወፍ አዳኙ’ መግቢያ ቀዳዳ እንዲያገኝ እናደርጋለን። በዚህም ምክንያት ይሖዋ በግል ሕይወታችንም ሆነ በጉባኤው ውስጥ መንፈስ ቅዱሱን እንዳይሰጠን እንቅፋት እንፈጥራለን። የጉባኤውን ሰላምና አንድነት የሚያደፈርስ ማንኛውም ነገር ደግሞ የስብከቱ ሥራ እንዲስተጓጎል ስለሚያደርግ ሰይጣንን ያስደስተዋል።—ኤፌሶን 4:27, 30-32

17. ከእምነት ባልንጀራችን ጋር አለመግባባት ቢፈጠር ችግሩን ለመፍታት ምን ማድረግ ይኖርብናል?

17 ከአንድ የእምነት ባልንጀራህ ጋር አለመግባባት ቢፈጠር ምን ማድረግ ትችላለህ? እርግጥ፣ እያንዳንዱ ሁኔታ ከሌላው የተለየ ነው። ችግሮች እንዲፈጠሩ የሚያደርጉ በርካታ ምክንያቶች ይኖራሉ፤ ያም ቢሆን ግን አለመግባባቶች መፍትሔ የማያገኙበት ምንም ምክንያት የለም። (ማቴዎስ 5:23, 24፤ 18:15-17) በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኘው ምክር በመንፈሱ አነሳሽነት የተጻፈ ከመሆኑም በላይ ፍጹም ነው። የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ተግባራዊ ካደረግናቸው ምንጊዜም ቢሆን ጥሩ ውጤት ያስገኛሉ።

18. ይሖዋን መምሰላችን አለመግባባቶችን በመፍታት ረገድ ሊረዳን የሚችለው እንዴት ነው?

18 ይሖዋ “ይቅር ባይ” ነው። (መዝሙር 86:5፤ 130:4) እኛም በዚህ ረገድ እሱን ስንመስል የተወደድን የይሖዋ ልጆች መሆናችንን እናሳያለን። (ኤፌሶን 5:1) ሁላችንም ኃጢአተኞች በመሆናችን የይሖዋ ምሕረት በእጅጉ ያስፈልገናል። በመሆኑም አንድን ሰው ይቅር ማለት የሚከብደን ከሆነ በኢየሱስ ምሳሌ ላይ እንደተገለጸው አገልጋይ እንዳንሆን መጠንቀቅ ይኖርብናል። ይህ አገልጋይ የነበረበትን ከፍተኛ ዕዳ ጌታው ይቅር ቢለውም እሱ ግን ወዳጁ ከእሱ የተበደረውን አነስተኛ ገንዘብ ይቅር ለማለት ፈቃደኛ አልነበረም። ጌታው ይህን ሲሰማ ይቅር ያላለውን አገልጋይ እስር ቤት አስገባው። ኢየሱስ ምሳሌውን ሲደመድም “እያንዳንዳችሁ ወንድሞቻችሁን ከልባችሁ ይቅር ካላላችሁ፣ የሰማዩ አባቴም እንደዚሁ ያደርግባችኋል” ብሏል። (ማቴዎስ 18:21-35) በዚህ ምሳሌ ላይ ማሰላሰላችንና ይሖዋ ስንት ጊዜ በነጻ ይቅር እንዳለን ማስታወሳችን ከወንድማችን ጋር የተፈጠረውን አለመግባባት ለመፍታት በምንጥርበት ወቅት ይረዳናል።—መዝሙር 19:14

በልዑል መጠጊያ” ተሸሽጋችሁ ኑሩ

19, 20. በዚህ አደገኛ ጊዜ ውስጥ ስንኖር የይሖዋን “መጠጊያ” እንዲሁም “ጥላ” እንዴት ልንመለከተው ይገባል?

19 የምንኖረው በአደገኛ ጊዜ ውስጥ ነው። ይሖዋ ፍቅራዊ ጥበቃ ባያደርግልን ኖሮ ሰይጣን ሁላችንንም ያጠፋን ነበር። እንግዲያው ‘በወፍ አዳኙ’ ወጥመድ ላለመያዝ በምሳሌያዊው የጥበቃ ቦታ ማለትም ‘በልዑል መጠጊያ ውስጥ መኖር’ እንዲሁም ‘ሁሉን በሚችል አምላክ ጥላ ሥር’ ማደር ይኖርብናል።—መዝሙር 91:1

20 ምንጊዜም ቢሆን የይሖዋን ማሳሰቢያዎችና መመሪያዎች ጥበቃ እንደሚያስገኙልን እንጂ እንደማያፈናፍኑ አድርገን አንመልከታቸው። ከሰው ልጆች የበለጠ ብልህ የሆነ ጠላት በሁላችንም ላይ ጥቃት ይሰነዝራል። ማናችንም ብንሆን የይሖዋን ፍቅራዊ እርዳታ ካላገኘን ከዚህ ወጥመድ ማምለጥ አንችልም። (መዝሙር 124:7, 8) እንግዲያው ይሖዋ ‘ከወፍ አዳኙ’ ወጥመድ እንዲያድነን እንጸልይ!—ማቴዎስ 6:13

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

a የታኅሣሥ 1, 1982 መጠበቂያ ግንብ (እንግሊዝኛ) ገጽ 3-7

b የታኅሣሥ 1, 1983 መጠበቂያ ግንብ (እንግሊዝኛ) ገጽ 23

ታስታውሳለህ?

• “ሰውን መፍራት” አደገኛ ወጥመድ ነው የምንለው ለምንድን ነው?

• ዲያብሎስ ሰዎችን ለማጥመድ በፍቅረ ንዋይ የሚጠቀመው እንዴት ነው?

• ሰይጣን ጎጂ መዝናኛን በመጠቀም አንዳንዶችን ወጥመዱ ውስጥ ያስገባቸው እንዴት ነው?

• ዲያብሎስ አንድነታችንን ለማናጋት ምን ዓይነት ወጥመድ ይጠቀማል?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አንዳንዶች “ሰውን መፍራት” ወጥመድ ሆኖባቸዋል

[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የምትዝናናው ይሖዋ በሚጠላቸው ነገሮች ነው?

[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በአንተና በእምነት ባልንጀራህ መካከል አለመግባባት ቢፈጠር ምን ማድረግ ትችላለህ?