በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መላእክት በሕይወታችን ውስጥ ምን ሚና ይጫወታሉ?

መላእክት በሕይወታችን ውስጥ ምን ሚና ይጫወታሉ?

መላእክት በሕይወታችን ውስጥ ምን ሚና ይጫወታሉ?

ነቢዩ ዳንኤል የአምላክን መላእክታዊ ቤተሰብ በተመለከተ ያየውን ራእይ ሲገልጽ:- “ሺህ ጊዜ ሺሆች [መላእክት፣ አምላክን] ያገለግሉት ነበር፤ እልፍ ጊዜ እልፍ በፊቱ ቆመዋል” ብሏል። (ዳንኤል 7:​10) ይህ አባባል አምላክ መላእክትን የፈጠረበት ዓላማ እርሱን እንዲያገለግሉትና መመሪያውን እንዲፈጽሙ መሆኑን ይገልጽልናል።

አምላክ ከሰዎች ጋር በተያያዘ አንዳንድ ነገሮችን እንዲሠሩ መላእክትን ይጠቀምባቸዋል። አምላክ ሰዎችን ለማበረታታትና ለመጠበቅ፣ መልእክት ለማድረስ እን​ዲሁም በክፉዎች ላይ የቅጣት ፍርዱን ለማስፈጸም መላእክትን እንዴት እንደተጠቀመባቸው እየተመለከትን እንሄዳለን።

መላእክት ያበረታታሉ እንዲሁም ጥበቃ ያደርጋሉ

እነዚህ መንፈሳዊ ፍጡራን ምድርም ሆነች የመጀመሪያዎቹ ሰዎች ሲፈጠሩ ያዩ በመሆኑ ስለ ሰው ልጆች በጥልቅ ያስባሉ። ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው ሆኖ ወደ ምድር ከመምጣቱ በፊት በጥበብ ተመስሎ “በሰው ልጆች ደስ እሰኝ ነበር” ብሏል። (ምሳሌ 8:​31) ከዚህም በላይ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ክርስቶስና የወደፊቱን ጊዜ በተመለከተ ለአምላክ ነቢያት ስለተነገሩት ነገሮች ለማወቅ “መላእክትም እንኳ ሳይቀሩ . . . ይመኛሉ” በማለት ይናገራል።​—⁠1 ጴጥሮስ 1:​11, 12

መላእክት፣ ጊዜያት እያለፉ ሲሄዱ አብዛኛው የሰው ልጅ አፍቃሪ ፈጣሪውን እንደማያገለግል ተመልክተዋል። እነዚህን ታማኝ መላእክት ሁኔታው ምን ያህል አሳዝኗቸው ይሆን! በሌላ በኩል አንድ ኃጢአተኛ ንስሐ ገብቶ ወደ ይሖዋ ሲመለስ “[በ]መላእክት ፊት ደስታ ይሆናል።” (ሉቃስ 15:​10) መላእክት አምላክን ለሚያገለግሉ ሰዎች ደኅንነት ጥልቅ አሳቢነት ያሳያሉ፤ ይሖዋም መላእክት በምድር ላይ የሚገኙትን ታማኝ አገልጋዮቹን እንዲያበረታቱና እንዲጠብቁ በተደጋጋሚ ጊዜያት ተጠቅሞባቸዋል። (ዕብራውያን 1:​14) እስቲ አንዳንድ ምሳሌዎችን እን​መልከት።

ሁለት መላእክት፣ ጻድቁን ሎጥንና ሁለት ሴቶች ልጆቹን ብልሹ በነበሩት የሰዶምና የገሞራ ከተሞች ላይ ከደረሰው ጥፋት እንዲተርፉ እየመሩ ከአካባቢው አውጥተዋቸዋል። a (ዘፍጥረት 19:​1, 15-26) ከብዙ መቶ ዘመናት በኋላ ደግሞ ነቢዩ ዳንኤል በአንበሶች ጉድጓድ ውስጥ ቢጣልም ምንም ጉዳት ሳይደርስበት ሊተርፍ ችሏል። ለምን? ዳንኤል “አምላኬ መልአኩን ልኮ የአንበሶቹን አፍ ዘጋ” ሲል ተናግሯል። (ዳንኤል 6:​22) ኢየሱስ ምድራዊ አገልግሎቱን ሲጀምር መላእክት ረድተውት ነበር። (ማርቆስ 1:​13) በተጨማሪም ኢየሱስ ከመሞቱ ከጥቂት ጊዜ በፊት አንድ መልአክ ተገልጦለት ‘አበረታቶታል።’ (ሉቃስ 22:​43) ኢየሱስ በሕይወቱ ውስጥ በጣም ወሳኝ በነበሩት በእነዚህ ጊዜያት መላእክታዊ ማበረታቻ ማግኘቱ በእጅጉ አጽናንቶት መሆን አለበት! ሐዋርያው ጴጥሮስንም አንድ መልአክ ከእስር አስፈትቶታል።​—⁠የሐዋርያት ሥራ 12:​6-11

ታዲያ መላእክት በዛሬው ጊዜስ ይጠብቁናል? ይሖዋን በቃሉ መሠረት የምናመልከው ከሆነ የማይታዩ ኀያላን መላእክቱ እንደሚጠብቁን እርግጠኞች መሆን እንችላለን። መጽሐፍ ቅዱስ “እግዚአብሔርን በሚፈሩት ዙሪያ የእግዚአብሔር መልአክ ይሰፍራል፤ ያድናቸዋልም” በማለት ተስፋ ይሰጣል።​—⁠መዝሙር 34:​7

ሆኖም መላእክት ዋነኛው ሥራቸው አምላክን እንጂ ሰዎችን ማገልገል እንዳልሆነ ማወቅ ይኖርብናል። (መዝሙር 103:​20, 21) መመሪያ የሚቀበሉት ከአምላክ ነው፤ የሰዎችን ጥሪ ወይም ጥያቄ አይመልሱም። ስለዚህም እርዳታ ለማግኘት መለመን ያለብን መላእክትን ሳይሆን ይሖዋን ነው። (ማቴዎስ 26:​53) እርግጥ መላእክትን ማየት ስለማንችል አምላክ ሰዎችን በተለያዩ ጉዳዮች ለመርዳት እስከ ምን ድረስ እንደሚጠቀምባቸው ልናውቅ አንችልም። ሆኖም ይሖዋ ‘በፍጹም ልባቸው የሚታመኑበትን እንደሚያበረታ’ እናውቃለን። (2 ዜና መዋዕል 16:​9፤ መዝሙር 91:​11) “ማንኛውንም ነገር እንደ ፈቃዱ ብንለምን እርሱ [አምላክ] ይሰማናል” የሚል ማረጋገጫም ተሰጥቶናል።​—⁠1 ዮሐንስ 5:​14

ጸሎቶቻችንንና አምልኳችንን ማቅረብ ያለብን በቀጥታ ለአምላክ ብቻ መሆን እንዳለበት ቅዱሳን ጽሑፎች ይነግሩናል። (ዘፀአት 20:​3-5፤ መዝሙር 5:​1, 2፤ ማቴዎስ 6:​9) ታማኝ መላእክት እንዲህ እንድናደርግ ያበረታቱናል። ለምሳሌ ሐዋርያው ዮሐንስ ለአንድ መልአክ ለመስገድ ሲሞክር መልአኩ “ተው! ይህን አታድርግ! . . . ለእግዚአብሔር ስገድ” በማለት ገሥጾታል።​—⁠ራእይ 19:​10

መላእክት የአምላክን መልእክት ያደርሳሉ

“መልአክ” የሚለው ቃል “መልእክተኛ” የሚል ትርጉም ያለው ሲሆን ይህም መላእክት አምላክን የሚያገለግሉበትን ሌላኛውን መንገድ ይጠቁመናል። መላእክት ከአምላክ የተላኩትን መልእክት ለሰዎች ያደርሳሉ። ለምሳሌ፣ መጽሐፍ ቅዱስ “እግዚአብሔር መልአኩ ገብርኤልን በገሊላ ወደምትገኘው ወደ ናዝሬት ከተማ ላከው” ይላል። ለምን? ማርያም ተብላ ወደምትጠራ አንዲት ወጣት ሴት በመሄድ ድንግል ብትሆንም እንኳ እንደምትፀንስና ኢየሱስ የሚባል ወንድ ልጅ እንደምትወልድ ለመንገር ነበር። (ሉቃስ 1:​26-31) አንድ መልአክ በሜዳ ላሉ እረኞች “ጌታ ክርስቶስ” መወለዱን እንዲያበስራቸውም ተልኳል። (ሉቃስ 2:​8-11) በተመሳሳይ መላእክት ለአብርሃም፣ ለሙሴ፣ ለኢየሱስና ታሪካቸው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ለተመዘገበ ለሌሎች ሰዎች ከአምላክ የተላከ መልእክት አድርሰዋል።​—⁠ዘፍጥረት 18:​1-5, 10፤ ዘፀአት 3:​1, 2፤ ሉቃስ 22:​39-43

መላእክት በዘመናችን የአምላክ መልእክተኞች ሆነው የሚያገለግሉት እንዴት ነው? ኢየሱስ፣ ለተከታዮቹ ይህ ሥርዓት ከመደምደሙ በፊት ማከናወን የሚገባቸውን ሥራ ሲገልጽ “ለሕዝብ ሁሉ ምስክር እንዲሆን፣ ይህ የመንግሥት ወንጌል በዓለም ሁሉ ይሰበካል፤ ከዚያም መጨረሻው ይመጣል” በማለት ተናግሯል። (ማቴዎስ 24:​3, 14) የይሖዋ ምሥክሮች የአምላክን መንግሥት ምሥራች በመስበክ በዓመት ከአንድ ቢሊዮን ሰዓት በላይ ያሳልፋሉ። ሆኖም በዚህ ሥራ ላይ መላእክትም እንደሚሳተፉ ታውቅ ነበር? ሐዋርያው ዮሐንስ ያየውን ራእይ ሲናገር “ሌላ መልአክ . . . አየሁ፤ እርሱም በምድር ላይ ለሚኖሩ ለሕዝብ፣ ለነገድ፣ ለቋንቋና ለወገን ሁሉ የሚሰብከውን የዘላለም ወንጌል ይዞ ነበር” ብሏል። (ራእይ 14:​6, 7) ይህ ጥቅስ በዛሬው ጊዜ መላእክት ለሰው ልጆች እያከናወኑ ያሉትን በጣም አስፈላጊ ሥራ ያጎላል።

የይሖዋ ምሥክሮች ከቤት ወደ ቤት እየሄዱ የሚያከናውኑት የስብከት ሥራ መላእክታዊ አመራር እንዳለበት የሚጠቁም ማስረጃ አላቸው። ብዙ ጊዜ፣ የአምላክን ዓላማ ለማወቅ እንዲችሉ እየጸለዩ ከነበሩ ሰዎች ጋር ተገናኝተዋል። ምሥክሮቹ በሚያከናውኑት ሥራ ላይ የመላእክት አመራር ታክሎበት በየዓመቱ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ይሖዋን ለማወቅ ችለዋል። እንግዲያው በመላእክት መሪነት ከሚካሄደው ሕይወት አድን ሥራ ተጠቃሚ እንድትሆን እንጋብዝ​ሃለን።

መላእክት የአምላክን የቅጣት ፍርድ ያስፈጽማሉ

መላእክት በሰዎች ላይ የመፍረድ ሥልጣን ባይኖራቸውም እንዲሁ ዳር ቆመው ተመልካቾች ግን አይደሉም። (ዮሐንስ 5:​22፤ ዕብራውያን 12:​22, 23) ባለፉት ጊዜያት የአምላክን ፍርድ በማስፈጸም ረገድ የቅጣት እርምጃ በመውሰድ አገልግለዋል። ለምሳሌ ያህል አምላክ፣ እስራኤላውያንን በባርነት የያዟቸውን የጥንት ግብፃውያንን ለማጥፋት በመላእክት ተጠቅሟል። (መዝሙር 78:​49) “የእግዚአብሔር መልአክ” በአንድ ምሽት ብቻ የአምላክ ሕዝብ ጠላቶች በሚገኙበት የጦር ሰፈር ውስጥ አንድ መቶ ሰማንያ አምስት ሺህ ወታደሮችን ገድሏል።​—⁠2 ነገሥት 19:​35

ወደፊትም ቢሆን መላእክት የአምላክን የቅጣት ፍርድ ያስፈጽማሉ። ኢየሱስ “በሚንበለበል እሳት ከኀያላን መላእክት ጋር ከሰማይ በሚገለጥበት ጊዜ . . . እግዚአብሔርን የማያውቁትንና . . . [ለ]ወንጌል የማይታዘዙትን ይበቀላል።” (2 ተሰሎንቄ 1:​7, 8) በዚያ ወቅት የሚጠፉት ግን በአሁኑ ጊዜ በምድር ዙሪያ በመላእክት እርዳታ እየተሰበከ ያለውን መልእክት የማይቀበሉ ሰዎች ብቻ ናቸው። አምላክን የሚፈልጉና ቅዱስ ጽሑፋዊውን መመሪያ የሚከተሉ ሰዎች ግን ጉዳት አይደርስባቸውም።​—⁠ሶፎንያስ 2:​3

የአምላክን ትእዛዝ ሁልጊዜ የሚከተሉ ታማኝ መላእክት በመኖራቸው ምንኛ አመስጋኝ መሆን ይገባናል! ይሖዋ በምድር ላይ የሚገኙትን ታማኝ አገልጋዮቹን ለመርዳትና ለመጠበቅ በመላእክት ይጠቀማል። እኛን መጉዳት የሚፈልጉ አጋንንት ተብለው የሚጠሩ አደገኛ መንፈሳዊ ፍጡራን ስላሉ ይህን ማወቃችን በጣም የሚያጽናና ነው።

አጋንንት እነማን ናቸው?

ሰይጣን በኤደን ውስጥ ሔዋንን ካታለላት በኋላ በነበሩት 1, 500 ዓመታት ውስጥ የአምላክ ቤተሰብ አባላት የሆኑት መላእክት፣ ሰይጣን ዲያብሎስ እንደ አቤል፣ ሄኖክና ኖኅ ካሉት ጥቂት ታማኞች በስተቀር ሁሉንም ሰዎች ከአምላክ ዞር በማድረግ ረገድ እንደተሳካለት ተመልክተዋል። (ዘፍጥረት 3:​1-7፤ ዕብራውያን 11:​4, 5, 7) አንዳንድ መላእክትም ቢሆኑ ሰይጣንን ተከትለዋል። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ እነርሱ ሲናገር “በኖኅ ዘመን” የነበሩ ታዛዥ ያልሆኑ መንፈሳዊ ፍጡራን እንደሆኑ አድርጎ ይገልጻቸዋል። (1 ጴጥሮስ 3:​19, 20) አለመታዘዛቸው በግልጽ የታየው እንዴት ነበር?

በኖኅ ዘመን ቁጥራቸው ያልተገለጸ ዓመጸኛ መላእክት በሰማይ የሚገኘውን የአምላክ ቤተሰብ ትተው ሥጋዊ አካል በመልበስ ወደ ምድር መጡ። ይህን ያደረጉት ለምን ነበር? ከሴቶች ጋር የጾታ ግንኙነት የመፈጸም ምኞት በውስጣቸው በማዳበራቸው ምክንያት ነበር። በዚህም ሁኔታ ኔፍሊም የተባሉ ልጆች የወለዱ ሲሆን እነርሱም ግዙፍና ዓመጸኛ ሰዎች ሆኑ። ከዚህም በተጨማሪ “የሰው ዐመፅ በምድር ላይ የበዛና የልቡም ሐሳብ ዘወትር ወደ ክፋት ብቻ ያዘነበለ” ነበር። ሆኖም ይሖዋ አምላክ ይህ የሰው ልጆች ዓመጽ እንዲቀጥል አልፈቀደም። ዓለም አቀፍ የጥፋት ውኃ በማምጣት ኔፍሊሞችን ጨምሮ ሁሉንም ክፉ ሰዎች ጠራርጎ አጠፋቸው። ከጥፋቱ የተረፉት ሰዎች የአምላክ ታማኝ አገልጋዮች ብቻ ነበሩ።​—⁠ዘፍጥረት 6:​1-7, 17፤ 7:​23

እነዚህ ዓመጸኛ መላእክት በዚያ ወቅት ከጥፋት ውኃ አምልጠዋል። ሥጋዊ አካላቸውን ትተው መንፈሳዊ ፍጡራን በመሆን ወደ መንፈሳዊው ዓለም ተመለሱ። ከዚያ በኋላ አጋንንት ተብለው መጠራት ጀመሩ። ‘የአጋንንት አለቃ’ ተብሎ ከሚጠራው ከሰይጣን ዲያብሎስ ጎን ለመቆም መረጡ። (ማቴዎስ 12:​24-27) ልክ እንደ አለቃቸው ሁሉ አጋንንትም በሰዎች መመለክ ይፈልጋሉ።

አጋንንት አደገኞች ቢሆኑም ልንፈራቸው አይገባም። ያላቸው ኃይል የተወሰነ ነው። እነዚህ ዓመጸኛ መላእክት ወደ ሰማይ ሲመለሱ የአምላክ ቤተሰብ አባላት ከሆኑት ታማኝ መላእክት ጋር እንዲቀላቀሉ አልተፈቀደላቸውም። ከዚህ ይልቅ የአምላክን መንፈሳዊ እውቀት እንዳያገኙ የተደረጉ ሲሆን የወደፊቱ ጊዜም ጨለማ ሆነባቸው። ታርታሩስ ተብሎ በሚጠራ በመንፈሳዊ ጨለማ በሆነ ሁኔታ ውስጥ እንዲቆዩ ተደረጉ። (2 ጴጥሮስ 2:​4 የግርጌ ማስታወሻ) በመንፈሳዊ ጨለማ ውስጥ እንዲሆኑ ይሖዋ “በዘላለም እስራት” ቀጥቷቸዋል። በተጨማሪም በአሁኑ ጊዜ ሥጋ መልበስ አይችሉም።​—⁠ይሁዳ 6

ምን ማድረግ ይኖርብሃል?

በአሁኑ ጊዜ አጋንንት በሰው ልጆች ላይ ተጽዕኖ እያሳደሩ ይሆን? አዎን፣ እንደ አለቃቸው እንደ ሰይጣን ዲያብሎስ እነርሱም ‘በተንኰል ሥራዎች’ ይጠቀማሉ። (ኤፌሶን 6:​11, 12) ሆኖም የአምላክ ቃል የሚሰጠውን ምክር በተግባር በማዋል አጋንንትን በድፍረት ልንቋቋማቸው እንችላለን። በተጨማሪም አምላክን የሚወዱ ሰዎች ኃያላን ከሆኑት መላእክት ጥበቃ ያገኛሉ።

አምላክ የሚፈልግብህን ብቃቶች ከቅዱሳን ጽሑፎች ማጥናትህና የተማርከውን ተግባራዊ ማድረግህ በጣም አስፈላጊ ነው! ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች ይበልጥ ለማወቅ ከፈለግህ በአካባቢህ ከሚገኙት የይሖዋ ምሥክሮች ጋር መገናኘት ወይም የዚህ መጽሔት አዘጋጆች ወደሆኑት ሰዎች መጻፍ ትችላለህ። የይሖዋ ምሥክሮች አንተን፣ በሚመችህ ጊዜና ያለ ክፍያ መጽሐፍ ቅዱስን በማስጠናት ይደሰታሉ።

[የግርጌ ማስታወሻ]

a መላእክት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በጉልምስና ዕድሜ ላይ እንደሚገኙ ወንዶች ተደርገው ተገልጸዋል። ለሰዎች ሲገለጡ ሁልጊዜ በተባዕታይ ፆታ ነው።

[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

መላእክት የተደራጁበት መንገድ

ይሖዋ በጣም ሰፊ የሆነውን መላእክታዊ ቤተሰቡን እንደሚከተለው አድርጎ አደራጅቶታል:-

በኃይልም ሆነ በሥልጣን ከሁሉም የሚበልጠው ሊቀ መልአክ የሆነው ሚካኤል ወይም ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። (1 ተሰሎንቄ 4:​16፤ ይሁዳ 9) በእርሱ ሥር ሱራፌል፣ ኪሩቤልና ሌሎች መላእክት አሉ።

ሱራፌል በአምላክ ዝግጅት ውስጥ እጅግ ከፍተኛውን ቦታ ይይዛሉ። በአምላክ ዙፋን አጠገብ ያገለግላሉ። የሥራ ምድባቸው የአምላክን ቅድስና ማወጅና ሕዝቦቹ ንጽሕናቸውን እንደያዙ እንዲቀጥሉ ማድረግን ይጨምራል።​—⁠ኢሳይያስ 6:​1-3, 6, 7

ኪሩቤል የአምላክ ዙፋን አጃቢዎችና የይሖዋን ታላቅነት የሚያስከብሩ ናቸው።​—⁠መዝሙር 80:​1፤ 99:​1፤ ሕዝቅኤል 10:​1, 2

ሌሎች መላእክት የይሖዋ ወኪሎች ሲሆኑ መለኮታዊውን ፈቃድ ያስፈጽማሉ።

[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

መላእክት ሎጥና ሁለት ሴቶች ልጆቹ ከጥፋቱ እንዲያመልጡ አድርገዋል

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሐዋርያው ዮሐንስ ለመልአኩ ለመስገድ ሲሞክር “ተው! ይህን አታድርግ!” ብሎታል

[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

መላእክት የአምላክን የቅጣት ፍርድ ያስፈጽማሉ

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በመላእክት መሪነት ከሚካሄደው የስብከት ሥራ እየተጠቀምክ ነው?