በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ይሖዋ ‘ከልብ ለሚሹት ዋጋ ይሰጣል’

ይሖዋ ‘ከልብ ለሚሹት ዋጋ ይሰጣል’

ይሖዋ ‘ከልብ ለሚሹት ዋጋ ይሰጣል’

“ወደ እግዚአብሔር የሚቀርብ ሁሉ እግዚአብሔር መኖሩንና ከልብ ለሚሹትም ዋጋ እንደሚሰጥ ማመን አለበት።”—ዕብራውያን 11:6

1, 2. አንዳንድ የይሖዋ አገልጋዮች ከአሉታዊ ስሜቶች ጋር መታገል የሚኖርባቸው ለምን ሊሆን ይችላል?

 ባርብራ የምትባል አንዲት እህት “የይሖዋ ምሥክር ከሆንኩ ወደ 30 ዓመት ገደማ ይጠጋኛል፤ ይሁንና በዚህ ስም ለመጠራት እንደምበቃ ተሰምቶኝ አያውቅም” በማለት ሐሳብ ሰጥታለች። a አክላም “አቅኚ መሆንና ሌሎች ልዩ መብቶች ማግኘት ብችልም ከእነዚህ መካከል አንዳቸውም የይሖዋ ምሥክር ተብዬ ለመጠራት እበቃለሁ ብዬ ከልቤ እንዳምን አላደረጉኝም” ብላለች። ኪት የተባለ ወንድምም የሚከተለውን ተመሳሳይ ሐሳብ ሰጥቷል:- “የይሖዋ አገልጋዮች ሊደሰቱባቸው የሚችሉ በርካታ ምክንያቶች ቢኖሩም እንኳን እኔ ደስተኛ አልነበርኩም፤ ስለዚህ አንዳንድ ጊዜ ዋጋ ቢስ እንደሆንኩ ይሰማኛል። ይህ ደግሞ ነገሮች እንዲባባሱ መንገድ የሚከፍት የጥፋተኝነት ስሜት ፈጥሮብኛል።”

2 ጥንትም ሆነ ዛሬ በርካታ ታማኝ የይሖዋ አገልጋዮች እነዚህን ከሚመስሉ ስሜቶች ጋር መታገል አስፈልጓቸዋል። አንተስ አንዳንድ ጊዜ እንዲህ ይሰማሃል? የእምነት ወንድሞችህ ደስተኛ ሕይወት ሲመሩና ያለ ጭንቀት ሲኖሩ አንተ ግን ችግር ተፈራርቆብህ ይሆናል። በዚህ ምክንያት የይሖዋ ሞገስ እንደተለየህ ወይም ደግሞ የእርሱን ትኩረት ማግኘት የማይገባህ ሰው እንደሆንክ ሊሰማህ ይችላል። ሆኖም እንዲህ ብለህ ለመደምደም አትቸኩል። መጽሐፍ ቅዱስ “[ይሖዋ] የተጨነቀውን ሰው ጭንቀት፣ አልናቀም፤ ቸልም አላለምና፤ ፊቱንም ከእርሱ አልሰወረም፤ ነገር ግን ድረስልኝ ብሎ ሲጮኽ ሰማው” የሚል ማረጋገጫ ይሰጠናል። (መዝሙር 22:24) እነዚህ ስለ መሲሑ የተነገሩ ትንቢታዊ ቃላት ይሖዋ ለእርሱ ታማኝ የሆኑ ሰዎችን መስማት ብቻ ሳይሆን የጥረታቸውንም ዋጋ እንደሚከፍላቸው ያሳያሉ።

3. ይህ ሥርዓት ከሚያስከትላቸው ጭንቀቶች ማምለጥ የማንችለው ለምንድን ነው?

3 ማንም ሰው ቢሆን ሌላው ቀርቶ የይሖዋ ምሥክሮች እንኳ ይህ ሥርዓት ከሚያስከትላቸው ጭንቀቶች ማምለጥ አይችሉም። ያለንበትን ዓለም የሚመራው የይሖዋ ዋነኛ ጠላት የሆነው ሰይጣን ዲያብሎስ ነው። (2 ቆሮንቶስ 4:4፤ 1 ዮሐንስ 5:19) የይሖዋ ምሥክሮች ተአምራዊ ጥበቃ አያገኙም፤ እንዲያውም በተቃራኒው የሰይጣን ዋነኛ ዒላማዎች ናቸው። (ኢዮብ 1:7-12፤ ራእይ 2:10) ስለዚህ ይሖዋ እንደሚያስብልን በመተማመን እርሱ እስከወሰነው ጊዜ ድረስ ‘በመከራ መታገሥና በጸሎት መጽናት’ ይኖርብናል። (ሮሜ 12:12) ይህ ዓለም የሚያደርስብን ጭንቀት ‘አምላካችን ይሖዋ አይወደንም’ ብሎ ወደ መደምደሙ እንዲያመራን መፍቀድ የለብንም!

በጥንት ዘመን የኖሩ የጽናት ምሳሌዎች

4. ያጋጠሟቸውን አሳዛኝ ሁኔታዎች ከተቋቋሙ ታማኝ የይሖዋ አገልጋዮች ውስጥ አንዳንዶቹን ጥቀስ።

4 በጥንት ዘመን ይኖሩ የነበሩ በርካታ የይሖዋ አገልጋዮች ያጋጠሟቸውን አሳዛኝ ሁኔታዎች መቋቋም ነበረባቸው። ለምሳሌ ያህል ሐና ልጅ ባለመውለዷ ምክንያት “በነፍሷ ተመርራ” ነበር፤ ይህ የደረሰባት አምላክ ስለረሳት እንደሆነ ታስብ ነበር። (1 ሳሙኤል 1:9-11) ኤልያስ ነፍሰ ገዳይዋ ንግሥት ኤልዛቤል ታሳድደው በነበረ ጊዜ ፍርሃት ስለተሰማው “እግዚአብሔር ሆይ፤ በቅቶኛል፤ እኔ ከቀደሙት አባቶቼ አልበልጥምና ነፍሴን ውሰዳት” በማለት ወደ ይሖዋ ጸልዮአል። (1 ነገሥት 19:4) ሐዋርያው ጳውሎስም “በጎ ነገር ለመሥራት ስፈልግ፣ ክፋት ከእኔ ጋር አለ። . . . እኔ ምን ዐይነት ጐስቋላ ሰው ነኝ!” በማለት የጻፈው አለፍጽምናው በጣም ስለከበደው መሆን አለበት።—ሮሜ 7:21-24

5. (ሀ) ሐና፣ ኤልያስና ጳውሎስ ወሮታቸውን ያገኙት እንዴት ነው? (ለ) ከአሉታዊ አመለካከት ጋር እየታገልን ከሆነ ከአምላክ ቃል ውስጥ ምን መጽናኛ ማግኘት እንችላለን?

5 በእርግጥ ሐና፣ ኤልያስና ጳውሎስ ይሖዋን ማገልገላቸውን እንደቀጠሉና እርሱም ወሮታቸውን አትረፍርፎ እንደከፈላቸው እናውቃለን። (1 ሳሙኤል 1:20፤ 2:21፤ 1 ነገሥት 19:5-18፤ 2 ጢሞቴዎስ 4:8) ይሁንና ሐዘንን፣ ተስፋ መቁረጥንና ፍርሃትን ከመሳሰሉ በሰው ልጆች ላይ ከሚደርሱ ሁሉም ዓይነት ስሜቶች ጋር መታገል አስፈልጓቸው ነበር። ስለዚህ አንዳንድ ጊዜ አሉታዊ አስተሳሰብ ቢፈጠርብን ልንደነቅ አይገባንም። ሆኖም በሕይወትህ ውስጥ የሚያጋጥሙህ ጭንቀቶች በእርግጥ ይሖዋ የሚወድህ መሆኑን እንድትጠራጠር ቢያደርጉህ ምን ማድረግ ትችላለህ? ከአምላክ ቃል መጽናኛ ማግኘት ትችላለህ። ለምሳሌ ያህል ባለፈው ርዕሰ ትምህርት ላይ ኢየሱስ “የራስ ጠጒራችሁ እንኳ አንድ ሳይቀር” በይሖዋ ተቆጥሯል በማለት ስለተናገረው ሐሳብ ተመልክተን ነበር። (ማቴዎስ 10:30) እነዚህ አበረታች ቃላት ይሖዋ ለእያንዳንዱ አገልጋዩ በጥልቅ እንደሚያስብ ያሳያሉ። እንዲሁም ኢየሱስ ስለ ድንቢጦች የተናገረውን ምሳሌ አስታውስ። ከእነዚህ ወፎች አንዷ እንኳ ያለ እርሱ ፈቃድ በምድር ላይ የማትወድቅ ከሆነ ይሖዋ የአንተን ችግር ላለመመልከት እንዴት ፊቱን ሊያዞር ይችላል?

6. መጽሐፍ ቅዱስ ከአሉታዊ አመለካከቶች ጋር እየተፋለሙ ላሉ ሰዎች የብርታት ምንጭ የሚሆነው እንዴት ነው?

6 እኛ ፍጽምና የሚጎድለን የሰው ልጆች፣ እጅግ ታላቅ ኃይል ባለው ፈጣሪ በይሖዋ አምላክ ፊት ውድ ልንሆን እንችላለን? እንዴታ! እንዲያውም ይህንን የሚያረጋግጡልን በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች አሉ። በእነዚህ ጥቅሶች ላይ ካሰላሰልን መዝሙራዊው “የውስጤ ጭንቀት በበዛ መጠን፣ ማጽናናትህ ነፍሴን ደስ አሰኛት” በማለት የተናገራቸውን ቃላት ማስተጋባት እንችላለን። (መዝሙር 94:19) በአምላክ ፊት ዋጋ እንዳለንና የእርሱን ፈቃድ መፈጸማችንን ከቀጠልን ወሮታችንን እንደሚከፍለን በይበልጥ ከሚያረጋግጡልን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከሚገኙት የሚያጽናኑ ቃላት መካከል ጥቂቶቹን እንመልከት።

የይሖዋ ‘ገንዘብ’

7. ይሖዋ በሚልክያስ በኩል ምግባረ ብልሹ ለነበረው ብሔር ምን የሚያበረታታ ትንቢት ተናገረ?

7 ከክርስቶስ ልደት በፊት በአምስተኛው መቶ ዘመን አይሁዳውያን አምላክን በሚያሳዝን ሁኔታ ውስጥ ይገኙ ነበር። ካህናቱ መሥዋዕት ሆነው ለመቅረብ የማይመጥኑ እንስሶችን ተቀብለው በይሖዋ መሠዊያ ላይ ያቀርቡ፣ ዳኞች ደግሞ አድልዎ ያደርጉ ነበር። እንዲሁም መተት፣ ሐሰት መናገር፣ ማታለልና ምንዝር ተስፋፍቶ ነበር። (ሚልክያስ 1:8፤ 2:9፤ 3:5) ሚልክያስ ምግባረ ብልሹነት በግልጽ ይታይበት የነበረውን ይህን ብሔር በተመለከተ የሚያስገርም ትንቢት ተናገረ። ይሖዋ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ሕዝቡ እንደገና ተቀባይነት ወደሚያገኝበት ሁኔታ እንዲመለስ ያደርገዋል። እንዲህ የሚል እናነባለን:- “‘እኔ በምሠራበት ቀን እነርሱ የገዛ ገንዘቤ ይሆናሉ’ ይላል እግዚአብሔር ጸባኦት፤ ‘አባት የሚያገለግለውን ልጁን እንደሚታደግ ሁሉ እኔም እታደጋቸዋለሁ።’”—ሚልክያስ 3:17

8. ሚልክያስ 3:17 በመሠረታዊ ሥርዓት ደረጃ በእጅግ ብዙ ሕዝቦችም ላይ ሊሠራ የሚችለው ለምንድን ነው?

8 የሚልክያስ ትንቢት፣ 144,000 አባላት ያሉትን መንፈሳዊ ብሔር ካዋቀሩት በመንፈስ የተቀቡ ክርስቲያኖች ጋር በተያያዘ ዘመናዊ ፍጻሜ አለው። በእርግጥም ይህ ብሔር የይሖዋ ‘ገንዘብ’ ወይም ይሖዋ ‘ለራሱ የለየው ሕዝብ’ ነው። (1 ጴጥሮስ 2:9) በተጨማሪም ‘ነጭ ልብስ ለብሰው በዙፋኑና በበጉ ፊት የቆሙት እጅግ ብዙ ሕዝብ’ ከሚልክያስ ትንቢት ማበረታቻ ማግኘት ይችላሉ። (ራእይ 7:4, 9) እነዚህ እጅግ ብዙ ሕዝቦችና ቅቡዓን በአንዱ እረኛ በኢየሱስ ክርስቶስ ሥር አንድ መንጋ ሆነዋል።—ዮሐንስ 10:16

9. የይሖዋ ሕዝቦች ለእርሱ ‘የገዛ ገንዘቡ’ የሆኑት ለምንድን ነው?

9 ይሖዋ እርሱን ለማገልገል የሚፈልጉትን ሰዎች እንዴት ይመለከታቸዋል? በሚልክያስ 3:17 ላይ እንደተገለጸው አንድ አፍቃሪ አባት ልጁን በሚመለከትበት መንገድ ያያቸዋል። እንዲሁም ሕዝቡን “የገዛ ገንዘቤ” በማለት በአክብሮት እንደጠራቸው ልብ በል። ሌሎች ትርጉሞችም ሐረጉን “የግሌ፣” “እጅግ ውድ የሆነ ንብረቴ፣” እና “ጌጦቼ” ብለው ተርጉመውታል። ይሖዋ አገልጋዮቹን ልዩ አድርጎ የሚመለከታቸው ለምንድን ነው? አንደኛው ምክንያት ውለታ የማይረሳ አምላክ በመሆኑ ነው። (ዕብራውያን 6:10) ከልባቸው የሚያገለግሉትን ሰዎች ይበልጥ ይቀርባቸዋል እንዲሁም ልዩ አድርጎ ይመለከታቸዋል።

10. ይሖዋ ለሕዝቡ ጥበቃ የሚያደርገው እንዴት ነው?

10 ከፍ አድርገህ የምትመለከተው የራስህ የሆነ ውድ ንብረት አለህ? ለዚህ ውድ ንብረትህ ጥንቃቄ አታደርግም? ይሖዋም ‘ለገዛ ገንዘቡ’ ተመሳሳይ ጥንቃቄ ያደርጋል። እርግጥ ነው፣ ይሖዋ ሕዝቡ ላይ ምንም ዓይነት ችግርና አሳዛኝ ሁኔታ እንዳይደርስ አይከላከልም። (መክብብ 9:11) ይሁንና ለታማኝ አገልጋዮቹ መንፈሳዊ ጥበቃ ማድረግ ይችላል፣ ደግሞም ያደርግላቸዋል። የሚያጋጥማቸውን ማንኛውንም ዓይነት ፈተና መታገሥ የሚችሉበትን ጥንካሬ ይሰጣቸዋል። (1 ቆሮንቶስ 10:13) በዚህ ምክንያት ሙሴ የአምላክ የጥንት ሕዝቦች ለነበሩት እስራኤላውያን “ብርቱና ደፋር ሁኑ፤ . . . አምላክህ እግዚአብሔር ካንተ ጋር ይሄዳልና፤ አይተውህም፤ አይጥልህምም” ብሏቸው ነበር። (ዘዳግም 31:6) ይሖዋ ለሕዝቡ ተገቢውን እንክብካቤ ያደርጋል። እንደ ‘ገዛ ገንዘቡ’ አድርጎም ይመለከታቸዋል።

‘ዋጋ የሚሰጠው’ ይሖዋ

11, 12. ይሖዋ ዋጋ የሚከፍል አምላክ መሆኑን ማመናችን የጥርጣሬን ስሜት ለመዋጋት የሚረዳን እንዴት ነው?

11 ይሖዋ ለአገልጋዮቹ ላቅ ያለ ግምት እንደሚሰጥ የሚያሳየው ሌላ ማረጋገጫ ደግሞ ዋጋቸውን የሚከፍላቸው መሆኑ ነው። ለእስራኤላውያን እንዲህ ብሏቸው ነበር:- “‘በዚህ እንድትፈትኑኝ . . .’ ይላል እግዚአብሔር ጸባኦት፤ ‘የሰማይን መስኮት የማልከፍትላችሁ፣ የተትረፈረፈ በረከትንም ማስቀመጫ እስክታጡ ድረስ የማላፈስላችሁ ከሆነ ተመልከቱ።’” (ሚልክያስ 3:10) ወደፊት ይሖዋ ለአገልጋዮቹ የዘላለምን ሕይወት ዋጋ አድርጎ እንደሚሰጣቸው የተረጋገጠ ነው። (ዮሐንስ 5:24፤ ራእይ 21:4) ይህ እጅግ ውድ የሆነ ዋጋ የይሖዋን ፍቅርና ለጋስነት ጥልቀት፣ እንዲሁም እርሱን ማገልገል የሚፈልጉ ሰዎችን ምን ያህል ከፍ አድርጎ እንደሚመለከታቸው ያሳያል። ይሖዋ በልግስና ዋጋ የሚከፍል አምላክ መሆኑን ማመናችን እርሱ እኛን ስለሚያይበት መንገድ የሚፈጠሩብንን ጥርጣሬዎች ሁሉ ለመዋጋት ይረዳናል። እንዲያውም ይሖዋ ራሱ እንዲህ አድርገን እንድንመለከተው አሳስቦናል! ጳውሎስ “ወደ እግዚአብሔር የሚቀርብ ሁሉ እግዚአብሔር መኖሩንና ከልብ ለሚሹትም ዋጋ እንደሚሰጥ ማመን አለበት” በማለት ጽፏል።—ዕብራውያን 11:6

12 በእርግጥ ይሖዋን የምናገለግለው ስለምንወደው እንጂ ዋጋ እንደሚከፍለን ቃል ስለገባልን አይደለም። ይሁንና የሚከፍለንን ወሮታ በጉጉት መጠባበቃችን ተገቢ ያልሆነ ፍላጎት ወይም ደግሞ የራስ ወዳድነት ምኞት አይደለም። (ቆላስይስ 3:23, 24) ይሖዋ ከልብ የሚፈልጉትን ሰዎች ስለሚወዳቸውና ከፍ አድርጎ ስለሚመለከታቸው በራሱ ተነሳሽነት ዋጋቸውን ይከፍላቸዋል።

13. የቤዛው ዝግጅት ይሖዋ ለእኛ ያለው ፍቅር ዋነኛ ማስረጃ ነው የምንለው ለምንድን ነው?

13 ይሖዋ የቤዛ ዝግጅት ማድረጉ የሰው ልጆች በእርሱ ፊት ምን ያህል ውድ እንደሆኑ የሚያሳይ ዋነኛው ማስረጃ ነው። ሐዋርያው ዮሐንስ “በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስከ መስጠት ድረስ ዓለምን እንዲሁ ወዶአልና” በማለት ጽፏል። (ዮሐንስ 3:16) ኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት ሆኖ መቅረቡ ‘ይሖዋ ከቁብ አይቆጥረንም ወይም አይወደንም’ ከሚለው ሐሳብ ጋር ይቃረናል። አዎን፣ ይሖዋ በጣም ከፍተኛ የሆነ ዋጋ ከከፈለልን ማለትም የአንድያ ልጁን ሕይወት ከሠዋልን እጅግ በጣም ይወደናል ማለት ነው።

14. ጳውሎስ ለቤዛው የነበረውን አመለካከት የሚያሳየው ምንድን ነው?

14 ስለዚህ አሉታዊ ስሜቶች ሲያይሉብህ በቤዛው ላይ አሰላስል። አዎን፣ ቤዛውን ከይሖዋ በግል እንዳገኘኸው ስጦታ አድርገህ ተመልከተው። ሐዋርያው ጳውሎስ ያደረገው ይህንኑ ነበር። “እኔ ምን ዐይነት ጐስቋላ ሰው ነኝ!” ብሎ እንደነበር አስታውስ። ይሁንና አክሎ “በወደደኝና ስለ እኔ ራሱን አሳልፎ በሰጠው በእግዚአብሔር ልጅ” “በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ምስጋና ለእግዚአብሔር ይሁን” በማለት ተናግሯል። (ሮሜ 7:24, 25፤ ገላትያ 2:20) ጳውሎስ እንዲህ ያለው ራሱን ለማዋደድ ሳይሆን ይሖዋ በግለሰብ ደረጃ ከፍ አድርጎ እንደሚመለከተው እምነት እንደነበረው ለመግለጽ ነው። አንተም ልክ እንደ ጳውሎስ ቤዛው በግል ከአምላክ ያገኘኸው ስጦታ እንደሆነ አድርገህ መመልከትን መማር አለብህ። ይሖዋ ታላቅ ኃይል ያለው አዳኝ ብቻ ሳይሆን በፍቅር ተነሳስቶ ዋጋ የሚከፍል አምላክ ነው።

በሰይጣን “የተንኰል ሥራ” እንዳትታለል ተጠንቀቅ

15-17. (ሀ) ዲያብሎስ አሉታዊ ስሜቶችን ተጠቅሞ የሚያጠቃን እንዴት ነው? (ለ) ከኢዮብ ታሪክ ምን ማበረታቻ ማግኘት እንችላለን?

15 እንዲህም ሆኖ በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኙት በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፉ ማጽናኛዎች በእርግጥ ለአንተም የሚሠሩ መሆናቸውን ማመኑ ይከብድህ ይሆናል። በአምላክ አዲስ ዓለም ውስጥ የዘላለም ሕይወት ሽልማት ማግኘት የሚችሉት ሌሎች ሰዎች እንጂ አንተ ለዚህ እንደማትበቃ ይሰማህ ይሆናል። እንዲህ የሚሰማህ ከሆነ ምን ማድረግ ትችላለህ?

16 “የዲያብሎስን የተንኰል ሥራ መቋቋም ትችሉ ዘንድ፣ የእግዚአብሔርን ሙሉ የጦር ዕቃ ልበሱ” በማለት ጳውሎስ ለኤፌሶን ክርስቲያኖች የነገራቸውን ማሳሰቢያ እንደምታውቅ ምንም አያጠራጥርም። (ኤፌሶን 6:11) ስለ ሰይጣን የማጥመጃ ዘዴዎች ስናስብ እንደ ፍቅረ ነዋይና ምግባረ ብልሹነት የመሳሰሉ ነገሮች ወዲያውኑ ወደ አእምሯችን ይመጡ ይሆናል፤ ደግሞም እውነት ነው። እንዲህ ያሉት ማታለያዎች የጥንቶቹንም ሆነ የዘመናችንን በርካታ የአምላክ ሕዝቦች አጥምደዋል። ይሁንና ሌላውንም የተንኮል ሥራውን ችላ ማለት አይገባንም፤ ሰዎች ይሖዋ አምላክ እንደማይወዳቸው ሆኖ እንዲሰማቸው ለማድረግ ይጥራል።

17 ሰይጣን ሰዎችን ከአምላክ እንዲርቁ ለማድረግ እንዲህ ባሉ ስሜቶች በመጠቀም ረገድ የተዋጣለት ነው። በልዳዶስ ለኢዮብ “ሰው በእግዚአብሔር ፊት ጻድቅ ይሆን ዘንድ፣ ከሴትስ የተወለደ ንጹሕ ይሆን ዘንድ ይችላልን? በፊቱ ጨረቃ እንኳ ብሩህ ካልሆነች፣ ከዋክብትም ንጹሓን ካልሆኑ፣ ይልቁን ከብል የሚቈጠር የሰው ልጅ፣ ትል የሆነውማ ሰው ምንኛ ያንስ!” በማለት ነግሮት እንደነበር አስታውስ። (ኢዮብ 25:4-6፤ ዮሐንስ 8:44) እነዚህ ቃላት ምን ያህል ቅስም እንደሚሰብሩ መገመት ትችላለህ! ሰይጣን ተስፋ እንዲያስቆርጥህ በጭራሽ አትፍቀድለት። በሌላ በኩል ደግሞ ትክክል የሆነውን ነገር ለማድረግ በምትጣጣርበት ጊዜ አስፈላጊውን ድፍረትና ጥንካሬ ለማግኘት እንድትችል የሰይጣንን እቅዶች እወቃቸው። (2 ቆሮንቶስ 2:11) ምንም እንኳን ይሖዋ ኢዮብን ማረም አስፈልጎት የነበረ ቢሆንም አጥቶት የነበረውን ነገር በሙሉ በድጋሚ እጥፍ አድርጎ በመስጠት ላሳየው ጽናት ዋጋውን ከፍሎታል።—ኢዮብ 42:10

ይሖዋ “ከልባችን ይልቅ ታላቅ ነው”

18, 19. አምላክ “ከልባችን ይልቅ ታላቅ” የሆነውና ‘ሁሉን ነገር የሚያውቀው’ እንዴት ነው?

18 የተስፋ መቁረጥ ስሜት ሥር ከሰደደ በኋላ ለማስወገድ በጣም ሊከብድ እንደሚችል የታመነ ነው። ይሁን እንጂ የይሖዋ መንፈስ ‘በእግዚአብሔር ዕውቀት ላይ የሚነሣውን’ በውስጥህ ‘የተመሸገ’ ሐሳብ ቀስ በቀስ እንድታፈርስ ሊረዳህ ይችላል። (2 ቆሮንቶስ 10:4, 5) አሉታዊ አስተሳሰቦች ሲያይሉብህ በሚከተሉት የሐዋርያው ዮሐንስ ቃላት ላይ አሰላስል:- “እኛ የእውነት ወገን መሆናችንን በዚህ እናውቃለን፤ ልባችንንም በፊቱ እናሳርፋለን፣ ይህም ልባችን በእኛ ላይ በሚፈርድብን ነገር ሁሉ ነው። እግዚአብሔር ከልባችን ይልቅ ታላቅ ነውና ሁሉን ነገር ያውቃል።”—1 ዮሐንስ 3:19, 20

19 “እግዚአብሔር ከልባችን ይልቅ ታላቅ ነው” የሚለው ሐረግ ምን ትርጉም አለው? አንዳንድ ጊዜ፣ በተለይ ደግሞ አለፍጽምናችንንና ጉድለታችንን በግልጽ ስንገነዘብ ልባችን ይወቅሰን ይሆናል። ወይም የምናደርገው ነገር ሁሉ በይሖዋ ዘንድ ተቀባይነት የሌለው ይመስል በአስተዳደጋችን ምክንያት ስለ ራሳችን ከልክ ያለፈ አሉታዊ ዝንባሌ ይኖረን ይሆናል። የሐዋርያው ዮሐንስ ቃላት ግን ይሖዋ ከልባችን አስተሳሰብ እንደሚልቅ ያረጋግጥልናል! በምንፈጽማቸው ስህተቶች ላይ አያተኩርም፤ ከዚህ ይልቅ መስተካከል መቻል አለመቻላችንን ያውቃል። ከዚህም በላይ አንድ ነገር ለማድረግ የተነሳሳንበትን ምክንያትና እቅዳችንን ያውቃል። ዳዊት “እርሱ አፈጣጠራችንን ያውቃልና፤ ትቢያ መሆናችንንም ያስባል” በማለት ጽፎ ነበር። (መዝሙር 103:14) አዎን፣ ይሖዋ እኛ ራሳችንን ከምናውቀው በላይ ያውቀናል!

“የክብር አክሊል” እና “የመንግሥት ዘውድ”

20. ይሖዋ በኢሳይያስ ያስነገረው የመልሶ መቋቋም ትንቢት አምላክ አገልጋዮቹን ስለሚመለከትበት መንገድ ምን ይገልጻል?

20 ይሖዋ የጥንት ሕዝቦቹን ዳግም እንደሚያቋቁማቸው በነቢዩ ኢሳይያስ በኩል ተስፋ ሰጥቷቸው ነበር። አዝነውና ተክዘው በባቢሎን የነበሩት ግዞተኞች በወቅቱ ያስፈልጋቸው የነበረው እንዲህ ዓይነት የሚያበረታታና የሚያጽናና ተስፋ ነው! ይሖዋ ወደ አገራቸው የሚመለሱበትን ጊዜ በተመለከተ እንዲህ ብሎ ነበር:- “በእግዚአብሔር እጅ የክብር አክሊል፣ በአምላክሽም እጅ የመንግሥት ዘውድ ትሆኛለሽ።” (ኢሳይያስ 62:3) እነዚህ ቃላት ይሖዋ ሕዝቡን ክብርና ውበት እንዳላበሰ ያሳያሉ። በአሁኑ ጊዜ ያለውን መንፈሳዊ እስራኤልም ሌሎች እስኪደነቁ ድረስ ከፍ ከፍ በማድረግ ተመሳሳይ ነገር ፈጽሟል።

21. ይሖዋ በታማኝነት ላሳየኸው ጽናት ወሮታ እንደሚከፍልህ እርግጠኛ መሆን የምትችለው እንዴት ነው?

21 ይህ ትንቢት ዋነኛ ፍጻሜውን የሚያገኘው በቅቡዓን ላይ ቢሆንም ይሖዋ የሚያገለግሉትን ሁሉ በክብር እንደሚይዛቸው እንደ ምሳሌ ሆኖ ያገለግላል። በጥርጣሬ ስሜት ስትዋጥ፣ ፍጹም ባትሆንም እንኳን ለይሖዋ ‘የክብርን አክሊል’ እና ‘የመንግሥትን ዘውድ’ ያህል ውድ መሆንህን አስታውስ። ስለዚህ የይሖዋን ፈቃድ ለማድረግ አጥብቀህ በመጣጣር ልቡን ደስ ማሰኘትህን ቀጥል። (ምሳሌ 27:11) እንዲህ ካደረግህ ይሖዋ በታማኝነት ላሳየኸው ጽናት ወሮታ እንደሚከፍልህ እርግጠኛ መሆን ትችላለህ!

[የግርጌ ማስታወሻ]

a አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።

ታስታውሳለህ?

• የይሖዋ ‘ገንዘብ’ የሆንነው እንዴት ነው?

• ይሖዋ ዋጋችንን እንደሚሰጠን ማመናችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

• የሰይጣንን “የተንኰል ሥራ” አጥብቀን መከላከል ያለብን ለምንድን ነው?

• አምላክ “ከልባችን ይልቅ ታላቅ ነው” የተባለው ለምንድን ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ጳውሎስ

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኤልያስ

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሐና

[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የአምላክ ቃል በርካታ የሚያጽናኑ ሐሳቦችን ይዟል