በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መጽሐፍ ቅዱስ ደስታ እንድታገኝ ሊረዳህ ይችላል

መጽሐፍ ቅዱስ ደስታ እንድታገኝ ሊረዳህ ይችላል

መጽሐፍ ቅዱስ ደስታ እንድታገኝ ሊረዳህ ይችላል

መጽሐፍ ቅዱስ የሕክምና መመሪያ መጽሐፍ ባይሆንም አንድ ግለሰብ ስለራሱ የሚኖረው ገንቢ አሊያም አፍራሽ አስተሳሰብ በአእምሯዊም ሆነ በአካላዊ ጤንነቱ ላይ ምን ውጤት እንደሚያስከትል ይናገራል። መጽሐፍ ቅዱስ “ደስተኛ ልብ ጥሩ መድኀኒት ነው” ካለ በኋላ “የተሰበረ መንፈስ ግን ዐጥንትን ያደርቃል” ብሏል። በተጨማሪም “በመከራ ጊዜ ፈራ ተባ ካልህ፣ [“ተስፋ ብትቆርጥ፣” NW] ዐቅምህ ምንኛ ደካማ ነው!” በማለት ይናገራል። (ምሳሌ 17:22፤ 24:10) የተስፋ መቁረጥ ስሜት የመለወጥም ሆነ እርዳታ የማግኘት ፍላጎት የሌለን ደካሞችና በቀላሉ የምንጎዳ ሰዎች እንድንሆን በማድረግ ኃይላችንን ሊያሟጥጥብን ይችላል።

ተስፋ መቁረጥ የአንድን ሰው መንፈሳዊነት ሳይቀር ሊነካ ይችላል። ምንም ዋጋ እንደሌላቸው የሚሰማቸው ሰዎች አብዛኛውን ጊዜ ከአምላክ ጋር ጥሩ ዝምድና ለመመሥረትም ሆነ ሞገሱን ለማግኘት ፈጽሞ እንደማይችሉ ይሰማቸዋል። በፊተኛው ርዕስ ላይ የተጠቀሰችው ሲሞን “አምላክ የሚደሰትበት ዓይነት ሰው” መሆኗን ትጠራጠር ነበር። ይሁን እንጂ የአምላክን ቃል መጽሐፍ ቅዱስን ስንመረምር አምላክ እርሱን ለማስደሰት የሚጥሩ ሰዎችን በበጎ ዓይን እንደሚመለከታቸው የሚናገር ሐሳብ እናገኛለን።

አምላክ በእርግጥ ያስብልናል

መጽሐፍ ቅዱስ “እግዚአብሔር ልባቸው ለተሰበረ ቅርብ ነው፤ መንፈሳቸው የተሰበረውንም ያድናቸዋል” በማለት ይነግረናል። አምላክ “የተሰበረውንና የተዋረደውን ልብ” አይንቅም፤ ከዚህ ይልቅ “የተሰበረ ልብ ካለውና በመንፈሱ ከተዋረደው ጋር” እንደሚሆን ቃል ገብቷል።—መዝሙር 34:18፤ 51:17፤ ኢሳይያስ 57:15

በአንድ ወቅት የአምላክ ልጅ ኢየሱስ፣ ይሖዋ የአገልጋዮቹን በጎ ጎን የሚመለከት መሆኑን ለደቀ መዛሙርቱ ማስረዳት አስፈልጎት ነበር። ኢየሱስ ብዙ ሰዎች እምብዛም ግምት የማይሰጧት አንዲት ድንቢጥ ምድር ላይ ስትወድቅ አምላክ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚመለከታት የሚገልጽ ምሳሌ ነገራቸው። እንዲሁም አምላክ ስለ ሰው ልጆች ትንሿን ዝርዝር ጉዳይ፣ ሌላው ቀርቶ በራሳቸው ላይ ያለውን የፀጉር ብዛት እንኳ አብጠርጥሮ እንደሚያውቅ ጎላ አድርጎ ገለጸላቸው። ከዚያም ኢየሱስ “ስለዚህ አትፍሩ፤ ከብዙ ድንቢጦች ይልቅ ዋጋችሁ የከበረ ነው” በማለት ምሳሌውን ደምድሟል። (ማቴዎስ 10:29-31) a ኢየሱስ ማንኛውም ግለሰብ ስለራሱ ያለው አመለካከት ምንም ይሁን ምን የእምነት ሰዎች በአምላክ ዓይን ዋጋ እንዳላቸው ግልጽ አድርጓል። እንዲያውም ሐዋርያው ጴጥሮስ “እግዚአብሔር ለማንም [አያዳላም] . . . ነገር ግን እርሱን የሚፈሩትንና ጽድቅን የሚያደርጉትን ሁሉ ከየትኛውም ወገን ቢሆኑ ይቀበላቸዋል” በማለት ያሳስበናል።—የሐዋርያት ሥራ 10:34, 35

ሚዛናዊ አመለካከት ማዳበር

የአምላክ ቃል ስለራሳችን ሚዛናዊ አመለካከት እንድናዳብር አጥብቆ ይመክረናል። ሐዋርያው ጳውሎስ በመንፈስ ተነሳስቶ “እግዚአብሔር ለእያንዳንዳችሁ በሰጣችሁ እምነት መጠን ራሳችሁን በአግባቡ መዝኑ እንጂ፣ ከሆናችሁት በላይ ራሳችሁን ከፍ አድርጋችሁ እንዳታስቡ በተሰጠኝ ጸጋ እያንዳንዳችሁን እመክራለሁ” በማለት ጽፏል።—ሮሜ 12:3

በእርግጥም ትዕቢተኞች እስክንሆን ድረስ ስለራሳችን ከልክ ያለፈ ግምት ማሳደር አይኖርብንም፤ እንዲሁም ምንም እንደማንጠቅም በማሰብም ወደ ሌላው ጽንፍ መሄድ አንፈልግም። ከዚህ ይልቅ የኛ ዓላማ የራሳችንን ጥንካሬ እንዲሁም ድክመት ከግምት ውስጥ የሚያስገባ ምክንያታዊ አመለካከት ማዳበር መሆን ይኖርበታል። አንዲት ክርስቲያን ሴት ሁኔታውን አንዲህ በማለት ገልጻዋለች:- “መጥፎ ሰው አይደለሁም፤ በጣም ጥሩ የምባልም አይደለሁም። እንደማንኛውም ሰው ሁሉ መልካምም ሆኑ ደስ የማይሉ ባሕርያት አሉኝ።”

እንዲህ ያለውን ሚዛናዊ አመለካከት በተግባር ማዋሉ የመናገሩን ያህል ቀላል እንዳልሆነ አይካድም። ስለራሳችን ስንት ዓመት ሙሉ ስናስበው የነበረውን አፍራሽ አመለካከት ማስወገድ ከፍተኛ ጥረት ይጠይቃል። የሆነ ሆኖ በአምላክ እርዳታ ባሕርያችንንም ሆነ ለሕይወት ያለንን አመለካከት መቀየር እንችላለን። እንደ እውነቱ ከሆነ የአምላክ ቃልም የሚመክረን ይህንኑ ነው። እንዲህ የሚል ሐሳብ እናነባለን:- “ቀድሞ ስለነበራችሁበት ሕይወትም፣ በሚያታልል ምኞቱ የጎደፈውን አሮጌ ሰውነታችሁን አውልቃችሁ እንድትጥሉ . . . ደግሞም በአእምሮአችሁ መንፈስ እንድትታደሱ፣ እውነተኛ በሆነው ጽድቅ እንዲሁም ቅድስና እግዚአብሔርን እንዲመስል የተፈጠረውን አዲሱን ሰው እንድትለብሱ ነው።”—ኤፌሶን 4:22-24

‘የአእምሮአችንን መንፈስ’ ማለትም ተጽዕኖ የሚያሳድርብንን የልብ ዝንባሌ ለመለወጥ ጥረት በማድረግ አፍራሽ የነበረውን አመለካከታችንን ወደ ገንቢ ልንቀይረው እንችላለን። በፊተኛው ርዕስ ላይ የተጠቀሰችው ሊና ማንም ሰው አይወደኝም ወይም ሊረዳኝ አይፈልግም የሚለውን አስተሳሰብ እስካላስወገደች ድረስ ስለራሷ ያላት አመለካከት ፈጽሞ ሊቀየር እንደማይችል ተረድታለች። ሊና፣ ሲሞን እንዲሁም ሌሎች ሰዎች ይህን ዓይነት የአመለካከት ለውጥ እንዲያደርጉ የረዷቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ምክሮች የትኞቹ ናቸው?

ደስታችንን ለመጨመር የሚረዱ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች

“የከበደህን ነገር በእግዚአብሔር ላይ ጣል፤ እርሱ ደግፎ ይይዝሃል።” (መዝሙር 55:22) ጸሎት ከምንም በላይ እውነተኛ ደስታ እንድናገኝ ሊረዳን ይችላል። ሲሞን “የተስፋ መቁረጥ ስሜት በተሰማኝ ቁጥር ይሖዋ እንዲረዳኝ እጠይቀዋለሁ። ያጋጠመኝ ነገር ምንም ይሁን ምን የእርሱን ብርታትና መመሪያ እንዳላገኘሁ የተሰማኝ ጊዜ የለም” በማለት ተናግራለች። መዝሙራዊው የከበደንን ነገር በይሖዋ ላይ እንድንጥል ምክር ሲሰጠን አምላክ እንደሚያስብልን ብቻ ሳይሆን የእርሱን እርዳታና ድጋፍ ማግኘት የሚገባን ሰዎች እንደሆንን አድርጎ የሚመለከተን መሆኑን በተዘዋዋሪ መንገድ ማስገንዘቡ ነው። በ33 ከክርስቶስ ልደት በኋላ የማለፍ በዓል በተከበረበት ዕለት ምሽት ላይ ኢየሱስ በቅርቡ እንደሚለያቸው ለደቀ መዛሙርቱ ሲነግራቸው በጣም አዝነው ነበር። ኢየሱስ ወደ አብ እንዲጸልዩ አጥብቆ ከመከራቸው በኋላ “ለምኑ ትቀበላላችሁ፤ ደስታችሁም ሙሉ ይሆናል” ብሏቸዋል።—ዮሐንስ 16:23, 24

“ከሚቀበል ይልቅ የሚሰጥ ብፁዕ [“ደስተኛ፣” NW] ነው።” (የሐዋርያት ሥራ 20:35) ኢየሱስ እንዳስተማረው በሕይወት ውስጥ እውነተኛ ደስታ ለማግኘት የሚረዳው ወሳኝ ነገር መስጠት ነው። ይህን የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት በተግባር ማዋላችን በራሳችን ድክመቶች ላይ ከማተኮር ይልቅ ለሌሎች ፍላጎት ትኩረት እንድንሰጥ ያደርገናል። ሌሎችን ረድተን በአጸፋው ምስጋና ስናገኝ ለራሳችን ጥሩ ግምት ያድርብናል። ሊና የመጽሐፍ ቅዱስን ምሥራች ዘወትር ለሌሎች መስበኳ በሁለት መንገዶች እንደጠቀማት ተረድታለች። “በመጀመሪያ ኢየሱስ የተናገረለትን ዓይነት ደስታና እርካታ አስገኝቶልኛል። ሁለተኛው ደግሞ ከሌሎች በጎ አስተያየቶችን ማግኘቴ ነው፤ ይህም ቢሆን ደስታ እንዳገኝ ረድቶኛል” ስትል ተናግራለች። ራሳችንን ሳንቆጥብ ሰዎችን ስንረዳ “ሌሎችን የሚያረካም ራሱ ይረካል” የሚለው የምሳሌ 11:25 ሐሳብ እውነት እንደሆነ መመልከት እንችላለን።

“የተጨቈኑ ሰዎች ዘመናቸው ሁሉ የከፋ ነው፤ በደስታ የተሞላ ልብ ግን የማይቋረጥ ፈንጠዝያ አለው።” (ምሳሌ 15:15) ሁላችንም ራሳችንንም ሆነ ያለንበትን ሁኔታ እንዴት ማየት እንደሚኖርብን የመወሰን ምርጫ አለን። ሁሉን ነገር አፍራሽ በሆነ መንገድ የሚያይና እንደተጨቆነ የሚሰማው ዓይነት ሰው መሆን እንችላለን፤ አሊያም ሁሉን ነገር በበጎ ዓይን በመመልከት ወይም ‘ልባችንን በደስታ በመሙላት’ ሁልጊዜ በፈንጠዝያ ወይም በግብዣ ላይ እንዳለ ሰው ደስተኛ መሆን እንችላለን። ሲሞን “በተቻለኝ መጠን ሁልጊዜ በጎ በጎውን ለማሰብ እጥራለሁ። በግል ጥናትና በአገልግሎት ራሴን አስጠምዳለሁ፤ እንዲሁም አዘውትሬ እጸልያለሁ። ብሩህ አመለካከት ካላቸው ሰዎች ጋር ለመቀራረብ ከመሞከሬም ባሻገር ሌሎችን በማንኛውም ነገር ለመርዳት ጥረት አደርጋለሁ” በማለት ተናግራለች። መጽሐፍ ቅዱስ “ጻድቃን ሆይ፤ በእግዚአብሔር ደስ ይበላችሁ፤ ሐሤትም አድርጉ፤ ቅን ልብ ያላችሁም ሁሉ እልል በሉ” በማለት ስለሚያሳስበን ይህን ዓይነቱን የልብ ዝንባሌ መያዝ እውነተኛ ደስታ ያስገኛል።—መዝሙር 32:11

“ወዳጅ ምንጊዜም ወዳጅ ነው፤ ወንድምም ለክፉ ቀን ይወለዳል።” (ምሳሌ 17:17) የሚሰማንን ነገር ለምንወደው ወይም ጥሩ ምክር እንደሚሰጠን ለምንተማመንበት ሰው ማካፈላችን በአፍራሽ አስተሳሰቦች ከመዋጥ ይልቅ ከውስጣችን ነቅለን እንድናወጣቸው ይረዳናል። ከሌሎች ጋር መጨዋወታችን ነገሮችን ሚዛናዊና ገንቢ በሆነ መንገድ እንድናያቸው ሊረዳን ይችላል። ሲሞን “ስሜትን አውጥቶ መናገር በጣም ይረዳል። ምን እንደሚሰማችሁ ለሰው መንገር ይኖርባችኋል። ብዙውን ጊዜ፣ መናገሩ ብቻ እንኳ በቂ ነው” በማለት የተሰማትን ተናግራለች። እንዲህ ማድረግህ “ሥጉ ልብ ሰውን በሐዘን ይወጥራል፤ መልካም ቃል ግን ደስ ያሰኘዋል” የሚለው ምሳሌ እውነት መሆኑን በተግባር እንድታይ ይረዳሃል።—ምሳሌ 12:25

ምን ማድረግ ትችላለህ?

አፍራሽ አስተሳሰቦችን አስወግደን ትክክለኛ ደስታ እንድናገኝ ሊረዱን ከሚችሉት ግሩም የሆኑ በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎች መካከል ጥቂቶቹን ተመልክተናል። ከሚሰማቸው የዋጋ ቢስነት ስሜት ጋር ትግል ከሚያደርጉ ሰዎች አንዱ ከሆንክ የአምላክን ቃል መጽሐፍ ቅዱስን በጥልቅ እንድትመረምር እናበረታታሃለን። ስለራስህ እንዲሁም ከአምላክ ጋር ስላለህ ግንኙነት ምክንያታዊና ሚዛናዊ የሆነ አስተሳሰብ ማዳበርን ተማር። በአምላክ ቃል ተመርተህ ከምታደርጋቸው ነገሮች ሁሉ እውነተኛ ደስታ እንድታገኝ እንመኛለን።

[የግርጌ ማስታወሻ]

a ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ በገጽ 22 እና 23 ላይ በሰፊው ተብራርቷል።

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች መመራት ደስታ ያስገኛል