በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ረጅም መንገድ ቢጓዙም ተክሰዋል

ረጅም መንገድ ቢጓዙም ተክሰዋል

ረጅም መንገድ ቢጓዙም ተክሰዋል

የሚከተለው ተሞክሮ ከኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፑብሊክ የተገኘ ነው፤ ሁለት እህትማማቾች ሊሳላ ከተማ በተደረገው “ለአምላክ ክብር ስጡት” በተባለው የአውራጃ ስብሰባ ላይ ለመገኘት በጦርነት የሚታመሱ አካባቢዎችን አቋርጠው ረጅም ጉዞ አደረጉ። እነዚህ እህቶች በስብሰባው ላይ ከሚያገኙት መንፈሳዊ ትምህርትና ክርስቲያናዊ ፍቅር በተጨማሪ ኪንሻሳ ካለው የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ የሚመጡ ተወካዮችን ለማግኘት ጓጉተው ነበር። አገሪቷ ውስጥ ባለው የእርስ በርስ ጦርነት ምክንያት በቅርንጫፍ ቢሮው የሚያገለግሉ ወንድሞችን ለዓመታት አይተዋቸው ስለማያውቁ ይህን አጋጣሚ ሊጠቀሙበት ፈለጉ።

እነዚህ እህቶች ከትውልድ ቀዬአቸው ከባሳንኩሱ ተነስተው ሊሳላ ለመድረስ ጫካዎችን አቆራርጠው በሚፈስሱ ሁለት ወንዞች ላይ የተጓዙት ከግንድ ተቦርቡሮ በተሠራ ታንኳ ነበር። ርቀቱ 300 ኪሎ ሜትር ያህል ሲሆን እዚያ ለመድረስ ሦስት ሳምንታት ፈጅቶባቸዋል። አንደኛዋ እህት ለ3 ዓመት ሌላዋ ደግሞ ለ19 ዓመታት በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ያሳለፉ ሲሆን ጉዟቸውን የመንግሥቱን ምሥራች ለማዳረስ ተጠቅመውበታል። በጉዞ ላይ ሳሉ ለሚያገኟቸው ሰዎች በመስበክ 110 ሰዓታት ያሳለፉ ሲሆን 200 ትራክቶችና 30 መጽሔቶች አበርክተዋል።

በወንዝ ላይ ሲጓዙ በአካባቢው በጣም የተለመዱት ጉማሬዎችና አዞዎች ያጋጥሟቸው ነበር። ከመሸ በኋላ በወንዙ ላይ መጓዝ በጣም አደገኛ ስለሆነ ማታ ማታ ጉዞ አያደርጉም! ከዚህም በላይ በየቦታው ወታደሮች የሚፈትሹባቸው በርካታ ኬላዎች ያጋጥሟቸው ነበር።

ጉዞው በጣም ረጅምና አድካሚ ቢሆንም እህቶች ሊወጡት በመቻላቸው ተደስተዋል። ሊሳላ በተደረገው ስብሰባ ላይ መገኘታቸው ልባቸው በአድናቆትና በሐሴት እንዲሞላ አድርጓል። ለእውነት ያላቸው ልባዊ ፍቅር ከመጨመሩም በላይ ስብሰባውን 7, 000 ከሚያህሉ ወንድሞችና እህቶች ጋር በመካፈላቸው ተበረታተዋል። ስብሰባው ካለቀ በኋላ ወደ ትውልድ ቀዬአቸው ሲመለሱ ተመሳሳይ ሁኔታዎችን ተጋፍጠዋል። እዚያም ቤተሰቦቻቸውን ሁሉ በደህና አግኝተዋል።