ለቆሮንቶስ ሰዎች የተጻፈ ሁለተኛው ደብዳቤ 10:1-18

  • ጳውሎስ ስለ አገልግሎቱ ተሟገተ (1-18)

    • “የጦር መሣሪያዎቻችን ሥጋዊ አይደሉም” (4, 5)

10  በመካከላችሁ ሆኜ ፊት ለፊት ስታይ እንደ ደካማ የምቆጠረውና+ ከእናንተ ስርቅ እንደ ደፋር የምታየው+ እኔ ጳውሎስ በክርስቶስ ገርነትና ደግነት+ እለምናችኋለሁ።  በመካከላችሁ በምገኝበት ጊዜ በሥጋዊ አስተሳሰብ እንደምንመላለስ አድርገው በሚቆጥሩን አንዳንድ ሰዎች ላይ በድፍረት ከባድ እርምጃ ለመውሰድ የሚያስገድድ ሁኔታ እንደማይፈጠር ተስፋ አደርጋለሁ።  ምንም እንኳ በሥጋ የምንኖር ቢሆንም የምንዋጋው በሥጋዊ መንገድ አይደለም።  የምንዋጋባቸው የጦር መሣሪያዎቻችን ሥጋዊ አይደሉምና፤+ ይሁን እንጂ ምሽግን ለመደርመስ የሚያስችል መለኮታዊ ኃይል ያላቸው ናቸው።+  ስለ አምላክ የሚገልጸውን እውቀት የሚጻረሩ የተሳሳቱ ሐሳቦችንና ይህን እውቀት የሚያግድን ማንኛውንም ከፍ ያለ ነገር እናፈርሳለን፤+ እንዲሁም ማንኛውንም ሐሳብ እየማረክን ለክርስቶስ እንዲታዘዝ እናደርጋለን፤  ሙሉ በሙሉ ታዛዦች መሆናችሁን ካሳያችሁ በኋላ በማንኛውም መንገድ ታዛዥ በማይሆን ግለሰብ ላይ የቅጣት እርምጃ ለመውሰድ ተዘጋጅተናል።+  እናንተ የምትመለከቱት ውጫዊውን ነገር ብቻ ነው። ማንም ሰው የክርስቶስ ነኝ ብሎ በራሱ የሚተማመን ከሆነ እሱ የክርስቶስ እንደሆነ ሁሉ እኛም የክርስቶስ እንደሆን በድጋሚ ሊያጤን ይገባዋል።  ጌታ እናንተን ለማፍረስ ሳይሆን ለማነጽ በሰጠን ሥልጣን እጅግ ብኮራም እንኳ+ ለኀፍረት አልዳረግምና።  እናንተን በደብዳቤዎቼ ለማስፈራራት እየሞከርኩ ያለሁ ሆኖ እንዲሰማችሁ አልፈልግም። 10  አንዳንዶች “ደብዳቤዎቹ ከባድና ኃይለኛ ናቸው፤ በመካከላችን በአካል ሲገኝ ግን ደካማ ከመሆኑም በላይ ንግግሩ የተናቀ ነው” ይላሉና። 11  እንዲህ ያለው ሰው፣ በአካል ሳንኖር በደብዳቤዎቻችን የምንናገረው ቃልና በአካል ስንገኝ የምናደርገው ነገር ምንም ልዩነት እንደሌለው መገንዘብ ይገባዋል።+ 12  እኛ ራሳቸውን ብቁ አድርገው ከሚያቀርቡ ሰዎች ጋር ራሳችንን ለመመደብ ወይም ለማነጻጸር አንደፍርምና።+ ይሁንና እነሱ ራሳቸውን በራሳቸው ሲመዝኑና ራሳቸውን ከራሳቸው ጋር ሲያነጻጽሩ ማስተዋል እንደሌላቸው ያሳያሉ።+ 13  እኛ ግን ከተሰጠን ወሰን ውጭ ባለው ነገር አንኩራራም፤ ከዚህ ይልቅ የምንኮራው አምላክ ለክቶ በሰጠን ክልል ውስጥ ባለው ነገር ብቻ ነው፤ ይህ ክልል ደግሞ እናንተንም ያጠቃልላል።+ 14  እናንተ ከክልላችን ውጭ ያላችሁ ይመስል እናንተ ጋር ለመድረስ ከክልላችን ውጭ መሄድ አላስፈለገንም፤ ስለ ክርስቶስ የሚገልጸውን ምሥራች በመጀመሪያ እናንተ እስካላችሁበት ድረስ ይዘን የመጣነው እኛ ነንና።+ 15  ከተመደበልን ወሰን ውጭ ሌላ ሰው በደከመበት ነገር እየተኩራራን አይደለም፤ ሆኖም እምነታችሁ እያደገ ሲሄድ በክልላችን ውስጥ ያከናወንነውን ሥራ በሚገባ እንደምትገነዘቡ ተስፋ እናደርጋለን። ይህም ይበልጥ እንድንሠራ ያደርገናል፤ 16  በመሆኑም በሌላው ሰው ክልል፣ አስቀድሞ በተሠራ ሥራ ከመኩራራት ይልቅ ከእናንተ ወዲያ ባሉት አገሮች ምሥራቹን እንሰብካለን። 17  “ሆኖም የሚኩራራ በይሖዋ* ይኩራራ።”+ 18  ተቀባይነት የሚያገኘው ራሱን ብቁ እንደሆነ አድርጎ የሚያቀርብ ሳይሆን+ ይሖዋ* ብቁ ነው የሚለው ሰው ነውና።+

የግርጌ ማስታወሻዎች

ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።