መዝሙር 22:1-31

  • ከተስፋ መቁረጥ ተላቆ ውዳሴ ማቅረብ

    • “አምላኬ ለምን ተውከኝ?” (1)

    • ‘በልብሴ ላይ ዕጣ ተጣጣሉ’ (18)

    • በጉባኤ መካከል አምላክን ማወደስ (22,25)

    • ምድር ሁሉ አምላክን ያመልካል (27)

ለሙዚቀኞች ቡድን መሪ፤ “በንጋት እንስት ርኤም።”* የዳዊት ማህሌት። 22  አምላኬ፣ አምላኬ ለምን ተውከኝ?+ እኔን ከማዳን፣ ከደረሰብኝም ሥቃይ የተነሳ የማሰማውን ጩኸት+ ከመስማትየራቅከው ለምንድን ነው?  2  አምላኬ ሆይ፣ በቀን ደጋግሜ እጣራለሁ፤ አንተ ግን አትመልስልኝም፤+በሌሊትም ዝም ማለት አልቻልኩም።  3  አንተ ግን ቅዱስ ነህ፤+እስራኤል በሚያቀርበው ውዳሴ ተከበሃል።*  4  አባቶቻችን እምነታቸውን በአንተ ላይ ጣሉ፤+በአንተ ተማመኑ፤ አንተም ሁልጊዜ ትታደጋቸው ነበር።+  5  ወደ አንተ ጮኹ፤ ደግሞም ዳኑ፤በአንተ ተማመኑ፤ የጠበቁት ሳይፈጸም ቀርቶም አላዘኑም።*+  6  እኔ ግን ትል እንጂ ሰው አይደለሁም፤ሰው ያፌዘብኝ፣* ሕዝብም የናቀኝ ነኝ።+  7  የሚያዩኝ ሁሉ ያላግጡብኛል፤+በንቀትና በፌዝ ጭንቅላታቸውን እየነቀነቁ እንዲህ ይሉኛል፦+  8  “ራሱን ለይሖዋ በአደራ ሰጥቷል። እስቲ እሱ ይታደገው! በእሱ እጅግ የተወደደ ስለሆነ እሱ ያድነው!”+  9  ከማህፀን ያወጣኸኝ አንተ ነህ፤+በእናቴ ጡት ተማምኜ እንድኖር ያደረግከኝ አንተ ነህ። 10  ስወለድ ጀምሮ ለአንተ በአደራ ተሰጠሁ፤*ከእናቴ ማህፀን ጀምሮ አንተ አምላኬ ነህ። 11  ችግር ሊደርስብኝ ስለሆነ ከእኔ አትራቅ፤+ደግሞም ሌላ ረዳት የለኝም።+ 12  ብዙ ወይፈኖች ከበውኛል፤+የባሳን ኃይለኛ ኮርማዎችም በዙሪያዬ ናቸው።+ 13  ያደነውን እንደሚቦጫጭቅ የሚያገሳ አንበሳ+አፋቸውን በእኔ ላይ ከፈቱ።+ 14  እንደ ውኃ ፈሰስኩ፤አጥንቶቼ ሁሉ ከመጋጠሚያቸው ወለቁ። ልቤ እንደ ሰም ሆነ፤+በውስጤም ቀለጠ።+ 15  ኃይሌ እንደ ገል ደረቀ፤+ምላሴ ከላንቃዬ ጋር ተጣበቀ፤+እንድሞትም ወደ ጉድጓድ አወረድከኝ።+ 16  ውሾች ከበውኛልና፤+እንደ ክፉ አድራጊዎች ሸንጎ በዙሪያዬ ሰፍረዋል፤+እንደ አንበሳ ሆነው እጆቼና እግሮቼ ላይ ተረባረቡ።*+ 17  አጥንቶቼን ሁሉ መቁጠር እችላለሁ።+ እነሱም አዩኝ፤ ትኩር ብለውም ተመለከቱኝ። 18  መደረቢያዎቼን እርስ በርሳቸው ተከፋፈሉ፤በልብሴም ላይ ዕጣ ተጣጣሉ።+ 19  አንተ ግን ይሖዋ ሆይ፣ ከእኔ አትራቅ።+ አንተ ብርታቴ ነህ፤ እኔን ለመርዳት ፍጠን።+ 20  ከሰይፍ አድነኝ፤*ውድ ሕይወቴን* ከውሾች መዳፍ* ታደጋት፤+ 21  ከአንበሳ አፍና ከዱር በሬዎች ቀንድ አድነኝ፤+መልስ ስጠኝ፤ ታደገኝም። 22  ስምህን ለወንድሞቼ አሳውቃለሁ፤+በጉባኤ መካከልም አወድስሃለሁ።+ 23  እናንተ ይሖዋን የምትፈሩ፣ አወድሱት! እናንተ የያዕቆብ ዘር ሁሉ፣ ከፍ ከፍ አድርጉት!+ እናንተ የእስራኤል ዘር ሁሉ፣ ለእሱ ታላቅ አክብሮት አሳዩ። 24  እሱ የተጨቆነውን ሰው መከራ አልናቀምና፤+ ደግሞም አልተጸየፈም፤ፊቱን ከእሱ አልሰወረም።+ ለእርዳታ ወደ እሱ በጮኸ ጊዜ ሰምቶታል።+ 25  በታላቅ ጉባኤ መካከል አወድስሃለሁ፤+እሱን በሚፈሩት ፊት ስእለቴን እፈጽማለሁ። 26  የዋሆች በልተው ይጠግባሉ፤+ይሖዋን የሚፈልጉት እሱን ያወድሱታል።+ ለዘላለም ተደስታችሁ ኑሩ።* 27  የምድር ዳርቻዎች ሁሉ ይሖዋን አስታውሰው ወደ እሱ ይዞራሉ። የሕዝቦች ነገዶች ሁሉ በፊትህ ይሰግዳሉ።+ 28  ንግሥና የይሖዋ ነውና፤+ብሔራትን ይገዛል። 29  በምድር ያሉ ባለጸጎች ሁሉ* ይበላሉ፤ ይሰግዳሉም፤ወደ አፈር የሚወርዱ ሁሉ በእሱ ፊት ይንበረከካሉ፤ከእነሱ መካከል አንዳቸውም ሕይወታቸውን* ማቆየት አይችሉም። 30  ዘሮቻቸው ያገለግሉታል፤መጪው ትውልድ ስለ ይሖዋ ይነገረዋል። 31  መጥተው ጽድቁን ያወራሉ። ገና ለሚወለድ ሕዝብ ያደረገውን ነገር ይናገራሉ።

የግርጌ ማስታወሻዎች

ቅኝት ወይም የሙዚቃ ስልት ሊሆን ይችላል።
ወይም “እስራኤል በሚያቀርበው ውዳሴ መካከል (ላይ) ነግሠሃል።”
ወይም “ኀፍረት አልደረሰባቸውም።”
ወይም “የነቀፈኝ።”
ቃል በቃል “በአንተ ላይ ተጣልኩ።”
ወይም “እጆቼንና እግሮቼን ቸነከሩ።”
ወይም “ነፍሴን ከሰይፍ አድናት።”
ቃል በቃል “አንድ ያለችኝን።” ነፍሱን ወይም ሕይወቱን ያመለክታል።
ቃል በቃል “እጅ።”
ቃል በቃል “ልባችሁ ለዘላለም ይኑር።”
ቃል በቃል “የሰቡት ሁሉ።”
ወይም “ነፍሳቸውን።”