በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

‘ራስህንም የሚሰሙህንም አድን’

‘ራስህንም የሚሰሙህንም አድን’

‘ራስህንም የሚሰሙህንም አድን’

“ለራስህና ለትምህርትህ [“ለማስተማር ሥራህ፣” የ1980 ትርጉም ] ተጠንቀቅ፣ . . . ይህን ብታደርግ፣ ራስህንም የሚሰሙህንም ታድናለህ።”​—⁠1 ጢሞቴዎስ 4:​16

1, 2. እውነተኛ ክርስቲያኖች ሕይወት አድን በሆነው ሥራ መካፈላቸውን እንዲቀጥሉ የሚገፋፋቸው ነገር ምንድን ነው?

 በሰሜናዊ ታይላንድ በሚገኝ በአንድ ገለልተኛ መንደር የሚኖሩ የይሖዋ ምሥክር የሆኑ ባልና ሚስት በኮረብታማ አካባቢ ከሚኖሩ የአንድ ጎሳ አባላት ጋር በቅርቡ በተማሩት አዲስ ቋንቋ ለመግባባት ጥረት እያደረጉ ነው። ባልና ሚስቱ በመንደሩ ለሚኖሩት ሰዎች የአምላክን መንግሥት ምሥራች ለማካፈል በቅርቡ የላሁን ቋንቋ ተምረዋል።

2 “በእነዚህ ደስ የሚሉ ሰዎች መካከል በመሥራታችን ያገኘነውን ደስታና እርካታ በቃላት መግለጽ ያዳግተናል” በማለት ባልዬው ይናገራል። “‘ለሕዝብ፣ ለነገድና ለቋንቋ’ እንደሚሰበክ በሚናገረው የራእይ 14:​6, 7 ትንቢት ፍጻሜ ውስጥ እኛም እንደተካፈልን ሆኖ ተሰምቶናል። ምሥራቹ ያልተዳረሰባቸው ጥቂት አካባቢዎች ያሉ ሲሆን ከእነዚህ መካከል አንዱ ይህ ቦታ ነው። ከአቅማችን በላይ ማለት ይቻላል፣ በርካታ ቁጥር ያላቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች አሉን።” እነዚህ ባልና ሚስት ራሳቸውን ብቻ ሳይሆን የሚሰሟቸውንም የማዳን ተስፋ እንዳላቸው ግልጽ ነው። እኛም ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን ተመሳሳይ የሆነ ነገር ለማድረግ አንጓጓምን?

“ለራስህ . . . ተጠንቀቅ”

3. ሌሎችን ለማዳን በመጀመሪያ እኛ ምን ማድረግ ይገባናል?

3 ሐዋርያው ጳውሎስ “ለራስህና ለማስተማር ሥራህ ተጠንቀቅ” በማለት ጢሞቴዎስን መክሮታል። ይህም ምክር ለሁሉም ክርስቲያኖች የሚሠራ ነው። (1 ጢሞቴዎስ 4:​16 የ1980 ትርጉም ) ሌሎች መዳንን እንዲያገኙ ለመርዳት ከፈለግን በመጀመሪያ ለራሳችን ጥንቃቄ ማድረግ አለብን። ይህን ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው? በመጀመሪያ ደረጃ በምንኖርበት በአሁኑ ጊዜ ንቁ ሆነን መመላለስ አለብን። ኢየሱስ ተከታዮቹ “የነገሮች ሥርዓት መደምደሚያ” የሚሆንበትን ጊዜ ማወቅ ይችሉ ዘንድ ጥምር ምልክት ሰጥቷቸዋል። ሆኖም ኢየሱስ መጨረሻው የሚመጣበትን ጊዜ በትክክል ማወቅ እንደማንችልም ጨምሮ ተናግሯል። (ማቴዎስ 24:​3, 36 NW ) ታዲያ ይህን ማወቃችን ምን እንድናደርግ ሊያነሳሳን ይገባል?

4. (ሀ) ይህ ሥርዓት ስለቀረው ጊዜ ምን ዓይነት አመለካከት ሊኖረን ይገባል? (ለ) ልናስወግደው የሚገባን አመለካከት ምንድን ነው?

4 እያንዳንዳችን እንደሚከተለው ብለን ልንጠይቅ እንችላለን:- ‘ይህ ሥርዓት የቀረው ጊዜ ምንም ያህል ይሁን ራሴንና የሚሰሙኝን ሰዎች ለማዳን እየተጠቀምኩበት ነው? ወይስ “መጨረሻው የሚመጣበትን ጊዜ ስለማናውቅ በዚህ ራሴን አላስጨንቅም” የሚል አስተሳሰብ አለኝ?’ ይኼኛው አመለካከት አደገኛ ነው። ኢየሱስ “እናንተ ደግሞ ተዘጋጅታችሁ ኑሩ፣ የሰው ልጅ በማታስቡበት ሰዓት ይመጣልና” በማለት ከተናገረው ምክር ጋር በቀጥታ የሚቃረን ነው። (ማቴዎስ 24:​44) በእርግጥም ይህ ጊዜ ለይሖዋ አገልግሎት ያለንን ቅንዓት የምናቀዘቅዝበት፣ ደህንነት ወይም እርካታ ለማግኘት ወደ ዓለም ዞር የምንልበት ጊዜ አይደለም።​—⁠ሉቃስ 21:​34-36

5. በቅድመ ክርስትና ዘመን የነበሩ ምሥክሮች ምን ምሳሌ ትተውልናል?

5 ለራሳችን የምንጠነቀቅ መሆናችንን ልናሳይ የምንችልበት ሌላኛው መንገድ በክርስትና ጎዳና በታማኝነት በመጽናት ነው። በጥንት ጊዜ የነበሩ የአምላክ አገልጋዮች መዳናቸውን ወዲያው እንደሚያገኙ አድርገው አሰቡም አላሰቡ በጽናት ኖረዋል። ጳውሎስ እንደ አቤል፣ ሄኖክ፣ ኖኅ፣ አብርሃም እና ሣራ ያሉ በቅድመ ክርስትና ዘመን የነበሩ ምሥክሮችን ምሳሌ ከጠቀሰ በኋላ እነዚህ “የተሰጣቸውን የተስፋ ቃል አላገኙምና፤ ዳሩ ግን ከሩቅ ሆነው አዩትና ተሳለሙት፣ በምድሪቱም እንግዶችና መጻተኞች እንዲሆኑ ታመኑ” በማለት ተናግሯል። የተመቻቸ ኑሮ የማግኘት ፍላጎት አላሸነፋቸውም፣ ወይም በአካባቢያቸው ለነበረው መጥፎ የሥነ ምግባር ተጽዕኖ አልተንበረከኩም። ከዚያ ይልቅ ‘የተሰጣቸውን የተስፋ ቃል ፍጻሜ’ በጉጉት ተጠባብቀዋል።​—⁠ዕብራውያን 11:​13፤ 12:​1

6. የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች መዳንን በተመለከተ የነበራቸው አመለካከት በአኗኗራቸው ላይ ተጽዕኖ ያሳደረው እንዴት ነው?

6 በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ ክርስቲያኖችም በዚህ ዓለም ውስጥ “እንግዶች” እንደሆኑ አድርገው ራሳቸውን ይመለከቱ ነበር። (1 ጴጥሮስ 2:​11) በ70 እዘአ በኢየሩሳሌም ላይ ከደረሰው ጥፋት ከዳኑ በኋላም እንኳ እውነተኛ ክርስቲያኖች መስበካቸውን አላቆሙም ወይም ወደ ኋላ ተመልሰው የዓለምን የአኗኗር ጎዳና አልተከተሉም። በታማኝነት የጸኑ ሰዎች ታላቅ መዳን እንደሚጠብቃቸው ያውቁ ነበር። እንዲያውም በ98 እዘአ እንኳ ሐዋርያው ዮሐንስ “ዓለሙም ምኞቱም ያልፋሉ፤ የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚያደርግ ግን ለዘላለም ይኖራል” በማለት ጽፏል።​—⁠1 ዮሐንስ 2:​17, 28

7. የይሖዋ ምሥክሮች በጊዜያችን ጽናት ያሳዩት እንዴት ነው?

7 በዛሬውም ጊዜ የይሖዋ ምሥክሮች ጭካኔ የተሞላበት ስደት ቢደርስባቸውም እንኳ በክርስቲያናዊ ሥራ ጸንተዋል። ያሳዩት ጽናት መና ቀርቷልን? በፍጹም። ኢየሱስ “እስከ መጨረሻ የሚጸና ግን እርሱ ይድናል” የሚል ማረጋገጫ ሰጥቶናል። ይህ እስከዚህ ሥርዓት መደምደሚያ ወይም እስከ ዕለተ ሞት ድረስ ሊሆን ይችላል። ይሖዋ በሞት ያንቀላፉ ታማኝ አገልጋዮቹን በሙሉ በትንሣኤ በማሰብ ወሮታ ይከፍላቸዋል።​—⁠ማቴዎስ 24:​13፤ ዕብራውያን 6:​10

8. በጥንት ጊዜ የነበሩ ክርስቲያኖች ያሳዩትን ጽናት የምናደንቅ መሆናችንን እንዴት ልናሳይ እንችላለን?

8 ከዚህም በላይ በጥንት ጊዜ የነበሩ የታመኑ ክርስቲያኖች ያሳስባቸው የነበረው የራሳቸው መዳን ብቻ እንዳልነበረ ማወቁ ያስደስተናል። ስለ አምላክ መንግሥት ልናውቅ የቻልነው እነርሱ ባደረጉት ጥረት በመሆኑ “ሂዱና አሕዛብን ሁሉ . . . ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው” በማለት ኢየሱስ የሰጠውን ተልዕኮ ለመፈጸም ያሳዩትን ጽናት እናደንቃለን። (ማቴዎስ 28:​19, 20) እኛም አጋጣሚው ክፍት ሆኖ እስከቆየልን ጊዜ ድረስ ምሥራቹን እስካሁን ላልሰሙ ሰዎች በመስበክ ያለንን አመስጋኝነት ልናሳይ እንችላለን። ይሁን እንጂ ስብከት ደቀ መዛሙርት የማድረጉን ሥራ ለማከናወን የሚወሰድ የመጀመሪያ እርምጃ ብቻ ነው።

“ለማስተማር ሥራህ ተጠንቀቅ”

9. አዎንታዊ አመለካከት መያዝ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለማስጀመር ሊረዳን የሚችለው እንዴት ነው?

9 የተሰጠን ተልእኮ መስበክ ብቻ ሳይሆን ማስተማርንም ይጨምራል። ኢየሱስ እርሱ የሰጠውን ትእዛዛት በሙሉ እንዲጠብቁ ሰዎችን እንድናስተምር ተልእኮ ሰጥቶናል። እርግጥ ነው፣ በአንዳንድ የአገልግሎት ክልሎች ውስጥ ስለ ይሖዋ ለመማር ፍላጎት ያላቸው ሰዎች እምብዛም የሚገኙ አይመስልም። ይሁን እንጂ ለክልሉ ያለን አመለካከት አፍራሽ ከሆነ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች ለማስጀመር የምናደርገውን ጥረት ሊያዳክምብን ይችላል። አንዳንዶች ፍሬ አልባ እንደሆነ አድርገው በሚቆጥሩት የአገልግሎት ክልል ውስጥ አቅኚ ሆና የምታገለግለው ኢቬት አፍራሽ አመለካከት ያልነበራቸው ከሌላ አካባቢ የመጡ አስፋፊዎች የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች እንዳገኙ ተገነዘበች። ኢቬት ይበልጥ አዎንታዊ የሆነ አመለካከት አዳበረችና እርሷም መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት የሚፈልጉ ሰዎችን አገኘች።

10. የመጽሐፍ ቅዱስ አስተማሪ በመሆን ልንጫወተው የሚገባው መሠረታዊ ሚና ምንድን ነው?

10 አንዳንድ ክርስቲያኖች ጥናት የመምራት ችሎታ እንዳላቸው ሆኖ ስለማይሰማቸው ፍላጎት ያላቸው ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንዲጀምሩ ለመጋበዝ ያመነቱ ይሆናል። እርግጥ ነው፣ ያለን ችሎታ ደረጃው ሊለያይ ይችላል። ይሁን እንጂ የተዋጣለት የአምላክ ቃል አስተማሪ መሆን ልዩ ችሎታ የሚጠይቅ ነገር አይደለም። ንጹሕ የሆነው የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት ኃይል አለው። እንዲሁም ኢየሱስ እንደተናገረው በግ መሰል የሆኑ ሰዎች የእውነተኛውን እረኛ ድምፅ ለይተው ያውቃሉ። ስለዚህ የእኛ ሥራ የመልካሙን እረኛ የኢየሱስን መልእክት የቻልነውን ያህል ጥርት ባለ መንገድ ማቅረብ ነው።​—⁠ዮሐንስ 10:​4, 14

11. የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪን በመርዳት ረገድ ይበልጥ ውጤታማ መሆን የምትችለው እንዴት ነው?

11 የኢየሱስን መልእክት ይበልጥ ውጤታማ በሆነ መንገድ ማቅረብ የምትችለው እንዴት ነው? በመጀመሪያ መጽሐፍ ቅዱስ ውይይት ስለሚደረግበት ርዕሰ ጉዳይ ምን እንደሚል በሚገባ ለመረዳት ጥረት አድርግ። አንድን ርዕሰ ጉዳይ ለሌሎች ከማስተማርህ በፊት በመጀመሪያ አንተ ልትረዳው ይገባል። በተጨማሪም በጥናቱ ወቅት አክብሮት የሚንጸባረቅበት ወዳጃዊ መንፈስ እንዲሰፍን ጥረት አድርግ። ትንንሽ ልጆችን ጨምሮ ተማሪዎች ዘና ሲሉና አስተማሪዎቻቸው አክብሮትና ደግነት ሲያሳዩዋቸው ትምህርቱን በተሻለ ሁኔታ ሊቀስሙ ይችላሉ።​—⁠ምሳሌ 16:​21

12. ተማሪው የምታስተምረው ትምህርት እንደገባው እርግጠኛ መሆን የምትችለው እንዴት ነው?

12 አስተማሪ እንደመሆንህ መጠን ተማሪህ የምታቀርባቸውን ነጥቦች እንዲሁ አድምጦ እንዲደግምልህ ብቻ እንደማትፈልግ የታወቀ ነው። ትምህርቱ እንዲገባው እርዳው። የአንድ ተማሪ የትምህርት ደረጃ፣ የሕይወት ተሞክሮና ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ያለው ትውውቅ የምትናገረውን ነገር በመረዳት ችሎታው ላይ ተጽዕኖ ያሳድራሉ። ስለዚህ ‘በሚጠናው ትምህርት ላይ የሰፈሩት ጥቅሶች ትርጉም ይገባዋልን?’ ብለህ ራስህን ልትጠይቅ ትችላለህ። በቀላሉ አዎን ወይም አይደለም የሚል መልስ የማይሰጥባቸውን ከዚያ ይልቅ ማብራሪያ የሚያሻቸውን ጥያቄዎች በመጠየቅ የልቡን አውጥቶ እንዲናገር ልታደርግ ትችላለህ። (ሉቃስ 9:​18-20) በሌላ በኩል ደግሞ አንዳንድ ተማሪዎች አስተማሪዎቻቸውን መጠየቅ ይፈራሉ። በዚህም ምክንያት ትምህርቱ ሙሉ በሙሉ ሳይገባቸው በጥናታቸው ይገፋሉ። ስለዚህ ተማሪው ጥያቄ እንዲጠይቅና አንዳንድ ነጥቦች ሳይገቡት ሲቀሩ እንዲነግርህ አበረታታው።​—⁠ማርቆስ 4:​10፤ 9:​32, 33

13. ተማሪህ አስተማሪ እንዲሆን ልትረዳው የምትችለው እንዴት ነው?

13 የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚመራበት አንዱ ዋና ዓላማ ተማሪው አስተማሪ እንዲሆን ለመርዳት ነው። (ገላትያ 6:​6) ይህንንም ለማሳካት በጥናታችሁ መጨረሻ ላይ ለክለሳ ያህል አንድ ነጥብ አንስተህ ለአንድ አዲስ ሰው እንደሚናገር ያህል ሆኖ ቀለል ባለ መንገድ እንዲያብራራልህ ልትጠይቀው ትችላለህ። ከዚያም በአገልግሎት ለመካፈል ብቁ በሚሆንበት ጊዜ በመስክ አብሮህ እንዲያገለግል ልትጋብዘው ትችላለህ። ከአንተ ጋር መሥራቱ ዘና ያለ ስሜት ሊፈጥርበትና የሚያገኘውም ተሞክሮ ራሱን ችሎ በአገልግሎት መካፈል እስከሚችልበት ጊዜ ድረስ በራስ የመተማመን መንፈሱን ሊያዳብርለት ይችላል።

ተማሪው የይሖዋ ወዳጅ እንዲሆን እርዳው

14. ስታስተምር ዋነኛ ግብህ ምንድን ነው? እዚህ ግብ ላይ እንድትደርስስ ምን ነገር አስተዋጽዖ ሊያበረክትልህ ይችላል?

14 የእያንዳንዱ ክርስቲያን አስተማሪ ዋነኛ ግብ ተማሪው ከይሖዋ ጋር እንዲወዳጅ መርዳት ነው። ይህንንም በቃል ብቻ ሳይሆን ራስህ ምሳሌ በመሆንም ልታከናውን ትችላለህ። ምሳሌ በመሆን ማስተማር በተማሪዎች ልብ ውስጥ ከፍተኛ ተጽእኖ ያሳድራል። በተለይ በተማሪዎች ልብ ውስጥ ጥሩ የሥነ ምግባር ባሕርያት ለመቅረጽና ቅንዓት ለመትከል ከተፈለገ ከቃላት ይበልጥ ድርጊት ከፍተኛ ሚና ይጫወታል። የምትናገራቸው ቃላትና የምታከናውናቸው ነገሮች ከይሖዋ ጋር ባለህ ጥሩ ዝምድና ላይ የተመሠረቱ ከሆኑ እርሱም እንዲህ ዓይነቱን ወዳጅነት ለማዳበር ይበልጥ ሊነሳሳ ይችላል።

15. (ሀ) ተማሪው ይሖዋን ለማገልገል ትክክለኛ የሆነ ውስጣዊ ግፊት ማዳበሩ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? (ለ) ተማሪው መንፈሳዊ እድገት ማድረጉን እንዲቀጥል ልትረዳው የምትችለው እንዴት ነው?

15 ተማሪህ ከአርማጌዶን ጥፋት ለመትረፍ ብሎ ሳይሆን ከፍቅር ተነሳስቶ ይሖዋን እንዲያገለግል ትፈልጋለህ። እንዲህ ያለ ንጹህ የሆነ ውስጣዊ ግፊት እንዲያዳብር በመርዳት በእምነቱ ላይ የሚደርሱበትን ፈተናዎች ለማለፍ በሚያስችሉት እሳትን የሚቋቋሙ ነገሮች ትገነባዋለህ። (1 ቆሮንቶስ 3:​10-15) አንተን ወይም ሌሎች ሰዎችን ለመኮረጅ ብሎ በተሳሳተ የውስጥ ግፊት የሚያደርገው ነገር ክርስቲያናዊ ያልሆኑ ተጽዕኖዎችን ለመቋቋም የሚያስችል ጥንካሬም ሆነ ትክክል የሆነውን ነገር ለማድረግ የሚያስችል ድፍረት አይሰጠውም። ሁልጊዜ አስተማሪው ሆነህ እንደማትቀጥል አስታውስ። አሁን አጋጣሚው ሳለህ የአምላክን ቃል በየዕለቱ በማንበብና ያነበበውን ነገር በማሰብ ወደ ይሖዋ ይበልጥ እንዲቀርብ ልታበረታታው ትችላለህ። እንዲህ የምታደርግ ከሆነ ታደርጉት የነበረው ጥናት ካቆመ ከረዥም ጊዜ በኋላም እንኳ በመጽሐፍ ቅዱስና መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች ላይ የሚገኘውን ‘የጤናማውን ቃል ምሳሌ’ መቅሰሙን ይቀጥላል።​—⁠2 ጢሞቴዎስ 1:​13

16. ተማሪው ከልቡ መጸለይን እንዲማር ልትረዳው የምትችለው እንዴት ነው?

16 ተማሪው ከልቡ መጸለይ እንዲችል በማስተማርም ወደ ይሖዋ ይበልጥ እንዲቀርብ ልትረዳው ትችላለህ። ይህን ልታደርግ የምትችለው እንዴት ነው? ምናልባት ኢየሱስ ያስተማረውን የናሙና ጸሎት እንዲሁም በመዝሙር መጽሐፍ ውስጥ እንዳሉት ዓይነት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተመዝግበው የሚገኙትን በርካታ ልባዊ ጸሎቶች ልታሳየው ትችል ይሆናል። (መዝሙር 17, 86, 143፤ ማቴዎስ 6:​9, 10) በተጨማሪም ተማሪህ ጥናት ስትጀምሩና ስትጨርሱ የምታቀርበውን ጸሎት ሲሰማ ለይሖዋ ያለህን ስሜት ይረዳል። ስለዚህ የምታቀርበው ጸሎት ሁልጊዜ ከልብ የመነጨና ግልጽነት የሚንጸባረቅበት እንዲሁም መንፈሳዊና ስሜታዊ ሚዛኑን የጠበቀ መሆን አለበት።

ልጆችህን ለማዳን መሥራት

17. ልጆች መዳን በሚገኝበት ጎዳና ላይ መጓዛቸውን እንዲቀጥሉ ወላጆች ሊረዷቸው የሚችሉት እንዴት ነው?

17 መዳን እንዲያገኙ ከምንመኝላቸው ሰዎች መካከል የቤተሰባችን አባላት እንደሚገኙበት የታወቀ ነው። ክርስቲያን ወላጆች ካሏቸው ልጆች መካከል ብዙዎቹ ቅኖችና ‘በእምነት የጸኑ ናቸው።’ ሌሎቹ ግን እውነት በልባቸው ውስጥ ሥር አልሰደደ ይሆናል። (1 ጴጥሮስ 5:​9፤ ኤፌሶን 3:​17፤ ቆላስይስ 2:​7) ከእነዚህ ልጆች መካከል ብዙዎች ሙሉ ሰው ወደሚሆኑበት ዕድሜ ሲቃረቡ ወይም ሙሉ ሰው ሲሆኑ የክርስትናን መንገድ ትተው ይወጣሉ። ወላጅ ከሆንክ ይህ ሁኔታ የሚከሰትበትን አጋጣሚ ለመቀነስ ምን ልታደርግ ትችላለህ? በመጀመሪያ፣ በቤተሰባችሁ ውስጥ ጤናማ መንፈስ እንዲፈጠር ጥረት ልታደርግ ትችላለህ። ጥሩ የቤተሰብ ኑሮ ለሥልጣን ጤናማ አመለካከት ለመያዝ፣ ተገቢ ለሆኑ የሥነ ምግባር ደንቦች አድናቆት ለማሳየትና ከሌሎች ጋር ደስተኛ ዝምድና ለመፍጠር የሚያስችል መሠረት ይጥላል። (ዕብራውያን 12:​9) ስለዚህ በቤተሰብ ውስጥ የተቀራረበ ግንኙነት መመሥረት አንድ ልጅ ከይሖዋ ጋር ያለውን ዝምድና ለማሳደግ እንዲችል መሠረት ሆኖ ሊያገለግለው ይችላል። (መዝሙር 22:​10) ምንም እንኳ ወላጆች የግል ጥቅም ለማግኘት ሊጠቀሙበት የሚችሉበትን ጊዜ መሥዋዕት እንዲያደርጉ የሚጠይቅባቸው ቢሆንም ጠንካራ ቤተሰቦች አንድ ላይ ሆነው ነገሮችን በሕብረት ያከናውናሉ። በዚህ መንገድ ልጆችህ በሕይወታቸው ውስጥ ትክክለኛ የሆኑ ውሳኔዎችን እንዲያደርጉ ራስህ ምሳሌ በመሆን ልታስተምራቸው ትችላለህ። ወላጆች፣ ልጆቻችሁ ከእናንተ በአብዛኛው የሚፈልጉት ነገር ቁሳዊ ጥቅም ሳይሆን እናንተን ማለትም ጊዜያችሁን፣ ጉልበታችሁንና ፍቅራችሁን ነው። እነዚህን ነገሮች ለልጆቻችሁ እየሰጣችሁ ነው?

18. ወላጆች ልጆቻቸው ለየትኞቹ ጥያቄዎች መልስ እንዲያገኙ መርዳት አለባቸው?

18 ክርስቲያን ወላጆች ልጆቻቸውም እነርሱን ተከትለው ክርስቲያን ይሆናሉ ብለው ማሰብ የለባቸውም። ሽማግሌና የአምስት ልጆች አባት የሆነው ዳንኤል እንዲህ በማለት ተናግሯል:- “ወላጆች ልጆቻቸው በትምህርት ቤትና በሌሎች ቦታዎች የሚቀስሟቸውን ጥርጣሬ የሚፈጥሩ ነገሮች እንዲያስወግዱ ለመርዳት ጊዜያቸውን ማዋል ይኖርባቸዋል። ወላጆች ልጆቻቸው እንደሚከተሉት ላሉት ጥያቄዎች መልስ እንዲያገኙ በትዕግሥት መርዳት አለባቸው:- ‘በእርግጥ የምንኖረው በመጨረሻው ጊዜ ነውን? ያለው እውነተኛ ሃይማኖት አንድ ብቻ ነውን? ሲያዩት ጨዋ የሚመስል አንድ የትምህርት ቤት ጓደኛ ጥሩ ወዳጅ ሊሆን የማይችለው ለምንድን ነው? ከጋብቻ በፊት የፆታ ግንኙነት መፈጸም ሁልጊዜ ስህተት ነውን?’” ወላጆች ሆይ፣ ይሖዋም ለልጆቻችሁ የሚያስብ በመሆኑ ጥረታችሁን እንደሚባርክላችሁ እርግጠኞች ልትሆኑ ትችላላችሁ።

19. ወላጆች ራሳቸው ከልጆቻቸው ጋር ማጥናታቸው ከሁሉ የተሻለ የሆነው ለምንድን ነው?

19 አንዳንድ ወላጆች ከራሳቸው ልጆች ጋር ለማጥናት እንደማይበቁ ሆኖ ሊሰማቸው ይችላል። ይሁን እንጂ ከእናንተ በተሻለ መንገድ ልጆቻችሁን ሊያስተምር የሚችል ሌላ ሰው ባለመኖሩ እንዲህ ሊሰማችሁ አይገባም። (ኤፌሶን 6:​4) ከልጆቻችሁ ጋር ማጥናታችሁ በልባቸውና በአእምሯቸው ውስጥ ያለውን ነገር ራሳችሁ በቀጥታ ማወቅ እንድትችሉ ይረዳችኋል። የሚናገሩት ከልባቸው ነው ወይስ ከአንገት በላይ ነው? የሚማሩትን ነገር በእርግጥ ያምኑበታል? ይሖዋ ለእነርሱ በእርግጥ እውን ነው? ለእነዚህና ለሌሎች እጅግ አስፈላጊ የሆኑ ጥያቄዎች መልስ ማግኘት የምትችሉት ራሳችሁ ከልጆቻችሁ ጋር የምታጠኑ ከሆነ ነው።​—⁠2 ጢሞቴዎስ 1:​5

20. ወላጆች የቤተሰብ ጥናቱ አስደሳችና ጠቃሚ እንዲሆን ማድረግ የሚችሉት እንዴት ነው?

20 የጀመራችሁትን የቤተሰብ ጥናት ሳታቋርጡ መቀጠል የምትችሉት እንዴት ነው? ሽማግሌና የአንድ ወንድና የአንዲት ሴት ልጅ አባት የሆነው ጆሴፍ እንዲህ ይላል:- “እንደ ሌሎቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች ሁሉ የቤተሰብ ጥናትም አስደሳችና እያንዳንዱ የቤተሰብ አባል በጉጉት የሚጠብቀው መሆን አለበት። በእኛም ቤተሰብ ውስጥ ይህ ሁኔታ እንዲሰፍን ለማድረግ እስከፈለግን ድረስ ጊዜን በተመለከተ ግትር አቋም ልንይዝ አንችልም። ጥናታችን ለአንድ ሰዓት የሚቆይ ሊሆን ይችላል። ሆኖም አልፎ አልፎ ለጥናት የሚኖረን ጊዜ አሥር ደቂቃ ብቻ እንኳ ቢሆን ከማጥናት ወደኋላ አንልም። ልጆቹ የሳምንቱን ጥናታችንን በጉጉት እንዲጠብቁ የሚያደርጋቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች መማሪያ መጽሐፌ  a የተባለውን መጽሐፍ ታሪኮች በድራማ መልክ የምንሠራቸው መሆኑ ነው። ትልቁ ነገር ብዙ አንቀጾች መሸፈናችን ሳይሆን ይህ ዓይነቱ ጥናት የሚያሳድረው ከፍተኛ ተጽዕኖና የሚያስገኘው እውቀት ነው።”

21. ወላጆች ልጆቻቸውን መቼ መቼ ሊያስተምሩ ይችላሉ?

21 እርግጥ ነው፣ ለልጆቻችሁ የምትሰጡት ትምህርት በተወሰነ የጥናት ክፍለ ጊዜ ብቻ መወሰን የለበትም። (ዘዳግም 6:​5-7) በመግቢያው ላይ የተጠቀሰው በታይላንድ የሚገኘው ምሥክር እንዲህ ብሏል:- “በብስክሌት ሆነን ከአባባ ጋር ራቅ ብሎ በሚገኘው የጉባኤያችን ክልል እናገለግልበት የነበረውን ወቅት እስከ አሁን ድረስ አስታውሳለሁ። ወላጆቻችን የተዉልን ምሳሌና በማንኛውም ወቅት ይሰጡን የነበረው ትምህርት የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ለመጀመር እንድንወስን እንደረዳን ምንም ጥርጥር የለውም። ትምህርቱ ውስጣችን ድረስ ዘልቆ ገብቷል። እስከ አሁን ድረስ ራቅ ብለው በሚገኙ የአገልግሎት ክልሎች በመሥራት ላይ እገኛለሁ።”

22. ‘ለራስህና ለትምህርትህ መጠንቀቅህ’ ምን ውጤት ያስገኝልሃል?

22 በቅርቡ ልክ የተቀጠረው ጊዜ ሲደርስ ኢየሱስ በዚህ ሥርዓት ላይ የአምላክን የቅጣት ፍርድ ለማስፈጸም ይመጣል። ያ ታላቅ ክንውን በአጽናፈ ዓለሙ ውስጥ የታሪክ አሻራ ጥሎ ያልፋል። ሆኖም የይሖዋ ታማኝ አገልጋዮች የዘላለም መዳንን ተስፋ እንደያዙ እርሱን ማገልገላቸውን ይቀጥላሉ። ከቤተሰብህና ከመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎችህ ጋር ሆነህ ከእነዚህ ሰዎች መካከል ለመገኘት ትፈልጋለህ? እንግዲያው “ለራስህና ለትምህርትህ ተጠንቀቅ፣ በእነዚህም ጽና፤ ይህን ብታደርግ፣ ራስህንም የሚሰሙህንም ታድና​ለህና” የሚለውን ምክር አስታውስ።​—⁠1 ጢሞቴዎስ 4:​16

[የግርጌ ማስታወሻ]

a ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የታተመ።

ልታብራራ ትችላለህ?

• አምላክ ፍርዱን የሚያስፈጽምበትን ጊዜ ስለማናውቅ ምን ዓይነት አመለካከት ሊኖረን ይገባል?

• በምን መንገዶች ‘ለትምህርታችን መጠንቀቅ’ እንችላለን?

• አንድ ተማሪ የይሖዋ ወዳጅ እንዲሆን እንዴት ልትረዳው ትችላለህ?

• ወላጆች ጊዜ ወስደው ልጆቻቸውን ማስተማራቸው አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አክብሮት የሚንጸባረቅበት ወዳጃዊ መንፈስ መኖሩ ተማሪው ትምህርቱን በተሻለ ሁኔታ እንዲቀስም ይረዳዋል

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሰሎሞን ለሁለቱ ጋለሞታዎች የሰጠውን ብያኔ የመሰሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮችን በድራማ መልክ መሥራት የቤተሰብ ጥናትን አስደሳች ያደርጋል