ለጢሞቴዎስ የተጻፈ ሁለተኛው ደብዳቤ 1:1-18

  • ሰላምታ (1, 2)

  • ጳውሎስ በጢሞቴዎስ እምነት የተነሳ አምላክን አመሰገነ (3-5)

  • የአምላክን ስጦታ ቸል አትበል (6-11)

  • ትክክለኛውን ትምህርት አጥብቀህ ያዝ (12-14)

  • የጳውሎስ ጠላቶችና ወዳጆች (15-18)

1  በክርስቶስ ኢየሱስ አማካኝነት የሚገኘውን ሕይወት+ በተመለከተ ከተገባው ቃል ጋር በሚስማማ ሁኔታ በአምላክ ፈቃድ የክርስቶስ ኢየሱስ ሐዋርያ ከሆነው ከጳውሎስ፣ 2  ለተወዳጁ ልጄ ለጢሞቴዎስ፦+ አባት ከሆነው አምላክና ከጌታችን ከክርስቶስ ኢየሱስ ጸጋ፣ ምሕረትና ሰላም ለአንተ ይሁን። 3  የቀድሞ አባቶቼ እንዳደረጉት ቅዱስ አገልግሎት የማቀርብለትንና በንጹሕ ሕሊና የማገለግለውን አምላክ አመሰግናለሁ፤ ደግሞም ሌት ተቀን አንተን ዘወትር በምልጃዬ አስታውሳለሁ። 4  እንባህን ሳስታውስ፣ በደስታ እሞላ ዘንድ ላይህ እናፍቃለሁ። 5  በአንተ ውስጥ ያለውን ግብዝነት የሌለበት እምነት+ አስታውሳለሁና፤ ይህ እምነት በመጀመሪያ በአያትህ በሎይድ እንዲሁም በእናትህ በኤውንቄ ዘንድ ነበር፤ ይሁንና በአንተም ውስጥ እንዳለ እርግጠኛ ነኝ። 6  ስለዚህ በአንተ ላይ እጄን በጫንኩበት+ ጊዜ የተቀበልከውን የአምላክ ስጦታ በቅንዓት እንድትጠቀምበት* አሳስብሃለሁ። 7  አምላክ የኃይል፣+ የፍቅርና የጤናማ አእምሮ መንፈስ እንጂ የፍርሃት መንፈስ አልሰጠንምና።+ 8  ስለሆነም ስለ ጌታችን መመሥከር አያሳፍርህ፤+ ደግሞም ለእሱ ስል እስረኛ በሆንኩት በእኔ አትፈር፤ ከዚህ ይልቅ በአምላክ ኃይል በመታመን+ አንተም ለምሥራቹ የበኩልህን መከራ ተቀበል።+ 9  እሱ በእኛ ሥራ ሳይሆን በራሱ ዓላማና ጸጋ የተነሳ አዳነን፤+ እንዲሁም ቅዱስ በሆነ ጥሪ ጠራን።+ ይህን ጸጋ ከረጅም ዘመናት በፊት በክርስቶስ ኢየሱስ አማካኝነት ሰጠን፤ 10  አሁን ግን ይህ ጸጋ አዳኛችን የሆነው ክርስቶስ ኢየሱስ በመገለጡ ግልጽ ሆኖ ታይቷል፤+ እሱ ሞትን አስወግዶ+ በምሥራቹ አማካኝነት+ ሕይወትንና አለመበስበስን+ በተመለከተ ብርሃን ፈንጥቋል፤+ 11  እኔም ለዚህ ምሥራች ሰባኪ፣ ሐዋርያና አስተማሪ ሆኜ ተሹሜአለሁ።+ 12  አሁን መከራ እየተቀበልኩ ያለሁትም ለዚሁ ነው፤+ ሆኖም አላፍርበትም።+ ያመንኩበትን እሱን አውቀዋለሁና፤ በአደራ የሰጠሁትንም እስከ ፍርድ ቀን ድረስ ጠብቆ ማቆየት እንደሚችል እተማመናለሁ።+ 13  ከእኔ የሰማኸውን የትክክለኛ* ትምህርት+ መሥፈርት* ከክርስቶስ ኢየሱስ ጋር ባለህ አንድነት ካገኘኸው እምነትና ፍቅር ጋር አጥብቀህ ያዝ። 14  ይህን መልካም አደራ በእኛ ውስጥ በሚኖረው መንፈስ ቅዱስ አማካኝነት ጠብቅ።+ 15  ፊጌሎስንና ሄርሞጌኔስን ጨምሮ በእስያ አውራጃ+ ያሉት ሁሉ ትተውኝ እንደሄዱ ታውቃለህ። 16  ጌታ ለኦኔሲፎሮስ+ ቤተሰብ ምሕረትን ይስጥ፤ እሱ ብዙ ጊዜ መንፈሴን አድሶልኛልና፤ በታሰርኩበት ሰንሰለትም አላፈረም። 17  እንዲያውም ሮም በነበረ ጊዜ አፈላልጎ አገኘኝ። 18  ጌታ ይሖዋ* በዚያ ቀን ምሕረቱን ይስጠው። ደግሞም በኤፌሶን ያከናወነውን አገልግሎት ሁሉ በሚገባ ታውቃለህ።

የግርጌ ማስታወሻዎች

^ ወይም “እንደ እሳት እንድታቀጣጥል።”
^ ወይም “የጤናማ፤ ጠቃሚ የሆነ።”
^ ወይም “ንድፍ።”
^ ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።