የሉቃስ ወንጌል 9:1-62

 • አሥራ ሁለቱ የአገልግሎት መመሪያ ተሰጣቸው (1-6)

 • ሄሮድስ ግራ ተጋባ (7-9)

 • ኢየሱስ 5,000 ሰዎችን መገበ (10-17)

 • ጴጥሮስ ‘አንተ ክርስቶስ ነህ’ አለው (18-20)

 • ኢየሱስ እንደሚሞት ተናገረ (21, 22)

 • እውነተኛ ደቀ መዝሙር (23-27)

 • ኢየሱስ በተአምራዊ ሁኔታ ተለወጠ (28-36)

 • ጋኔን ያደረበት ልጅ ተፈወሰ (37-43ሀ)

 • ኢየሱስ እንደሚሞት በድጋሚ ተናገረ (43ለ-45)

 • ደቀ መዛሙርቱ ማን ታላቅ እንደሚሆን ተከራከሩ (46-48)

 • እኛን የማይቃወም ሁሉ ከእኛ ጋር ነው (49, 50)

 • ሳምራውያን ኢየሱስን አልተቀበሉትም (51-56)

 • ኢየሱስን መከተል (57-62)

9  ከዚያም አሥራ ሁለቱን አንድ ላይ ጠርቶ አጋንንትን ሁሉ የማዘዝ+ እንዲሁም በሽታን የመፈወስ+ ኃይልና ሥልጣን ሰጣቸው።  ደግሞም የአምላክን መንግሥት እንዲሰብኩና የታመሙትን እንዲፈውሱ ላካቸው፤  እንዲህም አላቸው፦ “ለጉዟችሁ ምንም ነገር አትያዙ፤ በትርም ሆነ የምግብ ከረጢት፣ ዳቦም ሆነ ገንዘብ* እንዲሁም ሁለት ልብስ* አትያዙ።+  ሆኖም ወደ አንድ ቤት ስትገቡ ከተማዋን ለቃችሁ እስክትሄዱ ድረስ እዚያው ቆዩ፤+ ከዚያም ተነስታችሁ ሂዱ።  በየትኛውም ከተማ የሚቀበላችሁ ሰው ካጣችሁ፣ ከዚያ ከተማ ስትወጡ ምሥክር እንዲሆንባቸው የእግራችሁን አቧራ አራግፉ።”*+  እነሱም ወጥተው በሄዱበት ሁሉ ምሥራቹን እየተናገሩና የታመሙትን እየፈወሱ ከመንደር ወደ መንደር በመሄድ ክልሉን አዳረሱ።+  በዚህ ጊዜ የአውራጃ* ገዢ የሆነው ሄሮድስ* የተፈጸመውን ነገር ሁሉ ሰማ፤ አንዳንዶች ዮሐንስ ከሞት ተነስቷል ይሉ ስለነበረም በጣም ግራ ተጋባ፤+  ይሁንና ሌሎች ኤልያስ ተገልጧል፤ ሌሎች ደግሞ ከጥንት ነቢያት አንዱ ተነስቷል ይሉ ነበር።+  ሄሮድስም “ዮሐንስን አንገቱን ቆርጬዋለሁ።+ ታዲያ እንዲህ ሲወራለት የምሰማው ይህ ሰው ማን ነው?” አለ። ስለሆነም ሊያየው ይፈልግ ነበር።+ 10  ሐዋርያቱም በተመለሱ ጊዜ ያደረጉትን ነገር ሁሉ ለኢየሱስ ተረኩለት።+ እሱም ቤተሳይዳ ወደምትባል ከተማ ብቻቸውን ይዟቸው ሄደ።+ 11  ሆኖም ሕዝቡ ይህን ስላወቁ ተከተሉት። እሱም በደግነት ተቀብሎ ስለ አምላክ መንግሥት ይነግራቸው ጀመር፤ ፈውስ የሚያስፈልጋቸውንም ፈወሳቸው።+ 12  ቀኑም መምሸት ሲጀምር አሥራ ሁለቱ ሐዋርያት ወደ እሱ መጥተው “ያለንበት ስፍራ ገለል ያለ ስለሆነ ሕዝቡ በአካባቢው ወዳሉት መንደሮችና ገጠሮች ሄደው ማደሪያና ምግብ እንዲፈልጉ አሰናብታቸው” አሉት።+ 13  እሱ ግን “እናንተ የሚበሉት ነገር ስጧቸው” አላቸው።+ እነሱም “ሄደን ለዚህ ሁሉ ሕዝብ የሚሆን ምግብ ካልገዛን በስተቀር ከአምስት ዳቦና ከሁለት ዓሣ ሌላ ምንም የለንም” አሉት። 14  በዚያም 5,000 ያህል ወንዶች ነበሩ። እሱ ግን ደቀ መዛሙርቱን “ሕዝቡን በሃምሳ በሃምሳ ከፋፍላችሁ አስቀምጧቸው” አላቸው። 15  እነሱም በታዘዙት መሠረት ሕዝቡ እንዲቀመጥ አደረጉ። 16  ከዚያም አምስቱን ዳቦና ሁለቱን ዓሣ ይዞ ወደ ሰማይ ቀና በማለት ባረከ። ቆርሶም ለሕዝቡ እንዲያቀርቡ ለደቀ መዛሙርቱ ሰጣቸው። 17  ሁሉም በልተው ጠገቡ፤ የተረፈውንም ቁርስራሽ ሰበሰቡ፤ ቁርስራሹም 12 ቅርጫት ሙሉ ሆነ።+ 18  በኋላም ብቻውን ሆኖ እየጸለየ ሳለ ደቀ መዛሙርቱ ወደ እሱ መጡ፤ እሱም “ሕዝቡ እኔን ማን ይሉኛል?” ሲል ጠየቃቸው።+ 19  እነሱም መልሰው “አንዳንዶች መጥምቁ ዮሐንስ፣ ሌሎች ኤልያስ፣ ሌሎች ደግሞ ከጥንት ነቢያት አንዱ ተነስቷል ይላሉ” አሉት።+ 20  እሱም “እናንተስ ስለ እኔ ማንነት ምን ትላላችሁ?” አላቸው። ጴጥሮስም መልሶ “የአምላክ መሲሕ ነህ”* አለው።+ 21  ከዚያም ይህን ለማንም እንዳይናገሩ አጥብቆ አስጠነቀቃቸው፤+ 22  ቀጥሎም “የሰው ልጅ ብዙ መከራ መቀበሉ፣ እንዲሁም በሽማግሌዎች፣ በካህናት አለቆችና በጸሐፍት ተቀባይነት ማጣቱ ብሎም መገደሉና+ በሦስተኛው ቀን መነሳቱ+ አይቀርም” አላቸው። 23  ከዚያም ለሁሉም እንዲህ ሲል ተናገረ፦ “ሊከተለኝ የሚፈልግ ማንም ቢኖር ራሱን ይካድ፤+ የራሱን የመከራ እንጨት* በየዕለቱ ይሸከም፤ ያለማቋረጥም ይከተለኝ።+ 24  ሕይወቱን* ማዳን የሚፈልግ ሁሉ ያጣታልና፤ ለእኔ ሲል ሕይወቱን* የሚያጣ ሁሉ ግን ያድናታል።+ 25  ደግሞስ አንድ ሰው ዓለምን ሁሉ የራሱ ቢያደርግ፣ ነገር ግን ሕይወቱን ቢያጣ ወይም ለጉዳት ቢዳረግ ምን ይጠቅመዋል?+ 26  በእኔና በቃሌ የሚያፍር ሁሉ የሰው ልጅም በክብሩ እንዲሁም በአብና በቅዱሳን መላእክት ክብር ሲመጣ ያፍርበታል።+ 27  እውነት እላችኋለሁ፣ እዚህ ከቆሙት መካከል አንዳንዶች የአምላክን መንግሥት እስኪያዩ ድረስ ፈጽሞ ሞትን አይቀምሱም።”+ 28  በመሆኑም ይህን ከተናገረ ከስምንት ቀን ያህል በኋላ ጴጥሮስን፣ ዮሐንስንና ያዕቆብን ይዞ ለመጸለይ ወደ ተራራ ወጣ።+ 29  እየጸለየም ሳለ የፊቱ መልክ ተለወጠ፤ ልብሱም ነጭ ሆኖ አንጸባረቀ። 30  እነሆም ሁለት ሰዎች ይኸውም ሙሴና ኤልያስ ከእሱ ጋር ይነጋገሩ ነበር። 31  እነሱም በክብር ተገልጠው፣ በኢየሩሳሌም ስለሚፈጸመውና ከዚህ ዓለም ተለይቶ ስለሚሄድበት ሁኔታ ይነጋገሩ ጀመር።+ 32  በዚህ ጊዜ ጴጥሮስና አብረውት የነበሩት እንቅልፍ ተጫጭኗቸው ነበር፤ ሙሉ በሙሉ ሲነቁ ግን የኢየሱስን ክብር እንዲሁም አብረውት የቆሙትን ሁለት ሰዎች አዩ።+ 33  ሰዎቹ ከኢየሱስ ተለይተው ሲሄዱ ጴጥሮስ ኢየሱስን “መምህር፣ እዚህ መሆን ለእኛ መልካም ነው። ስለዚህ አንድ ለአንተ፣ አንድ ለሙሴና አንድ ለኤልያስ ሦስት ድንኳኖች እንትከል” አለው፤ ምን እየተናገረ እንዳለ አላስተዋለም ነበር። 34  ይህን እየተናገረ ሳለ ግን ደመና መጥቶ ጋረዳቸው። ደመናው ሲሸፍናቸው ፍርሃት አደረባቸው። 35  ከዚያም ከደመናው “የመረጥኩት ልጄ ይህ ነው።+ እሱን ስሙት”+ የሚል ድምፅ መጣ።+ 36  ድምፁም በተሰማ ጊዜ ኢየሱስን ብቻውን ሆኖ አዩት። እነሱም ዝም አሉ፤ ያዩትንም ነገር በዚያን ወቅት ለማንም አልተናገሩም።+ 37  በማግስቱ ከተራራው ሲወርዱ እጅግ ብዙ ሕዝብ ከኢየሱስ ጋር ተገናኘ።+ 38  እነሆም ከሕዝቡ መካከል አንድ ሰው ድምፁን ከፍ አድርጎ እንዲህ አለ፦ “መምህር፣ ልጄን እንድታይልኝ እለምንሃለሁ፤ ምክንያቱም ያለኝ ልጅ አንድ እሱ ብቻ ነው።+ 39  እነሆም፣ ርኩስ መንፈስ ይይዘውና በድንገት ይጮኻል፤ ጥሎም በአፉ አረፋ እያስደፈቀ ያንፈራግጠዋል፤ ጉዳት ካደረሰበትም በኋላ በስንት መከራ ይለቀዋል። 40  ደቀ መዛሙርትህ እንዲያስወጡት ለመንኳቸው፤ እነሱ ግን አልቻሉም።” 41  ኢየሱስም መልሶ “እምነት የለሽና ጠማማ ትውልድ ሆይ፣+ እስከ መቼ ከእናንተ ጋር መቆየትና እናንተን መታገሥ ሊኖርብኝ ነው? እስቲ ልጅህን ወደዚህ አምጣው” አለ።+ 42  ሆኖም ወደ እሱ እየመጣ ሳለ ጋኔኑ መሬት ላይ ጥሎ በኃይል አንፈራገጠው። ይሁንና ኢየሱስ ርኩሱን መንፈስ ገሠጸውና ልጁን ፈወሰው፤ ከዚያም ለአባቱ መልሶ ሰጠው። 43  በዚህ ጊዜ ሁሉም በአምላክ ታላቅ ኃይል ተደነቁ። ሰዎቹ ኢየሱስ ባደረገው ነገር ሁሉ እየተደነቁ ሳሉ ደቀ መዛሙርቱን እንዲህ አላቸው፦ 44  “ይህን የምነግራችሁን ቃል በጥሞና አዳምጡ፤ ደግሞም አስታውሱ፤ የሰውን ልጅ ለሰዎች አሳልፈው ይሰጡታልና።”+ 45  እነሱ ግን የነገራቸው ነገር አልገባቸውም። እንዲያውም እንዳያስተውሉት ነገሩ ተሰውሮባቸው ነበር፤ ስለዚህ ጉዳይ እንዳይጠይቁትም ፈሩ። 46  ከዚህ በኋላ ከመካከላቸው ማን እንደሚበልጥ እርስ በርሳቸው ይከራከሩ ጀመር።+ 47  ኢየሱስ የልባቸውን ሐሳብ ስላወቀ አንድ ትንሽ ልጅ አምጥቶ አጠገቡ አቆመ፤ 48  ከዚያም እንዲህ አላቸው፦ “ይህን ልጅ በስሜ የሚቀበል ሁሉ እኔንም ይቀበላል፤ እኔንም የሚቀበል ሁሉ የላከኝንም ይቀበላል።+ ምክንያቱም ታላቅ የሚባለው ራሱን ከሁላችሁ እንደሚያንስ አድርጎ የሚቆጥር ነው።”+ 49  ዮሐንስም “መምህር፣ አንድ ሰው በስምህ አጋንንት ሲያስወጣ አየን፤ ይሁንና ከእኛ ጋር ሆኖ አንተን ስለማይከተል ልንከለክለው ሞከርን” አለው።+ 50  ኢየሱስ ግን “የማይቃወማችሁ ሁሉ ከእናንተ ጋር ስለሆነ አትከልክሉት” አለው። 51  ኢየሱስ የሚያርግበት+ ጊዜ ሲቃረብ* ወደ ኢየሩሳሌም ለመሄድ ቆርጦ ተነሳ። 52  ስለዚህ አስቀድሞ መልእክተኞች ላከ። እነሱም ሄደው ለእሱ የሚያስፈልገውን ነገር ለማዘጋጀት ወደ አንድ የሳምራውያን መንደር ገቡ። 53   ሕዝቡ ግን ወደ ኢየሩሳሌም ለመሄድ ቆርጦ እንደተነሳ* ስላወቁ አልተቀበሉትም።+ 54  ደቀ መዛሙርቱ ያዕቆብና ዮሐንስ+ ይህን ባዩ ጊዜ “ጌታ ሆይ፣ እሳት ከሰማይ ወርዶ እንዲያጠፋቸው እንድናዝ ትፈልጋለህ?” አሉት።+ 55  እሱ ግን ዞር ብሎ ገሠጻቸው። 56  ስለዚህ ወደ ሌላ መንደር ሄዱ። 57   በመንገድ እየተጓዙም ሳሉ አንድ ሰው “ወደምትሄድበት ሁሉ እከተልሃለሁ” አለው። 58  ኢየሱስ ግን “ቀበሮዎች ጉድጓድ፣ የሰማይ ወፎችም ጎጆ አላቸው፤ የሰው ልጅ ግን ራሱን እንኳ የሚያሳርፍበት ቦታ የለውም” አለው።+ 59  ከዚያም ሌላውን “ተከታዬ ሁን” አለው። ሰውየውም “ጌታ ሆይ፣ በመጀመሪያ ሄጄ አባቴን እንድቀብር ፍቀድልኝ” አለው።+ 60  እሱ ግን “ሙታን+ ሙታናቸውን እንዲቀብሩ ተዋቸው፤ አንተ ግን ሄደህ የአምላክን መንግሥት በየቦታው አውጅ” አለው።+ 61  አንድ ሌላ ሰው ደግሞ “ጌታ ሆይ፣ እኔ እከተልሃለሁ፤ በመጀመሪያ ግን ቤተሰቤን እንድሰናበት ፍቀድልኝ” አለው። 62  ኢየሱስም “ዕርፍ ጨብጦ በኋላው ያሉትን ነገሮች የሚመለከት ሰው+ ለአምላክ መንግሥት የሚገባ አይደለም” አለው።+

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “ትርፍ ልብስ።”
ቃል በቃል “ብር።” ብር ከተባለው ማዕድን የተሠራ ገንዘብ።
የእግርን አቧራ ማራገፍ ከኃላፊነት ነፃ መሆንን ያመለክታል።
ቃል በቃል “የአራተኛው ክፍል።”
ሄሮድስ አንቲጳስን ያመለክታል። የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
ቃል በቃል “ክርስቶስ ነህ።”
ወይም “ነፍሱን።”
ወይም “ነፍሱን።”
ቃል በቃል “ቀኖቹ ሲሞሉ።”
ቃል በቃል “ፊቱን እንዳቀና።”