መዝሙር 143:1-12

  • ‘እንደ ደረቅ ምድር አምላክን ተጠማሁ’

    • ‘የእጆችህን ሥራ አውጠነጥናለሁ’ (5)

    • “ፈቃድህን እንድፈጽም አስተምረኝ” (10)

    • ‘መንፈስህ ይምራኝ’ (10)

የዳዊት ማህሌት። 143  ይሖዋ ሆይ፣ ጸሎቴን ስማ፤+እርዳታ ለማግኘት የማቀርበውን ልመና አዳምጥ። እንደ ታማኝነትህና እንደ ጽድቅህ መጠን መልስልኝ።   ሕያው የሆነ ማንኛውም ሰው በፊትህ ጻድቅ ሊሆን ስለማይችል፣+አገልጋይህን ለፍርድ አታቅርበው።   ጠላት ያሳድደኛልና፤*ሕይወቴንም አድቆ ከአፈር ደባልቋታል። ከረጅም ጊዜ በፊት እንደሞቱ ሰዎች በጨለማ ቦታ እንድኖር አድርጎኛል።   መንፈሴ* በውስጤ ዛለ፤+ልቤ በውስጤ ደነዘዘ።+   የጥንቱን ዘመን አስታውሳለሁ፤ባከናወንካቸው ነገሮች ሁሉ ላይ አሰላስላለሁ፤+የእጆችህን ሥራ በታላቅ ጉጉት አውጠነጥናለሁ።*   እጆቼን ወደ አንተ እዘረጋለሁ፤እንደ ደረቅ ምድር አንተን ተጠማሁ።*+ (ሴላ)   ይሖዋ ሆይ፣ ፈጥነህ መልስልኝ።+ጉልበቴ* ተሟጠጠ።+ ፊትህን ከእኔ አትሰውር፤+አለዚያ ወደ ጉድጓድ* እንደሚወርዱ ሰዎች እሆናለሁ።+   በአንተ ታምኛለሁና፣በማለዳ ታማኝ ፍቅርህን ልስማ። ፊቴን ወደ አንተ አዞራለሁና፣*ልሄድበት የሚገባውን መንገድ አሳውቀኝ።+   ይሖዋ ሆይ፣ ከጠላቶቼ ታደገኝ። የአንተን ጥበቃ እሻለሁ።+ 10  አንተ አምላኬ ስለሆንክ፣ፈቃድህን እንድፈጽም አስተምረኝ።+ መንፈስህ ጥሩ ነው፤በደልዳላ መሬት* ይምራኝ። 11  ይሖዋ ሆይ፣ ለስምህ ስትል በሕይወት አቆየኝ። በጽድቅህ ከጭንቅ ታደገኝ።*+ 12  በታማኝ ፍቅርህ ጠላቶቼን አስወግዳቸው፤*+አገልጋይህ ነኝና፣+የሚያጎሳቁሉኝን* ሰዎች ሁሉ አጥፋቸው።+

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “ነፍሴን ያሳድዳታልና።”
ወይም “ጉልበቴ።”
ወይም “አጠናለሁ።”
ወይም “ነፍሴ እንደ ደረቅ ምድር አንተን ተጠማች።”
ወይም “መቃብር።”
ቃል በቃል “መንፈሴ።”
ወይም “ነፍሴን ወደ አንተ አነሳለሁና።”
ወይም “በቅንነት ምድር።”
ወይም “ነፍሴን ከጭንቅ ታደጋት።”
ቃል በቃል “ጸጥ አሰኛቸው።”
ወይም “ነፍሴን የሚያጎሳቁሏትን።”