በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መጽሐፍ ቅዱስ—ትክክለኛ ትንቢት የያዘ መጽሐፍ—ክፍል—8

“መንግሥትህ ይምጣ”

መጽሐፍ ቅዱስ—ትክክለኛ ትንቢት የያዘ መጽሐፍ—ክፍል—8

በስምንት ተከታታይ “የንቁ!” እትሞች ላይ ከቀረበው ርዕስ የመጨረሻ በሆነው በዚህ ክፍል ውስጥ መጽሐፍ ቅዱስን ልዩ ከሚያደርጉት ገጽታዎች መካከል አንዱ ስለሆነው ማለትም በውስጡ ስለያዘው ትንቢት እንመረምራለን። ይህ ተከታታይ ርዕስ ለሚከተሉት ጥያቄዎች መልስ እንድታገኝ ይረዳሃል፦ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ጥሩ ችሎታ ያላቸው ሰዎች ያሰፈሯቸው ግምታዊ ሐሳቦች ናቸው? ወይስ እነዚህ ትንቢቶች በአምላክ መንፈስ መሪነት መጻፋቸውን የሚጠቁሙ ነገሮች አሉ? እስቲ ማስረጃዎቹን አብረን እንመርምር።

ላለፉት ሁለት ሺህ ዓመታት፣ ክርስቲያን ነን የሚሉ ሁሉ የአምላክ መንግሥት እንዲመጣ ሲጸልዩ ኖረዋል። እንዲህ የሚያደርጉት ኢየሱስ ራሱ ለደቀ መዛሙርቱ “መንግሥትህ ይምጣ። ፈቃድህ በሰማይ እየሆነ እንዳለ ሁሉ በምድርም ላይ ይሁን” ብለው እንዲጸልዩ ስላስተማራቸው ነው።—ማቴዎስ 6:10

ለመሆኑ ብዙ ሰዎች የሚጸልዩለት ይህ መንግሥት ምንድን ነው? የአምላክ መንግሥት በሰማይ የሚገኝ መስተዳድር ሲሆን ወደፊት ሌሎቹን መንግሥታት በሙሉ አጥፍቶ በምትኩ ይገዛል። ኢየሱስ ክርስቶስ የዚህ መንግሥት ንጉሥ ሆኖ የተሾመ እንደመሆኑ መጠን የአምላክ ፈቃድ በሰማይና በምድር እንዲፈጸም ያደርጋል። (ዳንኤል 2:44፤ 7:13, 14) አምላክ ወደፊት ክፋትንና መከራን በማስወገድ እንዲሁም “እጅግ ብዙ ሕዝብ” ለተባሉት ቁጥራቸው ላልተወሰነ ታማኝ አገልጋዮቹ መዳን በማስገኘት ለዚህ የጸሎት ናሙና መልስ ይሰጣል። (ራእይ 7:9, 10, 13-17) ከዚያም “ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ፤ በእርሷም ለዘላለም ይኖራሉ።”—መዝሙር 37:29

በክርስቶስ ግዛት ሥር ስለሚኖሩት ዝርዝር ሁኔታዎች በእርግጠኝነት ማወቅ የምንችልበት መንገድ ይኖራል? እንዴታ! ኢየሱስ ምድር ላይ በነበረበት ጊዜ የሰው ልጆችን ችግሮች ለማስወገድ ችሎታውም ሆነ ፍላጎቱ እንዳለው በተግባር አሳይቷል። ኢየሱስ በሰማይ የሚገኘው የአምላክ መንግሥት ንጉሥ በሚሆንበት ወቅት በዓለም ዙሪያ ምን እንደሚያደርግ ለመመልከት አራት የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶችንና ከእነዚህ ትንቢቶች ጋር በተያያዘ የፈጸማቸውን ናሙና የሚሆኑ ነገሮች እስቲ እንመርምር።

ትንቢት 1፦

ይሖዋ “ከዳር እስከ ዳር ጦርነትን ከምድር ያስወግዳል፤ ቀስትን ይሰብራል፤ ጦርን ያነክታል፤ ጋሻንም በእሳት ያቃጥላል።”—መዝሙር 46:9

ፍጻሜ፦ “የሰላም ልዑል” የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ምድራችን ላይ ዘላቂ የሆነ ሰላምና ጸጥታ እንዲሰፍን ያደርጋል። የአምላክ መንግሥት፣ በግዳጅ ሳይሆን ሰላማዊ በሆነ መንገድ የሚካሄድ የትምህርት መርሃ ግብር በመላው ምድር ላይ በመዘርጋትና የጦር መሣሪያዎች እንዲወገዱ በማድረግ የሰው ዘር በሙሉ በዓለም አቀፋዊ የወንድማማች ኅብረት እንዲታቀፍ ያደርጋል።—ኢሳይያስ 2:2-4፤ 9:6, 7፤ 11:9

ታሪክ ምን ያረጋግጣል?

ኢየሱስ ተከታዮቹ የጦር መሣሪያ እንዳያነሱና እርስ በርስ ተስማምተው በሰላም እንዲኖሩ አስተምሯቸዋል። ከኢየሱስ ደቀ መዛሙርት አንዱ እሱን ለመጠበቅ መሣሪያ ባነሳ ጊዜ “ሰይፍህን ወደ ቦታው መልስ፤ ሰይፍ የሚመዙ ሁሉ በሰይፍ ይጠፋሉ” ብሎታል። (ማቴዎስ 26:51, 52) ኢየሱስ እውነተኛ ክርስቲያኖች አንዳቸው ለሌላው በሚያሳዩት ፍቅር ተለይተው እንደሚታወቁ ተናግሯል።—ዮሐንስ 13:34, 35

ትንቢት 2፦

“በምድሪቱ ላይ እህል ይትረፍረፍ፤ በተራሮችም ዐናት ላይ ይወዛወዝ።”—መዝሙር 72:16

ፍጻሜ፦ የአምላክ መንግሥት ረሃብን የሚያስወግድ ከመሆኑም በላይ የተመጣጠነ ምግብ እንዲኖር ያደርጋል። በዚያን ጊዜ ሁሉም ሰው የሚፈልገውን ያህል ጥሩ ምግብ ያገኛል።

ታሪክ ምን ያረጋግጣል?

ኢየሱስ ለተራቡ ሰዎች ከልብ የመነጨ ርኅራኄ እንዳለው እንዲሁም ብዙ ሕዝብን በተአምር መመገብ እንደሚችል አሳይቷል። አንድ የዓይን ምሥክር የሚከተለውን ዘገባ አስፍሯል፦ “[ኢየሱስ] ሕዝቡ ሣሩ ላይ እንዲቀመጡ አዘዘና አምስቱን ዳቦና ሁለቱን ዓሣ ይዞ ወደ ሰማይ በማየት ባረከ፤ ዳቦውን ከቆረሰ በኋላም ለደቀ መዛሙርቱ አከፋፈለ፤ እነሱ ደግሞ ለሕዝቡ አከፋፈሉ። ሁሉም በልተው ጠገቡ፤ ከዚያም አሥራ ሁለት ቅርጫት ሙሉ የተረፈ ቁርስራሽ ሰበሰቡ። የበሉትም ሴቶችንና ልጆችን ሳይጨምር አምስት ሺህ ወንዶች ነበሩ።”—ማቴዎስ 14:14, 19-21

ትንቢት 3፦

“‘ታምሜአለሁ’ የሚል አይኖርም።” (ኢሳይያስ 33:24) “በዚያን ጊዜም የዕውር ዐይኖች ይገለጣሉ፤ የደንቈሮም ጆሮዎች ይከፈታሉ። አንካሳ እንደ ሚዳቋ ይዘላል፤ የድዳውም አንደበት በደስታ ይዘምራል።”—ኢሳይያስ 35:5, 6

ፍጻሜ፦ የአምላክ መንግሥት ማንኛውንም ዓይነት በሽታና የአካል ጉዳት ያስወግዳል። ዓይነ ስውራን ያያሉ፣ መስማት የተሳናቸው ይሰማሉ፤ እንዲሁም ይናገራሉ። ከዚያ በኋላ መድኃኒት፣ ሆስፒታል ወይም ሐኪም አያስፈልግም።

ታሪክ ምን ያረጋግጣል?

ኢየሱስ ሰዎችን ስለ አምላክ መንግሥት ያስተምር በነበረበት ጊዜ ከሕመማቸውና ካለባቸው የአካል ጉዳት በደስታ ፈውሷቸዋል። በዚህ መንገድ፣ የአምላክ መንግሥት ንጉሥ በሚሆንበት ጊዜ በምድር ላይ ምን እንደሚያደርግ በትንሹም ቢሆን አሳይቷል።—ሉቃስ 7:22፤ 9:11

ትንቢት 4፦

አምላክ “ሞትንም ለዘላለም ይውጣል።”—ኢሳይያስ 25:8

ፍጻሜ፦ ክርስቶስ፣ የአምላክ መንግሥት ንጉሥ ሆኖ በሚገዛበት ጊዜ “በመታሰቢያ መቃብር” ያሉ ሁሉ ተነስተው ገነት በምትሆነው ምድር ላይ ይኖራሉ። (ዮሐንስ 5:28, 29) ኢየሱስ የሰው ልጆች ክፉ ጠላት የሆነውን ሞትን ስለሚያስወግድ በደስታ ለዘላለም እንኖራለን።—መዝሙር 37:29

ታሪክ ምን ያረጋግጣል?

ኢየሱስ፣ ቢያንስ በሦስት አጋጣሚዎች የሞተን ሰው የማስነሳት ኃይል እንዳለው አሳይቷል። (ሉቃስ 7:11-15፤ 8:41-55፤ ዮሐንስ 11:38-44) ኢየሱስ ራሱ ከሞት መነሳቱን 500 የሚሆኑ ሰዎች መሥክረዋል።—1 ቆሮንቶስ 15:3-8

በዚህ ስምንት ክፍል ባለው ተከታታይ ርዕስ ሥር ፍጻሜያቸውን ያገኙ በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶችን ተመልክተናል። እነዚህና ሌሎች በርካታ ትንቢቶች፣ መጽሐፍ ቅዱስ ጥሩ ችሎታ ያላቸው ሰዎች ያሰፈሯቸውን ግምታዊ ሐሳቦች የያዘ እንዳልሆነ ያሳያሉ። ከዚህ ይልቅ እነዚህ ትንቢቶች መጽሐፍ ቅዱስ በአምላክ መንፈስ መሪነት መጻፉን ያረጋግጣሉ። እንግዲያው ‘ትንቢት በሰው ፈቃድ እንዳልመጣ ከዚህ ይልቅ ሰዎች ከአምላክ እንደተቀበሉት’ ምንም ጥርጥር የለውም።—2 ጴጥሮስ 1:21

መጽሐፍ ቅዱስ ትክክለኛ ትንቢቶችን የያዘ መጽሐፍ በመሆኑ በሚከተለው ተስፋ ላይ እምነት ለመጣል በቂ ምክንያት አለህ፦ “ለአፍታ እንጂ፣ ክፉ ሰው አይዘልቅም፤ ስፍራውንም ብታስስ አታገኘውም። ገሮች ግን ምድርን ይወርሳሉ፤ በታላቅ ሰላምም ሐሤት ያደርጋሉ።”—መዝሙር 37:10, 11