በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መጽሐፍ ቅዱስ—ትክክለኛ ትንቢት የያዘ መጽሐፍ—ክፍል—7

“መጨረሻው ይመጣል”

መጽሐፍ ቅዱስ—ትክክለኛ ትንቢት የያዘ መጽሐፍ—ክፍል—7

በእነዚህ ስምንት ተከታታይ “የንቁ!” እትሞች ላይ መጽሐፍ ቅዱስን ልዩ ከሚያደርጉት ገጽታዎች መካከል አንዱ ስለሆነው ማለትም በውስጡ ስለያዘው ትንቢት እንመረምራለን። ይህ ተከታታይ ርዕስ ለሚከተሉት ጥያቄዎች መልስ እንድታገኝ ይረዳሃል፦ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ጥሩ ችሎታ ያላቸው ሰዎች ያሰፈሯቸው ግምታዊ ሐሳቦች ናቸው? ወይስ እነዚህ ትንቢቶች በአምላክ መንፈስ መሪነት መጻፋቸውን የሚጠቁሙ ነገሮች አሉ? እስቲ ማስረጃዎቹን አብረን እንመርምር።

ምግባረ ብልሹ የሆኑ መንግሥታት ዜጎቻቸውን ሲጨቁኑና ሲበዘብዙ ያበሳጭሃል? ትላልቅ የንግድ ድርጅቶች ድሆችን እየበዘበዙ ባለጸጎችን ሲያደልቡ ስታይ ይህ የፍትሕ መጓደል ያናድድሃል? የሃይማኖት መሪዎች የምዕመኖቻቸውን ቤት ሲያራቁቱ ወይም የሐሰት ትምህርት ሲያስተምሩ ያስቆጣሃል? እንዲህ የሚሰማህ ከሆነ መጽሐፍ ቅዱስም እነዚህን ክፉ ድርጊቶች እንደሚያወግዝ ማወቅህ ሊያስደስትህ ይችላል። ይህ ርዕስ (1) ክፋትና ክፉ ሰዎች እንደሚጠፉ የሚናገሩትን የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች እንዲሁም (2) በእነዚህ ትንቢቶች ላይ ሙሉ በሙሉ መተማመን የምንችለው ለምን እንደሆነ ያብራራል።

የክፋት ፍጻሜ

ባለፈው እትም ላይ የቀረበው የዚህ ተከታታይ ርዕስ ስድስተኛ ክፍል፣ ኢየሱስ የዚህ ዓለም ፍጻሜ መቅረቡን እንደሚያመለክት የተናገረውን ምልክት የተለያዩ ገጽታዎች አብራርቶ ነበር። ከዚህ ምልክት ገጽታዎች አንዱ ስለ አምላክ መንግሥት የሚናገረው ምሥራች በመላው ዓለም የሚታወጅ መሆኑ ነው፤ የአምላክ መንግሥት በቅርቡ መላውን ምድር ያስተዳድራል። (ዳንኤል 2:44፤ ማቴዎስ 24:3, 14) ምሥራቹን የማወጁ ሥራ ሲጠናቀቅ ‘መጨረሻው እንደሚመጣ’ ኢየሱስ ተናግሯል። አምላክ በመጀመሪያ የሚያጠፋው ስለ እሱ የተሳሳተ ትምህርት የሚያስተምሩትን የሐሰት ሃይማኖቶች እንደሆነ ስታውቅ ትገረም ይሆናል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሐሰት ሃይማኖቶች “ታላቂቱ ባቢሎን” በምትባል ጋለሞታ ሴት ተመስለዋል።—ራእይ 17:1, 5 “የታላቂቱ ባቢሎንን ማንነት ማወቅ” የሚለውን በገጽ 13 ላይ የሚገኘውን ሣጥን ተመልከት።

ትንቢት 1፦

‘በታላቂቱ ባቢሎን ላይ መቅሰፍት፣ ሞትና ሐዘን እንዲሁም ረሃብ ይመጣባታል፤ ሙሉ በሙሉም በእሳት ትቃጠላለች፤ ምክንያቱም ፍርድ የበየነባት ይሖዋ አምላክ ብርቱ ነው።’—ራእይ 18:2, 8

ፍጻሜ፦ አምላክ እሱ በቀጠረው ጊዜ የዓለም የፖለቲካ ኃይሎች በታላቂቱ ባቢሎን ላይ እንዲነሱና እንዲያጠፏት እንደሚያደርግ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። መጽሐፍ ቅዱስ “ያወድሟታል፣ እርቃኗንም ያስቀሯታል፤ እንዲሁም ሥጋዋን ይበላሉ” ይላል። (ራእይ 17:16) በሌላ አባባል አሳፋሪ ድርጊቷን ያጋልጣሉ፤ እንዲሁም ከፍተኛ መጠን ያለውን ሀብቷን ይመዘብራሉ። የሚደርስባት ጥፋት ፈጣንና ሥር ነቀል ስለሚሆን አንዳች ርዝራዥ አይቀርላትም።—ራእይ 18:21

የፖለቲካ መሪዎች ይህን እርምጃ የወሰዱት በራሳቸው ተነሳስተው እንደሆነ ሊሰማቸው ይችላል። ይሁን እንጂ ይህ አስደናቂ ትንቢት በትክክል መፈጸሙ በባቢሎን ላይ ጥፋት ያመጣው አምላክ መሆኑን ያረጋግጣል። አምላክ “ሐሳቡን ዳር እንዲያደርሱ . . . ይህን በልባቸው” ያኖራል።—ራእይ 17:17

ትንቢት 2፦

“በነዚያ ነገሥታት ዘመን፣ የሰማይ አምላክ . . . መንግሥት ይመሠርታል፤ እነዚያን [ሰብዓዊ] መንግሥታት ሁሉ ያደቃል፤ እስከ መጨረሻውም ያጠፋቸዋል፤ ይህ መንግሥት ራሱ ግን ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል።”—ዳንኤል 2:44

ፍጻሜ፦ አምላክ የሐሰት ሃይማኖትን ካጠፋ በኋላ የትኩረት አቅጣጫውን ወደ ሌሎች ድርጅቶች ማለትም ወደ ፖለቲካና ንግድ ድርጅቶች አልፎ ተርፎም ወደ ክፉ ሰዎች ያዞራል። (ምሳሌ 2:22፤ ራእይ 19:17, 18) ንብረቱን የሚያበላሹ ተከራዮችን እንደሚያባርር አከራይ ሁሉ አምላክ ‘ምድርን እያጠፉ ያሉትን ያጠፋል።’ በዓመፅ አልፎ ተርፎም ወራዳ በሆኑ የፆታ ድርጊቶች ምድር እንድትበከል ያደረጉትን ሰዎች ያስወግዳል።—ራእይ 11:18፤ ሮም 1:18, 26-29

ይሁንና ከጥፋቱ የሚተርፉት እነማን ናቸው? መጽሐፍ ቅዱስ “ገሮች ግን ምድርን ይወርሳሉ፤ በታላቅ ሰላምም ሐሤት ያደርጋሉ” በማለት መልሱን ይሰጠናል።—መዝሙር 37:11፤ 72:7

ታዲያ በመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች መተማመን እንችላለን? አምላክ ክፋትንና መከራን እንደሚያስወግድና ጻድቃንን እንደሚጠብቅ እርግጠኞች መሆን እንችላለን? እንዴታ!

የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች አስተማማኝ ናቸው

የይሖዋ ምሥክሮች፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ባለቤት ይሖዋ አምላክ እንደሆነና እሱ ደግሞ ቃል የገባውን ነገር በሙሉ እንደሚፈጽም ያምናሉ። (2 ጢሞቴዎስ 3:16) ታዲያ ይህ እምነታቸው ምክንያታዊ ነው?

ከልብ የሚወድህና አንድም ጊዜ ዋሽቶህ የማያውቅ የረጅም ጊዜ ወዳጅ አለህ እንበል፤ ይህ ወዳጅህ አንድ ነገር እንደሚያደርግልህ ቃል ቢገባልህና ይህን ለማድረግ አቅሙ እንዳለው ብታውቅ ትጠራጠረዋለህ? እንደማትጠራጠረው የታወቀ ነው። አምላክ ደግሞ ከየትኛውም ሰብዓዊ ወዳጅ ይበልጣል። እሱ ፈጽሞ ‘ሊዋሽ አይችልም!’—ቲቶ 1:2

በእርግጥም ፈጣሪ የሐሰት ሃይማኖቶችን፣ ጨቋኝ መንግሥታትንና ስግብግብ የሆነውን የንግዱን ዓለም ሙሉ በሙሉ ያጠፋል። አምላክ እነዚህን እርምጃዎች ከወሰደ በኋላ የሚከናወነውን ነገር ማወቅ ትፈልጋለህ? ከሆነ የሚቀጥለውን የንቁ! እትም ጠቃሚ ሆኖ እንደምታገኘው ምንም ጥርጥር የለውም። መጽሔቱ የዚህን ተከታታይ ርዕስ የመጨረሻ ክፍል ይዞ ይወጣል።