በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ትዕግሥት የጠፋው ለምን ይሆን?

ትዕግሥት የጠፋው ለምን ይሆን?

ትዕግሥት ማጣት በዘመናችን ብቻ የሚታይ ነገር አይደለም። ሰዎች የትራፊክ መጨናነቅ በመፈጠሩ መንገድ ሲዘጋባቸው ወይም ተሰልፈው ተራ መጠበቅ በሚኖርባቸው ጊዜ ትዕግሥት ማጣታቸው አዲስ ነገር አይደለም። ይሁን እንጂ አንዳንድ ባለሙያዎች ሰዎች ከበፊቱ የበለጠ ትዕግሥት እያጡ እንደመጡ ይሰማቸዋል፤ ለዚህ ምክንያት የሆኑት ነገሮች ደግሞ አስገራሚ ናቸው።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ብዙ ሰዎች ትዕግሥት እያጡ ያሉት በቴክኖሎጂ ምክንያት እንደሆነ አንዳንድ ተንታኞች ይናገራሉ። በሞንትሪያል፣ ካናዳ የሚታተመው ዘ ጋዜት እንደሚለው ከሆነ አንዳንድ ተመራማሪዎች “እንደ ሞባይል ስልክ፣ ካሜራ፣ ኢ-ሜይልና አይፖድ ያሉት ዲጂታል ቴክኖሎጂዎች ሕይወታችንን እየለወጡት” እንደሆነ ይሰማቸዋል። ጋዜጣው አክሎ እንደገለጸው “እነዚህን ቴክኖሎጂዎች ስንጠቀም ቅጽበታዊ ምላሽ ማግኘታችን በሌሎቹም የሕይወታችን ዘርፎች ነገሮች በፍጥነት እንዲከናወኑ እንድንፈልግ አድርጎናል።”

የቤተሰብ የሥነ ልቦና ተመራማሪ የሆኑት ዶክተር ጄኒፈር ሀርትሽታይን በዚህ ረገድ የሰጡት አስተያየት ጉዳዩን በቁም ነገር እንድናስብበት የሚያደርግ ነው። እኚህ ሴት እንዲህ ብለዋል፦ “ፍላጎታችን በቅጽበት እንዲሟላልን የመፈለግ ዝንባሌ አዳብረናል፤ ነገሮች በፍጥነት እንዲሁም ቅልጥፍ ባለና በምንፈልገው መንገድ እንዲከናወኑ እንጠብቃለን። ይህ ሳይሆን ሲቀር ቶሎ መበሳጨትና መነጫነጭ ይቀናናል፤ ይህም ትዕግሥት የለሾች እንደሆንን የሚጠቁም ነው።” አክለውም “ተረጋግቶና ዘና ብሎ መሥራት የሚለው ነገር እየጠፋብን ነው” ብለዋል።

አንዳንዶች በኢ-ሜይል መልእክት መለዋወጥ ተወዳጅነቱን እያጣ እንደሆነና በቅርቡ ዘመን ያለፈበት እንደሚሆን ይሰማቸዋል። ለምን? ምክንያቱም መልእክት የሚላላኩ ብዙ ሰዎች ምላሽ ለማግኘት ለሰዓታት ሌላው ቀርቶ ለደቂቃዎች እንኳ ለመጠበቅ ትዕግሥቱ የላቸውም። በተጨማሪም እንደ ደብዳቤ ሁሉ የኢ-ሜይል መልእክት ስንጽፍም አብዛኛውን ጊዜ በመልእክቱ መጀመሪያና መጨረሻ ላይ ሰላምታና የስንብት ሐሳብ እንድንጽፍ ይጠበቅብናል። ይሁን እንጂ ብዙ ሰዎች እንዲህ ማድረግ አሰልቺና ጊዜ የሚያባክን ነገር እንደሆነ ይሰማቸዋል። ከዚህ ይልቅ እንደ ኢ-ሜይል ተጨማሪ ሥራ የማይጠይቀውን አጭር የጽሑፍ መልእክት ይመርጣሉ። ሰዎች የአክብሮት መግለጫ የሆኑትን የሰላምታና የስንብት ሐሳቦች እንኳ ለማስፈር ትዕግሥት ያጡ ይመስላል! ብዙ ሰዎች የጻፉት ነገር ስህተት እንደሌለበት ለማረጋገጥ ደግመው ለማንበብ አይሞክሩም። በዚህም የተነሳ ደብዳቤዎችና የኢ-ሜይል መልእክቶች ወደተሳሳተ አድራሻ ሊሄዱ ወይም በርካታ የሰዋስውና የፊደል ስህተት ሊገኝባቸው ይችላል።

ብዙ ሰዎች ረዘም ያለ ጽሑፍ አንብበው ለመጨረስ ትዕግሥት የላቸውም

ሰዎች አፋጣኝ ምላሽ ለማግኘት ያላቸው ጉጉት የሚታየው ከመልእክት መለዋወጫ ዘዴዎች ጋር በተያያዘ ብቻ አይደለም። በሌሎች የሕይወታቸው መስኮችም በትዕግሥት መጠበቅ እየተሳናቸው ይመስላል። ለምሳሌ ያህል፣ አንተ ራስህ አንዳንድ ጊዜ ቸኮል ቸኮል እያልክ እንደምታወራ፣ ቶሎ ቶሎ እንደምትበላ፣ በፍጥነት እንደምትነዳ ወይም ገንዘብ ቶሎ እንደምታጠፋ አስተውለሃል? የአሳንሰር ቁልፍ ተጭነህ እስኪመጣ፣ የትራፊክ መብራት እስኪለወጥ ወይም ኮምፒዩተር ካበራህ በኋላ እስኪነሳ ድረስ የሚወስደው ጥቂት ጊዜ ረጅም መስሎ ሊታይህ ይችላል።

ብዙ ሰዎች ረዘም ያለ ጽሑፍ አንብበው ለመጨረስ ትዕግሥት እንደሌላቸው ተመራማሪዎች ታዝበዋል። ለምን? ምክንያቱም ድረ ገጾችን በሚቃኙበት ጊዜ ዋናውን ነጥብ ቶሎ ለማግኘት ሲሉ ጎላ ብለው የተጻፉትን ነገሮች ብቻ ማንበብ ወይም ሌሎቹን ነጥቦች ገረፍ ገረፍ አድርገው ማለፍ ለምዶባቸዋል።

ትዕግሥት የጠፋው ለምን ይሆን? ባለሙያዎች፣ ለትዕግሥት መጥፋት መንስኤ የሆኑትን ሁሉንም ነገሮች አያውቁም። ሆኖም ትዕግሥት ማጣት ጎጂ እንደሆነ የሚጠቁም ጠንካራ ማስረጃ አለ። ቀጥሎ የሚቀርቡት ርዕሶች ትዕግሥት ማጣት ከሚያስከትላቸው አደጋዎች ውስጥ አንዳንዶቹን የሚያነሱ ከመሆኑም ሌላ ይበልጥ ታጋሽ ለመሆን ምን ማድረግ እንደምትችል ያብራራሉ።

ብዙ ሰዎች ድረ ገጾችን በሚቃኙበት ጊዜ ጎላ ብለው የተጻፉትን ነገሮች ብቻ ገረፍ ገረፍ አድርገው ማለፍ ለምዶባቸዋል