መጽሐፍ ቅዱስ—ትክክለኛ ትንቢት የያዘ መጽሐፍ—ክፍል—6
‘የመጨረሻዎቹ ቀኖች’
በእነዚህ ስምንት ተከታታይ “የንቁ!” እትሞች ላይ መጽሐፍ ቅዱስን ልዩ ከሚያደርጉት ገጽታዎች መካከል አንዱ ስለሆነው ማለትም በውስጡ ስለያዘው ትንቢት እንመረምራለን። ይህ ተከታታይ ርዕስ ለሚከተሉት ጥያቄዎች መልስ እንድታገኝ ይረዳሃል፦ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ጥሩ ችሎታ ያላቸው ሰዎች ያሰፈሯቸው ግምታዊ ሐሳቦች ናቸው? ወይስ እነዚህ ትንቢቶች በአምላክ መንፈስ መሪነት መጻፋቸውን የሚጠቁሙ ነገሮች አሉ? እስቲ ማስረጃዎቹን አብረን እንመርምር።
የምንኖረው እጅግ አስቸጋሪ በሆነ ዘመን ውስጥ ነው። ከሁሉም የዓለም ክፍሎች የመዓትና የሕዝባዊ ዓመፅ ዜና ይጎርፋል። በአሁኑ ጊዜ በዓለም ላይ ያለው ሁኔታ የተለየ ትርጉም ይኖረው ይሆን?
መጽሐፍ ቅዱስ ከ2,000 ዓመታት ገደማ በፊት፣ የዓለም ችግሮች ‘በዚህ ሥርዓት መደምደሚያ’ እየተባባሱ ሄደው ከፍተኛ ደረጃ ላይ እንደሚደርሱ ተንብዮአል። (ማቴዎስ 24:3) ይህ ሲባል ግን ብዙዎች በሚያስቡት መንገድ “የዓለም መጨረሻ” ይመጣል ማለት አይደለም። ከዚህ ይልቅ መጽሐፍ ቅዱስ ‘የመጨረሻዎቹ ቀኖች’ ተብሎ በሚጠራው ዘመን ውስጥ በስፋት ስለሚታዩ ሁኔታዎችና ባሕርያት ወይም ምልክት ይገልጻል። (2 ጢሞቴዎስ 3:1) ኢየሱስ ‘እነዚህ ነገሮች ከተከሰቱ’ ብዙም ሳይቆይ እፎይታ የሚገኝበት ዘመን እንደሚመጣ ለተከታዮቹ ተናግሯል። (ሉቃስ 21:31) እስቲ የምንኖርበትን ዘመን ልዩ የሚያደርጉትን አንዳንድ ትንቢቶች እንመልከት።
ትንቢት 1፦
“ሕዝብ በሕዝብ ላይ . . . ይነሳል።”—ማቴዎስ 24:7
ፍጻሜ፦ ብዙ ሰዎች በ20ኛው መቶ ዘመን መጀመሪያ ላይ ዘላቂ ሰላም እንደሚመጣ ጠብቀው ነበር። ይሁንና አንደኛው የዓለም ጦርነት ሲፈነዳ መላው ዓለም የተናወጠ ሲሆን ከዚያ በፊት ታይቶ የማያውቅ የጦርነት ዘመን ጀመረ። የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሆነው የራእይ መጽሐፍ እንደተነበየው “ሰዎች እርስ በርሳቸው ይተራረዱ ዘንድ ሰላም” ከምድር ተወሰደ።—ራእይ 6:4
ታሪክ ምን ያረጋግጣል?
-
“አንደኛው የዓለም ጦርነት በ1914 መፈንዳቱ አንድ ዘመን አልቆ ሌላ ዓይነት ዘመን መተካቱን የሚያሳይ ክስተት ሆኗል።”—በ1992 የታተመው ዚ ኦሪጅንስ ኦቭ ዘ ፈርስት ዎርልድ ዋር.
-
አንደኛው የዓለም ጦርነት ያስከተለውን እልቂት በትክክል ማወቅ ባይቻልም አንድ ኢንሳይክሎፒዲያ እንደገመተው የተገደሉት መለዮ ለባሾች ቁጥር ብቻ እንኳ 8,500,000 ይደርሳል።
-
ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ደግሞ እጅግ የከፋ ሲሆን የተገደሉት ወታደሮችና ሰላማውያን ሰዎች ቁጥር ከ35 ሚሊዮን እስከ 60 ሚሊዮን እንደሚደርስ ይገመታል።
-
ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማብቂያ እስከ 2010 ባሉት ዓመታት በዓለም ዙሪያ በ151 ቦታዎች 246 ውጊያዎች ተካሂደዋል።
ትንቢት 2፦
“የምግብ እጥረት . . . ይከሰታል።” —ማቴዎስ 24:7
ፍጻሜ፦ በ20ኛው መቶ ዘመን ከ70 ሚሊዮን የሚበልጡ ሰዎች በረሃብ ምክንያት ያለቁ ሲሆን ረሃብ ዛሬም ድረስ ዓለም አቀፍ ችግር ነው።
ታሪክ ምን ያረጋግጣል?
-
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንደገለጸው የዓለማችን ትልቁ የጤና ጠንቅ ረሃብ ነው፤ በአሁኑ ጊዜ በመላው ዓለም ከሰባት ሰዎች አንዱ በቂ ምግብ አያገኝም።
-
“በዘመናችን ያለው ረሃብ በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የተከሰተ የአንድ ወቅት ችግር ሳይሆን በአራት አሳሳቢ ምክንያቶች የተነሳ የመጣ የረጅም ጊዜ ችግር ነው። እነሱም የሕዝብ ቁጥር በፍጥነት ማሻቀብ፣ የአፈር መሸርሸር፣ የውኃ እጥረት መስፋፋትና የሙቀት መጠን መጨመር ናቸው።”—ሳይንቲፊክ አሜሪካን
ትንቢት 3፦
“ታላላቅ የምድር ነውጦች ይከሰታሉ።”—ሉቃስ 21:11
ፍጻሜ፦ በርካታ ሰዎች ለምድር ነውጥ በተጋለጡ አካባቢዎች ስለሚኖሩ በምድር ነውጥ ምክንያት ሕይወታቸውን የሚያጡ ወይም ከመኖሪያቸው የሚፈናቀሉ ሰዎች ብዛት በእጅጉ ጨምሯል።
ታሪክ ምን ያረጋግጣል?
-
ዎርልድ ዲዛስተርስ ሪፖርት 2010 “ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በምድር ነውጥ ምክንያት የሞቱት ሰዎች ቁጥር በሌላ ማንኛውም አደጋ ከሞቱት ሰዎች ቁጥር በጣም በልጧል” ሲል ገልጿል።
-
ከ1970 እስከ 2001 ባሉት ዓመታት በየዓመቱ በአማካይ ለ19,547 ሰዎች ሞት ምክንያት የሆኑ 19 የምድር ነውጥ አደጋዎች * ሪፖርት ተደርገዋል። ከ2012 በፊት በነበሩት አሥር ዓመታት በየዓመቱ የሚከሰተው የምድር ነውጥ አደጋ ቁጥር በአማካይ ወደ 28 ከፍ ያለ ሲሆን በዚሁ አደጋ ምክንያት የሞቱት ሰዎች ቁጥር በአማካይ 67,954 ደርሷል።
ትንቢት 4፦
“በተለያየ ስፍራም ቸነፈር . . . ይሆናል።”—ሉቃስ 21:11
ፍጻሜ፦ በሕክምናው መስክ ከፍተኛ እድገት የተገኘ ቢሆንም በዛሬው ጊዜም እንኳ በየዓመቱ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በተዛማች በሽታዎች ምክንያት ይሞታሉ። ብዙ ሰዎች ከአገር ወደ አገር መጓዛቸውና የከተማ ነዋሪዎች ቁጥር እየበዛ መምጣቱ በሽታዎች በፍጥነት እንዲዛመቱ አመቺ ሁኔታ ፈጥሯል።
ታሪክ ምን ያረጋግጣል?
-
በ20ኛው መቶ ዘመን የፈንጣጣ በሽታ ከ300 ሚሊዮን እስከ 500 ሚሊዮን የሚደርሱ ሰዎችን ሕይወት ቀጥፏል።
-
ዎርልድዎች የተባለው ተቋም ባለፉት ሦስት አሥርተ ዓመታት “እንደ ኢቦላ፣ ኤች አይ ቪ፣ ሃንታቫይረስና ሳርስ ያሉ ከሠላሳ የሚበልጡ ከዚህ በፊት የማይታወቁ አደገኛ በሽታዎች ብቅ ብለዋል” በማለት ሪፖርት አድርጓል።
-
የዓለም የጤና ድርጅት፣ ጀርሞች መድኃኒት የመቋቋም አቅማቸው እየጨመረ እንደመጣ ሲያስጠነቅቅ እንዲህ ብሏል፦ “ዓለማችን ወደ ድህረ አንቲባዮቲክ ዘመን እያመራች ሲሆን ይህ ደግሞ በርካታ ተራ በሽታዎች መድኃኒት እንዲያጡ እንዲሁም የብዙዎች ሕይወት እንዲቀጠፍ ያደርጋል።”
ትንቢት 5፦
“አንዱ ሌላውን አሳልፎ ይሰጣል፣ [ሰዎች] እርስ በርሳቸውም ይጠላላሉ። . . . የብዙዎች ፍቅር ይቀዘቅዛል።”—ማቴዎስ 24:10, 12
ፍጻሜ፦ በጥላቻ ምክንያት የተቀሰቀሱ የዘር ማጥፋት ዘመቻዎች በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ለሞት ዳርገዋል። በብዙ አገሮች የተካሄዱ የትጥቅ ትግሎችና የወንጀል ድርጊቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ለመጣ ፍርሃትና ዓመፅ መንገሥ ምክንያት ሆነዋል።
ታሪክ ምን ያረጋግጣል?
-
የናዚ አገዛዝ ስድስት ሚሊዮን የሚያክሉ አይሁዳውያንንና ሌሎች ሰዎችን ጨፍጭፏል። ዚግሙንት ባውማን የተባሉት ደራሲ ተራ ዜጎች የተሰማቸውን ስሜት ሲገልጹ እንዲህ ብለዋል፦ “ከጅምላ እልቂቱ በኋላ የቁጣና የተቃውሞ ድምፅ አልተሰማም፤ ይልቁንም ግዴለሽነት የሚንጸባረቅበት ዝምታ ሰፍኖ ነበር።”
-
ቢቢሲ የዜና አገልግሎት እንደዘገበው በጥቂት ወራት ውስጥ ብቻ ወደ 800,000 ገደማ የሚሆኑ ቱትሲዎችና አክራሪ ያልሆኑ ሁቱዎች ተገድለዋል። አንድ ተመራማሪ በጅምላ ጭፍጨፋው የተካፈሉት ሰዎች ቁጥር 200,000 እንደሚደርስ ገምተዋል።
-
በየዓመቱ 740,000 የሚያክሉ ሰዎች በወንጀልና በትጥቅ ትግል ምክንያት ይሞታሉ።
ትንቢት 6፦
“ሰዎች ራሳቸውን የሚወዱ፣ ገንዘብ የሚወዱ፣ . . . ተፈጥሯዊ ፍቅር የሌላቸው” ይሆናሉ።—2 ጢሞቴዎስ 3:2, 3
ፍጻሜ፦ ዘመናችን ስግብግብነትና ልቅ የሆነ ሥነ ምግባር የሞላበት ነው። እነዚህ ባሕርያት ለበርካታ ማኅበራዊ ችግሮች መንስኤ ሆነዋል።
ታሪክ ምን ያረጋግጣል?
-
ዩኒሴፍ ዩኬ ስለ ዩናይትድ ኪንግደም ሕፃናት ደኅንነት ያወጣው አንድ ሪፖርት ወላጆችና ልጆች “የመግዛት አባዜ የተጠናወታቸው ይመስላል” ብሏል። ቤተሰቦች “ከሌሎች ጋር ባላቸው ግንኙነት ላሉባቸው ችግሮችና ማኅበረሰቡ ለሚፈጠርባቸው ያለመተማመን ስሜት ማካካሻ እንዲሆን በማሰብ” ሸቀጦችን ይገዛሉ።
-
በዓለም ዙሪያ 275 ሚሊዮን ገደማ የሚሆኑ ሕፃናት በገዛ ቤታቸው ለሚፈጸም የኃይል ድርጊት የተጋለጡ ናቸው።
-
“በዩናይትድ ስቴትስ ብቻ በየዓመቱ ከ500,000 የሚበልጡ አረጋውያን በደል እንደሚፈጸምባቸው ወይም ችላ እንደሚባሉ ይታመናል።”—የዩናይትድ ስቴትስ የበሽታ መቆጣጠሪያና መከላከያ ማዕከል
ትንቢት 7፦
“ይህ የመንግሥቱ ምሥራች . . . በመላው ምድር ይሰበካል።”—ማቴዎስ 24:14
ፍጻሜ፦ የአምላክ መንግሥት ሰማይ ሆኖ ምድርን የሚገዛ እውን መስተዳድር እንደሆነና ንጉሡም ኢየሱስ እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ያስተምራል። በሰማይ የተቋቋመው ይህ መንግሥት “[ሰብዓዊ መንግሥታትን] ሁሉ ያደቃል፤ እስከ መጨረሻውም ያጠፋቸዋል፤ ይህ መንግሥት ራሱ ግን ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል።”—ዳንኤል 2:44
የይሖዋ ምሥክሮች በዓለም ዙሪያ የሚያስተምሩት ትምህርት ዋነኛ መልእክት የአምላክ መንግሥት ሲሆን ይህ ትምህርት የመንግሥቱን ምንነትና የሚያከናውናቸውን ነገሮች ይገልጻል።
ታሪክ ምን ያረጋግጣል?
-
በመላው ዓለም ከ230 በሚበልጡ አገሮች የሚገኙት ከሰባት ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ የይሖዋ ምሥክሮች ሰዎችን ስለ አምላክ መንግሥት ያስተምራሉ።
-
የይሖዋ ምሥክሮች በጽሑፎችና በኢንተርኔት አማካኝነት ከ500 በሚበልጡ ቋንቋዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎችን ያሰራጫሉ።
ምልክቱና የአንተ የወደፊት ሕይወት
በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ማስረጃዎቹን ከመረመሩ በኋላ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሰው የመጨረሻዎቹ ቀናት ምልክት በመፈጸም ላይ እንደሆነ መገንዘብ ችለዋል። በዚህ ጭብጥ ሥር በቀረቡት ስድስት ተከታታይ ርዕሶች ላይ መመልከት እንደተቻለው መጽሐፍ ቅዱስ በእርግጥም እንከን የማይገኝበት የትንቢት መጽሐፍ ነው።
መጽሐፍ ቅዱስ የወደፊቱን ጊዜ በተመለከተ የተናገራቸው ትንቢቶች ፍጻሜያቸውን እንደሚያገኙም መተማመን ትችላለህ። አምላክ እነዚህን አስጨናቂ የሆኑ የመጨረሻ ቀኖች ወደ ፍጻሜ እንደሚያመጣቸው ቃል ስለገባ እነዚህ ትንቢቶች በግለሰብ ደረጃ አንተንም የሚመለከቱ ናቸው። በዚህ ጭብጥ ሥር የሚወጡት የቀሩት ሁለት ተከታታይ ርዕሶች ‘የመጨረሻዎቹ ቀኖች’ ፍጻሜያቸውን ስለሚያገኙበት መንገድ እንዲሁም የሰው ልጆችና ምድር ስለሚጠብቃቸው አስደናቂ የወደፊት ጊዜ ይገልጻሉ።
^ አን.22 ዘ ሴንተር ፎር ሪሰርች ኦን ዚ ኤፒዲሚዮሎጂ ኦቭ ዲዛስተርስ የተባለው ስለ ተፈጥሮ አደጋዎች የሚያጠና የምርምር ማዕከል የምድር ነውጥ “አደጋ” ለሚለው አገላለጽ የሰጠው ፍቺ የሚከተለው ነው፦ አንድ የመሬት ነውጥ “አደጋ” ነው የሚባለው 10 ወይም ከዚያ በላይ ሰዎች የሞቱበት፣ 100 ወይም ከዚያ የሚበልጡ ሰዎች የተጎዱበት፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የታወጀበት ወይም ዓለም አቀፍ እርዳታ የተጠየቀበት ከሆነ ነው።