በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ድርብ የሱፍ ካፖርት የለበሰችው ላም

ድርብ የሱፍ ካፖርት የለበሰችው ላም

ግንባሯ ላይ ዘንፈል ያለው ፀጉሯና ቆልመም ያሉት ቀንዶቿ እንዲሁም ፈርጣማ ገላዋን እንደ ካፖርት የሸፈነው ጥቅጥቅ ያለ ፀጉር የደጋዋን ላም በቀላሉ ተለይታ እንድትታወቅ ያደርጓታል።

ጥንታዊ ዝርያ ካላቸው ከብቶች ተርታ የምትመደበው ፈርጣማዋ የደጋ ላም አስቸጋሪ የአየር ጠባይ ባላቸው የስኮትላንድ ደጋማ አካባቢዎችና ደሴቶች ላይ ለብዙ ዘመናት ስትኖር ቆይታለች። ከዚህ ቀደም ሁለት ዓይነት ዝርያዎች ነበሩ፤ ርቀው በሚገኙት ደጋማ አካባቢዎች የሚሠማሩት ከብቶች ተለቅ ያሉና ቀይ ፀጉር የነበራቸው ሲሆን ከምዕራባዊ የባሕር ዳርቻ ማዶ ካሉት ደሴቶች የመጡት ግን አነስ ያሉና አብዛኛውን ጊዜም ጥቁር ቀለም ያላቸው ነበሩ። በዛሬው ጊዜ ግን ሰዎች የደጋዋን ላም እንደ አንድ ዝርያ የሚቆጥሯት ሲሆን ቀለሟ ቀይ፣ ጥቁር፣ ነጣ ያለ ቡኒ አልፎ ተርፎም ቢጫና ነጭ ሊሆን ይችላል።

ላሟ ፊት ላይ ዘንፈል ብሎ የሚታየው አስቂኝ ፀጉር ብዙ ጥቅም አለው። በክረምት ከኃይለኛ ነፋስ፣ ከዝናብና ከበረዶ ፊቷን ይከላከልላታል። በበጋ ደግሞ ሊያቆስሏት ከሚችሉ በራሪ ነፍሳት ይጠብቃታል።

በጥንት ጊዜ ጭሰኞች፣ በመግቢያው በኩል ክፍት በሆነና ከዐለት በተሠራ በረት ውስጥ ከብቶቻቸውን ያሳድሩ ነበር። ይህን የሚያደርጉት ከብቶቻቸውን ከከባድ የአየር ንብረትና ከተኩላ ለመጠበቅ ነው።

አስደናቂ ካፖርት

የደጋዋን ላም ከሌሎች ከብቶች ልዩ የሚያደርጋት ድርብ ፀጉር ያላት መሆኑ ነው። ጥቅጥቅ ያለው የላይኛው ፀጉሯ አንዳንድ ጊዜ እስከ 33 ሴንቲ ሜትር ድረስ ሊያድግ ይችላል። የላይኛው ፀጉሯ ቅባትነት ስላለው ዝናብና በረዶ ሲመታት ተንሸራትቶ ይወርዳል እንጂ ወደ ውስጥ ዘልቆ አይገባም። ከሥር ያለው ለስላሳ ፀጉር ደግሞ የላሟ ሙቀት እንዲጠበቅ ያደርጋል።

ለብዙ ዓመታት የደጋ ላሞችን የተንከባከበው ጂም “ፀጉራቸውን በውኃ ማራስ ስለሚያስቸግር እነሱን በሳሙና ማጠብ በጣም ከባድ ነው!” በማለት ገልጿል። የደጋዋ ላም በፀጉር የተሸፈነች በመሆኗ ሌሎች የከብት ዝርያዎች ሊቋቋሙት በማይችሉት ቦታ ይኸውም ዶፍ ዝናብና የሚያቆራምድ ውርጭ በሚበዛበት ተራራማ አካባቢ ተመችቷት መኖርና መራባት ትችላለች።

በበጋ የአየሩ ጠባይ በጣም ሞቃትና ደረቅ ከሆነ፣ ከሁኔታው ጋር ራሷን ማስማማት የምትችለው የደጋዋ ላም ጥቅጥቅ ያለውን ፀጉሯን ታራግፋለች። ቅዝቃዜና እርጥበት ያዘለው የአየር ጠባይ ሲመጣ ደግሞ አዲስ ፀጉር ታበቅላለች።

ያላት ከፍተኛ ጥቅም

በጎች፣ ሥራ ሥሮችንና ቀንበጦችን ጠራርገው በመብላት ሣር ቅጠሉን የሚያጠፉ ሲሆን የደጋዋን ላም ጨምሮ ሌሎች ከብቶች ግን እንዲህ አያደርጉም። እንዲያውም የደጋዋ ላም በመጥፎ ሁኔታ ላይ ያለን የግጦሽ መሬት እንዲሻሻል ታደርጋለች። እንዴት? ረጅምና ኃይለኛ በሆኑት ቀንዶቿ እንዲሁም በሰፊው አፏ ተጠቅማ፣ ሌሎች የከብት ዝርያዎች ፈጽሞ የማይነኳቸውን የማይፈለጉ ቁጥቋጦዎች ታጸዳለች። ይህ ማጽዳት ሥራ ደግሞ ሣርና ዛፎች እንደገና እንዲያቆጠቁጡ ያደርጋል።

የደጋዋ ላም ያላት ድርብ ፀጉር ሌላም ትልቅ ጥቅም አለው። ሙቀት የሚሰጥ ተጨማሪ ስብ በሰውነቷ ውስጥ ስለማያስፈልጋት ከሌሎች የከብት ዝርያዎች ይልቅ የእሷ ሥጋ አነስተኛ የስብና የኮሌስትሮል ይዘት አለው፤ እንዲሁም ሥጋዋ በፕሮቲንና በብረት የበለጸገ ነው። በዚህ ላይ ደግሞ ይህን ምርጥ ሥጋ ለማግኘት በውድ ዋጋ መኖ መሸመት አያስፈልግም!

ጥንቃቄ የሚያሻው ጉዳይ

የደጋ ላሞች ከረጅም ጊዜ ጀምሮ ከሰዎች ጋር ተቀራርበው ሲኖሩ ቆይተዋል። የቀድሞዎቹ የስኮትላንድ ሕዝቦች ከብቶቹን በፎቅ ቤታቸው ምድር ቤት ውስጥ ያኖሯቸው ነበር። ከብቶቹ ከሥር መኖራቸው ቤተሰቡ የሚኖርበት የላይኛው ክፍል እንዳይቀዘቅዝ አስተዋጽኦ ያደርጋል።

አብዛኛውን ጊዜ ለማዳ ከብቶች ሰላማዊና በቀላሉ የሚታዘዙ ቢሆኑም የደጋ ከብቶች ግን አደገኛ የሚሆኑበት ጊዜ አለ። ለምሳሌ ያህል፣ የወለደች ላም ወደ ጥጃዋ ማንንም ላታስጠጋ ትችላለች። በተጨማሪም አንድ ሰው ወደ መንጋው ሲጠጋ ዙሪያውን መሄድ እንጂ ወደ መሃል መግባት አይኖርበትም።

የደጋዋ ላም ሁለገብ ባሕርይ በዓለም ዙሪያ ተወዳጅ የከብት ዝርያ እንድትሆን አድርጓታል። በሰሜን ከአላስካ እስከ ስካንዲኔቪያ አገሮች ድረስ ተስማምቷት የምትኖር ሲሆን 3,000 ሜትር ከፍታ ባላቸው የአንዴስ ተራሮች አካባቢም ሣር ስትግጥ ልትገኝ ትችላለች። ይህች ላም በሞቃት አካባቢዎችም ምንም ሳትቸገር መኖር ትችላለች።

ስኮትላንድ ታርታንና ኪልት በሚባሉት አልባሳት እንዲሁም ባግፓይፕ ተብሎ በሚጠራው ባለ ወናፍ ዋሽንት ብቻ ሳይሆን ውብ በሆኑትና በቀላሉ በሚታወቁት የደጋ ከብቶቿም ትታወቃለች። አንተ በምትኖርበት አካባቢ ድርብ የሱፍ ካፖርት የለበሱ ላሞች አሉ?