በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ነጋ ጠባ ስለ ተቃራኒ ፆታ ማሰቤን ማቆም የምችለው እንዴት ነው?

ነጋ ጠባ ስለ ተቃራኒ ፆታ ማሰቤን ማቆም የምችለው እንዴት ነው?

ምዕራፍ 29

ነጋ ጠባ ስለ ተቃራኒ ፆታ ማሰቤን ማቆም የምችለው እንዴት ነው?

“ሐሳቤ ሁሉ ስለ ሴት ብቻ ሆኗል፤ አጠገቤ ሴት የሚባል ባይኖርም እንኳ የማስበው ስለ እነሱ ነው” በማለት ሚካኤል የተባለ ወጣት ይናገራል። “በጣም ያናድዳል። አንዳንድ ጊዜ ሐሳቤን እንኳ መሰብሰብ ያቅተኛል!”

አንተም እንደ ሚካኤል ስለ ተቃራኒ ፆታ ከማሰብ ውጪ ሌላ ሥራ የለህም? ከሆነ ከሐሳብህ ጋር ጦርነት የገጠምክ ያህል ሆኖ ይሰማህ ይሆናል። ስለ ተቃራኒ ፆታ የሚመጡብህ ሐሳቦች ልክ እንደ ጠላት ወታደሮች በአእምሮህ ላይ ወረራ እንዳካሄዱ ሊሰማህ ይችላል። ሚካኤል “እንዲህ ያለው ሐሳብ አእምሮህን ሊቆጣጠረው ይችላል” በማለት ተናግሯል። “አንዲትን ቆንጆ ልጅ ለማየት ብለህ ያለ መንገድህ ዙሪያ ጥምጥም ልትሄድ ወይም በገበያ ቦታ አንዲትን ወጣት ጠጋ ብለህ ለማየት ስትል መሄድ በማያስፈልግህ አቅጣጫ ልትሄድ ትችላለህ።”

የፆታ ፍላጎት በራሱ መጥፎ ነገር እንዳልሆነ አስታውስ። ደግሞም አምላክ ወንድና ሴትን የፈጠራቸው በመካከላቸው ጠንካራ መሳሳብ እንዲኖር አድርጎ ነው፤ በመሆኑም በትዳር ውስጥ እስከሆነ ድረስ የፆታ ስሜትን ማርካት ምንም ስህተት የለውም። ይሁንና ለትዳር ባትደርስም ኃይለኛ የፆታ ስሜት ሊኖርህ ይችላል። እንደዚህ የሚሰማህ ከሆነ መጥፎ ሰው እንደሆንክ ወይም የሥነ ምግባር ንጽሕናህን መጠበቅ እንደማትችል አድርገህ አታስብ። ከፈለግህ የሥነ ምግባር ንጽሕናህን መጠበቅ ትችላለህ! በዚህ ረገድ እንዲሳካልህ ከፈለግህ ግን ተቃራኒ ፆታን በተመለከተ ወደ አእምሮህ የሚመጡትን ሐሳቦች መቆጣጠር ይኖርብሃል። ይህን ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው?

ከእነማን ጋር እንደምትውል አስብ። አብረውህ የሚማሩት ልጆች የብልግና ወሬ ማውራት ቢጀምሩ ከእነሱ ላለመለየት ስትል አንተም በጨዋታው ለመሳተፍ ትፈተን ይሆናል። ይሁንና እንዲህ ማድረግህ በአእምሮህ የሚመላለሱትን ሐሳቦች ለመቆጣጠር የምታደርገው ትግል ይበልጥ አስቸጋሪ እንዲሆንብህ ከማድረግ ውጪ የሚጠቅምህ ነገር የለም። ‘ታዲያ ምን ላድርግ? ትቻቸው ልሂድ?’ ብለህ ታስብ ይሆናል። አዎን፣ ትክክለኛው እርምጃ ይህ ነው፤ ደግሞም እንዲህ ማድረግህ ሊያሳፍርህ አይገባም! እንደተመጻደቅህ በማያስመስል መንገድ ወይም ለፌዝ የሚጋብዝ ነገር ሳታደርግ ትተሃቸው ልትሄድ ትችል ይሆናል።

የፆታ ብልግና ከሚንጸባረቅባቸው መዝናኛዎች ራቅ። እርግጥ ነው፣ ሁሉም ፊልምና ሙዚቃ መጥፎ ነው ማለት አይደለም። ያም ቢሆን በዛሬው ጊዜ ያለው አብዛኛው መዝናኛ ተገቢ ያልሆነ የፆታ ስሜትን ለማነሳሳት ታልሞ የተዘጋጀ ነው። ታዲያ መጽሐፍ ቅዱስ ምን ምክር ይሰጣል? “ሥጋንና መንፈስን ከሚያረክስ ነገር ሁሉ ራሳችንን እናንጻ፤ እንዲሁም አምላካዊ ፍርሃት በማሳየት ቅድስናችንን ፍጹም እናድርግ” ይላል። (2 ቆሮንቶስ 7:1) የብልግና ሐሳቦች ወደ አእምሮህ እንዲመጡ ሊያደርግ የሚችል ማንኛውም ዓይነት መዝናኛ ባለበት ላለመድረስ ጥረት አድርግ። *

የማስተርቤሽን ልማድ

አንዳንድ ወጣቶች የፆታ ስሜታቸው ሲቀሰቀስ እንዲህ ካለው ስሜት ለመገላገል ሲሉ ማስተርቤሽን (ስሜትን ለማርካት ብሎ የፆታ ብልትን የማሻሸት ልማድ) ይፈጽማሉ። ይሁንና ይህን ማድረግ ከባድ ችግሮች ያስከትላል። መጽሐፍ ቅዱስ ለክርስቲያኖች እንዲህ የሚል ማሳሰቢያ ይሰጣል፦ “በምድራዊ የአካል ክፍሎቻችሁ ውስጥ ያሉትን ዝንባሌዎች ግደሉ፤ እነሱም ዝሙት፣ ርኩሰት፣ የፆታ ምኞት፣ መጥፎ ፍላጎትና ጣዖት አምልኮ የሆነው መጎምጀት ናቸው።” (ቆላስይስ 3:5) ማስተርቤሽን የሚፈጽም ሰው ‘የፆታ ምኞቱን ገድሏል’ ማለት እንደማይቻል ምንም ጥያቄ የለውም። እንዲያውም ይህ ልማድ የፆታ ምኞትን የሚቀሰቅስና የሚያባብስ ነው!

ማስተርቤሽን ለምኞትህ ተገዢ እንድትሆን ሊያደርግህ ይችላል። (ቲቶ 3:3) ይህን ልማድ ለማሸነፍ ከሚረዱህ እርምጃዎች አንዱ ስለ ጉዳዩ የምታምነውን ሰው ማማከር ነው። ለብዙ ዓመታት ይህን ልማድ ለማሸነፍ ሲታገል የቆየ አንድ ክርስቲያን እንዲህ ብሏል፦ “ወጣት ሳለሁ ስለዚህ ጉዳይ ከአንድ ሰው ጋር ለመወያየት የሚያስችል ድፍረት በነበረኝ ኖሮ ብዬ ሁልጊዜ እቆጫለሁ! ለብዙ ዓመታት በጥፋተኝነት ስሜት ስሠቃይ የኖርኩ ከመሆኑም ሌላ ይህ ችግር ከሌሎች ጋር ያለኝን ግንኙነት ከሁሉ በላይ ደግሞ ከይሖዋ ጋር ያለኝን ዝምድና በእጅጉ ነክቶታል።”

ታዲያ ስለ ጉዳዩ ማንን ማማከር ትችላለህ? ይበልጥ ምክንያታዊ የሚሆነው ወላጆችህን ብታማክር ነው። አሊያም ደግሞ አንድ የጎለመሰ ክርስቲያን ሊረዳህ ይችላል። እንዲህ ብለህ መጀመር ትችላለህ፦ “በጣም ስላስጨነቀኝ አንድ ችግር ላወያይህ ፈልጌ ነበር።”

አንድሬ ለአንድ ክርስቲያን ሽማግሌ ችግሩን ያወያየው ሲሆን እንዲህ በማድረጉም ተደስቷል። እንዲህ ብሏል፦ “ሐሳቤን በምናገርበት ጊዜ ሽማግሌው ዓይኑ እንባ አቀረረ። አውርቼ እስክጨርስ ዝም ብሎ ካዳመጠኝ በኋላ ይሖዋ እንደሚወደኝ በመግለጽ አበረታታኝ። እንዲህ ያለ ችግር ያለብኝ እኔ ብቻ እንዳልሆንኩ ነገረኝ። የማደርገውን ለውጥ እንደሚከታተልና ይህን ጉዳይ በተመለከተ ከመጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች ላይ ተጨማሪ መረጃዎችን እንደሚያመጣልኝ ቃል ገባልኝ። ከእሱ ጋር መነጋገሬ ችግሩ በሌላ ጊዜ ቢያገረሽብኝ እንኳ በማደርገው ትግል ለመቀጠል እንድቆርጥ አድርጎኛል።”

ማርዮ ደግሞ አባቱን ያነጋገረ ሲሆን አባቱም ስሜቱንና ችግሩን በሚገባ ተረዳለት። እንዲያውም እሱ ራሱ ወጣት ሳለ ይህንን ልማድ ለማሸነፍ መታገል አስፈልጎት እንደነበረ ለማርዮ ገለጸለት። ማርዮ እንዲህ በማለት ይናገራል፦ “አባቴ ግልጽ መሆኑና ሊረዳኝ ከልቡ መፈለጉ በጣም አበረታታኝ። እሱ ይህን ልማድ ማሸነፍ ከቻለ እኔም የማልችልበት ምክንያት የለም ብዬ አሰብኩ። የአባቴ ሁኔታ ልቤን ስለነካው ስሜቴን መቆጣጠር አቅቶኝ አለቀስኩ።”

እንደ አንድሬና ማርዮ አንተም ብትሆን የማስተርቤሽንን ልማድ ለማሸነፍ በምታደርገው ጥረት እርዳታ ማግኘት ትችላለህ። ይህ ልማድ ቢያገረሽብህም እንኳ የምታደርገውን ጥረት አታቋርጥ! በትግሉ ማሸነፍ እንደምትችል እርግጠኛ ሁን! *

ሐሳብህን መቆጣጠር

ሐዋርያው ጳውሎስ “ሰውነቴን እየጎሰምኩ እንደ ባሪያ እንዲገዛልኝ አደርገዋለሁ” ብሏል። (1 ቆሮንቶስ 9:27) አንተም ከተቃራኒ ፆታ ጋር በተያያዘ ተገቢ ያልሆኑ ሐሳቦች ወደ አእምሮህ እየመጡ የሚያስቸግሩህ ከሆነ እነዚህን ሐሳቦች ላለማስተናገድ ቆራጥ መሆን ይኖርብሃል። እነዚህን ሐሳቦች ከአእምሮህ ማውጣት ካስቸገረህ ስፖርታዊ እንቅስቃሴ አድርግ። መጽሐፍ ቅዱስ “የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በጥቂቱ ይጠቅማል” ይላል። (1 ጢሞቴዎስ 4:8) ወደ አእምሮህ እየመጡ የሚረብሹህን ሐሳቦች ለማባረር የእግር ጉዞ ማድረግ ወይም ለጥቂት ደቂቃዎች ስፖርት መሥራት ብቻ በቂ ሊሆን ይችላል።

ከሁሉ በላይ ደግሞ በሰማይ ያለው አባትህ ሊሰጥህ የሚችለውን እርዳታ አቅልለህ አትመልከተው። አንድ ክርስቲያን “የፆታ ስሜቴ ሲቀሰቀስብኝ አጥብቄ እጸልያለሁ” በማለት ተናግሯል። በእርግጥ አምላክ ለተቃራኒ ፆታ ያለህን ስሜት እንደማያጠፋው የታወቀ ነው። ሆኖም ልታስባቸው የምትችላቸው ሌሎች ብዙ ነገሮች መኖራቸውን እንድትገነዘብ ሊረዳህ ይችላል።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.7 መዝናኛንና ጊዜ ማሳለፊያዎችን በተመለከተ ክፍል 8 ሰፋ ያለ ማብራሪያ ይዟል።

^ አን.14 ስለ ማስተርቤሽን ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት የዚህን መጽሐፍ ጥራዝ 1 ምዕራፍ 25

ቁልፍ ጥቅስ

“በጎ የሆነውን ሁሉና ምስጋና የሚገባውን ነገር ሁሉ ማሰባችሁን አታቋርጡ።”​—ፊልጵስዩስ 4:8

ጠቃሚ ምክር

የማስተርቤሽን ልማድህ ቢያገረሽብህም የምታደርገውን ትግል አታቋርጥ! ይህ ልማድ እንዲያገረሽብህ ያደረገህ ምን እንደሆነ ለማወቅና ተመሳሳይ ስህተት ላለመፈጸም ጥረት አድርግ።

ይህን ታውቅ ነበር?

በአእምሮህ የምታውጠነጥነው ነገር በማንነትህና በድርጊትህ ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል።​—ያዕቆብ 1:14, 15

ላደርጋቸው ያሰብኳቸው ነገሮች

ስለ ተቃራኒ ፆታ ማሰቤን ለማቆም እንዲህ አደርጋለሁ፦ ․․․․․

አብረውኝ የሚማሩ ልጆች የብልግና ወሬ ማውራት ከጀመሩ እንዲህ አደርጋለሁ፦ ․․․․․

ከዚህ ርዕሰ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ወላጆቼን ልጠይቃቸው የምፈልገው ነገር ․․․․․

ምን ይመስልሃል?

● የፆታ ስሜት ሁልጊዜ መጥፎ ነገር እንደሆነ ተደርጎ መታየት የሌለበት ለምንድን ነው?

● የፆታ ስሜትህን መቆጣጠር የሚያስፈልግህ ለምንድን ነው?

● ሁልጊዜ ስለ ተቃራኒ ፆታ እንድታስብ ሊያደርግህ የሚችለው ምን ዓይነት መዝናኛ ነው?

● የብልግና ወሬ ሲነሳ አካባቢውን ትተህ መሄድ የሚያስፈልግህ ለምንድን ነው?

[በገጽ 240 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

እኔን የረዳኝ ስለ ሌላ ነገር ለማሰብ መሞከሬና ስሜቴ እንዲቀሰቀስ በሚያደርጉት ነገሮች ላይ ላለማውጠንጠን ጥረት ማድረጌ ነው። ይህ ስሜት ወይም ፍላጎት ቀስ በቀስ ሊጠፋ እንደሚችል ራሴን አሳምነዋለሁ።”​—ስኮት

[በገጽ 239 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ምግብህ ውስጥ መርዝ ሲጨመር ዝም ብለህ ትመለከታለህ? ታዲያ ብልግና ያለባቸው መዝናኛዎችስ አእምሮህን እንዲመርዙት ለምን ትፈቅዳለህ?