በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በድብቅ የፍቅር ጓደኝነት ብጀምር ምን ችግር አለው?

በድብቅ የፍቅር ጓደኝነት ብጀምር ምን ችግር አለው?

ምዕራፍ 2

በድብቅ የፍቅር ጓደኝነት ብጀምር ምን ችግር አለው?

ጄሲካ አጣብቂኝ ውስጥ ገብታ ነበር። ችግሩ የጀመረው ጄረሚ የተባለ የክፍሏ ልጅ ዓይኑን እንደጣለባት ባወቀችበት ጊዜ ነበር። ጄሲካ እንዲህ ብላለች፦ “በጣም ቆንጆ ልጅ ነው፤ በዚያ ላይ ጓደኞቼ በጣም ጨዋ ልጅ እንደሆነና እንደ እሱ ያለ ጓደኛ እንደማላገኝ ይነግሩኝ ነበር። ብዙ ወጣቶች ከእሱ ጋር የፍቅር ጓደኝነት ለመጀመር የሞከሩ ቢሆንም እሱ ግን አንዳቸውንም አልፈለጋቸውም። እሱ የወደደው እኔን ብቻ ነበር።”

ብዙም ሳይቆይ ጄረሚ የፍቅር ጓደኛው እንድትሆን ጄሲካን ጠየቃት። ጄሲካም የይሖዋ ምሥክር ስለሆነች የእሷ እምነት ተከታይ ካልሆነ ሰው ጋር የፍቅር ጓደኝነት መመሥረት እንደማይፈቀድላት ነገረችው። “ጄረሚ ግን ‘ለምን ወላጆችሽ ሳያውቁ አንጀምርም?’ የሚል ሐሳብ አቀረበልኝ” በማለት ተናግራለች።

አንተስ ዓይንህን የጣልክባት አንዲት ወጣት እንዲህ ዓይነት ሐሳብ ብታቀርብልህ ምን ምላሽ ትሰጣለህ? ጄሲካ በጄረሚ ሐሳብ እንደተስማማች ስታውቅ ትገረም ይሆናል። ጄሲካ “ከእሱ ጋር የፍቅር ጓደኝነት ከመሠረትኩ ይሖዋን እንዲወድ ልረዳው እንደምችል ተሰምቶኝ ነበር” ብላለች። ታዲያ መጨረሻቸው ምን ሆነ? ይህን በኋላ ላይ እንመለስበታለን። በመጀመሪያ ግን አንዳንዶች እንዲህ ባለ ወጥመድ ውስጥ የሚወድቁት እንዴት እንደሆነ እስቲ እንመልከት።

እንዲህ የሚያደርጉት ለምንድን ነው?

አንዳንዶች በድብቅ የፍቅር ጓደኝነት የሚመሠርቱት ለምንድን ነው? ዴቪድ የተባለ አንድ ወጣት “ወላጆቻቸው እንደማይፈቅዱላቸው ስለሚያውቁ አይነግሯቸውም” በማለት ምክንያቱን በአጭሩ አስቀምጦታል። ጄን ደግሞ እንዲህ በማለት ሌላኛውን ምክንያት ጠቅሳለች፦ “በድብቅ የፍቅር ጓደኝነት መመሥረት በራስህ ለመመራት እንደምትፈልግ የምትገልጽበት አንዱ መንገድ ነው። አንተ ትልቅ ሰው እንደሆንክ ብታስብም ወላጆችህ እንደዚያ አድርገው እንደማይመለከቱህ ከተሰማህ ለእነሱ ሳትነግራቸው የፈለግኸውን ነገር ለማድረግ ትወስናለህ።”

አንተስ አንዳንዶች በድብቅ የፍቅር ጓደኝነት ለመጀመር እንዲነሳሱ የሚያደርጓቸውን ሌሎች ምክንያቶች መጥቀስ ትችላለህ? ያሰብካቸውን ምክንያቶች ከዚህ በታች አስፍራቸው።

․․․․․

መጽሐፍ ቅዱስ ለወላጆችህ መታዘዝ እንዳለብህ የሚሰጠውን መመሪያ እንደምታውቅ ግልጽ ነው። (ኤፌሶን 6:1) ወላጆችህ የፍቅር ጓደኝነት መጀመርህ ተገቢ እንዳልሆነ የሚሰማቸው ከሆነ እንዲህ ያሉበት በቂ ምክንያት መኖር አለበት። ሆኖም እንደሚከተሉት ያሉ ሐሳቦች ወደ አእምሮህ ቢመጡ ሊገርምህ አይገባም፦

 ከእኔ በቀር ሁሉም የፍቅር ጓደኛ ስላላቸው የቀረብኝ ነገር እንዳለ ይሰማኛል።

የእኔ እምነት ተከታይ ካልሆነች ወጣት ጋር ፍቅር ይዞኛል።

ለማግባት ዕድሜዬ ገና ቢሆንም ከአንዲት ክርስቲያን ጋር የፍቅር ጓደኝነት መጀመር እፈልጋለሁ።

ወላጆችህ እንዲህ እንደምታስብ ቢያውቁ ምን እንደሚሉህ ታውቅ ይሆናል። ደግሞም ወላጆችህ ትክክል እንደሆኑ ልብህ ያውቀዋል። ያም ሆኖ ግን ማናሚ እንደተባለችው ወጣት ይሰማህ ይሆናል፦ “የፍቅር ጓደኝነት እንድመሠርት የሚደረግብኝ ግፊት በጣም ከባድ ከመሆኑ የተነሳ እንዲህ ዓይነቱን ግንኙነት ላለመጀመር የወሰድኩት አቋም ትክክል መሆኑን የምጠራጠርበት ጊዜ አለ። በዛሬው ጊዜ ያሉ ወጣቶች የፍቅር ጓደኛ አለመያዝ የማይታሰብ ነገር እንደሆነ ይሰማቸዋል። በዚያ ላይ ደግሞ የፍቅር ጓደኛ ሳይኖረኝ ብቻዬን መታየት ደስ የሚል ነገር አይደለም!” እንዲህ የሚሰማቸው አንዳንድ ወጣቶች ከወላጆቻቸው ተደብቀው የፍቅር ጓደኝነት ጀምረዋል። እንዴት?

“ለማንም እንዳንናገርባቸው ነገሩን”

“በድብቅ የፍቅር ጓደኝነት መጀመር” የሚለው ሐሳብ በራሱ ይህ ድርጊት በተወሰነ መጠንም ቢሆን ማታለል እንዳለበት ይጠቁማል፤ ደግሞም ግንኙነቱ ድብቅ እንዲሆን ስትሉ አንዳንድ ጊዜ መዋሸታችሁ አይቀርም። አንዳንዶች የመሠረቱት የፍቅር ጓደኝነት እንዳይታወቅባቸው ሲሉ በዋነኝነት የሚገናኙት በስልክ ወይም በኢንተርኔት አማካኝነት ነው። ሰዎች ፊት ሲሆኑ ተራ ጓደኛሞች ይመስላሉ፤ በኢንተርኔትና በሞባይል ስልክ አማካኝነት የሚለዋወጡት መልእክት ቢታይ እንዲሁም በስልክ የሚያወሩት ነገር ቢሰማ ግን ታሪኩ ሌላ ነው።

የፍቅር ጓደኝነት የጀመሩ ወጣቶች ግንኙነታቸው እንዳይታወቅባቸው የሚጠቀሙበት ሌላው ዘዴ ደግሞ ከጓደኞቻቸው ጋር በቡድን ሆነው ለመገናኘት ፕሮግራም ማዘጋጀት ነው፤ ይህን የሚያደርጉት ግን ከሌሎቹ ገንጠል ብለው ለማውራት እንዲያመቻቸው ሲሉ ነው። ጄምስ እንዲህ ብሏል፦ “በአንድ ወቅት የተወሰንን ወጣቶች በአንድ ዝግጅት ላይ እንድንገኝ ተጋብዘን ነበር፤ በኋላ ላይ እንደገባኝ ግን ለካስ ዝግጅቱ የተደረገው ከመካከላችን ሁለቱ አብረው የሚሆኑበትን አጋጣሚ ለማመቻቸት ነበር። ከዚያም ለማንም እንዳንናገርባቸው ነገሩን።”

ጄምስ እንደተናገረው በድብቅ የፍቅር ጓደኝነት የጀመሩ ወጣቶች መገናኘት እንዲችሉ አብዛኛውን ጊዜ ጓደኞቻቸው ይተባበሯቸዋል። ካሮል “ብዙውን ጊዜ፣ ቢያንስ ከጓደኞቻቸው አንዱ ስለ ጉዳዩ ያውቃል፤ ሆኖም ቢናገር ጓደኛው እንደሚቀየመው ስለሚያውቅ ዝምታን ይመርጣል” ብላለች። እንዲያውም በድብቅ የፍቅር ጓደኝነት የጀመሩ ወጣቶች አንዳንዴ ዓይን ያወጣ ውሸት ይናገራሉ። ቤዝ የተባለች የ17 ዓመት ወጣት “ብዙዎች የፍቅር ጓደኝነት መጀመራቸው እንዳይታወቅባቸው ሲሉ የት እንደሚሄዱ ወላጆቻቸው ሲጠይቋቸው ይዋሻሉ” ብላለች። የ19 ዓመቷ ሚሳኪ ተመሳሳይ ነገር ታደርግ ነበር፤ እንዲህ ብላለች፦ “የሌለ ታሪክ በመፍጠር ለመሸወድ እሞክር ነበር። ሆኖም የወላጆቼን አመኔታ ላለማጣት ስል፣ ከጀመርኩት የፍቅር ጓደኝነት ጋር የተያያዘ ካልሆነ በቀር ሌላ ምንም ዓይነት ውሸት ላለመናገር እጠነቀቅ ነበር።”

በድብቅ የፍቅር ጓደኝነት መመሥረት የሚያስከትላቸው ችግሮች

በድብቅ የፍቅር ጓደኝነት የመጀመር ፍላጎት ካለህ አሊያም በአሁኑ ወቅት እንዲህ እያደረግህ ከሆነ የሚከተሉትን ሁለት ጥያቄዎች ራስህን መጠየቅ ያስፈልግሃል፦

ይህ አካሄዴ ወዴት ይመራኛል? የወደድካትን ወጣት በቅርቡ የማግባት ሐሳብ አለህ? ኢቫን የተባለ የ20 ዓመት ወጣት “የማግባት እቅድ ሳይኖራችሁ የፍቅር ጓደኝነት መመሥረት የማትሸጡትን ዕቃ የማስተዋወቅ ያህል ነው” በማለት ተናግሯል። እንዲህ ማድረግ ምን ያስከትላል? ምሳሌ 13:12 (የ1954 ትርጉም) “የምትዘገይ ተስፋ ልብን ታሳዝናለች” ይላል። የምትወዳትን ወጣት ልብ ማሳዘን ትፈልጋለህ? ልታስብበት የሚገባው ሌላው ነጥብ ደግሞ በድብቅ የፍቅር ጓደኝነት መጀመርህ ወላጆችህና ስለ አንተ የሚያስቡ ሌሎች ትልልቅ ሰዎች ሊሰጡህ ይችሉ የነበረውን ጠቃሚ ምክር የሚያሳጣህ መሆኑ ነው። በዚህም የተነሳ የፆታ ብልግና ለመፈጸም ትጋለጥ ይሆናል።​—ገላትያ 6:7

ይሖዋ አምላክ ስለ ድርጊቴ ምን ይሰማዋል? መጽሐፍ ቅዱስ “ተጠያቂዎች በሆንበት በእሱ ዓይኖች ፊት ሁሉም ነገር የተራቆተና ገሃድ የወጣ ነው” ይላል። (ዕብራውያን 4:13) አንተ ወይም አንድ ጓደኛህ በድብቅ የፍቅር ጓደኝነት ጀምራችሁ ይሆናል፤ ይህንን ሌሎች እንዳያውቁ የምትሸፋፍን ከሆነ ቀድሞውንም ቢሆን ይሖዋ ጉዳዩን እንደሚያውቀው ማስታወስ ይኖርብሃል። የምትዋሽ ከሆነ ደግሞ ነገሩ ሊያሳስብህ ይገባል። ምክንያቱም ይሖዋ አምላክ ውሸትን አጥብቆ ይጠላል። ይሖዋ እንደሚጸየፋቸው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከተዘረዘሩት ነገሮች መካከል በዋነኝነት የተጠቀሰው “ሐሰተኛ ምላስ” ነው!​—ምሳሌ 6:16-19

ድብብቆሹን ማቆም

በድብቅ የፍቅር ጓደኝነት ጀምረህ ከሆነ ጉዳዩን በተመለከተ ከወላጆችህ ወይም ከአንድ የጎለመሰ ክርስቲያን ጋር መነጋገርህ የጥበብ እርምጃ እንደሆነ ጥርጥር የለውም። በድብቅ የፍቅር ጓደኝነት የጀመረ ጓደኛ ካለህ ድርጊቱን ለመሸፋፈን በመሞከር ከእሱ ጋር መተባበር የለብህም። (1 ጢሞቴዎስ 5:22) ደግሞስ የጓደኛህ አካሄድ ጎጂ ውጤቶችን ቢያስከትል ምን ይሰማሃል? በተወሰነ መጠንም ቢሆን ተጠያቂ የምትሆን አይመስልህም?

ነጥቡን በምሳሌ ለማስረዳት፣ የስኳር በሽታ እያለበት ጣፋጭ ምግቦችን በድብቅ የሚበላ አንድ ጓደኛ አለህ እንበል። ስለ ሁኔታው ብታውቅና ጓደኛህ ለማንም እንዳትናገርበት ቢለምንህ ምን ታደርጋለህ? ይበልጥ የሚያሳስብህ የጓደኛህን ሚስጥር መጠበቅህ ነው ወይስ ሕይወቱን ለማዳን እርምጃ መውሰድህ?

አንድ ጓደኛህ በድብቅ የፍቅር ግንኙነት እንደጀመረ የምታውቅ ከሆነም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። ‘ብናገር ጓደኝነታችን ያከትማል’ የሚል ስጋት ሊያድርብህ አይገባም! ይዋል ይደር እንጂ እውነተኛ ጓደኛ ይህን ያደረግኸው ለእሱ ጥቅም ብለህ መሆኑን መገንዘቡ አይቀርም።​—መዝሙር 141:5

በሚስጥር መያዝ ሁልጊዜ ስህተት ነው?

የፍቅር ጓደኝነትን በሚስጥር መያዝ ሁልጊዜ ስህተት ነው ማለት አይደለም። ለምሳሌ፣ አንድ ወንድና አንዲት ሴት ለመጠናናት ፈለጉ እንበል፤ ሆኖም ጉዳዩን ለጊዜው ብዙ ሰው እንዲያውቀው አልፈለጉም። ቶማስ የተባለ አንድ ወጣት እንደተናገረው ይህን ያደረጉት “ሰዎች ‘መቼ ነው የምትጋቡት?’ እንደሚሉት ያሉ ጥያቄዎችን በማንሳት እንዳያሸማቅቋቸው ፈርተው ሊሆን ይችላል።”

በእርግጥም ሌሎች ተገቢ ያልሆነ ግፊት ማድረጋቸው ጎጂ ውጤት ሊኖረው ይችላል። (ማሕልየ መሓልይ 2:7) በመሆኑም አንዳንድ ጥንዶች ጓደኝነት እንደጀመሩ ጉዳዩን ብዙ ሰው እንዲያውቀው አለማድረጉ የጥበብ እርምጃ እንደሆነ ይሰማቸው ይሆናል። (ምሳሌ 10:19) የ20 ዓመቷ አና እንዲህ ብላለች፦ “እንደዚህ ማድረጋቸው ሁለቱ ሰዎች ዘላቂ የሆነ ጥምረት መመሥረት ይችሉ እንደሆነ አስበውበት ለመወሰን ጊዜ ይሰጣቸዋል። እንዲህ ዓይነት ውሳኔ ላይ ከደረሱ ያን ጊዜ ጉዳዩን ለሰዎች ማሳወቅ ይችላሉ።”

በሌላ በኩል ግን የፍቅር ጓደኝነት ስትጀምር ስለ ግንኙነታችሁ ማወቅ ከሚገባቸው ሰዎች ለምሳሌ ከወላጆችህ ወይም ከእሷ ወላጆች ጉዳዩን መደበቅ ስህተት ይሆናል። የፍቅር ጓደኝነት መጀመርህን ለወላጆችህ በግልጽ መናገር ከከበደህ ምክንያትህ ምን እንደሆነ ራስህን መጠየቅ ይገባሃል። መናገር የከበደህ ወላጆችህ ምርጫህን የሚቃወሙበት በቂ ምክንያት እንደሚኖራቸው ስለምታውቅ ይሆን?

“ምን ማድረግ እንዳለብኝ አወቅሁ”

መግቢያው ላይ የተጠቀሰችው ጄሲካ ከእሷ ጋር የሚመሳሰል ሁኔታ ያጋጠማትን የአንዲት ክርስቲያን ተሞክሮ ስትሰማ ከጄረሚ ጋር በድብቅ የጀመረችውን የፍቅር ግንኙነት ለማቆም ወሰነች። ጄሲካ “ያቺ እህት ግንኙነቷን እንዴት እንዳቆመች ስሰማ እኔም ምን ማድረግ እንዳለብኝ አወቅሁ” ብላለች። ጄሲካ ከጄረሚ ጋር ያላትን ግንኙነት ማቋረጥ ቀላል ሆኖላት ነበር? አልሆነላትም! “በሕይወቴ የወደድኩት እሱን ብቻ ነበር፤ ለበርካታ ሳምንታት ሥራዬ ማልቀስ ብቻ ሆኖ ነበር” ብላለች።

ይሁንና ጄሲካ ይሖዋን ትወዳለች። ለተወሰነ ጊዜ የተሳሳተ ጎዳና ተከትላ የነበረ ቢሆንም እንኳ ትክክል የሆነውን ነገር ለማድረግ ከልቧ ትፈልጋለች። ግንኙነቱን ማቋረጧ ያስከተለባት ሥቃይ እያደር እየቀነሰ ሄደ። ጄሲካ “አሁን ከይሖዋ ጋር ያለኝ ግንኙነት ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ የተሻለ ነው። ይሖዋ የሚያስፈልገንን መመሪያ በትክክለኛው ወቅት ስለሚሰጠን በጣም አመስጋኝ ነኝ!” በማለት ተናግራለች።

በሚቀጥለው ምዕራፍ

የፍቅር ጓደኝነት ለመጀመር ደርሰህ ብሎም የምትወዳት ወጣት አግኝተህ ይሆናል፤ ይሁንና አንተም ሆንክ እሷ አንዳችሁ ለሌላው ትሆኑ እንደሆነና እንዳልሆነ ማወቅ የምትችሉት እንዴት ነው?

ቁልፍ ጥቅስ

‘በሁሉም ነገር በሐቀኝነት ለመኖር እንመኛለን።’​—ዕብራውያን 13:18

ጠቃሚ ምክር

የፍቅር ጓደኝነት መጀመርህን አገር እንዲያውቅልህ ማድረግ አያስፈልግህም። ይሁንና ማወቅ ለሚገባቸው ሰዎች መናገር ይኖርብሃል። አብዛኛውን ጊዜ የአንተም ሆኑ የእሷ ወላጆች ጉዳዩን ማወቅ ይኖርባቸዋል።

ይህን ታውቅ ነበር?

የፍቅር ግንኙነት ዘላቂ እንዲሆን በመተማመን ላይ የተመሠረተ ሊሆን ይገባል። በድብቅ የፍቅር ጓደኝነት መጀመር የወላጆችህን አመኔታ የሚያሳጣህ ከመሆኑም ሌላ ከፍቅር ጓደኛህ ጋር ያለህ ግንኙነት ጠንካራ መሠረት እንዳይኖረው ያደርጋል።

ላደርጋቸው ያሰብኳቸው ነገሮች

የእምነት ባልንጀራዬ ከሆነች አንዲት ክርስቲያን ጋር በድብቅ የፍቅር ጓደኝነት ጀምሬ ከሆነ እንዲህ አደርጋለሁ፦ ․․․․․

አንድ ጓደኛዬ በድብቅ የፍቅር ግንኙነት ጀምሮ ከሆነ እንዲህ አደርጋለሁ፦ ․․․․․

ከዚህ ርዕሰ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ወላጆቼን ልጠይቃቸው የምፈልገው ነገር ․․․․․

ምን ይመስልሃል?

 በገጽ 22 ላይ ደመቅ ብለው የተጻፉትን ሦስት ነጥቦች መለስ ብለህ ተመልከት። አንተስ አንዳንድ ጊዜ እንደዚያ ይሰማሃል? ከሆነ የአንተን ስሜት የሚያንጸባርቀው የትኛው ነው?

● በድብቅ የፍቅር ጓደኝነት ሳትጀምር ለዚህ ሁኔታ መፍትሔ ማግኘት የምትችለው እንዴት ነው?

● አንድ ጓደኛህ በድብቅ የፍቅር ጓደኝነት እንደጀመረ ብታውቅ ምን ታደርጋለህ? እንዲህ የምታደርገው ለምንድን ነው?

[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

በድብቅ የጀመርኩትን የፍቅር ጓደኝነት አቆምኩ። በእርግጥ በየቀኑ ትምህርት ቤት ልጁን ሳየው ውስጤ ይረበሽ ነበር። ይሁን እንጂ ይሖዋ አምላክ ሁሉንም ነገር ማወቅ የሚችል ሲሆን እኛ ግን እንዲህ ማድረግ አንችልም። ከእኛ የሚፈለገው በይሖዋ መታመን ብቻ ነው።”​—ጄሲካ

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አንድ ጓደኛህ በድብቅ የጀመረው የፍቅር ግንኙነት እንዳይታወቅበት መሸፋፈንህ የስኳር በሽታ እያለበት ጣፋጭ ምግቦችን በድብቅ ለሚበላ ጓደኛህ ከመሸፋፈን ተለይቶ አይታይም