ከአንደኛው ወላጄ ጋር ብቻ እየኖርኩ ደስተኛ መሆን እችላለሁ?
ምዕራፍ 25
ከአንደኛው ወላጄ ጋር ብቻ እየኖርኩ ደስተኛ መሆን እችላለሁ?
“ከሁለቱም ወላጆቻቸው ጋር የሚኖሩ ልጆች የራሳቸው መኝታ ክፍል ሊኖራቸው እንዲሁም አዳዲስ ልብስ ሊገዛላቸው ይችላል። እኔ ግን የራሴ ክፍል የለኝም፤ የምፈልገው ዓይነት ልብስ የሚገዛልኝም ከስንት አንዴ ነው። እማዬ የወደድኩትን ልብስ እንድትገዛልኝ ስጠይቃት አቅሟ እንደማይፈቅድ ትነግረኛለች። እሷ ሥራ ስትውል ቤት ውስጥ ብዙ ስለምሠራ የቤት ሠራተኛ እንደሆንኩና የልጅነት ጊዜዬ እያለፈብኝ እንደሆነ ይሰማኛል።”—ሻሎንዳ፣ 13
ልጆች ከሁለቱም ወላጆቻቸው ጋር መኖራቸው ተመራጭ እንደሆነ ምንም ጥርጥር የለውም። አባትና እናት አንድ ላይ ሲሆኑ አብዛኛውን ጊዜ ለልጆቻቸው የተሻለ መመሪያና ድጋፍ ሊሰጧቸው እንዲሁም ጥበቃ ሊያደርጉላቸው ይችላሉ። መክብብ 4:9
መጽሐፍ ቅዱስ “ለሥራቸው መልካም ውጤት ስለሚያገኙ፣ ከአንድ፣ ሁለት መሆን ይሻላል” ይላል።—ከላይ የተገለጸው እውነት መሆኑ አይካድም፤ ያም ሆኖ ሁለቱም ወላጆች አብረው የሚኖሩባቸው ቤተሰቦች ቁጥር በጣም እየተመናመነ ከመምጣቱ የተነሳ እነዚህ ቤተሰቦች፣ ዝርያቸው ሊጠፋ የተቃረበ እንስሳት ዝርዝር ውስጥ ከገባ አንድ እንስሳ ጋር ሊመሳሰሉ ይችላሉ። ለምሳሌ ያህል፣ በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ከሚኖሩ ልጆች መካከል ከግማሽ በላይ የሚሆኑት 18 ዓመት እስከሚሆናቸው ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ ለተወሰነ ጊዜም ቢሆን ከአንደኛው ወላጃቸው ጋር ብቻ የሚኖሩበት ወቅት አለ።
በአንድ ወላጅ ብቻ ማደግ እየተለመደ የመጣ ነገር ቢሆንም እንደዚህ ባለ ቤተሰብ ውስጥ የሚኖሩ አንዳንድ ወጣቶች ያሉበት ሁኔታ ያሸማቅቃቸዋል። ሌሎች ደግሞ በሕይወታቸው ውስጥ የሚያጋጥማቸው ችግርና የሚደርስባቸው ጫና ከአቅማቸው በላይ እንደሆነ ይሰማቸዋል። የምትኖረው በአንድ ወላጅ ብቻ በሚተዳደር ቤተሰብ ውስጥ ነው? ከሆነ ምን ዓይነት ችግሮች ያጋጥሙሃል? በጣም የሚያስጨንቅህን ችግር ከታች ባለው መስመር ላይ ጻፍ።
․․․․․
የአንደኛውን ወላጅህን ፍቅርና እንክብካቤ ሁልጊዜ ስለማታገኝ በሕይወትህ ደስተኛ መሆን አትችልም ማለት ነው? በፍጹም! ደስተኛ መሆንህ በአብዛኛው የተመካው በአመለካከትህ ላይ ነው። ምሳሌ 15:15 (የ1954 ትርጉም) “ልቡ የሚያዝን ሰው ዘመኑ ሁሉ የከፋች ናት፤ የልብ ደስታ ግን ሁልጊዜ እንደ ግብዣ ነው” ይላል። ይህ ምሳሌ እንደሚጠቁመው አብዛኛውን ጊዜ አንድ ሰው ደስተኛ መሆን አለመሆኑን የሚወስነው ያለበት ሁኔታ ሳይሆን አመለካከቱ ነው። ታዲያ ያለህበት ሁኔታ ምንም ይሁን ምን “የልብ ደስታ” ለማግኘት ምን ማድረግ ትችላለህ?
አሉታዊ ስሜቶችን ተዋጋ
በመጀመሪያ፣ ሌሎች በሚሰነዝሩት አሳቢነት የጎደለው አስተያየት ላለመጎዳት ጥረት አድርግ። ለምሳሌ ያህል፣ አንዳንድ አስተማሪዎች በአንድ ወላጅ በሚተዳደር ቤተሰብ ውስጥ የሚኖሩ ተማሪዎችን ስሜት የሚጎዳ ነገር በግልጽ ሲናገሩ ይታያል። እንዲያውም አንዳንዶች በእነዚህ ልጆች ላይ የሚታየው ማንኛውም የባሕርይ ችግር በአንድ ወላጅ ብቻ የሚያድጉ ከመሆናቸው ጋር የተያያዘ እንደሆነ አድርገው ያስባሉ። ሆኖም እንዲህ እያልክ ራስህን ጠይቅ፦ ‘እንዲህ ያሉ
አስተያየቶችን የሚሰጡት ሰዎች እኔንም ሆነ ቤተሰቤን በደንብ ያውቁናል? ወይስ በነጠላ ወላጅ ስለሚተዳደሩ ቤተሰቦች ሌሎች ሲናገሩ የሰሙትን ነገር እንደ ገደል ማሚቶ እያስተጋቡ ነው?’‘አባት የሌለው ልጅ’ እንደሚለው ያሉ አገላለጾች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ብዙ ጊዜ የሚገኙ መሆናቸው ትኩረት የሚስብ ነው። ይህ አገላለጽ አንድም ጊዜ ቢሆን እነዚህን ልጆች ዝቅ በሚያደርግ መንገድ አልተሠራበትም። እንዲያውም ይህ ዓይነቱ አገላለጽ በተጠቀሰባቸው በሁሉም ቦታዎች ላይ ማለት ይቻላል ይሖዋ አንድ ወላጅ ብቻ ለሚያሳድጋቸው ልጆች ልዩ ትኩረት እንደሚሰጥ አሳይቷል። *
በሌላ በኩል ደግሞ አንዳንዶች ከአንተ ጋር በሚያወሩበት ጊዜ ከአሳቢነት የተነሳ ለሚናገሩት ነገር ከሚገባው በላይ ይጠነቀቁ ይሆናል። ለምሳሌ ያህል፣ አንተን ቅር እንዳያሰኙህ ወይም እንዳያሸማቅቁህ ስለሚፈሩ “አባት፣” “ጋብቻ፣” “ፍቺ” ወይም “ሞት” እንደሚሉት ያሉ ቃላትን ከመጠቀም ይቆጠቡ ይሆናል። እንዲህ ማድረጋቸው ይረብሽሃል? ከሆነ ያን ያህል መጨነቅ እንደማያስፈልጋቸው በዘዴ አሳውቃቸው። የ14 ዓመቱ ቶማስ አባቱ ማን እንደሆነ አያውቅም። ቶማስ አንዳንዶች የተወሰኑ ቃላትን ላለመጥራት እንደሚጠነቀቁ ይናገራል። እሱ ግን ከእነዚህ ሰዎች ጋር ሲያወራ ሆን ብሎ በእነዚያ ቃላት ይጠቀማል። “ባለሁበት ሁኔታ የማላፍር መሆኔን እንዲያውቁ እፈልጋለሁ” ብሏል።
“ቢሆን ኖሮ” ብለህ አታስብ
ወላጆችህ በፍቺ ተለያይተው ወይም አንደኛውን ወላጅህን በሞት አጥተህ ከሆነ በነገሩ ብታዝንና ናፍቆት ቢያስቸግርህ የሚያስገርም አይሆንም። ያም ቢሆን ግን ያለህበትን ሁኔታ እያደር መቀበል ይኖርብሃል። መጽሐፍ ቅዱስ “‘ከእነዚህ ቀናት የቀድሞዎቹ ለምን ተሻሉ?’ አትበል” የሚል ምክር ይሰጣል። (መክብብ 7:10) የ13 ዓመቷ ሣራ ወላጆቿ የተፋቱት የ10 ዓመት ልጅ እያለች ነበር፤ እንዲህ የሚል ሐሳብ ሰጥታለች፦ “‘እንዲህ ቢሆን ኖሮ’ እያልክ አትተክዝ፤ ወይም አሁን ያሉብህ ችግሮች የተፈጠሩት አንደኛው ወላጅህ ስለተለየህ እንደሆነ በማሰብ አትቆዝም፤ አሊያም ሁለቱም ወላጆች ባሉበት ቤተሰብ ውስጥ የሚኖሩ ልጆች ሕይወታቸው አልጋ በአልጋ እንደሆነ አድርገህ አታስብ።” ይህ ጥሩ ምክር ነው። እንደ እውነቱ ከሆነ ሁለቱም ወላጆች አብረው በሚኖሩበት ቤተሰብ ውስጥም ጨርሶ ችግሮች አይፈጠሩም ማለት አይቻልም።
እስቲ ራስህንና የቤተሰብህን አባላት በአንድ ጀልባ ላይ ሆነው በኅብረት እንደሚቀዝፉ ሰዎች አድርገህ አስብ። በመሠረቱ ቀዛፊዎቹ የተሟሉ ቢሆኑ ተመራጭ ነው። በነጠላ ወላጅ በሚተዳደሩ ቤተሰቦች ውስጥ ግን ከቀዛፊዎቹ አንዱ ስለማይኖር ሌሎች የቤተሰቡ አባላት ይበልጥ መሥራት ይጠበቅባቸዋል። ታዲያ ይህ መሆኑ ቤተሰቡ ስኬታማ እንዳይሆን ያደርገዋል? በጭራሽ! ሌሎቹ ቀዛፊዎች ተባብረው እስከሠሩ ድረስ ጀልባዋ ጉዞዋን በመቀጠል የተፈለገበት ቦታ ትደርሳለች።
ኃላፊነትህን እየተወጣህ ነው?
አንተም ከሌሎቹ የቤተሰብህ አባላት ጋር በመተባበር ኃላፊነትህን ለመወጣት ልታከናውናቸው የምትችላቸው አንዳንድ ነገሮች ምንድን ናቸው? ከዚህ ቀጥሎ የቀረቡትን ሦስት ሐሳቦች ተመልከት፦
ቆጣቢ መሆንን ተማር። በአንድ ወላጅ ብቻ የሚተዳደሩ አብዛኞቹን ቤተሰቦች በዋነኝነት ከሚያሳስቧቸው ነገሮች አንዱ ገንዘብ ነው። በዚህ ረገድ ቤተሰብህን ለመርዳት ምን ማድረግ ትችላለህ? ቀደም ሲል የተጠቀሰው ቶማስ እንዲህ ይላል፦ “በትምህርት ቤታችን ያሉ ልጆች፣ ውድ የሆኑ ጫማዎችና ልብሶች ካልተገዙልን ብለው ወላጆቻቸውን ያስቸግራሉ። የፈለጉት ነገር ካልተገዛላቸው ትምህርት ቤት አልሄድም ይላሉ። እኔ ግን ፋሽን የሆኑ ውድ ልብሶች ባይኖሩኝም ልብሶቼ ንጹሕና ሥርዓታማ ናቸው፤ ደግሞም ያሉኝን ነገሮች በደንብ እይዛለሁ። እናቴ አቅሟ የሚፈቅደውን ሁሉ እያደረገች እኔ ተጨማሪ ሸክም ልሆንባት አልፈልግም።” አንተም የተወሰነ ጥረት የምታደርግ ከሆነ “ባለኝ ረክቼ መኖርን ተምሬያለሁ” በማለት የተናገረውን የጳውሎስን ምሳሌ መከተል ትችላለህ። ጳውሎስ “በማንኛውም ነገርና በሁሉም ሁኔታ” ባለው ረክቶ ይኖር ነበር።—ቆጣቢ መሆን የምትችልበት ሌላው መንገድ ደግሞ አባካኝነትን ማስወገድ ነው። (ዮሐንስ 6:12) ሮድኒ የተባለው ወጣት እንዲህ ብሏል፦ “ቤት ውስጥ ዕቃዎች እንዳይሰበሩ ወይም እንዳይጠፉ እጠነቀቃለሁ፤ ምክንያቱም ዕቃዎቹን መጠገንም ሆነ መተካት ገንዘብ ያስወጣል። ኤሌክትሪክ ብዙ እንዳይቆጥርብን ሳያስፈልግ መብራት አላበራም፤ እንዲሁም የኤሌክትሪክ ዕቃዎችን የማልጠቀምባቸው ከሆነ አጠፋቸዋለሁ።”
በራስህ ተነሳሽነት ቤተሰብህን አግዝ። በርካታ ነጠላ ወላጆች፣ ልጆቻቸው የቤት ውስጥ መመሪያዎችን እንዲያከብሩ መጫን ወይም በቤት ውስጥ ሥራ እንዲያግዟቸው መጠየቅ ይከብዳቸዋል። ለምን? አንዳንድ ነጠላ ወላጆች፣ ልጆቹ አንደኛውን ወላጃቸውን በማጣታቸው ሆድ ስለሚብሳቸው ሕይወት ከባድ እንዳይሆንባቸው በማድረግ ሁኔታውን ማካካስ እንዳለባቸው ይሰማቸዋል። ‘ልጆቼ፣ የልጅነት ጊዜያቸውን እንደ ልብ ሳይቦርቁበት እንዲያልፍ አልፈልግም’ ብለው ያስቡ ይሆናል።
በነጠላ ወላጅ የሚያድጉ አንዳንድ ልጆች ወላጆቻቸው እንዲህ የሚሰማቸው መሆኑ በፈጠረው አጋጣሚ በመጠቀም እንደፈለጉ ለመሆን ይሞክራሉ። አንተም እንዲህ ለማድረግ ይቃጣሃል? እንዲህ ማድረግህ በወላጅህ ላይ ጫና ይጨምራል እንጂ ነገሮችን አያቀልም። ታዲያ በራስህ ተነሳሽነት ቤተሰብህን ለመርዳት ለምን አትሞክርም? ቶማስ ምን ያደርግ እንደነበር እንመልከት። እንዲህ ብሏል፦ “እናቴ የምትሠራው ሆስፒታል ውስጥ ሲሆን የሥራ ልብሷ መተኮስ አለበት። ስለዚህ እኔ እተኩስላታለሁ።” ይሄ የሴት ሥራ አይደለም እንዴ? “አንዳንዶች እንደዚያ ይሰማቸው ይሆናል። እኔ ግን ምንም አይመስለኝም፤ ምክንያቱም ለእናቴ ሥራ ያቀልላታል” ብሏል ቶማስ።
አድናቆትህን ግለጽ። በነጠላ ወላጅ የሚያድጉ ልጆች ቤተሰባቸውን በሥራ ከማገዝ በተጨማሪ አድናቆታቸውን መግለጻቸው ብቻ እንኳ ወላጆቻቸውን በጣም ሊያበረታታቸው ይችላል። አንዲት ነጠላ እናት እንዲህ ስትል
ጽፋለች፦ “አብዛኛውን ጊዜ ተስፋ የመቁረጥ ስሜት በተሰማኝ ወይም በሥራ ቦታ አስቸጋሪ ሁኔታ አጋጥሞኝ ብስጭትጭት ባልኩበት ቀን ቤት ስደርስ ልጄ ጠረጴዛውን አሰናድታ ራት እየሠራች አገኛታለሁ።” አክላም “ወንድ ልጄም እቅፍ አድርጎ ሰላም ይለኛል” ብላለች። ይህች እናት ልጆቿ እንዲህ ዓይነት አሳቢነት ሲያሳይዋት ምን ይሰማታል? “ጭንቀቴን ሁሉ እረሳዋለሁ፤ መንፈሴም ይታደሳል” ብላለች።ከላይ ከተዘረዘሩት ሦስት ነጥቦች መካከል ይበልጥ ልትሠራበት እንደሚገባ የሚሰማህን በክፍት ቦታው ላይ ጻፍ። ․․․․․
በአንድ ወላጅ ብቻ በሚተዳደር ቤተሰብ ውስጥ መኖርህ ራስ ወዳድ እንዳትሆን የሚረዳህ ከመሆኑም ሌላ ርኅራኄ እንድታዳብርና ኃላፊነት የሚጣልብህ ሰው እንድትሆን አጋጣሚ ይሰጥሃል። በተጨማሪም ኢየሱስ “ከመቀበል ይልቅ መስጠት የበለጠ ደስታ ያስገኛል” ብሏል። (የሐዋርያት ሥራ 20:35) ወላጅህን ለመርዳት ራስህን የምታቀርብ ከሆነ ታላቅ ደስታ ታገኛለህ።
እርግጥ ነው፣ አልፎ አልፎ ‘ምነው አባቴ አብሮን በኖረ’ ብለህ ትመኝ ይሆናል። ይሁን እንጂ አሁን ባለህበት ሁኔታም ደስተኛ ለመሆን ምን ማድረግ እንደምትችል መማር ትችላለህ። ኒያ የተባለች አንዲት ወጣት እንዲህ ማድረግ እንደሚቻል ተገንዝባለች። እንዲህ ብላለች፦ “አባቴ ሲሞት አንዲት እህት ‘ደስተኛ መሆን አለመሆንሽ በአመለካከትሽ ላይ የተመካ ነው’ አለችኝ። ይህ አባባል ፈጽሞ ከአእምሮዬ አይጠፋም። ያለሁበት ሁኔታ ደስታዬን እንዲያሳጣኝ ማድረግ እንደሌለብኝ ያስታውሰኛል።” አንተም እንዲህ ዓይነት አመለካከት ማዳበር ትችላለህ። ደስተኛ መሆን አለመሆንህ ባለህበት ሁኔታ ላይ ሳይሆን ለነገሮች ባለህ አመለካከትና ሁኔታውን ለማሻሻል በምትወስደው እርምጃ ላይ የተመካ መሆኑን አስታውስ።
ተጨማሪ ሐሳብ ለማግኘት የዚህን መጽሐፍ ጥራዝ 1 ምዕራፍ 4 ተመልከት
[የግርጌ ማስታወሻ]
^ አን.11 ለምሳሌ ዘዳግም 24:19-21ን እና መዝሙር 68:5ን በ1980 ትርጉም ተመልከት።
ቁልፍ ጥቅስ
“ስለ ራሳችሁ ጉዳይ ብቻ ከማሰብ ይልቅ እያንዳንዳችሁ ለሌሎች ሰዎች ጉዳይም ትኩረት ስጡ።”—ፊልጵስዩስ 2:4
ጠቃሚ ምክር
ከአቅምህ በላይ ኃላፊነት እንደተጫነብህ ከተሰማህ እናትህ የሚከተሉትን ነጥቦች ተግባራዊ እንድታደርግ በዘዴ ሐሳብ አቅርብላት፦
● እያንዳንዱ የቤተሰብ አባል ሊያከናውን የሚገባውን ሥራ የያዘ ዝርዝር መለጠፍ።
● አስፈላጊ ሲሆን የእያንዳንዱን የቤተሰብ አባል አቅም ግምት ውስጥ በማስገባት ሥራ መቀያየር።
ይህን ታውቅ ነበር?
በቤት ውስጥ ኃላፊነት መሸከምህ ከሁለቱም ወላጆቻቸው ጋር ስለሚኖሩ ብዙም ኃላፊነት ከሌለባቸው ወጣቶች ይልቅ ቶሎ እንድትበስል ይረዳሃል።
ላደርጋቸው ያሰብኳቸው ነገሮች
አሉታዊ ስሜት ሲሰማኝ እንዲህ አደርጋለሁ፦ ․․․․․
ሰዎች ከእኔ ጋር ሲሆኑ ለሚናገሩት ነገር በጣም የሚጠነቀቁ ከሆነ እንዲህ እላቸዋለሁ፦ ․․․․․
ከዚህ ርዕሰ ጉዳይ ጋር በተያያዘ እናቴን ልጠይቃት የምፈልገው ነገር ․․․․․
ምን ይመስልሃል?
● አንዳንድ ሰዎች በነጠላ ወላጅ የሚያድጉ ልጆችን ዝቅ አድርገው የሚያዩዋቸው ለምንድን ነው?
● እናትህ በቤት ውስጥ ሥራ እንድታግዛት ልትጠይቅህ የማትፈልገው ለምን ሊሆን ይችላል?
● ለእናትህ ያለህን አድናቆት እንዴት መግለጽ ትችላለህ?
[በገጽ 211 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
ወላጆቼ ከተፋቱ በኋላ እኔና እናቴ የልባችንን አውጥተን ማውራት ችለናል፤ በጣም ተቀራርበናል።”—ሜላኒ
[በገጽ 210 እና 211 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አንድ ወላጅ ብቻ ያለበት ቤተሰብ አባላት፣ አንደኛው ቀዛፊ ሳይኖር አንድን ጀልባ በኅብረት ከሚቀዝፉ ሰዎች ጋር ሊመሳሰሉ ይችላሉ፤ የተቀሩት አባላት ይበልጥ መሥራት ቢጠበቅባቸውም ተባብረው ከሠሩ ሊሳካላቸው ይችላል