የኤሌክትሮኒክ ጨዋታዎችን ብጫወትስ?
ምዕራፍ 30
የኤሌክትሮኒክ ጨዋታዎችን ብጫወትስ?
“የኮምፒውተር ጨዋታዎችን መጫወት ደስ ይላል፤ በጣም ይመቻል” በማለት ብራያን የተባለ አንድ ወጣት ይናገራል። “የምር ቢሆን ኖሮ በጭራሽ የማትሞክራቸውን ነገሮች ጌም ስትጫወት ግን ልታደርጋቸው ትችላለህ፤ ማለቴ ጌም ስትጫወት ምንም ችግር አይደርስብህም።” ዲቦራም የኮምፒውተር ጨዋታዎችን መጫወት እንደምትወድ ትናገራለች። ሆኖም ጥንቃቄ የሚያሻው ጉዳይ እንዳለ ስትገልጽ “ጊዜ ሊወስዱና ሱስ ሊሆኑ ይችላሉ” ብላለች።
የኤሌክትሮኒክ ጨዋታዎች (የቪዲዮ ወይም የኮምፒውተር ጌሞች) ለመዝናኛነት ብቻ የሚያገለግሉ የረቀቁ የቴክኖሎጂ ውጤቶች አይደሉም። የኤሌክትሮኒክ ጨዋታዎች አእምሮህን የሚያሠሩ ሲሆን ድብር ሲልህ ዘና ለማለት ይረዱሃል። ይሁንና ከዚያም ያለፈ ጠቀሜታ አላቸው። እንደዚህ ያሉ ጨዋታዎችን መጫወት ለነገሮች ፈጣን ምላሽ የመስጠት ችሎታህን ያዳብርልሃል። እንዲያውም አንዳንዶቹ የሒሳብና የማንበብ ችሎታህ እንዲሻሻል ይረዱህ ይሆናል። ከዚህም በላይ በትምህርት ቤት ውስጥ ጓደኞችህ አብዛኛውን ጊዜ የሚያወሩት በቅርቡ ስለወጣው የኤሌክትሮኒክ ጨዋታ መሆኑ የታወቀ ነው። ይህንን ጨዋታ ከተጫወትክ ከጓደኞችህ ጋር የምታወራው ነገር ይኖርሃል ማለት ነው።
እንዲህ ያሉ ጨዋታዎችን በጥንቃቄ የምትመርጥ ከሆነ አስደሳችና ለክርስቲያኖች የሚሆን የኤሌክትሮኒክ ጨዋታ እንደምታገኝ ጥርጥር የለውም። ለመሆኑ ጥንቃቄ ማድረጉ ለምን አስፈለገ?
የኤሌክትሮኒክ ጨዋታዎች መጥፎ ገጽታ
የሚያሳዝነው ጤናማ ሊባሉ የሚችሉት ሁሉም የኤሌክትሮኒክ ጨዋታዎች አይደሉም። በዛሬው ጊዜ የሚገኙት አብዛኞቹ ጌሞች መጽሐፍ ቅዱስ “የሥጋ ሥራዎች” ብሎ የሚጠራቸውን በአምላክ የተጠሉ ርኩስ ድርጊቶች በግልጽ ያበረታታሉ።—ገላትያ 5:19-21
የ18 ዓመቱ አድሪያን ታዋቂ በሆነ አንድ ጌም ውስጥ “ደም መፋሰስና በተለያዩ ቡድኖች መካከል የሚደረግ ፍልሚያ እንዲሁም ሰዎች አደገኛ ዕፆችን ሲወስዱ፣ የፆታ ግንኙነት በግልጽ ሲፈጽሙ፣ ጸያፍ ነገር ሲናገሩ ብሎም አሰቃቂ የዓመፅ ድርጊቶችንና ዘግናኝ ነገሮችን ሲፈጽሙ” እንደሚታይ ገልጿል። አንዳንዶቹ ጨዋታዎች
መናፍስታዊ ድርጊቶችን እንደ ጥሩ ነገር አድርገው ያቀርባሉ። አዳዲስ የኤሌክትሮኒክ ጨዋታዎች በወጡ ቁጥር የበፊቶቹ ብዙም የዓመፅ ድርጊት የሌላቸው ይመስላሉ። ሰዎች አብዛኛውን ጊዜ እንዲህ ያሉትን ዓመፅ የሞላባቸው ጨዋታዎች በኢንተርኔት አማካኝነት ከሌላ ሰው ጋር መጫወት ይችላሉ። ይህ ደግሞ የኮምፒውተር ጨዋታ ይበልጥ አጓጊና ችሎታን የሚፈትን እንዲሆን አድርጎታል። የ19 ዓመቱ ጄምስ፣ “ቤትህ ቁጭ ብለህ በሌላው የዓለም ክፍል ከሚገኙ ሰዎች ጋር መጋጠም ትችላለህ” ብሏል።ሰዎች በኢንተርኔት ላይ አንድን ገጸ ባሕርይ ተላብሰው እንዲጫወቱ የሚያስችሏቸው ጌሞች በጣም ተወዳጅ እየሆኑ መጥተዋል። እነዚህን ጌሞች የሚጫወቱት ሰዎች ቢፈልጉ ሰው አሊያም እንስሳ ወይም ደግሞ እንስሳም ሰውም የሆነ ገጸ ባሕርይ መፍጠር ይችላሉ። በሺህ የሚቆጠሩ እንደነዚህ ዓይነት ገጸ ባሕርያት ባሉበት በኮምፒውተር ላይ በተፈጠረው በዚህ ዓለም ውስጥ ሱቆች፣ መኪኖች፣ መኖሪያ ቤቶች እንዲሁም የጭፈራና የዝሙት አዳሪ ቤቶች ይገኛሉ፤ በሌላ አነጋገር በገሃዱ ዓለም ውስጥ ያሉት ነገሮች ሁሉ ይገኙበታል። እነዚህን ጨዋታዎች በኢንተርኔት የሚጫወቱት ሰዎች እርስ በርስ መልእክት በመለዋወጥ በኮምፒውተር ላይ የፈጠሯቸው ገጸ ባሕርያት እንዲነጋገሩ ማድረግ ይችላሉ።
ኮምፒውተር ላይ በተፈጠረው በዚህ ዓለም ውስጥ ከሚኖሩት መጥፎ ገጸ ባሕርያት መካከል ማፊያዎች፣ ዝሙት አዳሪዎችና የእነሱ ደላሎች፣ ማጅራት መቺዎች፣ አጭበርባሪዎችና ነፍሰ ገዳዮች ይገኙበታል። በእነዚህ ጨዋታዎች ላይ የሚካፈሉት ሰዎች በገሃዱ ዓለም ውስጥ በጭራሽ የማያደርጓቸውን ነገሮች በጌም ውስጥ ይፈጽማሉ። ሰዎቹ የተወሰኑ የኮምፒውተር ቁልፎችን በመጫን ብቻ በኮምፒውተሩ ውስጥ የፈጠሯቸው ገጸ ባሕርያት የፆታ ግንኙነት እንዲፈጽሙ ማድረግ የሚችሉ ሲሆን እነሱ ራሳቸው ደግሞ በዚያው ሰዓት ስለ ፆታ ግንኙነት መልእክት ይለዋወጣሉ። በአንዳንድ ጌሞች ላይ አዋቂ ሰዎችንና ልጆችን የሚወክሉ ገጸ ባሕርያትን መፍጠርና እነዚህ ገጸ ባሕርያት የፆታ ግንኙነት እንዲፈጽሙ ማድረግ ይቻላል። ልጆችን እንደማስነወር ያሉ አስጸያፊ ድርጊቶች በጨዋታ
መልክ መቅረባቸው አንዳንዶችን ያሳሰባቸው መሆኑ አያስገርምም።ምርጫህ ለውጥ ያመጣል!
ዓመፅ የሚንጸባረቅባቸውንና የፆታ ብልግና በግልጽ የሚታይባቸውን የኤሌክትሮኒክ ጨዋታዎች የሚጫወቱ ሰዎች “ማንም ሰው እስካልተጎዳ ድረስ ምን ችግር አለው? ይሄ እኮ ጨዋታ እንጂ የእውነት አይደለም” ይሉ ይሆናል። ይሁን እንጂ እንዲህ ባለው የተሳሳተ አስተሳሰብ አትታለል!
መጽሐፍ ቅዱስ “ሕፃን እንኳ ጠባዩ ንጹሕና ቅን መሆኑ፣ ከአድራጎቱ ይታወቃል” ይላል። (ምሳሌ 20:11) ዓመፅና የሥነ ምግባር ብልግና የሚታይባቸውን የኤሌክትሮኒክ ጨዋታዎች የምትጫወት ከሆነ ንጹሕና ቅን አስተሳሰብ አለህ ሊባል ይችላል? ዓመፅ የሚበዛባቸውን መዝናኛዎች የሚመለከቱ ሰዎች ጠበኞች የመሆን አጋጣሚያቸው እንደሚጨምር በተደጋጋሚ ጊዜ የተደረጉ ጥናቶች አሳይተዋል። እንዲያውም አንዳንድ ባለሙያዎች እንደተናገሩት የኤሌክትሮኒክ ጨዋታዎች ተጫዋቾቹን ስለሚያሳትፉ ከቴሌቪዥን የበለጠ ተጽዕኖ ሊያሳድሩ ይችላሉ።
ዓመፅ ወይም የሥነ ምግባር ብልግና የሚታይባቸውን የኤሌክትሮኒክ ጨዋታዎች መጫወት መርዛማ በሆነ ኬሚካል የመጫወት ያህል አደገኛ ነው፤ ኬሚካሉ የሚያደርሰው አደጋ ወዲያውኑ የሚታይ ባይሆን እንኳ ውሎ አድሮ ጉዳት ማስከተሉ አይቀርም። እንደዚህ ላለው ኬሚካል መጋለጥ ለበሽታ ይዳርጋል። በተመሳሳይም የፆታ ግንኙነት በግልጽ የሚታይባቸውንና ዘግናኝ የዓመፅ ድርጊቶች ኤፌሶን 4:19፤ ገላትያ 6:7, 8
የሚፈጸሙባቸውን የኤሌክትሮኒክ ጨዋታዎች መጫወት ‘የሥነ ምግባር ስሜትህን’ የሚያደነዝዘው ከመሆኑም ባሻገር ሥጋዊ ምኞቶች አስተሳሰብህንና ድርጊትህን እንዲቆጣጠሩት ያደርጋል።—ምን ዓይነት የኤሌክትሮኒክ ጨዋታዎችን ብመርጥ ይሻላል?
ወላጆችህ የኤሌክትሮኒክ ጨዋታዎች እንድትጫወት የሚፈቅዱልህ ከሆነ የትኞቹን መምረጥ እንዳለብህ ማወቅ የምትችለው እንዴት ነው? በመጫወት የምታሳልፈው ጊዜ ምን ያህል መሆን እንዳለበት ለመወሰንስ ምን ሊረዳህ ይችላል? ራስህን የሚከተሉትን ጥያቄዎች ጠይቅ፦
ምርጫዬ አምላክ ስለ እኔ በሚኖረው አመለካከት ላይ ምን ለውጥ ያመጣል? መዝሙር 11:5 “እግዚአብሔር ጻድቁንና ኀጥኡን ይመረምራል፤ ዐመፃን የሚወዱትን ግን፣ ነፍሱ ትጠላቸዋለች” ይላል። በመናፍስታዊ ድርጊቶች የሚካፈሉ ሰዎችን በተመለከተ ደግሞ የአምላክ ቃል “እነዚህን የሚያደርግ ሁሉ በእግዚአብሔር ዘንድ አስጸያፊ ነው” በማለት ይናገራል። (ዘዳግም 18:10-12) የአምላክ ወዳጅ መሆን ከፈለግህ በመዝሙር 97:10 ላይ የሚገኘውን “ክፋትን ጥሉ” የሚለውን ምክር ተግባራዊ ማድረግ ይኖርብሃል።
1 ቆሮንቶስ 6:18) የፆታ ስሜትን የሚያነሳሱ ምስሎች ወይም ንግግሮች ያሉባቸው የኤሌክትሮኒክ ጨዋታዎች አእምሮህ ጽድቅ፣ ንጹሕና በጎ በሆኑ ነገሮች ላይ እንዲያተኩር አይረዱህም።—ፊልጵስዩስ 4:8
ጨዋታው በአስተሳሰቤ ላይ ምን ተጽዕኖ ያሳድራል? “ይህንን ጌም መጫወቴ ‘ከዝሙት ለመሸሽ’ የማደርገውን ጥረት ቀላል ያደርግልኛል ወይስ ያከብድብኛል?” ብለህ ራስህን ጠይቅ። (የኤሌክትሮኒክ ጨዋታዎችን በመጫወት ምን ያህል ጊዜ አጠፋለሁ? ጤናማ የሚባሉት የኤሌክትሮኒክ ጨዋታዎች እንኳ በጣም ብዙ ጊዜ ሊወስዱ ይችላሉ። እስቲ በጨዋታ የምታጠፋውን ጊዜ መዝግብ። ይበልጥ አስፈላጊ በሆኑ እንቅስቃሴዎች ልታሳልፈው የሚገባውን ጊዜ እየተሻማብህ ነው? በጨዋታ የምታሳልፈውን ጊዜ መመዝገብህ ቅድሚያ ልትሰጣቸው የሚገቡህን ነገሮች እንድታስቀድም ይረዳሃል።—ኤፌሶን 5:15, 16
እርግጥ ነው፣ መጽሐፍ ቅዱስ መላ ሕይወትህ በጥናትና በሥራ ብቻ የተጠመደ መሆን እንዳለበት አይናገርም። ከዚህ ይልቅ “ለመሣቅም ጊዜ አለው፤ . . . ለጭፈራም ጊዜ አለው” በማለት ሁላችንም ልንዘነጋው የማይገባውን ሐቅ ይገልጻል። (መክብብ 3:4) ይሁንና “ጭፈራ” የሚለው ቃል መጫወትን ብቻ ሳይሆን አካላዊ እንቅስቃሴ ማድረግንም የሚጨምር መሆኑ ትኩረት የሚስብ ነው። ታዲያ የእረፍት ጊዜህን ኮምፒውተር ላይ ብቻ ተተክለህ ከማሳለፍ ይልቅ አካላዊ እንቅስቃሴ ማድረግ በሚጠይቁ ጨዋታዎች ለምን አትካፈልም?
በጥበብ ምረጥ
በተለይ ጎበዝ ተጫዋች ከሆንክ የኤሌክትሮኒክ ጨዋታዎችን መጫወት አስደሳች እንደሚሆንልህ ግልጽ ነው። የምትጫወተውን ጨዋታ በጥበብ መምረጥ የሚኖርብህም ለዚህ ነው። ‘በትምህርት ቤት ጥሩ ውጤት የማመጣው በየትኞቹ የትምህርት ዓይነቶች ነው?’ በማለት ራስህን ጠይቅ። በአብዛኛው በምትወዳቸው የትምህርት ዓይነቶች አይደለም? እንዲያውም አንድን ትምህርት በወደድከው መጠን የምትማረው ነገር ይበልጥ በአእምሮህ እየተቀረጸ ይሄዳል። እስቲ ራስህን እንደሚከተለው በማለት ጠይቅ፦ ‘በጣም የምወደው የኤሌክትሮኒክ ጨዋታ የትኛው ነው? ይህ ጨዋታ በሥነ ምግባር ረገድ ምን ያስተምረኛል?’
አንድን የኤሌክትሮኒክ ጨዋታ ጓደኞችህ ስለተጫወቱት ብቻ ከመጫወት ይልቅ ሁኔታዎቹን አመዛዝነህ የራስህን ምርጫ ለማድረግ ቆራጥ አቋም ውሰድ። ከሁሉም በላይ ደግሞ “በጌታ ዘንድ ተቀባይነት ያለው ነገር ምን እንደሆነ ምንጊዜም መርምራችሁ አረጋግጡ” የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር ተግባራዊ አድርግ።—ኤፌሶን 5:10
ሙዚቃ ትወዳለህ? ይህ ምንም ስህተት የለውም። ይሁንና ያለ ሙዚቃ መኖር እንደማትችል እስኪሰማህ ድረስ ተቆጣጥሮሃል?
ቁልፍ ጥቅስ
“እናንተ ይሖዋን የምትወዱ፣ ክፉ የሆነውን ነገር ጥሉ።”—መዝሙር 97:10 NW
ጠቃሚ ምክር
መጫወት የምትፈልገውን የእያንዳንዱን የኤሌክትሮኒክ ጨዋታ ዓላማና ይህን ዓላማ ከግብ ለማድረስ የምትጠቀምባቸውን ዘዴዎች በአጭሩ ለመጻፍ ሞክር። ስለ ጨዋታው የጻፍካቸውን ነገሮች፣ በዚህ ምዕራፍ ውስጥ ከተጠቀሱት የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች አንጻር በመገምገም የኤሌክትሮኒክ ጨዋታው ጥሩ ነው ወይስ አይደለም የሚለውን ወስን።
ይህን ታውቅ ነበር?
በኢንተርኔት አማካኝነት የኤሌክትሮኒክ ጨዋታዎችን የመጫወት ሱስ የያዛቸውን ሰዎች ከዚህ ሱስ እንዲላቀቁ ለመርዳት በዓለማችን የመጀመሪያው የሕክምና ተቋም በ2006 በአምስተርዳም፣ ኔዘርላንድ ተከፍቷል።
ላደርጋቸው ያሰብኳቸው ነገሮች
አንድ ጓደኛዬ ዓመፅ ወይም የሥነ ምግባር ብልግና ያለበት የኤሌክትሮኒክ ጨዋታ እንድጫወት ቢጠይቀኝ እንዲህ እለዋለሁ፦ ․․․․․
የኤሌክትሮኒክ ጨዋታዎች በመጫወት የማሳልፈው ጊዜ በሳምንት ከ ․․․․․ ሰዓት እንዳይበልጥ አደርጋለሁ፤ በዚህ ውሳኔዬ ለመጽናት እንዲህ አደርጋለሁ፦ ․․․․․
ከዚህ ርዕሰ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ወላጆቼን ልጠይቃቸው የምፈልገው ነገር ․․․․․
ምን ይመስልሃል?
● የኤሌክትሮኒክ ጨዋታዎች በአንድ ሰው አስተሳሰብና ስሜት ላይ ምን ተጽዕኖ ሊያሳድሩ ይችላሉ?
● አንድን ጨዋታ በምትመርጥበት ጊዜ የይሖዋን የሥነ ምግባር መሥፈርቶች ከግምት ማስገባቱ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
● ታናሽ ወንድምህ ወይም እህትህ መጥፎ የሆነ የኤሌክትሮኒክ ጨዋታ የመጫወት ሱስ ቢኖርባቸው እንዴት ልትረዳቸው ትችላለህ?
[በገጽ 249 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
በርካታ የኤሌክትሮኒክ ጨዋታዎች እንደ ዓመፅ፣ ጸያፍ ንግግርና የፆታ ብልግና ለመሳሰሉት ነገሮች ያለህ ጥላቻ እየቀነሰ እንዲሄድና በሌሎቹ የሕይወት ዘርፎች በሚያጋጥሙህ ፈተናዎች በቀላሉ እንድትሸነፍ ሊያደርጉ ይችላሉ። የምትጫወታቸውን የኤሌክትሮኒክ ጨዋታዎች በጥንቃቄ መምረጥ ይኖርብሃል።”—ኤሚ
[በገጽ 250 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ዓመፅ ወይም የሥነ ምግባር ብልግና የሚታይባቸውን የኤሌክትሮኒክ ጨዋታዎች መጫወት መርዛማ በሆነ ኬሚካል የመጫወት ያህል አደገኛ ነው፤ ውጤቱ ወዲያውኑ የሚታይ ባይሆን እንኳ ውሎ አድሮ ጉዳት ማስከተሉ አይቀርም