በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የብልግና ምስሎችን ብመለከት ምን ችግር አለው?

የብልግና ምስሎችን ብመለከት ምን ችግር አለው?

ምዕራፍ 33

የብልግና ምስሎችን ብመለከት ምን ችግር አለው?

የብልግና ምስሎች ሳታስበው የሚያጋጥሙህ ምን ያህል ነው?

□ ጨርሶ አያጋጥመኝም

□ አልፎ አልፎ

□ በየጊዜው

አብዛኛውን ጊዜ የሚያጋጥሙህ የት ነው?

□ ኢንተርኔት ላይ

□ ትምህርት ቤት

□ ቴሌቪዥን ላይ

□ ሌላ ቦታ

እንዲህ ያሉ ምስሎች ሲያጋጥሙህ ምን ታደርጋለህ?

□ ፊቴን ቶሎ አዞራለሁ።

□ የማወቅ ጉጉት ስለሚያድርብኝ በትንሹ አየት አደርገዋለሁ።

□ በደንብ አየዋለሁ፤ እንዲያውም ተጨማሪ ለማግኘት እሞክራለሁ።

ወላጆችህ በአንተ ዕድሜ በነበሩበት ጊዜ የብልግና ምስሎችን በቀላሉ ማግኘት አይቻልም ነበር። ዛሬ ግን የብልግና ምስሎች አንተ ባትፈልጋቸውም እነሱ ራሳቸው የሚመጡብህ ይመስላል። አንዲት የ19 ዓመት ልጅ እንዲህ ብላለች፦ “አንዳንድ ጊዜ የተለያዩ ድረ ገጾችን ስቃኝ አሊያም በኢንተርኔት አማካኝነት በምገበያይበት ወይም የባንክ ሒሳቤን በምመለከትበት ጊዜ እንኳ የብልግና ምስል የያዘ ድረ ገጽ ድንገት ብቅ ይላል!” እንዲህ ያለው ነገር የተለመደ ነው። አንድ ጥናት እንዳመለከተው ከ8 እስከ 16 ዓመት ባለው የዕድሜ ክልል ውስጥ ከሚገኙ ወጣቶች መካከል 90 በመቶ የሚሆኑት ኢንተርኔት እየተጠቀሙ እያለ ድንገት የብልግና ምስሎች እንዳጋጠሟቸው ተናግረዋል፤ ብዙውን ጊዜ እንዲህ ያለው ሁኔታ የሚያጋጥማቸው የቤት ሥራቸውን በመሥራት ላይ ሳሉ ነው!

የብልግና ምስሎች ይህን ያህል የተስፋፉ መሆናቸው ‘ይህ ነገር በእርግጥ ጎጂ ነው?’ ብለህ እንድትጠይቅ ያደርግህ ይሆናል። መልሱ አዎን የሚል ነው! የብልግና ምስል፣ የተመልካቾቹንም ሆነ በምስሉ ላይ የሚታዩትን ሰዎች ክብር ያዋርዳል፤ ከዚህም በላይ እንዲህ ያሉ ምስሎችን መመልከት ብዙውን ጊዜ የፆታ ብልግና ወደ መፈጸም ይመራል። ሆኖም ጉዳቱ በዚህ አያበቃም።

የብልግና ምስሎችን መመልከት ሱስ ሊሆንና ዘላቂ ብሎም አስከፊ ጉዳት ሊያስከትል ይችላል። ለምሳሌ ያህል፣ ጄፍ የተባለ አንድ ሰው ከዚህ ሱስ ከተላቀቀ ከ14 ዓመት በኋላም እንኳ ምን እንዳለ እንመልከት፦ “አሁንም በየቀኑ ትግል ማድረግ ይጠይቅብኛል። እነዚህን ምስሎች እንዳይ የሚገፋፋኝ ስሜት የቀድሞውን ያህል ኃይለኛ ባይሆንም ዛሬም አለ። አሁንም እይ እይ የሚለኝ ጊዜ አለ። ምስሎቹ አሁን ድረስ ከአእምሮዬ አልጠፉም። ምነው እንዲህ ያለውን ቀፋፊ ነገር ማየት ባልጀመርኩ ኖሮ! መጀመሪያ ላይ ምንም ችግር ያለው አልመሰለኝም ነበር። አሁን ግን ጉዳቱ ገብቶኛል። የብልግና ምስሎችን መመልከት ጎጂና አስጸያፊ ከመሆኑም በላይ የሚሠሩትንም ሆነ የሚመለከቱትን ሰዎች የሚያዋርድ ነው። ይህን ድርጊት የሚደግፉ ሰዎች ምንም ይበሉ ምን የብልግና ምስሎች እርባና ቢስና አንዳች ጥቅም የማይገኝባቸው ነገሮች ናቸው።”

ሁኔታውን መገምገም

ሳታስበውም እንኳ የብልግና ምስሎችን ላለመመልከት ምን እርምጃዎችን መውሰድ ትችላለህ? በቅድሚያ ሁኔታውን ገምግም። በአብዛኛው የሚያጋጥምህ በምን መንገድ ነው? እስቲ የሚከተሉትን ምሳሌዎች ተመልከት፦

አንዳንድ የክፍልህ ልጆች በኢሜይል ወይም በሞባይል የብልግና ምስሎችን የመላክ ልማድ አላቸው? ከሆነ የሚልኩልህን ነገር ሳትከፍተው ማጥፋትህ ብልህነት ነው።

ኢንተርኔት እየተጠቀምክ ሳለ መረጃ ለመፈለግ አንዳንድ ቃላትን ስትጽፍ ሌላ ድረ ገጽ እንድትከፍት የሚጋብዝ መልእክት ወይም ምስል ብቅ ይላል? ይህ ሊያጋጥም እንደሚችል ማወቅህ በምትጽፋቸው ቃላት ረገድ ይበልጥ ጥንቃቄ እንድታደርግ ይረዳሃል።

የብልግና ምስልን ሳትፈልገው እንድታይ ያደረጉህ ሌሎች አጋጣሚዎች አሉ? ከዚህ በታች ጻፋቸው።

․․․․․

የብልግና ምስሎችን ድንገት የምታይባቸውን አጋጣሚዎች ለመቀነስ ወይም ለማስቀረት ማድረግ የምትችለው ነገር አለ? ለማድረግ ያሰብከውን ነገር ከዚህ በታች ጻፍ።

․․․․․

ሱስ ከሆነብህ ምን ማድረግ ትችላለህ?

ሳታስበው የብልግና ምስሎችን መመልከት አንድ ነገር ነው፤ እንዲህ ያሉትን ምስሎች ሆን ብሎ መመልከት ግን ሌላ ጉዳይ ነው። እንዲህ ያሉ ምስሎችን ሆን ብለህ ከመመልከት ባለፈ ድርጊቱ ልማድ እየሆነብህ ከመጣ ምን ማድረግ ትችላለህ? ከዚህ ልማድ መላቀቅ ቀላል እንዳልሆነ ምንም ጥያቄ የለውም። ሁኔታውን በምሳሌ ለማስረዳት፦ እጆችህ በክር ታስረዋል እንበል፤ ክሩ እጅህ ላይ የተጠመጠመው አንድ ዙር ብቻ ከሆነ በቀላሉ ልትበጥሰውና እጅህን ልታስለቅቅ ትችል ይሆናል። ይሁንና ክሩን ብዙ ጊዜ በማዞር እጅህ ትብትብ ተደርጎ የታሰረ ቢሆንስ? ክሩን መበጠስ ይበልጥ አዳጋች ይሆንብሃል። የብልግና ምስሎችን መመልከት ልማድ የሆነባቸው ሰዎች ሁኔታም ተመሳሳይ ነው። እንዲህ ያሉ ምስሎችን ደጋግመው በተመለከቱ ቁጥር ይህ ልማድ ይበልጥ ተብትቦ ይይዛቸዋል። አንተም እንዲህ ዓይነት ሁኔታ አጋጥሞህ ከሆነ ከዚህ ልማድ መላቀቅ የምትችለው እንዴት ነው?

የብልግና ምስል ርካሽ ነገር መሆኑን ተገንዘብ። የብልግና ምስሎች ይሖዋ ክቡር አድርጎ የፈጠረውን ነገር ለማራከስ ሰይጣን የሚጠቀምባቸው መሣሪያዎች መሆናቸው ግልጽ ነው። ሁኔታውን ከዚህ አንጻር መመልከትህ ‘ክፋትን እንድትጠላ’ ይረዳሃል።​—መዝሙር 97:10

የሚያስከትላቸውን መዘዞች አስብ። የብልግና ምስሎችን መመልከት ለትዳር መፍረስ ምክንያት ይሆናል። እንዲሁም በምስሉ ላይ የሚታዩትን ሰዎች ክብር ያዋርዳል። የሚመለከተውንም ሰው ክብር ይቀንሳል። መጽሐፍ ቅዱስ “አስተዋይ ሰው አደጋ ሲያይ መጠጊያ ይሻል” ማለቱ የተገባ ነው። (ምሳሌ 22:3) የብልግና ምስሎችን የመመልከት ልማድ ቢኖርህ ሊያጋጥምህ የሚችለውን አደጋ ወይም መዘዝ ከዚህ በታች ጻፍ።

․․․․․

ለራስህ ቃል ግባ። ታማኝ የነበረው ኢዮብ “ወደ ኰረዳዪቱ ላለመመልከት፣ ከዐይኔ ጋር ቃል ኪዳን ገብቻለሁ” ሲል ተናግሯል። (ኢዮብ 31:1) አንተም እንደሚከተለው እያልክ ለራስህ ‘ቃል መግባት’ ትችላለህ፦

ቤት ውስጥ ብቻዬን ከሆንኩ ኢንተርኔት አልጠቀምም።

የብልግና ምስሎችን የያዙ ድረ ገጾች ካጋጠሙኝ ወይም እንዲህ ያሉ ምስሎችን እንድመለከት የሚጋብዙ መልእክቶች ከመጡ ወዲያውኑ አጠፋቸዋለሁ።

ችግሩ ካገረሸብኝ ጉዳዩን ጎልማሳ ለሆነ አንድ የምቀርበው ሰው አጫውተዋለሁ።

ከዚህ ልማድ ጋር በምታደርገው ትግል አሸናፊ ለመሆን ለራስህ ቃል ልትገባ የምትችላቸው ሌሎች ነገሮች አሉ? ከሆነ አንድ ሁለቱን ከዚህ በታች ጻፍ።

․․․․․

ጉዳዩን አስመልክተህ ጸልይ። መዝሙራዊው “ከንቱ ነገር ከማየት ዐይኖቼን መልስ” በማለት ወደ ይሖዋ ጸልዮአል። (መዝሙር 119:37) ይሖዋ አምላክ ይህን ችግር እንድታሸንፍ ስለሚፈልግ ትክክል የሆነውን ነገር ለማድረግ የሚያስፈልግህን ጥንካሬ ይሰጥሃል!​—ፊልጵስዩስ 4:13

አንድ ሰው አማክር። ለምትተማመንበት አንድ ሰው ችግርህን ማማከርህ ብዙውን ጊዜ ይህን ልማድ ለማሸነፍ የሚረዳህ ወሳኝ እርምጃ ነው። (ምሳሌ 17:17) ይህን ጉዳይ አንስተህ ለማናገር የማይከብድህን አንድ የጎለመሰ ሰው ስም ከዚህ በታች ጻፍ።

․․․․․

ከዚህ ሱስ ለመላቀቅ በምታደርገው ትግል አሸናፊ መሆን እንደምትችል እርግጠኛ ሁን። እንዲያውም የብልግና ምስሎችን ለመመልከት የሚያጋጥምህን ፈተና ባለፍክ ቁጥር ከፍተኛ ድል እንዳገኘህ ሊሰማህ ይገባል። ፈተናውን ባለፍክ ቁጥር ስለ ሁኔታው ወደ ይሖዋ በመጸለይ ጥንካሬ ስለሰጠህ አመስግነው። ለብዙ መከራና ሥቃይ የሚዳርገውን የብልግና ምስሎችን የመመልከት ልማድ ስታስወግድ የይሖዋን ልብ ደስ እንደምታሰኝ ምንጊዜም አትዘንጋ!​—ምሳሌ 27:11

ቁልፍ ጥቅስ

“ስለዚህ በምድራዊ የአካል ክፍሎቻችሁ ውስጥ ያሉትን ዝንባሌዎች ግደሉ፤ እነሱም ዝሙት፣ ርኩሰት፣ የፆታ ምኞት፣ መጥፎ ፍላጎትና ጣዖት አምልኮ የሆነው መጎምጀት ናቸው።”​—ቆላስይስ 3:5

ጠቃሚ ምክር

ኮምፒውተርህ የብልግና ምስሎች የሚታዩባቸውን ድረ ገጾች እንዳያስተናግድ አድርገህ አስተካክለው። ከዚህም በተጨማሪ የማታውቃቸው ሰዎች በሚልኩት ኢሜይል ላይ የሚገኙ ሌላ ድረ ገጽ እንድትከፍት የሚጋብዙ ሊንኮችን ወይም መልእክቶችን ለመክፈት አትሞክር።

ይህን ታውቅ ነበር?

የብልግና ምስሎችን የመመልከት ልማድ ያላቸው ሰዎች ለእነዚህ ነገሮች ያላቸው ፍላጎት፣ በኖኅ ዘመን የነበሩት ክፉ መናፍስት ከተፈጥሮ ውጪ የሆነ የፆታ ግንኙነት እንዲፈጽሙ ካነሳሳቸው ስሜት ጋር ይመሳሰላል።​​—ዘፍጥረት 6:2

ላደርጋቸው ያሰብኳቸው ነገሮች

ሳላስበው የብልግና ምስሎችን ላለማየት እንዲህ አደርጋለሁ፦ ․․․․․

ከዚህ ርዕሰ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ወላጆቼን ልጠይቃቸው የምፈልገው ነገር ․․․․․

ምን ይመስልሃል?

የብልግና ምስሎች ክቡር የሆነውን ነገር የሚያዋርዱት እንዴት ነው?

ወንድምህ ወይም እህትህ የብልግና ምስሎችን የማየት ችግር ካለባቸው እንዴት ልትረዳቸው ትችላለህ?

[በገጽ 278 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ከመጀመሬ በፊት ያልወሰድኩት የአደንዛዥ ዕፅ ዓይነት የለም ማለት ይቻላል፤ ኃይለኛ የሆኑትን እነዚህን ዕፆች በብዛት እወስድ ነበር። ሱስ ከሆኑብኝ ነገሮች ሁሉ ለመላቀቅ በጣም የከበደኝ ግን የብልግና ምስሎች የማየት ልማዴ ነበር። ይሖዋ ባይረዳኝ ኖሮ ይህን ችግር ማሸነፍ አልችልም ነበር።”​—ጄፍ

[በገጽ 276 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የብልግና ምስሎችን መመልከት እጅን በክር ከመታሰር ጋር ሊመሳሰል ይችላል፤ ክሩ እጅህ ላይ በተጠመጠመ ቁጥር እጅህን ማላቀቁ ከባድ እንደሚሆን ሁሉ እነዚህን ምስሎች ደጋግመህ በተመለከትክ ቁጥር ልማዱ ይበልጥ ተብትቦ ይይዝሃል