በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የፍቅር ጓደኝነት ለመመሥረት ደርሻለሁ?

የፍቅር ጓደኝነት ለመመሥረት ደርሻለሁ?

ምዕራፍ 1

የፍቅር ጓደኝነት ለመመሥረት ደርሻለሁ?

“የወንድ ጓደኛ እንድይዝ ከየአቅጣጫው ከፍተኛ ግፊት ይደረግብኛል። በዚህ ላይ ደግሞ ቆንጆ የሆኑ ወንዶች ሞልተዋል።”​—ዊትኒ

“አንዳንዶቹ ሴቶች ዓይን አውጥተው ይጠይቁኛል፤ በዚህ ጊዜ እሺ ለማለት ይቃጣኛል። ሆኖም ወላጆቼን ብጠይቃቸው እንደማይፈቅዱልኝ አውቃለሁ።”​—ፊሊፕ

ከምትወዳትና እሷም ለአንተ የተለየ የፍቅር ስሜት ካላት ወጣት ጋር አብረህ ጊዜ የማሳለፍ ከፍተኛ ፍላጎት ይኖርህ ይሆናል፤ እንዲህ ዓይነቱ ስሜት ገና በልጅነትህም እንኳ ሊያድርብህ ይችላል። ጄኒፈር “ሌሎች ልጆች የፍቅር ጓደኛ ይዘው ስመለከት እኔም ገና በ11 ዓመቴ የወንድ ጓደኛ የመያዝ ፍላጎት አድሮብኝ ነበር” በማለት ታስታውሳለች። ብሪትኒ ደግሞ “ግለሰቡ ማንም ይሁን ማን በትምህርት ቤት አንድ የፍቅር ጓደኛ ካልያዛችሁ የሆነ ችግር እንዳለባችሁ ይሰማችኋል” ብላለች።

አንተስ? የፍቅር ጓደኛ ለመያዝ ደርሰሃል? ለዚህ ጥያቄ መልስ ለማግኘት በቅድሚያ ልናነሳው የሚገባ መሠረታዊ የሆነ ጥያቄ አለ፦

“የፍቅር ጓደኝነት” ሲባል ምን ማለት ነው?

ለሚከተሉት ጥያቄዎች መልስ የምትለው ላይ ምልክት አድርግ፦

ከአንዲት ወጣት ጋር በተደጋጋሚ ጊዜ እየተገናኛችሁ ትጫወታላችሁ። የፍቅር ጓደኝነት ጀምረሃል ማለት ይቻላል?

□ አዎ

□ አይ

ደስ የምትልህ አንዲት ወጣት አለች፤ እሷም ለአንተ ልዩ ስሜት አላት። በቀን ውስጥ ብዙ ጊዜ በሞባይል መልእክት ትላላካላችሁ አሊያም በስልክ ታወራላችሁ። የፍቅር ጓደኝነት ጀምረሃል ማለት ይቻላል?

□ አዎ

□ አይ

ከጓደኞችህ ጋር ጊዜ ስታሳልፍ ሁልጊዜ ከአንዲት ወጣት ጋር ነጠል ብለህ ታወራለህ። የፍቅር ጓደኝነት ጀምረሃል ማለት ይቻላል?

□ አዎ

□ አይ

የመጀመሪያውን ጥያቄ ለመመለስ ብዙም እንደማትቸገር ግልጽ ነው። ይሁን እንጂ ሁለተኛውንና ሦስተኛውን ጥያቄ ለመመለስ አመንትተህ ይሆናል። ለመሆኑ “የፍቅር ጓደኝነት” ሲባል ምን ማለት ነው? ለአንዲት ወጣት የፍቅር ስሜት ካለህና እሷም እንደ አንተ የሚሰማት ከሆነ የምትገናኙበት መንገድ ምንም ይሁን ምን በመካከላችሁ መፈላለጉ እስካለ ድረስ የፍቅር ጓደኝነት ጀምራችኋል ሊባል ይችላል። በመሆኑም ከላይ የቀረቡት የሦስቱም ጥያቄዎች መልስ አዎ የሚለው ነው። አንተና አንዲት ወጣት አንዳችሁ ለሌላው የፍቅር ስሜት ካላችሁና በየጊዜው የምታወሩ ከሆነ የምትገናኙት በስልክም ይሁን በአካል ወይም ደግሞ በግልጽም ይሁን በድብቅ የፍቅር ጓደኝነት ጀምራችኋል ማለት ነው። ይህን ለማድረግ ዝግጁ ነህ? ሦስት ጥያቄዎችን መመርመራችን መልሱን ለማግኘት ይረዳሃል።

የፍቅር ጓደኝነት መመሥረት የምትፈልገው ለምንድን ነው?

በብዙ ባሕሎች ውስጥ አንድ ወንድና አንዲት ሴት የፍቅር ጓደኝነት መመሥረታቸው በሚገባ ለመተዋወቅ እንደሚያስችላቸው ጥሩ አጋጣሚ ተደርጎ ይታያል። ይሁን እንጂ የፍቅር ጓደኝነት የሚመሠረትበት ዓላማ ክብር ያለው መሆን ይኖርበታል፤ ዓላማው አንድ ወንድና አንዲት ሴት በትዳር መጣመር ይችሉ እንደሆነና እንዳልሆነ ለመወሰን የሚያስችል አጋጣሚ መፍጠር ሊሆን ይገባል።

እርግጥ ነው፣ አንዳንድ እኩዮችህ የፍቅር ጓደኝነት መመሥረትን በቁም ነገር አይመለከቱት ይሆናል። ምናልባትም ምንም የጋብቻ እቅድ ሳይኖራቸው ተቃራኒ ፆታ ካለው አንድ ግለሰብ ጋር ልዩ ቅርርብ መፍጠር ያስደስታቸው ይሆናል። እንዲያውም አንዳንዶች እንዲህ ዓይነት ጓደኝነት የሚመሠርቱት ተፈላጊ መሆናቸውን ለማሳየት ሊሆን ይችላል፤ አሊያም ከተቃራኒ ፆታ ጋር አብረው መታየቱን እንደ ጀብዱ ይቆጥሩት ይሆናል። ይሁንና ይህ ዓይነቱ ጓደኝነት አብዛኛውን ጊዜ በአጭሩ ይቀጫል። ሄዘር የተባለች አንዲት ወጣት “የፍቅር ጓደኝነት የመሠረቱ ብዙ ወጣቶች በአንድ ወይም በሁለት ሳምንት ጊዜ ውስጥ ይለያያሉ” በማለት ተናግራለች። አክላም እንዲህ ብላለች፦ “እነዚህ ወጣቶች የፍቅር ጓደኝነትን የሚመለከቱት ጊዜያዊ እንደሆነ አድርገው ነው፤ በመሆኑም እንዲህ ያለው ግንኙነት ለፍቺ እንጂ ለትዳር ሕይወት አያዘጋጃቸውም።”

ከአንዲት ወጣት ጋር የፍቅር ጓደኝነት ስትጀምር ስሜቷን ግምት ውስጥ ማስገባት ይኖርብሃል። ዓላማህ ጤናማ ሊሆን ይገባል። እስቲ አስበው፦ አንድ ልጅ አሻንጉሊቱን ሲፈልግ እያነሳ እንደሚጫወትበትና ሲሰለቸው ደግሞ እንደሚጥለው ሁሉ አንድ ሰውም በስሜትህ እንዲጫወት ትፈልጋለህ? ቼልሲ የተባለች ወጣት እንዲህ ብላለች፦ “የፍቅር ጓደኝነት የሚመሠረተው ደስ የሚል ስሜት ስለሚፈጥር ብቻ እንደሆነ የሚሰማኝ ጊዜ አለ። ይሁን እንጂ አንደኛው ወገን ጓደኝነቱን በቁም ነገር እየተመለከተው ሌላኛው እንደ ዋዛ የሚያየው ከሆነ እንዲህ ዓይነቱ ግንኙነት የደስታ ስሜት ይፈጥራል ብሎ ማሰብ ከባድ ነው።”

ለመሆኑ ዕድሜህ ስንት ነው?

ወጣቶች በስንት ዓመታቸው የፍቅር ጓደኝነት ቢጀምሩ ጥሩ ነው ትላለህ? ․․․․․

ይህንኑ ጥያቄ ለወላጆችህ ካቀረብክላቸው በኋላ የሚሰጡህን መልስ ጻፍ። ․․․․․

አንተ የጻፍከው ዕድሜ ወላጆችህ ከነገሩህ ያነሰ እንደሚሆን መገመት ይቻላል። በእርግጥ ላያንስም ይችላል። የማያንስ ከሆነ፣ ትክክለኛ ፍላጎታቸውን በደንብ የሚያውቁበት ዕድሜ ላይ እስኪደርሱ ድረስ የፍቅር ጓደኝነት ከመመሥረት በመቆጠብ አስተዋይነት የሚንጸባረቅበት ውሳኔ ካደረጉት በርካታ ወጣቶች አንዱ ነህ ማለት ነው። የ17 ዓመቷ ዳንየል እንዲህ ዓይነት ውሳኔ አድርጋለች። እንዲህ ብላለች፦ “ከሁለት ዓመት በፊት የነበረኝን አመለካከት መለስ ብዬ ሳስበው የትዳር ጓደኛዬ እንዲሆን ከምፈልገው ሰው እጠብቀው የነበረው ነገር አሁን ከምፈልገው በጣም የተለየ ነው። በመሠረቱ አሁንም እንኳ እንዲህ ዓይነቱን ውሳኔ ማድረግ እችላለሁ ብዬ በራሴ አልተማመንም። ለተወሰኑ ዓመታት ራሴን ከፈተሽኩ በኋላ የሰከነ አቋም እንዳለኝ እርግጠኛ ስሆን ያን ጊዜ የፍቅር ጓደኝነት ስለ መመሥረት ማሰብ እጀምራለሁ።”

የፍቅር ጓደኝነት ለመመሥረት አለመጣደፍ የጥበብ እርምጃ ነው የምንልበት ሌላም ምክንያት አለ። መጽሐፍ ቅዱስ፣ የፆታ ፍላጎትና የፍቅር ስሜት የሚያይልበትን ጊዜ ለማመልከት “አፍላ የጉርምስና ዕድሜ” የሚለውን ሐረግ ይጠቀማል። (1 ቆሮንቶስ 7:36) ‘በአፍላ የጉርምስና ዕድሜ’ ላይ እያለህ ከአንዲት ወጣት ጋር ልዩ ቅርርብ መፍጠርህ የፆታ ስሜትህን ይበልጥ ሊያቀጣጥለውና መጥፎ ድርጊት ወደ መፈጸም ሊመራህ ይችላል። እርግጥ ለእኩዮችህ ይህ ምንም ማለት ላይሆን ይችላል። አብዛኞቹ የፆታ ግንኙነት የመፈጸም ከፍተኛ ፍላጎት አላቸው። አንተ ግን እንዲህ ዓይነቱ አመለካከት ተጽዕኖ እንዳያሳድርብህ ማድረግ ትችላለህ። (ሮም 12:2) መጽሐፍ ቅዱስ ‘የፆታ ብልግና ከመፈጸም እንድትርቅ’ ያሳስብሃል። (1 ቆሮንቶስ 6:18 ኒው ኢንተርናሽናል ቨርዥን) ‘አፍላ የጉርምስና ዕድሜህ’ እስኪያልፍ ድረስ የፍቅር ጓደኝነት ከመመሥረት በመቆጠብ ‘ክፉ ነገርን ማስወገድ’ ትችላለህ።​—መክብብ 11:10

ለማግባት ዝግጁ ነህ?

ይህንን ጥያቄ ለመመለስ እንድትችል ከዚህ በታች ከተዘረዘሩት ነጥቦች አኳያ ራስህን በጥንቃቄ መርምር፦

ከሌሎች ጋር ያለህ ግንኙነት፦ ከወላጆችህ ብሎም ከወንድሞችህና ከእህቶችህ ጋር ያለህ ግንኙነት ምን ይመስላል? ብዙ ጊዜ ከእነሱ ጋር ስትነጋገር ከቁጥጥር ውጭ ትሆናለህ? ምናልባትም ስሜትህን ለመግለጽ ሻካራ ቃል ወይም የሽሙጥ አነጋገር ትጠቀማለህ? በዚህ ረገድ እነሱ ስለ አንተ ምን ይላሉ? የቤተሰብህን አባላት የምትይዝበት መንገድ የትዳር ጓደኛ ብትኖርህ እንዴት እንደምትይዛት ይጠቁማል።​—ኤፌሶን 4:31⁠ን አንብብ።

አመለካከትህ፦ ለነገሮች ያለህ አመለካከት አዎንታዊ ነው ወይስ አሉታዊ? ምክንያታዊ ነህ ወይስ ሁልጊዜ እኔ ያልኩት ካልሆነ ትላለህ? ውጥረት የሚፈጥሩ ሁኔታዎችን በረጋ መንፈስ መያዝ ትችላለህ? ትዕግሥተኛ ነህ? የአምላክን መንፈስ ፍሬ ከአሁኑ ለማፍራት ጥረት ማድረግህ ትዳር ስትመሠርት ጥሩ ባል ለመሆን ይረዳሃል።​—ገላትያ 5:22, 23⁠ን አንብብ።

የገንዘብ አያያዝ፦ በገንዘብ አያያዝ ረገድ እንዴት ነህ? ብዙ ጊዜ ትበደራለህ? በአንድ ሥራ ላይ መቆየት ትችላለህ? ካልሆነ ምክንያቱ ምንድን ነው? የሥራው ጸባይ ነው ወይስ የአሠሪህ ባሕርይ? ወይስ ማስተካከል የሚያስፈልጉህ አንዳንድ መጥፎ ባሕርያት ወይም ልማዶች አሉህ? ከአሁኑ ገንዘብ አያያዝ ካልተማርክ እንዴት አድርገህ ቤተሰብ ማስተዳደር ትችላለህ?​—1 ጢሞቴዎስ 5:8⁠ን አንብብ።

መንፈሳዊነት፦ የይሖዋ ምሥክር ከሆንክ ጥሩ መንፈሳዊ አቋም አለህ? ማንም ሳይጎተጉትህ የአምላክን ቃል ለማንበብ፣ በአገልግሎት ለመካፈልና በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ ለመሳተፍ ጥረት ታደርጋለህ? የምታገባት ሴት ጠንካራ መንፈሳዊ አቋም ያለው ባል ያስፈልጋታል ቢባል አትስማማም?​—መክብብ 4:9, 10⁠ን አንብብ።

ማድረግ የምትችለው ነገር

ዝግጁ ሳትሆን የፍቅር ጓደኝነት እንድትጀምር የሚደረግብህ ጫና በደንብ ያልተማርከውን ትምህርት እንድትፈተን ከመገደድ ጋር ሊመሳሰል ይችላል። ይህ ምክንያታዊ እንዳልሆነ ግልጽ ነው! ፈተና ላይ የሚቀርቡትን ጥያቄዎች መመለስ እንድትችል ትምህርቱን ለማጥናት ጊዜ ያስፈልግሃል።

የፍቅር ጓደኝነት በመመሥረት ረገድም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። ቀደም ሲል እንደተመለከትነው የፍቅር ጓደኝነት መመሥረት እንደ ዋዛ የሚታይ ነገር አይደለም። በመሆኑም ከአንዲት ወጣት ጋር የፍቅር ጓደኝነት ስለመጀመር ከማሰብህ በፊት በጣም አስፈላጊ የሆነን አንድ “ትምህርት” ለማጥናት ይኸውም ወዳጅነት መመሥረት የሚቻልበትን መንገድ ለመማር በቂ ጊዜ ያስፈልግሃል። እንዲህ ካደረግህ ከጊዜ በኋላ የምትሆንህን ወጣት ስታገኝ ጠንካራ ግንኙነት ለመመሥረት የተሻለ አቋም ይኖርሃል። ጥሩ ጋብቻ የሁለት ጥሩ ጓደኛሞች ጥምረት መሆኑን አትዘንጋ።

የፍቅር ጓደኝነት ሳትጀምር መቆየትህ ነፃነትህን እንደሚገድብብህ ማሰብ የለብህም። እንዲያውም ‘የወጣትነትህን ጊዜ አስደሳች’ በሆነ መንገድ ለማሳለፍ የበለጠ ነፃነት ይሰጥሃል። (መክብብ 11:9) ከዚህም በተጨማሪ ጥሩ ባሕርያትን በማዳበርና ከምንም በላይ ደግሞ መንፈሳዊነትህን በማጠናከር ራስህን ለማዘጋጀት የሚያስችል ጊዜ ይኖርሃል።​—ሰቆቃወ ኤርምያስ 3:27

እስከዚያው ድረስ ግን ተቃራኒ ፆታ ካላቸው ወጣቶች ጋር ጥሩ ጊዜ ማሳለፍ ትችላለህ። ይህን ለማድረግ ከሁሉ የተሻለው መንገድ ምንድን ነው? ትልልቅ ሰዎች ባሉበት በቡድን ሆኖ (ከወንዶችም ሆነ ከሴቶች ጋር) መጫወት ይቻላል። ታሚ የተባለች ወጣት እንዲህ ብላለች፦ “እንደዚያ ሲሆን ይበልጥ የሚያስደስት ይመስለኛል። ብዙ ጓደኞች ቢኖሩን የተሻለ ነው።” ሞኒካም በዚህ ሐሳብ ትስማማለች። “በቡድን ሆኖ መጫወት በጣም ጥሩ ነው፤ ምክንያቱም የተለያየ ባሕርይ ያላቸውን ሰዎች ማወቅ ትችላላችሁ” በማለት ተናግራለች።

በሌላ በኩል ግን ያለ ዕድሜህ በአንድ ሰው ላይ ብቻ ትኩረት የምታደርግ ከሆነ ራስህን ለአደጋ ታጋልጣለህ። ስለዚህ አትቸኩል። ከዚህ ይልቅ ይህንን ዕድሜህን ወዳጅነት መመሥረትና ዘላቂ እንዲሆን ማድረግ የምትችለው እንዴት እንደሆነ ለመማር ተጠቀምበት። እንዲህ ካደረግህ አንድ ቀን የፍቅር ጓደኝነት ለመመሥረት ስትወስን የራስህን ፍላጎትም ሆነ የዕድሜ ልክ የትዳር አጋርህ ከምትሆነው ሴት የምትጠብቃቸውን ባሕርያት በሚገባ ታውቃለህ።

ተጨማሪ ሐሳብ ለማግኘት የዚህን መጽሐፍ ጥራዝ 1 ምዕራፍ 29 እና 30 ተመልከት

በሚቀጥለው ምዕራፍ

ወላጆችህ ሳያውቁ የፍቅር ጓደኝነት ለመጀመር ተፈትነሃል? እንዲህ ማድረግ ከምታስበው በላይ ብዙ ችግሮች ያስከትላል።

ቁልፍ ጥቅስ

“አስተዋይ ግን ርምጃውን ያስተውላል።”​—ምሳሌ 14:15

ጠቃሚ ምክር

የፍቅር ጓደኝነት ለመጀመርና ጋብቻ ለመመሥረት ዝግጁ መሆን እንድትችል 2 ጴጥሮስ 1:5-7⁠ን ካነበብክ በኋላ ልታዳብረው የሚገባህን አንድ ባሕርይ ምረጥ። ከአንድ ወር በኋላ ስለዚህ ባሕርይ ምን ያህል እንዳወቅክና ይህን ባሕርይ በማዳበር ረገድ ምን ማሻሻያ እንዳደረክ ራስህን ገምግም።

ይህን ታውቅ ነበር?

በርካታ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ከሆነ ዕድሜያቸው 20 ዓመት ሳይሞላ ትዳር የሚመሠርቱ ወጣቶች በአምስት ዓመት ጊዜ ውስጥ የመፋታታቸው አጋጣሚ ሰፊ ነው።

ላደርጋቸው ያሰብኳቸው ነገሮች

ለጋብቻ ዝግጁ ለመሆን የሚከተሉትን ባሕርያት ማዳበር ያስፈልገኛል፦ ․․․․․

እነዚህን ባሕርያት ለማፍራት እንዲህ አደርጋለሁ፦ ․․․․․

ከዚህ ርዕሰ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ወላጆቼን ልጠይቃቸው የምፈልገው ነገር ․․․․․

ምን ይመስልሃል?

ተቃራኒ ፆታ ካላቸው ወጣቶች ጋር አብረህ ጊዜ ለማሳለፍ ምን ብታደርግ የተሻለ ነው?

ያለ ዕድሜው የፍቅር ጓደኝነት ለመጀመር የሚፈልግ ወንድም ካለህ እርምጃው ትክክል እንዳልሆነ ልታስረዳው የምትችለው እንዴት ነው?

የማግባት ሐሳብ ሳይኖርህ ከአንዲት ወጣት ጋር የፍቅር ጓደኝነት ብትመሠርት ስሜቷን ልትጎዳ የምትችለው እንዴት ነው?

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

እንደ እኔ አመለካከት፣ ከአንድ ሰው ጋር የፍቅር ጓደኝነት መጀመር የሚኖርባችሁ ያንን ሰው በሕይወታችሁ ውስጥ ትልቅ ቦታ የምትሰጡት ከሆነና ወደፊት አብራችሁ መኖር እንደምትችሉ ከተሰማችሁ ነው። ትኩረታችሁን የሳበው ግለሰቡ እንጂ የፍቅር ጓደኝነት መመሥረቱ አይደለም።”​—አምበር

[በገጽ 16 እና 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አንድ ልጅ አዲስ አሻንጉሊት ሲያገኝ ተጫውቶበት ሲሰለቸው እንደሚጥለው ሁሉ አንተም የማግባት እቅድ ሳይኖርህ የፍቅር ጓደኝነት የምትመሠርት ከሆነ በሌላ ሰው ስሜት እየተጫወትክ ነው