በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ስሜቴን መቆጣጠር የምችለው እንዴት ነው?

ስሜቴን መቆጣጠር የምችለው እንዴት ነው?

ምዕራፍ 26

ስሜቴን መቆጣጠር የምችለው እንዴት ነው?

‘እሳት ጠቃሚ ነው ወይስ ጎጂ?’ ተብለህ ብትጠየቅ ምን ብለህ ትመልሳለህ? ‘ሊጠቅምም ሊጎዳም ይችላል’ ብለህ ትመልስ ይሆናል። ቀዝቃዛ በሆነ ምሽት እሳት ማንደድ ሙቀት ለማግኘት ስለሚረዳ ጠቃሚ ነው። ጥንቃቄ ካልተደረገ ግን እሳቱ ከቁጥጥር ውጭ ሊሆንና ቤቱን ሊያወድመው ስለሚችል ጎጂም ሊሆን ይችላል።

ስሜትህን በተመለከተም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። ስሜትህን መቆጣጠር ከቻልክ ከሌሎች ጋር ሞቅ ያለ ወዳጅነት በመመሥረት ጥቅም ማግኘት ትችላለህ። ስሜትህን የማትቆጣጠረው ከሆነ ግን አንተ ብቻ ሳትሆን ሌሎች ሰዎችም ሊጎዱ ይችላሉ።

በጉርምስና ዕድሜ ላይ ስትሆን አንዳንድ ጊዜ በቁጣ ትገነፍል ወይም በሐዘን ስሜት ትዋጥ ይሆናል። እነዚህን ስሜቶች መቆጣጠር የምትችለው እንዴት ነው? ይህን ማድረግ የምትችለው እንዴት እንደሆነ እስቲ ተራ በተራ እንመልከት።

ቁጣን ማብረድ

ሰዎች ተገቢ ያልሆነ ነገር ሲያደርጉብህ ስሜትህ እንደሚጎዳ የታወቀ ነው፤ በዚህ ጊዜ የደረሰብህን የስሜት ጉዳት መቋቋም ቀላል ላይሆንልህ ይችላል። አንዳንዶች እንደዚህ ዓይነት ሁኔታ ሲያጋጥማቸው ራሳቸውን መቆጣጠር ያቅታቸዋል። መጽሐፍ ቅዱስም “ግልፍተኛ” እና “ቍጡ” ስለሆኑ ሰዎች ይናገራል። (ምሳሌ 22:24፤ 29:22) ይህ በቀላሉ የሚታይ ጉዳይ አይደለም። ቁጣህን መቆጣጠር ካልቻልክ፣ በኋላ ላይ የምትጸጸትበት እርምጃ ልትወስድ ትችላለህ። ታዲያ ሌሎች ተገቢ ያልሆነ ነገር ሲያደርጉብህ ስሜትህን መቆጣጠር የምትችለው እንዴት ነው?

በመጀመሪያ ጉዳዩን በሐቀኝነት ለማየት ሞክር፤ ከልብህ ጋር በመነጋገር ጉዳዩ በአንተ ማለቅ ይችል እንደሆነ አስብ። * (መዝሙር 4:4) “በክፉ ፋንታ ክፉ” መመለስ ችግሩን ከማባባስ ውጭ የሚያመጣው ጥቅም እንደሌለ አስታውስ። (1 ተሰሎንቄ 5:15) ጉዳዩን በጥሞና ካሰብክበት እንዲሁም ከጸለይክበት በኋላ ቅሬታህን እርግፍ አድርገህ መተዉ የተሻለ እንደሆነ ይሰማህ ይሆናል። እንዲህ ካደረግህ ቁጣህ አይቆጣጠርህም።​—መዝሙር 37:8

ይሁንና ቅሬታው ከውስጥህ አልወጣ ካለህስ? መጽሐፍ ቅዱስ “ለዝምታ ጊዜ አለው፤ ለመናገርም ጊዜ አለው” ይላል። (መክብብ 3:7) የጎዳህን ሰው ቀርበህ ማናገር ትችል ይሆን? እንዲህ ማድረጉ ጥሩ ካልሆነ ለወላጆችህ ወይም ጎልማሳ ለሆነ አንድ የምትቀርበው ሰው የሚሰማህን ልትናገር ትችላለህ። አንድ ልጅ ሆን ብሎ የሚያበሳጭህን ነገር የሚያደርግ ከሆነ ከሌሎች በተለየ ይህን ግለሰብ በደግነት ለመያዝ ጥረት አድርግ። በሌላ በኩል ደግሞ አንዳንድ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙህ በስሜታዊነት እርምጃ የመውሰድ አዝማሚያ ይኖርህ ይሆናል፤  በገጽ 221 ላይ የሚገኘው ሠንጠረዥ ከላይ ከተገለጸው ሐሳብ በተጨማሪ ልትወስዳቸው የምትችላቸውን እርምጃዎች ለማሰብ ይረዳሃል።

በጎዳህ ግለሰብ ላይ ቂም እንዳትይዝ እንዲረዳህ ይሖዋን ከመጠየቅ ወደኋላ አትበል። አንድ ነገር አስታውስ፦ የተፈጠረውን ሁኔታ መለወጥ ባትችልም ለሁኔታው የምትሰጠውን ምላሽ ግን መለወጥ ትችላለህ። ቂም የምትቋጥር ከሆነ በመንጠቆ እንደተያዘ ዓሣ ትሆናለህ፤ ዓሣውን የሚቆጣጠረው መንጠቆውን የያዘው ግለሰብ እንደሆነ ሁሉ የአንተንም አስተሳሰብና ስሜት የሚቆጣጠረው ሌላ ሰው ይሆናል። ከዚህ በተለየ መልኩ ስሜትህን የምትቆጣጠረው አንተ ራስህ ብትሆን አትመርጥም?​—ሮም 12:19

የሐዘን ስሜትን መቋቋም

“ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ስሜቴ ቶሎ ቶሎ ይቀያየርብኛል፤ በዚያ ላይ ደግሞ ከሚገባው በላይ ራሴን እኮንናለሁ” በማለት የ16 ዓመቷ ሎራ ትናገራለች። አክላም “ጨርሶ ደስተኛ አይደለሁም። እንቅልፍ እስኪወስደኝ ድረስ አለቅሳለሁ” ብላለች። እንደ ሎራ ሁሉ በርካታ ወጣቶች በሕይወታቸው ውስጥ የሚያጋጥሟቸው ነገሮች የሚያሳድሩት ጫና ከአቅማቸው በላይ እንደሆነ ይሰማቸዋል። አንተስ? ወላጆችህ፣ ጓደኞችህና አስተማሪዎችህ የሚጠብቁብህ ነገሮች ወይም ከጉርምስና ዕድሜ ጋር ተያይዘው የሚመጡት አካላዊና ስሜታዊ ለውጦች አሊያም ደግሞ ባሉብህ ጥቃቅን ድክመቶች የተነሳ የሚሰማህ የከንቱነት ስሜት በሐዘን እንድትዋጥ አድርጎህ ይሆን?

አንዳንድ ወጣቶች በውስጣቸው ያለውን የስሜት ሥቃይ ለማስታገስ በማሰብ በአካላቸው ላይ ጉዳት ያደርሳሉ። * እንዲህ የማድረግ ልማድ ካለህ መንስኤውን ለማወቅ ሞክር። ብዙውን ጊዜ ሰዎች በአካላቸው ላይ ጉዳት የሚያደርሱበት አንዱ ምክንያት የሚሰማቸውን ጭንቀት ለመቋቋም ሲሉ ነው። ምናልባት ከቤተሰብህ ወይም ከጓደኞችህ ጋር በተያያዘ እንድትጨነቅ ያደረገህ ሁኔታ አለ?

መጥፎ ስሜት ሲያድርብህ ሁኔታውን ለመቋቋም ከሚረዱህ ግሩም መንገዶች አንዱ ወላጆችህን ወይም በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ የሚገኝን አንድ የጎለመሰ ሰው ማነጋገር ነው፤ እንዲህ ያለው ሰው ‘ለክፉ ቀን እንደተወለደ’ ወዳጅ ሊሆንልህ ይችላል። (ምሳሌ 17:17) የ16 ዓመቷ ሊሊያና በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ለሚገኙ አንዳንድ የጎለመሱ እህቶች የልቧን አውጥታ አጫወተቻቸው። “በዕድሜ ከእኔ ስለሚበልጡ ጠቃሚ ምክር ይሰጡኛል። አሁን ጓደኛሞች ሆነናል” ብላለች። * የ15 ዓመቷ ዲና፣ በክርስቲያናዊው አገልግሎት የምታደርገውን ተሳትፎ ከፍ ማድረጓ በተወሰነ መጠን እፎይታ እንዳስገኘላት ትናገራለች። “ከዚህ የተሻለ ላደርገው የምችለው ነገር አልነበረም። በሕይወቴ ውስጥ እንደዚያን ጊዜ ተደስቼ አላውቅም!” ብላለች።

ከሁሉ በላይ ደግሞ የሐዘን ወይም የጭንቀት ስሜት ሲሰማህ ከመጸለይ ወደኋላ አትበል። ብዙ መከራዎች የደረሱበት መዝሙራዊው ዳዊት “የከበደህን ነገር በእግዚአብሔር ላይ ጣል፤ እርሱ ደግፎ ይይዝሃል” ሲል ጽፏል። (መዝሙር 55:22) ይሖዋ በምን ዓይነት ሥቃይ ውስጥ እንዳለህ ያውቃል። ከዚያም በላይ ‘ስለ አንተ ያስባል።’ (1 ጴጥሮስ 5:7) ልብህ የሚኮንንህ ከሆነ ‘አምላክ ከልብህ ይበልጥ ታላቅ እንደሆነና ሁሉንም ነገር እንደሚያውቅ’ አስታውስ። (1 ዮሐንስ 3:20) የተጨነቅህበትን ምክንያት ከአንተ ይበልጥ የሚረዳልህ ከመሆኑም ሌላ ሸክም የሆነብህን የሐዘን ስሜት ያቀልልሃል።

የሚሰማህ የሐዘን ስሜት በተወሰነ ጊዜ ውስጥ ሊወገድ ካልቻለ ምናልባት እንደ መንፈስ ጭንቀት ያለ የጤና እክል ይኖርብህ ይሆናል። * እንዲህ ያለ የጤና እክል ካለብህ የሕክምና እርዳታ ማግኘትህ የተሻለ ነው። ጉዳዩን ችላ ማለት የመኪናው ሞተር ችግር እንዳለው የሚጠቁመውን ድምፅ ላለመስማት ስትል የመኪናውን ሬዲዮ ድምፅ ከፍ እንደማድረግ ነው። ለችግሩ መፍትሔ መፈለጉ እጅግ የተሻለ ይሆናል። እውነቱን ለመናገር፣ የመንፈስ ጭንቀት ስለያዘህ የምትሳቀቅበት ምንም ምክንያት የለም። የመንፈስ ጭንቀትም ሆነ ከዚያ ጋር የተያያዙ የጤና እክሎች ያሉባቸው በርካታ ወጣቶች የሕክምና እርዳታ አግኝተዋል።

ስሜትህ ከእሳት ጋር እንደሚመሳሰል አትዘንጋ። ከተቆጣጠርከው ይጠቅምሃል፤ ዝም ብለህ ከተውከው ግን ይጎዳሃል። ስሜትህ ከቁጥጥር ውጭ እንዳይሆንብህ የተቻለህን ጥረት አድርግ። እውነት ነው፣ በኋላ ላይ እንድትቆጭ የሚያደርግህን አንድ ነገር መናገርህ ወይም ማድረግህ አይቀርም። ያም ቢሆን ተስፋ አትቁረጥ። ስሜትህ እንዲቆጣጠርህ ከመፍቀድ ይልቅ ስሜትህን መቆጣጠርን በጊዜ ሂደት ትማራለህ።

በሚቀጥለው ምዕራፍ

ከራስህ ፍጽምና ትጠብቃለህ? ከሆነ ስህተት ስትሠራ የሚሰማህን መጥፎ ስሜት እንዴት መቋቋም ትችላለህ?

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.8 ጉልበተኞች ጥቃት የሚሰነዝሩብህ ከሆነ ምን ማድረግ እንደምትችል ለማወቅ ምዕራፍ 14⁠ን ተመልከት። በሌላ በኩል ደግሞ አንድ ጓደኛህ የሚያበሳጭህ ነገር አድርጎብህ ከሆነ በምዕራፍ 10 ላይ የሚገኘውን ሐሳብ ጠቃሚ ሆኖ ታገኘው ይሆናል።

^ አን.13 አንዳንዶች ሆን ብለው ሰውነታቸውን በመቁረጥ፣ በማቃጠል ወይም በመቧጨር ራሳቸውን የሚጎዱ ከመሆኑም ሌላ ሰውነታቸው እስኪበልዝ ድረስ አካላቸውን የሚጎዱ ሌሎች ነገሮች ያደርጋሉ።

^ አን.14 ፊት ለፊት መነጋገር የሚከብድህ ከመሰለህ ደብዳቤ በመጻፍ ወይም ስልክ በመደወል ሐሳብህን መግለጽ ትችላለህ። ስሜትህን ለሌሎች መግለጽህ ከጭንቀትህ ለመላቀቅ የሚረዳህ ጠቃሚ እርምጃ ነው።

^ አን.16 ስለ መንፈስ ጭንቀት ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት የዚህን መጽሐፍ ጥራዝ 1 ምዕራፍ 13 ተመልከት።

ቁልፍ ጥቅስ

“በክፉ አትሸነፍ፤ ከዚህ ይልቅ ምንጊዜም ክፉውን በመልካም አሸንፍ።”​—ሮም 12:21

ጠቃሚ ምክር

ትንሽም ቢሆን እንኳ ያጋጠመህን ደስ የሚያሰኝ ነገር በየቀኑ ለወላጆችህ ንገራቸው። እንዲህ ካደረግህ ከበድ ያለ ችግር ሲያጋጥምህ እነሱን ማናገር አይከብድህም። እነሱም ቢሆኑ የምትነግራቸውን ማዳመጥ ይበልጥ ቀላል ይሆንላቸዋል።

ይህን ታውቅ ነበር?

ሰውነትህ በቂ እረፍትና የተመጣጠነ ምግብ ካላገኘ ስሜትህን መቆጣጠር አስቸጋሪ ሊሆንብህ ይችላል።

ላደርጋቸው ያሰብኳቸው ነገሮች

ብዙ ጊዜ የሚያስቸግረኝ መጥፎ ስሜት ․․․․․

ይህንን ስሜት ለማሸነፍ እንዲህ አደርጋለሁ፦ ․․․․․

ከዚህ ርዕሰ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ወላጆቼን ልጠይቃቸው የምፈልገው ነገር ․․․․․

ምን ይመስልሃል?

● ከቁጥጥር ውጭ የሆነ ቁጣ አምላክን የሚያሳዝነው ለምንድን ነው?

● ቁጣህን መቆጣጠር አለመቻል የሚጎዳህ እንዴት ነው?

● የሐዘን ስሜትን ለመቋቋም የሚረዱህ አንዳንድ መንገዶች የትኞቹ ናቸው?

[በገጽ 223 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

ከልብ የሚያስብልኝና ሁሉ ነገር ጭልም ሲልብኝ ላናግረው የምችለው ሰው መኖሩን ማወቄ ለእኔ ትልቅ ነገር ነው።”​—ጄኒፈር

[በገጽ 221 ላይ የሚገኝ ሠንጠረዥ/​ሥዕል]

 የመልመጃ ሣጥን

ቁጣህን ተቆጣጠር

ሠንጠረዡን ሙላ

ያጋጠመኝ ሁኔታ

አብሮኝ የሚማር ልጅ አሾፈብኝ

ስሜታዊ እርምጃ

ሙልጭ አድርጎ መስደብ

የተሻለው ምላሽ

ሰምቶ እንዳልሰማ ሆኜ በማለፍ ልጁ ሊያበሳጨኝ እንደማይችል ማሳየት

ያጋጠመኝ ሁኔታ

እህቴ የምወደውን ጫማ ሳታስፈቅደኝ አደረገችው

ስሜታዊ እርምጃ

እኔም የእሷን እቃ ሳላስፈቅድ መውሰድ

የተሻለው ምላሽ

․․․․․

ያጋጠመኝ ሁኔታ

ወላጆቼ የምወደውን ነገር በመከልከል ቀጡኝ

ስሜታዊ እርምጃ

․․․․․

የተሻለው ምላሽ

․․․․․

[በገጽ 220 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ቂም የሚቋጥር ሰው በመንጠቆ እንደተያዘ ዓሣ ነው፤ ሁለቱንም የሚቆጣጠራቸው ሌላ ሰው ነው