ለቲቶ የተጻፈ ደብዳቤ 3:1-15

  • ተገቢ ታዛዥነት ማሳየት (1-3)

  • ለመልካም ሥራ ዝግጁ መሆን (4-8)

  • ሞኝነት ከሚንጸባረቅበት ክርክርና ከኑፋቄ መራቅ (9-11)

  • ለቲቶ የተሰጠ መመሪያና ሰላምታ (12-15)

3  ለመንግሥታትና ለባለሥልጣናት እንዲገዙና እንዲታዘዙ+ እንዲሁም ለመልካም ሥራ ሁሉ ዝግጁ እንዲሆኑ አሳስባቸው፤ 2  ደግሞም ስለ ማንም ክፉ ነገር እንዳይናገሩ፣ ጠበኞች እንዳይሆኑ ከዚህ ይልቅ ምክንያታዊ እንዲሆኑና+ ለሰው ሁሉ ገርነትን በተሟላ ሁኔታ እንዲያንጸባርቁ አሳስባቸው።+ 3  እኛም በአንድ ወቅት የማናመዛዝን፣ የማንታዘዝ፣ የምንስት፣ ለተለያየ ምኞትና ሥጋዊ ደስታ የምንገዛ፣ በክፋትና በቅናት የምንኖር፣ በሰዎች ዘንድ የምንጠላና እርስ በርስ የማንዋደድ ነበርን። 4  ይሁን እንጂ አዳኛችን የሆነው አምላክ ደግነትና+ ለሰው ልጆች ያለው ፍቅር በተገለጠ ጊዜ 5  (እኛ በሠራነው የጽድቅ ሥራ ሳይሆን+ በምሕረቱ)+ እኛን አጥቦ ሕያው በማድረግና በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት በማደስ+ አዳነን።+ 6  ይህን መንፈስ አዳኛችን በሆነው በኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት በእኛ ላይ አትረፍርፎ* አፈሰሰው፤+ 7  ይህን ያደረገው በእሱ ጸጋ አማካኝነት ከጸደቅን+ በኋላ ከተስፋችን ጋር በሚስማማ ሁኔታ የዘላለም ሕይወትን+ እንድንወርስ ነው።+ 8  እነዚህ ቃላት እምነት የሚጣልባቸው ናቸው፤ ደግሞም በአምላክ ያመኑ ሁሉ መልካም ሥራዎችን በመሥራት ላይ እንዲያተኩሩ እነዚህን ጉዳዮች በተመለከተ ዘወትር አስረግጠህ እንድትናገር እፈልጋለሁ። እነዚህ ነገሮች መልካምና ለሰዎች ጠቃሚ ናቸው። 9  ሆኖም ሞኝነት ከሚንጸባረቅበት ክርክር፣ ከትውልድ ሐረግ ቆጠራ፣ ከጭቅጭቅና ሕጉን በተመለከተ ከሚነሳ ጠብ ራቅ፤ እነዚህ ነገሮች ምንም የማይጠቅሙና ከንቱ ናቸው።+ 10  ኑፋቄ+ የሚያስፋፋን ሰው ከአንዴም ሁለቴ አጥብቀህ ምከረው።*+ ካልሰማህ ግን ከእሱ ራቅ፤+ 11  እንዲህ ዓይነቱ ሰው ከትክክለኛው መንገድ የወጣና ኃጢአት እየሠራ ያለ ከመሆኑም ሌላ በራሱ ላይ እንደፈረደ እወቅ። 12  አርጤማስን ወይም ቲኪቆስን+ ወደ አንተ ስልክ፣ እኔ ወዳለሁበት ወደ ኒቆጶሊስ ለመምጣት የተቻለህን ሁሉ አድርግ፤ ክረምቱን በዚያ ለማሳለፍ ወስኛለሁና። 13  ሕጉን ጠንቅቆ የሚያውቀው ዜናስም ሆነ አጵሎስ ለጉዟቸው የሚያስፈልጋቸው ነገር ሁሉ እንዲሟላላቸው የተቻለህን ሁሉ ጥረት አድርግ።+ 14  ይሁን እንጂ አሳሳቢ ችግር ሲፈጠር መርዳት እንዲችሉና+ ፍሬ ቢሶች እንዳይሆኑ የእኛም ሰዎች በመልካም ሥራ መጠመድን ይማሩ።+ 15  አብረውኝ ያሉት ሁሉ ሰላምታ ያቀርቡልሃል። ለሚወዱን የእምነት ባልንጀሮቻችን ሰላምታ አቅርብልኝ። የአምላክ ጸጋ ከሁላችሁ ጋር ይሁን።

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “በልግስና።”
ወይም “አስጠንቅቀው።”