በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ለአምላክ መንግሥት የበቁ ሆኖ መቆጠር

ለአምላክ መንግሥት የበቁ ሆኖ መቆጠር

ለአምላክ መንግሥት የበቁ ሆኖ መቆጠር

‘ይህ ሁሉ የአምላክ ፍርድ ቅን መሆኑን የሚያመለክት ነው፤ ለአምላክ መንግሥት የበቃችሁ ሆናችሁ ትቈጠራላችሁ።’—2 ተሰ. 1:5

1, 2. ከፍርድ ጋር በተያያዘ የአምላክ ዓላማ ምንድን ነው? ፈራጁስ ማን ነው?

በ50 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ገደማ ሐዋርያው ጳውሎስ በአቴና ነበር። በዚህ ወቅት በከተማዋ ተስፋፍቶ የተመለከተው የጣዖት አምልኮ በጣም ስላበሳጨው ግሩም የሆነ ምሥክርነት ለመስጠት ተነሳስቷል። ጳውሎስ በንግግሩ መደምደሚያ ላይ የተናገራቸው ቃላት ጣዖት አምላኪ የሆኑትን አድማጮቹን ትኩረት ስበው መሆን አለበት። ጳውሎስ እንዲህ ብሏል:- “አሁን ግን [አምላክ] በየቦታው ያሉ ሰዎች ሁሉ ንስሓ እንዲገቡ ያዛል፤ በመረጠው ሰው አማካይነት በዓለም ላይ በጽድቅ የሚፈርድበትን ቀን ወስኖአልና፤ እርሱንም ከሙታን በማስነሣቱ ለሰዎች ሁሉ ይህን አረጋግጦአል።”—ሥራ 17:30, 31

2 አምላክ በሰው ዘር ላይ የሚበይንበት የፍርድ ቀን ያለ መሆኑ በቁም ነገር ሊታሰብበት የሚገባው ጉዳይ ነው! በዚህ ቀን ፍርዱን የሚያስፈጽመው፣ ጳውሎስ በአቴና ባቀረበው ንግግር ላይ በስም ያልጠቀሰው ከሞት የተነሳው ኢየሱስ ክርስቶስ መሆኑን እናውቃለን። ኢየሱስ የሚበይነው ፍርድ ሕይወት ወይም ሞት ነው።

3. ይሖዋ ከአብርሃም ጋር ቃል ኪዳን የገባው ለምንድን ነው? ይህን ቃል ኪዳን ከዳር ለማድረስ ከፍተኛ ሚና የሚጫወተው ማን ነው?

3 ይህ የፍርድ ቀን ለ1,000 ዓመት ያህል ይቆያል። ኢየሱስ የአምላክ መንግሥት ንጉሥ እንደመሆኑ መጠን ይሖዋን በመወከል የፍርዱን ሂደት በበላይነት ይቆጣጠራል። ይሁንና የሚፈርደው ብቻውን አይደለም። ይሖዋ፣ ለ1,000 ዓመት በሚቆየው የፍርድ ቀን ከኢየሱስ ጋር አብረው የሚነግሡና የሚፈርዱ ሰዎችን መርጧል። (ከሉቃስ 22:29, 30 ጋር አወዳድር።) ይሖዋ ከዛሬ 4,000 ዓመት ገደማ በፊት ከታማኝ አገልጋዩ ከአብርሃም ጋር ቃል ኪዳን በገባበት ወቅት ለዚህ የፍርድ ቀን መሠረት ጥሏል። (ዘፍጥረት 22:17, 18ን አንብብ።) ይህ ቃል ኪዳን በሥራ ላይ መዋል የጀመረው ከ1943 ከክርስቶስ ልደት በፊት አንስቶ ነው። እርግጥ ነው፣ አብርሃም ቃል ኪዳኑ ለሰው ልጆች ምን ትርጉም እንደሚኖረው የተሟላ ግንዛቤ አልነበረውም። እኛ ግን በቃል ኪዳኑ ውስጥ የተጠቀሰው የአብርሃም ዘር፣ አምላክ በሰው ልጆች ላይ ለመፍረድ ያለውን ዓላማ ዳር ለማድረስ ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወት እናውቃለን።

4, 5. (ሀ) የአብርሃም ዋነኛ ዘር ማን ነው? ይህ ዘር ስለ መንግሥቱ ምን ብሏል? (ለ) የአምላክ መንግሥት አባላት የመሆን መብት የተከፈተው ከመቼ ጀምሮ ነው?

4 ዋነኛው የአብርሃም ዘር፣ በ29 ከክርስቶስ ልደት በኋላ በመንፈስ ቅዱስ የተቀባውና ተስፋ የተደረገበት መሲሕ ወይም ክርስቶስ የሆነው ኢየሱስ መሆኑ ተረጋግጧል። (ገላ. 3:16) ኢየሱስ ከተጠመቀ በኋላ ያለውን ሦስት ዓመት ተኩል፣ የመንግሥቱን ምሥራች ለአይሁድ ብሔር በመስበክ አሳልፏል። መጥምቁ ዮሐንስ ከታሰረ በኋላ ኢየሱስ ሰዎች የመንግሥቱ አባላት ለመሆን ተስፋ ሊያደርጉ እንደሚችሉ ሲያመለክት እንዲህ ብሏል:- “ከመጥምቁ ዮሐንስ ዘመን ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ መንግሥተ ሰማይ በብዙ ትገፋለች [‘ሰዎች የሚጋደሉላት ግብ ሆናለች፣’ NW]፤ የሚያገኟትም ብርቱዎች ናቸው።”—ማቴ. 11:12

5 ኢየሱስ መንግሥተ ሰማያትን ‘ስለሚያገኟት’ ሰዎች ከመናገሩ በፊት እንደሚከተለው ማለቱ ትኩረት የሚስብ ነው:- “እውነት እላችኋለሁ፤ ከሴት ከተወለዱት መካከል እንደ መጥምቁ ዮሐንስ ያለ አልተነሣም፤ ሆኖም በመንግሥተ ሰማያት ከሁሉ የሚያንሰው ይበልጠዋል።” (ማቴ. 11:11) ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል? ምክንያቱም በ33 ከክርስቶስ ልደት በኋላ በጰንጠቆስጤ ዕለት መንፈስ ቅዱስ በአምላክ አገልጋዮች ላይ እስከወረደበት ጊዜ ድረስ የአምላክ መንግሥት ገዢዎች የመሆን መብት ሙሉ በሙሉ ክፍት አልነበረም። በዚያን ጊዜ ደግሞ መጥምቁ ዮሐንስ ሞቷል።—ሥራ 2:1-4

የአብርሃም ዘር ጻድቅ ሆኖ ተቆጥሯል

6, 7. (ሀ) የአብርሃም ዘር “እንደ ሰማይ ከዋክብት” የሚሆነው በምን መንገድ ነው? (ለ) አብርሃም ምን በረከት አግኝቷል? ዘሩስ ምን ተመሳሳይ በረከት ያገኛል?

6 አብርሃም፣ ዘሩ “እንደ ሰማይ ከዋክብት” እና በባሕር ዳር እንዳለ አሸዋ እንደሚበዛ ተነግሮት ነበር። (ዘፍ. 13:16፤ 22:17) በሌላ አባባል በአብርሃም ዘመን የነበሩ ሰዎች የዘሩ አባላት ምን ያህል እንደሚሆኑ ማወቅ አይችሉም ነበር። ይሁንና ከጊዜ በኋላ የአብርሃም መንፈሳዊ ዘር አባላት ትክክለኛ ቁጥር ታውቋል። ይህ ዘር ከኢየሱስ በተጨማሪ 144,000 ሰዎችን ያቀፈ ይሆናል።—ራእይ 7:4፤ 14:1

7 የአምላክ ቃል የአብርሃምን እምነት አስመልክቶ ሲናገር “[አብርሃም] እግዚአብሔርን አመነ፤ እርሱም ጽድቅ አድርጎ ቈጠረለት” ይላል። (ዘፍ. 15:5, 6) እርግጥ ነው፣ ፍጹም ጻድቅ የሆነ ሰው የለም። (ያዕ. 3:2) የሆነ ሆኖ አብርሃም ታላቅ እምነት ስለነበረው ይሖዋ ጻድቅ እንደሆነ አድርጎ የቆጠረው ከመሆኑም ሌላ ወዳጄ ሲል ጠርቶታል። (ኢሳ. 41:8) የአብርሃም መንፈሳዊ ዘር አባላት በመሆን ከኢየሱስ ጋር የሚተባበሩት ሰዎችም ጻድቅ ተደርገው ተቆጥረዋል። ይህ ደግሞ አብርሃም ካገኘው የሚበልጥ በረከት ያስገኝላቸዋል።

8. የአብርሃም ዘር አባላት ምን በረከት ያገኛሉ?

8 ቅቡዓን ክርስቲያኖች በኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት ላይ በማመናቸው ጻድቅ ተደርገው ተቆጥረዋል። (ሮሜ 3:24, 28) በይሖዋ ዓይን ከኃጢአት ነጻ እንደሆኑ ተደርገው ይታያሉ። በመሆኑም የአምላክ መንፈሳዊ ልጆችና የኢየሱስ ክርስቶስ ወንድሞች ለመሆን በመንፈስ ቅዱስ ሊቀቡ ይችላሉ። (ዮሐ. 1:12, 13) እነዚህ ክርስቲያኖች ወደ አዲሱ ቃል ኪዳን በመግባት አዲስ ብሔር ማለትም ‘የአምላክ እስራኤል’ ሆነዋል። (ገላ. 6:16፤ ሉቃስ 22:20) ይህ እንዴት ያለ ታላቅ መብት ነው! አምላክ ለእነሱ ሲል ይህን ሁሉ ስላደረገላቸው ቅቡዓን ክርስቲያኖች በምድር ላይ ለዘላለም ለመኖር ተስፋ አያደርጉም። በፍርድ ቀን ከኢየሱስ ጋር መተባበርና በሰማይ ከእሱ ጋር መግዛት ለሚያስገኘው ታላቅ ደስታ ሲሉ በምድር ላይ ለዘላለም ለመኖር ያላቸውን አጋጣሚ መሥዋዕት ያደርጋሉ።ሮሜ 8:17ን አንብብ።

9, 10. (ሀ) ክርስቲያኖች ለመጀመሪያ ጊዜ በመንፈስ ቅዱስ የተቀቡት መቼ ነው? ምን ተስፋስ ተዘርግቶላቸዋል? (ለ) ቅቡዓን ክርስቲያኖች ምን እርዳታ አግኝተዋል?

9 በ33 ከክርስቶስ ልደት በኋላ በዋለው የጰንጠቆስጤ በዓል ላይ የተገኙ ታማኝ የአምላክ አገልጋዮች በፍርድ ቀን ከክርስቶስ ጋር ከሚገዙት ሰዎች መካከል የመሆን መብት ተከፈተላቸው። በዚህ ቀን 120 የሚያህሉ የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት በመንፈስ ቅዱስ በመጠመቅ የመጀመሪያዎቹ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ሆኑ። ይሁን እንጂ ይህ በሰማይ ለሚያገኙት ሽልማት የመጀመሪያ እርምጃ ብቻ ነበር። ከዚያ በኋላ ሰይጣን የትኛውንም ዓይነት ፈተና ቢያመጣባቸው ለይሖዋ ታማኝ መሆናቸውን ማሳየት ነበረባቸው። በሰማይ የሕይወት አክሊል ለማግኘት እስከ ሞት ድረስ ታማኝ መሆን ይጠበቅባቸው ነበር።—ራእይ 2:10

10 ለዚህም ሲባል ይሖዋ በቃሉና በክርስቲያን ጉባኤ አማካኝነት ለቅቡዓን ክርስቲያኖች የሚያስፈልጋቸውን ምክርና ማበረታቻ ሰጥቷቸዋል። ለምሳሌ ያህል፣ ሐዋርያው ጳውሎስ በተሰሎንቄ ለነበሩት ቅቡዓን ክርስቲያኖች እንዲህ በማለት ጽፎላቸዋል:- “አባት ለገዛ ልጆቹ እንደሚሆን እኛም [እያንዳንዳችሁን] . . . ወደ መንግሥቱና ወደ ክብሩ ለጠራችሁ ለእግዚአብሔር እንደሚገባ ትኖሩ ዘንድ አበረታታናችሁ፤ አጽናና[ና]ችሁ፤ አጥብቀንም ለመንናችሁ።”—1 ተሰ. 2:11, 12

11. ይሖዋ ‘ለአምላክ እስራኤል’ አባላት የትኛው ዘገባ በጽሑፍ እንዲሰፍርላቸው አድርጓል?

11 የቅቡዓን ክርስቲያኖች ጉባኤ የመጀመሪያዎቹ አባላት ከተመረጡ በኋላ በነበሩት አሥርተ ዓመታት ውስጥ፣ ይሖዋ የኢየሱስ ምድራዊ አገልግሎትና በመጀመሪያው መቶ ዘመን ከኖሩት ቅቡዓን ክርስቲያኖች ጋር ያለው ግንኙነት፣ እንዲሁም የሰጣቸው ምክር በቋሚ መዝገብ ላይ እንዲሰፍሩ አድርጓል። በዚህ መንገድ፣ ይሖዋ በመንፈስ ቅዱስ አነሳሽነት የተጻፉት የግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ቀደም ብለው በተጻፉት የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ላይ እንዲጨመሩ አደረገ። የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት መጀመሪያ ላይ የተጻፉት ለሥጋዊ እስራኤላውያን ነበር። በዚያን ወቅት ብሔሩ ከይሖዋ ጋር ልዩ ዝምድና ነበረው። የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ደግሞ በዋነኝነት የተጻፉት የክርስቶስ ወንድሞችና የአምላክ መንፈሳዊ ልጆች እንዲሆኑ ለተቀቡት ‘ለአምላክ እስራኤል’ ነው። ይህ ሲባል ግን እስራኤላውያን ያልሆኑ ሰዎች የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍትን በማጥናት ጥቅም ማግኘት አይችሉም ማለት አይደለም። በተመሳሳይም በመንፈስ ቅዱስ ያልተቀቡ ክርስቲያኖች ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍትን በማጥናትና ከምክሮቹ ጋር ተስማምተው በመኖር ይህ ነው የማይባል ጥቅም ማግኘት ይችላሉ።—2 ጢሞቴዎስ 3:15-17ን አንብብ።

12. ጳውሎስ ለቅቡዓን ክርስቲያኖች ምን ማሳሰቢያ ሰጥቷቸዋል?

12 በመጀመሪያው መቶ ዘመን ይኖሩ የነበሩት ክርስቲያኖች ጻድቅ ሆነው የተቆጠሩት እንዲሁም በመንፈስ ቅዱስ የተቀቡት ሰማያዊ ውርሻቸውን እንዲያገኙ ነው። በመንፈስ ቅዱስ መቀባታቸው እዚሁ ምድር ላይ እያሉ በሌሎች ቅቡዓን ወንድሞቻቸው ላይ ነገሥታት እንዲሆኑ አላደረጋቸውም። አንዳንድ የጥንት ክርስቲያኖች ይህንን እውነታ በመዘንጋት በጉባኤ ውስጥ ባሉ ወንድሞቻቸው ላይ ለመሠልጠን ሞክረው እንደነበር ከሁኔታዎች መረዳት ይቻላል። በዚህም ምክንያት ጳውሎስ እንደሚከተለው ለማለት ተገድዷል:- “አሁንስ የሚያስፈልጋችሁን ሁሉ አግኝታችኋል! ሀብታምም ሆናችኋል! ከእኛም ተለይታችሁ ነግሣችኋል! በእርግጥ ብትነግሡማ እኛም ከእናንተ ጋር በነገሥን ነበር።” (1 ቆሮ. 4:8) በመሆኑም ጳውሎስ በዘመኑ የነበሩትን ቅቡዓን “ደስ እንዲላችሁ ከእናንተ ጋር እንሠራለን እንጂ በእምነታችሁ ላይ ለመሠልጠን አይደለም” ብሏቸዋል።—2 ቆሮ. 1:24

በትንቢት የተነገረውን የአምላክ እስራኤል ቁጥር ማሟላት

13. ከ33 ከክርስቶስ ልደት በኋላ የቅቡዓን ክርስቲያኖች መጠራት የተከናወነው እንዴት ነው?

13 ሁሉም 144,000 ቅቡዓን ክርስቲያኖች የተመረጡት በመጀመሪያው መቶ ዘመን አልነበረም። የቅቡዓን ክርስቲያኖች መጠራት በሐዋርያት ዘመን የቀጠለ ሲሆን ከዚያ በኋላ ባሉት በርካታ መቶ ዓመታት የተመረጡት ሰዎች በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታይ ቁጥራቸው አነስተኛ ይመስላል። ይሁንና የቅቡዓን መመረጥ እነዚህን ዓመታት ጨምሮ እስከ ዘመናችንም ድረስ ቀጥሏል። (ማቴ. 28:20) ከዚያም፣ ኢየሱስ በ1914 መግዛት ሲጀምር ሁኔታው ይበልጥ ተፋጠነ።

14, 15. ከቅቡዓን ክርስቲያኖች መጠራት ጋር በተያያዘ በዘመናችን ምን ተፈጽሟል?

14 በመጀመሪያ ኢየሱስ ሰማይን የአምላክን አገዛዝ ከሚቃወም ከማንኛውም ኃይል አጸዳ። (ራእይ 12:10, 12ን አንብብ።) ከዚያም የ144,000ዎቹን ቁጥር ለማሟላት ትኩረቱን የመንግሥቱ አባላት የሚሆኑትን ሰዎች በመሰብሰቡ ሥራ ላይ አደረገ። ይህ የመሰብሰብ ሥራ በ1930ዎቹ አጋማሽ ላይ ወደ መጠናቀቁ የተቃረበ ሲሆን በዚያን ጊዜ ለስብከቱ ሥራ ምላሽ ከሰጡት ሰዎች ውስጥ አብዛኞቹ ወደ ሰማይ የመሄድ ፍላጎት አልነበራቸውም። መንፈስ ቅዱስ የአምላክ ልጆች እንደሆኑ አልመሰከረላቸውም። (ከሮሜ 8:16 ጋር አወዳድር።) ከዚህ ይልቅ እነዚህ ሰዎች ራሳቸውን ገነት በሆነች ምድር ላይ ለዘላለም የመኖር ተስፋ ያላቸው ‘የሌሎች በጎች’ አባላት አድርገው ይቆጥሩ ነበር። (ዮሐ. 10:16) በመሆኑም ከ1935 ወዲህ የስብከቱ ሥራ ሐዋርያው ዮሐንስ በራእይ ያያቸውንና “ከታላቁ መከራ” በሕይወት የሚተርፉትን ‘እጅግ ብዙ ሕዝቦች’ በመሰብሰቡ ሥራ ላይ ያተኮረ ሆነ።—ራእይ 7:9, 10, 14

15 ይሁን እንጂ፣ ከ1930ዎቹ በኋላ ባሉት ዓመታትም አንዳንድ ክርስቲያኖች ለሰማያዊ ተስፋ ተጠርተዋል። ይህ የሆነው ለምንድን ነው? አንዳንዶቹ የተጠሩት ታማኝነታቸውን ባልጠበቁ ቅቡዓን ምትክ ሊሆን ይችላል። (ከራእይ 3:16 ጋር አወዳድር።) ጳውሎስ እሱ የሚያውቃቸው አንዳንድ ግለሰቦች እውነትን መተዋቸውን ተናግሯል። (ፊልጵ. 3:17-19) ታዲያ ይሖዋ ታማኝ ባልሆኑት ምትክ የሚመርጠው እነማንን ነው? እርግጥ ነው፣ ይህን የሚወስነው ይሖዋ ነው። ያም ሆኖ ይሖዋ የሚመርጠው አዳዲስ አማኞችን ሳይሆን፣ ኢየሱስ የመታሰቢያውን በዓል ሲያቋቁም ስለ ደቀ መዛሙርቱ እንደተናገረው፣ ታማኝነታቸውን ያስመሰከሩ ክርስቲያኖችን እንደሚሆን መጠበቃችን ምክንያታዊ ነው። *ሉቃስ 22:28

16. ቅቡዓኑን በተመለከተ አመስጋኞች የምንሆንበት ምን ምክንያት አለን? ምን እንደሚፈጸምስ እርግጠኞች መሆን እንችላለን?

16 ይሁንና ከ1930ዎቹ ጀምሮ ለሰማያዊ ተስፋ የተጠሩት ሁሉም ሰዎች ታማኝነታቸውን ባልጠበቁ ክርስቲያኖች ፈንታ የተተኩ አይመስልም። “ታላቂቱ ባቢሎን” እስከምትጠፋበት እስከዚህ ሥርዓት የመጨረሻ ቀናት ድረስ ቅቡዓን ክርስቲያኖች አብረውን እንደሚሆኑ ይሖዋ ማረጋገጫ ሰጥቶናል። * (ራእይ 17:5) በተጨማሪም፣ ይሖዋ የወሰነው ጊዜ ሲደርስ የ144,000ዎቹ ቁጥር እንደሚሞላና በመጨረሻም ሁሉም በመንግሥቱ ውስጥ ያላቸውን ቦታ እንደሚይዙ እርግጠኞች መሆን እንችላለን። ከዚህም ባሻገር ቁጥሩ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የሚሄደው እጅግ ብዙ ሕዝብ በቡድን ደረጃ እስከመጨረሻው ታማኝ እንደሚሆን የተነገረው ትንቢት እንደሚፈጸም እናምናለን። በቅርቡ ይህ ሕዝብ በሰይጣን ዓለም ላይ ከሚመጣው ‘ታላቅ መከራ በሕይወት ተርፎ’ አምላክ ወዳዘጋጀው አዲስ ዓለም በደስታ ይገባል።

የአምላክ መንግሥት ገዥዎች ቁጥር ሊሞላ ተቃርቧል!

17. በአንደኛ ተሰሎንቄ 4:15-17 እና በራእይ 6:9-11 መሠረት ታማኝ ሆነው የሞቱ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ምን አግኝተዋል?

17 ከ33 ከክርስቶስ ልደት በኋላ አንስቶ በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ጠንካራ እምነት እንዳላቸው ያሳዩ ሲሆን እስከ ሞት ድረስ በታማኝነት ጸንተዋል። እነዚህ ክርስቲያኖች መንግሥትን ለመቀበል የበቁ እንደሆኑ ተደርገው ተቆጥረዋል። ከክርስቶስ መገኘት በኋላ ብዙም ሳይቆይ ሰማያዊ ሽልማታቸውን እንደተቀበሉ ምንም ጥርጥር የለውም።—1 ተሰሎንቄ 4:15-17ን እና ራእይ 6:9-11ን አንብብ።

18. (ሀ) በአሁኑ ጊዜ በምድር ላይ የሚገኙት ቅቡዓን ስለ ምን ነገር እርግጠኞች ናቸው? (ለ) ሌሎች በጎች ቅቡዓን ወንድሞቻቸውን እንዴት ይመለከቷቸዋል?

18 በአሁኑ ጊዜ በምድር ላይ የሚገኙት ቅቡዓን ክርስቲያኖችም በታማኝነት እስከቀጠሉ ድረስ በቅርቡ ሽልማታቸውን እንደሚያገኙ ቅንጣት ታክል አይጠራጠሩም። በሚሊዮን የሚቆጠሩት ሌሎች በጎች የቅቡዓን ወንድሞቻቸውን እምነት ሲመለከቱ ልክ እንደ ሐዋርያው ጳውሎስ ለመናገር ይገፋፋሉ። ጳውሎስ በተሰሎንቄ ይኖሩ ለነበሩት ቅቡዓን ክርስቲያኖች እንዲህ ብሏቸዋል:- “በደረሰባችሁ ስደትና መከራ ሁሉ በመጽናታችሁ፣ እኛ ራሳችን ስለ ትዕግሥታችሁና ስለ እምነታችሁ በእግዚአብሔር አብያተ ክርስቲያናት ዘንድ እንመካለን። ይህ ሁሉ የእግዚአብሔር ፍርድ ቅን መሆኑን የሚያመለክት ነው፤ ከዚህም የተነሣ መከራን ለምትቀበሉለት ለእግዚአብሔር መንግሥት የበቃችሁ ሆናችሁ ትቈጠራላችሁ።” (2 ተሰ. 1:3-5) የመጨረሻው ቅቡዕ ምድራዊ ሕይወቱን የሚያጠናቅቀው መቼም ይሁን መች፣ በዚያን ጊዜ የአምላክ መንግሥት ገዥዎች ቁጥር የተሟላ ይሆናል። ይህ በሰማይም ሆነ በምድር እንዴት ያለ ደስታ ያስገኛል!

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.15 የመጋቢት 1, 1992 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 20 አንቀጽ 17⁠ን ተመልከት።

^ አን.16 በግንቦት 1, 2007 መጠበቂያ ግንብ ላይ የወጣውን “የአንባቢያን ጥያቄዎች” አምድ ተመልከት።

ልታብራራ ትችላለህ?

• አምላክ ከፍርድ ቀን ጋር በተያያዘ ለአብርሃም ምን ገልጾለታል?

• አብርሃም ጻድቅ ተደርጎ የተቆጠረው ለምንድን ነው?

• ጻድቅ ሆኖ መቆጠር የአብርሃም ዘር ለሆኑት ምን ያስገኝላቸዋል?

• ሁሉም ክርስቲያኖች ምን ነገር በእርግጠኝነት መጠበቅ ይችላሉ?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኢየሱስ ተከታዮቹን ወደ መንግሥተ ሰማይ ለመግባት ብርቱ ጥረት እንዲያደርጉ አበረታቷቸዋል

[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በ33 ከክርስቶስ ልደት በኋላ በዋለው የጰንጠቆስጤ በዓል ዕለት ይሖዋ የአብርሃምን ሁለተኛ ደረጃ ዘር መምረጥ ጀመረ

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሌሎች በጎች፣ ቅቡዓን ክርስቲያኖች በመጨረሻዎቹ ቀናት አብረዋቸው በመሆናቸው አመስጋኞች ናቸው