በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የአንባቢያን ጥያቄዎች

የአንባቢያን ጥያቄዎች

የአንባቢያን ጥያቄዎች

ወደ ሰማይ የመሄድ ተስፋ ያላቸው ክርስቲያኖች መጠራት የሚያበቃው መቼ ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ ለዚህ ጥያቄ ግልጽ የሆነ መልስ አይሰጥም። በሰማይ ውርሻ ያላቸው የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት መቀባት የጀመሩት በ33 ከክርስቶስ ልደት በኋላ እንደሆነ እናውቃለን። (የሐዋርያት ሥራ 2:1-4) ከዚህም በላይ ሐዋርያት ከሞቱ በኋላ፣ “በስንዴ” የተመሰሉት እውነተኛ ቅቡዓን ክርስቲያኖች እንደ “እንክርዳድ” ተደርገው ከተገለጹት ሐሰተኛ ክርስቲያኖች ጋር ‘አብረው እንዳደጉ’ እናውቃለን። (ማቴዎስ 13:24-30) ከዚያም ከ1800ዎቹ መገባደጃ አንስቶ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ጎላ ያለ እንቅስቃሴ ማድረግ ጀመሩ። በ1919 መታጨድ የጀመረው “የምድር መከር” የቅቡዓኑን የመጨረሻ አባላት መሰብሰብንም የሚጨምር ነበር።—ራእይ 14:15, 16

ከ1800ዎቹ መገባደጃ እስከ 1931 ባለው ጊዜ ውስጥ የስብከቱ ሥራ የክርስቶስ አካል የሆኑትን ቀሪዎች በመሰብሰብ ላይ ያተኮረ ነበር። በ1931 የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች፣ በቅዱሳን መጻሕፍት ላይ በተመሠረተው የይሖዋ ምሥክሮች በሚለው ስም መጠራት ጀመሩ፤ የኅዳር 15, 1933 መጠበቂያ ግንብ ይህ ልዩ ስም በማቴዎስ 20:1-16 በሚገኘው የኢየሱስ ምሳሌ ላይ የተገለጸውን “ዲናር” እንደሚያመለክት የሚጠቁም ሐሳብ ይዞ ነበር። በምሳሌው ላይ የተገለጹት 12 ሰዓታት ከ1919 እስከ 1931 ያሉትን 12 ዓመታት እንደሚያመለክቱ ይታመን ነበር። ይህ መጠበቂያ ግንብ ከወጣ በኋላ በነበሩት በርካታ ዓመታት፣ በሰማይ በሚገኘው መንግሥት የሚገዙ ሰዎች መጠራት በ1931 እንዳበቃ እንዲሁም በ1930 እና በ1931 ከክርስቶስ ጋር ተባባሪ ገዢዎች እንዲሆኑ የተጠሩት ክርስቲያኖች ‘የመጨረሻዎቹ’ እንደሆኑ ይታመን ነበር። (ማቴዎስ 20:6-8 የ1980 ትርጉም) ይሁን እንጂ በ1966 ይህንን ምሳሌ አስመልክቶ በወጣው ትምህርት ላይ ማስተካከያ በመደረጉ ምሳሌው ከቅቡዓን ጥሪ ማብቃት ጋር ምንም ግንኙነት እንደሌለው ግልጽ ሆነ።

በ1935 በራእይ 7:9-15 ላይ የተገለጸው “እጅግ ብዙ ሕዝብ” ምድራዊ ተስፋ ያላቸው “ሌሎች በጎች” ክፍል እንደሆነ ግልጽ ሆነ፤ ይህ እጅግ ብዙ ሕዝብ የሚሰበሰበው “በመጨረሻው ዘመን” እንደሆነና በቡድን ደረጃ ከአርማጌዶን እንደሚተርፍም ታወቀ። (ዮሐንስ 10:16፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:1፤ ራእይ 21:3, 4) ከዚያ ዓመት በኋላ ደቀ መዛሙርት የማድረጉ ሥራ በዋነኝነት ይህን እጅግ ብዙ ሕዝብ በመሰብሰቡ ላይ ያተኮረ ሆነ። በዚህም የተነሳ በተለይ ከ1966 ወዲህ ባሉት ዓመታት፣ ወደ ሰማይ የመሄድ ተስፋ ያላቸው ክርስቲያኖች መጠራት በ1935 እንዳበቃ ይታመን ነበር። ከ1935 ወዲህ የተጠመቁ ክርስቲያኖች በሙሉ ማለት ይቻላል ምድራዊ ተስፋ እንዳላቸው የሚያምኑ መሆናቸው ይህንን የሚያረጋግጥ ይመስል ነበር። ከዚያ በኋላ ወደ ሰማይ ለመሄድ የተጠሩ ክርስቲያኖች ቢኖሩ ታማኝነታቸውን ያጎደሉ ቅቡዓንን የሚተኩ እንደሆነ ይታመን ነበር።

ከቅቡዓን ክርስቲያኖች አንዱ ኃጢአት ሠርቶ ንስሐ የማይገባ ከሆነ ይሖዋ በእርሱ ምትክ ሌላ ግለሰብ እንደሚጠራ ምንም ጥርጥር የለውም። (ሮሜ 11:17-22) ይሁን እንጂ ታማኝነታቸውን ያጎደሉት እውነተኛ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ቁጥር ብዙ ላይሆን ይችላል። በሌላ በኩል ግን፣ ጊዜ እያለፈ ሲሄድ ከ1935 ወዲህ የተጠመቁ አንዳንድ ክርስቲያኖች ወደ ሰማይ የመሄድ ተስፋ እንዳላቸው መንፈስ ቅዱስ መስክሮላቸዋል። (ሮሜ 8:16, 17) ከዚህ መመልከት እንደምንችለው ወደ ሰማይ የመሄድ ተስፋ ያላቸው ክርስቲያኖች መጠራት የሚያበቃበትን ትክክለኛ ጊዜ መናገር አንችልም።

አንድ ግለሰብ የተቀባ እንደሆነ በልቡ ቢወስንና በመታሰቢያው በዓል ላይ ከምሳሌያዊው ቂጣና ወይን መካፈል ቢጀምር እንዴት ልንመለከተው ይገባል? ጉዳዩ በእርሱና በይሖዋ መካከል ስለሆነ ልንፈርድበት አይገባም። (ሮሜ 14:12) ያም ቢሆን ግን እውነተኛ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ልዩ ትኩረት እንዲሰጣቸው አይፈልጉም። እነዚህ ክርስቲያኖች፣ የተቀቡ መሆናቸው ከአንዳንድ የጎለመሱ የእጅግ ብዙ ሕዝብ አባላት እንኳ የበለጠ ልዩ “ማስተዋል” እንዲኖራቸው እንደሚያደርግ አያምኑም። ባልንጀሮቻቸው ከሆኑት ሌሎች በጎች ይበልጥ መንፈስ ቅዱስ ሊኖራቸው እንደሚገባም አያምኑም። ከዚህም በላይ ሌሎች እንዲያገለግሏቸው አይጠብቁም፤ ወይም ደግሞ ከምሳሌያዊው ቂጣና ወይን መካፈላቸው በጉባኤው ውስጥ ካሉት የተሾሙ ሽማግሌዎች በላይ እንዲሆኑ እንደሚያደርጋቸው አይሰማቸውም። በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ አንዳንድ ቅቡዓን ወንዶች፣ ሽማግሌዎች ወይም የጉባኤ አገልጋዮች ለመሆን ብቁ እንዳልነበሩ በትሕትና ይገነዘባሉ። (1 ጢሞቴዎስ 3:1-10, 12, 13፤ ቲቶ 1:5-9፤ ያዕቆብ 3:1) እንዲያውም አንዳንድ ቅቡዓን ክርስቲያኖች በመንፈሳዊ ደክመው ነበር። (1 ተሰሎንቄ 5:14) ከዚህም በላይ እህቶች የተቀቡ ቢሆኑም እንኳ በጉባኤ አላስተማሩም።—1 ጢሞቴዎስ 2:11, 12

በመሆኑም ቅቡዓን ክርስቲያኖች የሌሎች በጎች አባላት ከሆኑት ባልንጀሮቻቸው ጋር በመሆን በመንፈሳዊ ጠንካራ ሆነው ለመኖር፣ የመንፈስ ፍሬ ለማፍራትና በጉባኤው ውስጥ ሰላም እንዲሰፍን የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ለማድረግ ይጥራሉ። ቅቡዓንም ሆኑ ሌሎች በጎች፣ ክርስቲያኖች በሙሉ የበላይ አካሉ በሚሰጠው መመሪያ መሠረት ምሥራቹን በመስበኩና ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ በትጋት ይካፈላሉ። ቅቡዓን ክርስቲያኖች ይሖዋን እያገለገሉ በምድር ላይ እንዲቆዩ አምላክ እስከፈቀደበት ጊዜ ድረስ ይህን በደስታ ያደርጋሉ።