በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ጊዜ የማይሽረው ጥልቅ ሐዘን

ጊዜ የማይሽረው ጥልቅ ሐዘን

ጊዜ የማይሽረው ጥልቅ ሐዘን

በቅርቡ አንድ ተመራማሪ፣ የሚወዷቸውን ሰዎች በሞት ያጡ ግለሰቦች ጊዜ ቢያልፍም ምን እንደሚሰማቸው ለማወቅ ምርምር አካሂዶ ነበር። ከብዙ ዓመታት በፊት ልጆቻቸውን በሞት ላጡ በርካታ ወላጆች መጠይቆችን ላከ። ለመጠይቁ ምላሽ የሰጡት ግን ሁሉም ወላጆች አልነበሩም። ከአምስት ዓመት በፊት ልጁን በሞት ያጣ ቭላድሚር የተባለ አንድ አባት ስለ ልጁ አንስቶ ማውራት አሁንም በጣም እንደሚከብደው ገልጿል። a

ልጆቻቸውን በሞት ያጡ ወላጆች ሐዘናቸው ለረጅም ጊዜ መቆየቱ ያልተለመደ ነገር አይደለም። ዊልያም የ18 ዓመት ወንድ ልጁ ውኃ ውስጥ ሰምጦ ከሞተ አሥር ዓመታት ቢያልፉም “የልጄ ሐዘን አሁንም በውስጤ አለ፤ በሕይወት እስካለሁ ድረስ ሐዘኑ በልቤ ይኖራል” ሲል ጽፏል። ወንድ ልጇን ከአምስት ዓመታት በፊት በድንገተኛ ሕመም ያጣችው ሉሲ እንዲህ ብላ ጽፋለች:- “ለመጀመሪያዎቹ ጥቂት ቀናት ‘ይህ እውነት ሊሆን አይችልም’ ብዬ አስብ ነበር። መጥፎ ቅዠት እንደሆነና ከጥቂት ጊዜ በኋላ እንደምነቃ ሆኖ ይሰማኝ ነበር። ከጊዜ በኋላ ግን ልጄ ወደ ቤት እንደማይመለስና መሞቱም እውነት እንደሆነ ተገነዘብኩ። ልጄ ከሞተ አምስት ዓመታት ያለፉ ቢሆንም አሁንም አንዳንድ ጊዜ ብቻዬን ስሆን እርሱን እያሰብኩ አለቅሳለሁ።”

እንደ ቭላድሚር፣ ዊልያምና ሉሲ ያሉ በሐዘን የተደቆሱ ወላጆች እንዲህ ያለ ጊዜ የማይሽረው ጥልቅ ሐዘን የሚሰማቸው ለምን እንደሆነ አንዳንድ ምክንያቶችን እንመልከት።

ይህን ያህል ከባድ ሐዘን የሚሰማቸው ለምንድን ነው?

በአንድ ቤተሰብ ውስጥ ልጅ ሲወለድ ወላጆች በየትኛውም ዝምድና ውስጥ የማይገኝ ልዩ ስሜት ይሰማቸዋል። ሕፃን ልጃቸውን በማቀፍ፣ ሲተኛ በማየት ወይም ደስ የሚል ፈገግታውን በመመልከት ታላቅ ደስታና እርካታ ያገኛሉ። አፍቃሪ የሆኑ ወላጆች ልጆቻቸውን ይንከባከባሉ። የታረመና ሥርዓታማ ባሕርይ እንዲኖራቸው ያሠለጥኗቸዋል። (1 ተሰሎንቄ 2:7, 11) ልጆቹም ለእንደዚህ ዓይነቱ ጥረት ምላሽ ሲሰጡ ወላጆች በልጆቻቸው ይኮራሉ፤ እንዲሁም ጥሩ ደረጃ ላይ እንደሚደርሱላቸው ተስፋ ያደርጋሉ።

አሳቢ የሆኑ ወላጆች፣ ልጆቻቸው የሚያስፈልጋቸውን ለማቅረብ ተግተው ይሠራሉ። ልጆቻቸው ወደፊት የራሳቸውን ቤተሰብ እንዲመሠርቱ የሚረዳቸውን ገንዘብ ወይም የሚያስፈልጓቸውን ቁሳዊ ነገሮች አዘውትረው ያጠራቅሙላቸው ይሆናል። (2 ቆሮንቶስ 12:14) ወላጆች ለልጆቻቸው የሚያሳዩት ጥልቅ ስሜት፣ የሚያጠፉት ጊዜ፣ የሚያደርጉት ከፍተኛ ጥረትና የሚያወጡት ገንዘብ አንድ እውነታ ግልጽ ያደርግልናል፤ ወላጆች ልጆቻቸውን የሚያሳድጉት እንዲኖሩ እንጂ እንዲሞቱ አይደለም። አንድ ልጅ ሲሞት ግን አባትና እናት ልጃቸውን በማሳደግ ረገድ ሲያከናውኑት የነበረው ሥራ በአጭሩ ይቀጫል፤ እንዲሁም ተስፋቸው ሁሉ መና ይቀራል። ወላጆች ለልጆቻቸው የሚያሳዩት ጥልቅ ፍቅር በሞት ይገደባል። ለወንድ ወይም ለሴት ልጃቸው በልባቸው ውስጥ ሰጥተውት የነበረው ቦታ ባዶ ይሆናል። ወላጆች በቀላሉ ከልባቸው የማይወጣ ጥልቅ ሐዘን ይሰማቸዋል።

በሐዘን የተደቆሱ ወላጆች በጣም ጥልቅ የሆነና በቀላሉ ከልባቸው የማይወጣ ሐዘን እንደሚገጥማቸው መጽሐፍ ቅዱስ ያረጋግጣል። የእምነት አባት የሆነው ያዕቆብ፣ ልጁ ዮሴፍ እንደተገደለ ሲሰማ ምን እንዳደረገ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ በማለት ይነግረናል:- “ያዕቆብ ልብሱን ቀደደ፤ ማቅም ለብሶ ስለ ልጁ ብዙ ቀን አለቀሰ፤ ወንዶችና ሴቶች ልጆቹም ሁሉ ሊያጽናኑት መጡ፤ እርሱ ግን ሊጽናና ባለመቻሉ ‘በሐዘን እንደ ተኰራመትሁ ልጄ ወዳለበት መቃብር እወርዳለሁ’ አለ።” ዓመታት ካለፉ በኋላም እንኳ ያዕቆብ ሞቷል ብሎ ስላሰበው ልጁ ያዝን ነበር። (ዘፍጥረት 37:34, 35፤ 42:36-38) መጽሐፍ ቅዱስ ሁለት ወንዶች ልጆቿን በሞት ስላጣችው ኑኃሚን ስለተባለች ታማኝ ሴትም ይነግረናል። ይህች ሴት በጣም ከማዘኗ የተነሳ “ደስታዬ” የሚል ትርጉም ያለው ኑኃሚን የተባለው ስሟን “መራራ” የሚል ትርጉም ወዳለው ማራሐ ወደተባለ ስም ለመቀየር ፈልጋ ነበር።—ሩት 1:3-5, 20, 21

ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ ወላጆች ሐዘን እንደሚያጋጥማቸው በመግለጽ ብቻ አይወሰንም። ይሖዋ በሐዘን ላይ ያሉትን እንዴት እንደሚያበረታቸውም ይጠቁማል። አምላክ በሐዘን የተደቆሱ ሰዎችን የሚያጽናናባቸውን አንዳንድ መንገዶች በሚቀጥለው ርዕስ ላይ እንመለከታለን።

[የግርጌ ማስታወሻ]

a አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።