ሩት 1:1-22
1 መሳፍንት+ ፍትሕን ያስፈጽሙ* በነበረበት ዘመን በምድሪቱ ላይ ረሃብ ተከሰተ፤ አንድ ሰው ከሚስቱና ከሁለት ወንዶች ልጆቹ ጋር የባዕድ አገር ሰው ሆኖ ለመኖር በይሁዳ ከምትገኘው ከቤተልሔም+ ተነስቶ ወደ ሞዓብ+ ምድር አቀና።
2 የሰውየው ስም ኤሊሜሌክ፣* የሚስቱ ስም ናኦሚ፣* የሁለቱ ወንዶች ልጆቹ ስም ደግሞ ማህሎን* እና ኪሊዮን* ነበር። እነሱም በይሁዳ በምትገኘው በቤተልሔም የሚኖሩ ኤፍራታውያን ነበሩ። ወደ ሞዓብም መጥተው በዚያ መኖር ጀመሩ።
3 ከጊዜ በኋላም የናኦሚ ባል ኤሊሜሌክ ሞተ፤ ስለሆነም ናኦሚ ከሁለት ልጆቿ ጋር ቀረች።
4 በኋላም ልጆቿ ሞዓባውያን ሴቶችን አገቡ፤ የአንደኛዋ ስም ዖርፋ፣ የሌላኛዋ ደግሞ ሩት+ ነበር። በዚያም ለአሥር ዓመት ያህል ኖሩ።
5 ከዚያም ሁለቱ ወንዶች ልጆቿ ማህሎንና ኪሊዮን ሞቱ፤ ናኦሚም ሁለት ልጆቿንና ባሏን አጥታ ብቻዋን ቀረች።
6 እሷም በሞዓብ ምድር ሳለች ይሖዋ ለሕዝቡ እህል በመስጠት ፊቱን ወደ እነሱ እንደመለሰ ስለሰማች ከምራቶቿ ጋር ወደ አገሯ ለመመለስ ከሞዓብ ተነሳች።
7 ከሁለቱ ምራቶቿም ጋር ትኖርበት የነበረውን ቦታ ትታ ሄደች። ወደ ይሁዳ ምድር ለመመለስ ወደዚያ የሚወስደውን መንገድ ይዘው እየሄዱ ሳሉም
8 ናኦሚ ሁለቱን ምራቶቿን እንዲህ አለቻቸው፦ “ሂዱ፣ ሁለታችሁም ወደ እናቶቻችሁ ቤት ተመለሱ። ለሞቱት ባሎቻችሁና ለእኔ ታማኝ ፍቅር+ እንዳሳያችሁ ሁሉ ይሖዋም ለእናንተ ታማኝ ፍቅር ያሳያችሁ።
9 ይሖዋ በየባላችሁ ቤት+ ያለስጋት እንድትኖሩ ያድርጋችሁ።”* ከዚያም ሳመቻቸው፤ እነሱም ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ማልቀስ ጀመሩ።
10 እንዲህም አሏት፦ “በፍጹም! ከአንቺ ጋር ወደ ወገኖችሽ እንሄዳለን።”
11 ናኦሚ ግን እንዲህ አለቻቸው፦ “ልጆቼ፣ ተመለሱ። ለምን ከእኔ ጋር ትሄዳላችሁ? ለእናንተ ባሎች ሊሆኑ የሚችሉ ወንዶች ልጆች አሁንም ልወልድ የምችል ይመስላችኋል?+
12 ልጆቼ፣ ተመለሱ። እኔ እንደሆነ በጣም ስላረጀሁ ከእንግዲህ ባል ላገባ አልችልም፤ ስለዚህ ሂዱ። ዛሬ ማታ ባል የማግኘትና ልጆች የመውለድ ተስፋ ቢኖረኝ እንኳ
13 እስኪያድጉ ድረስ ትጠብቃላችሁ? እነሱን በመጠበቅስ ባል ሳታገቡ ትቆያላችሁ? ልጆቼ፣ ይሄማ አይሆንም፤ የይሖዋ እጅ በእኔ ላይ ስለተነሳ የእናንተን ሁኔታ ሳስብ ሕይወቴ መራራ ይሆንብኛል።”+
14 እነሱም እንደገና ድምፃቸውን ከፍ አድርገው አለቀሱ፤ ከዚያም ዖርፋ አማቷን ስማ ተሰናበተቻት። ሩት ግን ከእሷ ላለመለየት የሙጥኝ አለች።
15 ናኦሚም “ተመልከች፣ መበለት የሆነችው የባልሽ ወንድም ሚስት ወደ ወገኖቿና ወደ አማልክቷ ተመልሳለች። አብረሻት ተመለሽ” አለቻት።
16 ሩት ግን እንዲህ አለቻት፦ “ከአንቺ እንድለይና ትቼሽ እንድመለስ አትማጸኚኝ፤ እኔ እንደሆነ ወደምትሄጂበት እሄዳለሁ፤ በምታድሪበት አድራለሁ። ሕዝብሽ ሕዝቤ፣ አምላክሽም አምላኬ ይሆናል።+
17 በምትሞቺበት እሞታለሁ፤ በዚያም እቀበራለሁ። ከሞት በቀር ከአንቺ የሚለየኝ ቢኖር ይሖዋ አንዳች ነገር ያምጣብኝ፤ ከዚያም የከፋ ያድርግብኝ።”
18 ናኦሚ፣ ሩት ከእሷ ጋር ለመሄድ እንደቆረጠች ስታውቅ መወትወቷን አቆመች።
19 ከዚያም ወደ ቤተልሔም ጉዟቸውን ቀጠሉ።+ ቤተልሔም እንደደረሱም በእነሱ ምክንያት መላ ከተማዋ ታመሰች፤ ሴቶቹም “ይህች ናኦሚ አይደለችም እንዴ?” ይሉ ነበር።
20 እሷም እንዲህ ትላቸው ነበር፦ “ናኦሚ* ብላችሁ አትጥሩኝ። ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ ሕይወቴን መራራ አድርጎታልና ማራ* ብላችሁ ጥሩኝ።+
21 ከዚህ ስወጣ ሙሉ ነበርኩ፤ ይሖዋ ግን ባዶ እጄን እንድመለስ አደረገኝ። ይሖዋ ተቃውሞኝና ሁሉን የሚችለው አምላክ መከራ አምጥቶብኝ ሳለ ለምን ናኦሚ ብላችሁ ትጠሩኛላችሁ?”+
22 እንግዲህ ናኦሚ ምራቷ ከሆነችው ከሞዓባዊቷ ሩት ጋር ከሞዓብ ምድር+ የተመለሰችው በዚህ ሁኔታ ነበር። ቤተልሔም የደረሱትም የገብስ አዝመራ መሰብሰብ በጀመረበት ወቅት ነበር።+
የግርጌ ማስታወሻዎች
^ ቃል በቃል “ይፈርዱ።”
^ “አምላኬ ንጉሥ ነው” የሚል ትርጉም አለው።
^ “ደስታዬ” የሚል ትርጉም አለው።
^ “ደካማ፤ በሽተኛ” የሚል ትርጉም ካለው የዕብራይስጥ ቃል የተገኘ ሳይሆን አይቀርም።
^ “የሚወድቅ፤ ያበቃለት” የሚል ትርጉም አለው።
^ ቃል በቃል “ማረፊያ ስፍራ ይስጣችሁ።”
^ ይህ ስም “ደስታዬ” የሚል ትርጉም አለው።
^ “መራራ” የሚል ትርጉም አለው።