በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

‘ለማስተማር ጥበብህ’ ትኩረት ስጥ

‘ለማስተማር ጥበብህ’ ትኩረት ስጥ

 ‘ለማስተማር ጥበብህ’ ትኩረት ስጥ

“ቃሉን ስበክ፤ . . . በታላቅ ትዕግሥትና በማስተማር [“በማስተማር ጥበብ፣” NW] አቅና፤ ገሥጽ፤ አበረታታም።”—2 ጢሞ. 4:2

1. ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ ምን ትእዛዝ ሰጥቷቸዋል? ምን ምሳሌስ ትቷል?

ኢየሱስ በምድር ላይ ባገለገለበት ወቅት ሰዎችን በመፈወስ አስደናቂ ተዓምራትን ሠርቷል። ያም ሆኖ በዋነኝነት ይታወቅ የነበረው በፈዋሽነቱ ወይም በተአምር ሠሪነቱ ሳይሆን በአስተማሪነቱ ነበር። (ማር. 12:19፤ 13:1) የኢየሱስ ተቀዳሚ ተግባር የአምላክን መንግሥት ምሥራች ማወጅ እንደነበረ ሁሉ በዛሬው ጊዜ ያሉት ተከታዮቹም ቅድሚያ የሚሰጡት ለዚሁ ሥራ ነው። ክርስቲያኖች ኢየሱስ ያዘዘውን ሁሉ እንዲጠብቁ ሰዎችን በማስተማር፣ ደቀ መዛሙርት የማድረጉን ሥራ እንዲቀጥሉ ተልእኮ ተሰጥቷቸዋል።—ማቴ. 28:19, 20

2. የስብከት ተልእኳችንን ለመወጣት ምን ማድረግ ይኖርብናል?

2 ሌሎችን ደቀ መዛሙርት እንድናደርግ የተሰጠንን ተልእኮ መወጣት እንድንችል የማስተማር ችሎታችንን ለማሻሻል ዘወትር ጥረት እናደርጋለን። ሐዋርያው ጳውሎስ ለአገልግሎት ጓደኛው ለጢሞቴዎስ በጻፈለት ደብዳቤ ላይ የማስተማር ጥበብን አስፈላጊነት በአጽንኦት ገልጿል። ጳውሎስ እንዲህ ብሏል:- “ለሕይወትህና ለትምህርትህ ተጠንቀቅ [“ትኩረት ስጥ፣” NW]፤ በእነዚህም ጽና፤ ይህን ብታደርግ፣ ራስህንና የሚሰሙህንም ታድናለህ።” (1 ጢሞ. 4:16) ጳውሎስ እዚህ ላይ እየተናገረ የነበረው እንዲያው እውቀትን ስለማስተላለፍ ብቻ አልነበረም። ውጤታማ ክርስቲያን አገልጋዮች የመጽሐፍ  ቅዱስን እውነት በሰዎች ልብ ውስጥ ይተክላሉ፤ እንዲሁም የሚያስተምሯቸው ሰዎች በሕይወታቸው ውስጥ ለውጥ እንዲያደርጉ ይረዷቸዋል። ይህ ደግሞ ጥበብ ነው። ታዲያ የአምላክን መንግሥት ምሥራች ለሌሎች ስንናገር ‘የማስተማር ጥበብን’ ማዳበር የምንችለው እንዴት ነው?—2 ጢሞ. 4:2 NW

‘የማስተማር ጥበብ’ ማዳበር

3, 4. (ሀ) ‘የማስተማር ጥበብ’ ማዳበር የምንችለው እንዴት ነው? (ለ) ቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ውጤታማ አስተማሪዎች እንድንሆን የሚረዳን እንዴት ነው?

3 አንድ መዝገበ ቃላት “ጥበብ” ተብሎ ለተተረጎመው የእንግሊዝኛ ቃል “በጥናት፣ ትምህርትን በተግባር በማዋል ወይም በማየት የሚገኝ ችሎታ” የሚል ፍቺ ሰጥቶታል። የመንግሥቱን ምሥራች ውጤታማ በሆነ መንገድ ለማስተማር ለእነዚህ ሦስት ነገሮች ትኩረት መስጠት አለብን። አንድን ርዕሰ ጉዳይ በትክክል መረዳት የምንችለው ጸሎት የታከለበት ጥናት ካደረግን ብቻ ነው። (መዝሙር 119:27, 34ን አንብብ።) ጥሩ ችሎታ ያላቸው አገልጋዮች ሲያስተምሩ ማየታችን የማስተማር ዘዴያቸውን ለመማርና እነሱን ለመኮረጅ ያስችለናል። ከዚያም የተማርነውን ነገር አዘውትረን በተግባር ለማዋል ብርቱ ጥረት ማድረጋችን የማስተማር ችሎታችንን ይበልጥ ለማሻሻል ይረዳናል።—ሉቃስ 6:40፤ 1 ጢሞ. 4:13-15

4 ይሖዋ ታላቅ አስተማሪያችን ነው። በምድር ላይ ያሉት አገልጋዮቹ የተሰጣቸውን የመስበክ ተልእኮ መወጣት እንዲችሉ በሚታየው የድርጅቱ ክፍል አማካኝነት መመሪያ ይሰጣቸዋል። (ኢሳ. 30:20, 21) ከዚህ ጋር በተያያዘ በእያንዳንዱ ጉባኤ ውስጥ በየሳምንቱ ቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ይካሄዳል። የዚህ ትምህርት ቤት ዓላማ ተማሪዎቹ ውጤታማ የአምላክ መንግሥት አዋጅ ነጋሪዎች እንዲሆኑ መርዳት ነው። የትምህርት ቤቱ ዋነኛ የመማሪያ መጽሐፍ፣ መጽሐፍ ቅዱስ ነው። በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈው የይሖዋ ቃል ምን ማስተማር እንዳለብን ይነግረናል። ከዚህም በላይ፣ ውጤታማና ተገቢ የሆኑት የማስተማሪያ ዘዴዎች የትኞቹ እንደሆኑ ይጠቁመናል። ትምህርታችን በአምላክ ቃል ላይ የተመሠረተ እንዲሆን ካደረግን፣ ጥያቄዎችን ውጤታማ በሆነ መንገድ ከተጠቀምን፣ ቀለል ባለ መንገድ ካስተማርንና ለሌሎች ልባዊ አሳቢነት ለማሳየት ጥረት ካደረግን ውጤታማ አስተማሪዎች መሆን እንደምንችል ከቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ዘወትር እንማራለን። እስቲ እነዚህን ነጥቦች አንድ በአንድ እንመርምር። ከዚያም የተማሪዎቻችንን ልብ እንዴት መንካት እንደምንችል እንመለከታለን።

ትምህርትህ በአምላክ ቃል ላይ የተመሠረተ ይሁን

5. ለትምህርታችን መሠረት ሊሆን የሚገባው ምንድን ነው? ለምንስ?

5 ከየትኛውም ሰብዓዊ አስተማሪ የሚበልጠው ኢየሱስ ትምህርቶቹ በቅዱሳን መጻሕፍት ላይ የተመሠረቱ ነበሩ። (ማቴ. 21:13፤ ዮሐ. 6:45፤ 8:17) ያስተማረው ትምህርት ከራሱ ሳይሆን ከላከው የመጣ ነበር። (ዮሐ. 7:16-18) እኛም ይህንኑ ምሳሌ እንከተላለን። ከቤት ወደ ቤት ስናገለግልም ይሁን የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ስንመራ የምናስተምረው ነገር በአምላክ ቃል ላይ የተመሠረተ መሆን አለበት። (2 ጢሞ. 3:16, 17) ከራሳችን አመንጭተን የምንናገረው የትኛውም ጥበብ ያዘለ ሐሳብ በመንፈስ ቅዱስ አነሳሽነት የተጻፉት ቅዱሳን መጻሕፍት ካላቸው ልብ የመንካት ኃይል ጋር ፈጽሞ አይወዳደርም። መጽሐፍ ቅዱስ ኃይል አለው። አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ እንዲረዳ የምንፈልገው ነጥብ ምንም ይሁን ምን፣ ከሁሉ የተሻለው ዘዴ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ጉዳዩ ምን እንደሚል እንዲያነብ ማድረግ ነው።—ዕብራውያን 4:12ን አንብብ።

6. አንድ አስተማሪ፣ ተማሪው የሚወያዩበትን ርዕሰ ጉዳይ ፍሬ ሐሳብ እንዲገነዘብ መርዳት የሚችለው እንዴት ነው?

6 እንዲህ ሲባል ግን አንድ ክርስቲያን አስተማሪ መጽሐፍ ቅዱስን ለማስጠናት ምንም ዓይነት ቅድመ ዝግጅት  ማድረግ አያስፈልገውም ማለት አይደለም። ከዚህ በተቃራኒ፣ በጥናቱ ወቅት የትኞቹን ጥቅሶች እሱ ራሱ ወይም ተማሪው ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ እንደሚያነብ ለመወሰን በጥንቃቄ ማሰብ ያስፈልገዋል። በአብዛኛው ለእምነታችን መሠረት የሆኑትን ጥቅሶች ማንበብ ጥሩ ነው። በተጨማሪም ተማሪው የሚያነበውን የእያንዳንዱን ጥቅስ ፍሬ ሐሳብ እንዲያስተውል መርዳት ያስፈልጋል።—1 ቆሮ. 14:8, 9

ውጤታማ የሆኑ ጥያቄዎችን ተጠቀም

7. ጥያቄዎችን መጠቀም ውጤታማ የማስተማሪያ ዘዴ የሆነው ለምንድን ነው?

7 ጥያቄዎችን ውጤታማ በሆነ መንገድ መጠቀም አእምሮን ያመራምራል እንዲሁም አስተማሪው የተማሪውን ልብ ለመንካት ያስችለዋል። በመሆኑም ጥቅሶችን ለተማሪህ አንተ ከምታብራራለት ይልቅ ራሱ እንዲያብራራልህ ጠይቀው። ተማሪህ ትክክለኛ ግንዛቤ እንዲያገኝ ለመርዳት አልፎ አልፎ ተጨማሪ ጥያቄ ወይም ተከታታይ ጥያቄዎችን መጠየቅ ሊያስፈልግህ ይችላል። በዚህ መንገድ ተማሪው በመማር ማስተማር ሂደቱ ውስጥ ሲሳተፍ ስለ ጉዳዩ የተሰጠው ማብራሪያ ምክንያታዊ መሆኑን እንዲገነዘብ ብቻ ሳይሆን ራሱም እንዲያምንበት ትረዳዋለህ።—ማቴ. 17:24-26፤ ሉቃስ 10:36, 37

8. በተማሪያችን ልብ ውስጥ ያለው ምን እንደሆነ ማስተዋል የምንችለው እንዴት ነው?

8 ሰዎችን መጽሐፍ ቅዱስ ለማስጠናት በምንጠቀምባቸው ጽሑፎች ላይ ያለው የማስተማሪያ ዘዴ ጥያቄና መልስ ነው። የምናስጠናቸው አብዛኞቹ ሰዎች በማስጠኛ ጽሑፉ ላይ የሚገኘውን መልስ መመለስ እንደማይከብዳቸው ግልጽ ነው። ያም ሆኖ አስተዋይ የሆነ መምህር ተማሪው ትክክለኛውን መልስ በመመለሱ ብቻ አይረካም። ለምሳሌ ያህል፣ ተማሪው መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ዝሙት ምን እንደሚል በትክክል ማብራራት ይችል ይሆናል። (1 ቆሮ. 6:18) ይሁንና አንዳንድ የአመለካከት ጥያቄዎችን በዘዴ በመጠየቅ እየተማረ ስላለው ነገር በእርግጥ ምን እንደሚያስብ ማወቅ ይቻላል። አስተማሪው እንደሚከተሉት ያሉ ጥያቄዎችን ሊጠይቀው ይችላል:- “መጽሐፍ ቅዱስ ከጋብቻ ውጪ የሚፈጸምን የጾታ ግንኙነት የሚያወግዘው ለምንድን ነው? አምላክ ስላወጣው ስለዚህ ገደብ ምን ይሰማሃል? ከአምላክ የሥነ ምግባር መሥፈርቶች ጋር ተስማምቶ መኖር ጥቅም ያስገኛል ብለህ ታምናለህ?” ተማሪው ለእነዚህ ጥያቄዎች የሚሰጠው መልስ በልቡ ውስጥ ያለው ምን እንደሆነ በግልጽ ሊያሳይ ይችላል።—ማቴዎስ 16:13-17ን አንብብ።

ቀላል በሆነ መንገድ አስተምር

9. ለሰዎች ቅዱስ ጽሑፋዊ ሐሳብ ስናካፍል ምን ማስታወስ ይኖርብናል?

9 በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኙት አብዛኞቹ እውነቶች በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታይ ለመረዳት ቀላል ናቸው። ይሁንና መጽሐፍ ቅዱስን የምናስጠናቸው ሰዎች በሐሰት ሃይማኖት መሠረተ ትምህርቶች ግራ የተጋቡ ሊሆኑ ይችላሉ። አስተማሪዎች እንደመሆናችን መጠን መጽሐፍ ቅዱስን ለመረዳት ቀላል በሆነ መንገድ ማስተማር ይኖርብናል። ውጤታማ አስተማሪ ትምህርቱን ቀላልና ግልጽ በሆነ መንገድ እንዲሁም በትክክል ያስተላልፋል። እነዚህን መመሪያዎች የምንከተል ከሆነ ሰዎች እውነትን መረዳት እስኪቸግራቸው ድረስ አናወሳስብባቸውም። አላስፈላጊ ዝርዝር ሐሳቦችን ከመናገር መቆጠብ አለብን። ያነበብነው ጥቅስ የያዘውን እያንዳንዱን ሐሳብ ማብራራት አስፈላጊ አይደለም። ከዚህ ይልቅ እየተወያየንበት ያለነውን ርዕሰ ትምህርት በሚደግፉት ነጥቦች ላይ ብቻ እናተኩራለን። የተማሪው ግንዛቤ ይበልጥ እየጨመረ ሲሄድ ጥልቅ የሆኑ መንፈሳዊ እውነቶችን ቀስ በቀስ መረዳት ይችላል።—ዕብ. 5:13, 14

10. በአንድ የጥናት ክፍለ ጊዜ ምን ያህል አንቀጽ መሸፈን እንዳለበት የሚወስነው ምንድን ነው?

 10 በአንድ የጥናት ክፍለ ጊዜ ምን ያህል አንቀጽ መሸፈን ይኖርበታል? ይህን መወሰን ማስተዋል ይጠይቃል። የተማሪውም ሆነ የአስተማሪው ችሎታና ሁኔታ ሊለያይ ቢችልም፣ አስተማሪዎች እንደመሆናችን መጠን ዋናው ግባችን ተማሪያችን ጠንካራ እምነት እንዲገነባ መርዳት መሆኑን መዘንጋት አይኖርብንም። በመሆኑም ተማሪው በአምላክ ቃል ውስጥ ያሉትን እውነቶች ለማንበብ፣ ለማገናዘብና ለማመን የሚያስችለው በቂ ጊዜ ልንሰጠው ይገባል። ተማሪው ሊረዳው ከሚችለው በላይ ብዙ ሐሳቦችን በአንዴ ለማስጠናት መሞከር የሌለብን ቢሆንም ጥናቱ በተገቢው ፍጥነት እንዲቀጥል እናደርጋለን። ተማሪው ነጥቡን ከተረዳው ወደሚቀጥለው ሐሳብ እናልፋለን።—ቈላ. 2:6, 7

11. ማስተማርን በተመለከተ ከሐዋርያው ጳውሎስ ምን እንማራለን?

11 ሐዋርያው ጳውሎስ፣ ለመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት አዲስ ለሆኑ ሰዎች ምሥራቹን በሚሰብክበት ጊዜ መልእክቱን ቀለል ባለ መንገድ ያቀርብ ነበር። ጳውሎስ ከፍተኛ ትምህርት የነበረው ቢሆንም የተራቀቁ ቃላትን አልተጠቀመም። (1 ቆሮንቶስ 2:1, 2ን አንብብ።) የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ቀለል ባለ መንገድ የቀረበ መሆኑ ልበ ቅን የሆኑ ሰዎችን የሚማርክ ከመሆኑም ሌላ መንፈሳዊ ፍላጎታቸውን ያረካላቸዋል። አንድ ሰው የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ለመረዳት ምሑር መሆን አያስፈልገውም።—ማቴ. 11:25፤ ሥራ 4:13፤ 1 ቆሮ. 1:26, 27

ተማሪዎች የሚማሩትን ነገር እንዲያደንቁ እርዳቸው

12, 13. አንድ ተማሪ የተማረውን ነገር በተግባር ላይ እንዲያውል የሚያነሳሳው ምን መሆን አለበት? በምሳሌ አስረዳ።

12 ውጤታማ ለመሆን ከፈለግን ትምህርታችን የተማሪውን ልብ መንካት ይኖርበታል። ተማሪው ትምህርቱ በእሱ ላይ የሚሠራው እንዴት እንደሆነ፣ እንዴት እንደሚጠቅመውና የመጽሐፍ ቅዱስን መመሪያዎች ከተከተለ ሕይወቱ እንዴት ሊሻሻል እንደሚችል መገንዘብ አለበት።—ኢሳ. 48:17, 18

13 ለምሳሌ ያህል፣ ክርስቲያኖች በመንፈሳዊ ለመነቃቃትና ፍቅራቸውን ለመግለጽ ከእምነት አጋሮቻቸው ጋር እንዲሰበሰቡ የሚያበረታታውን በዕብራውያን 10:24, 25 ላይ የሚገኘውን ሐሳብ እየተወያየን ነው እንበል። ተማሪው በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ መገኘት ካልጀመረ ስብሰባዎቹ እንዴት እንደሚካሄዱና በዚያ ስለሚቀርቡት ትምህርቶች በአጭሩ ልንገልጽለት እንችላለን። በተጨማሪም የጉባኤ ስብሰባዎች የአምልኳችን ክፍል እንደሆኑና እኛን እንዴት እንደጠቀሙን ልንነግረው እንችላለን። ከዚያም ተማሪውን በስብሰባዎች ላይ እንዲገኝ ልንጋብዘው እንችል ይሆናል። ቅዱስ ጽሑፋዊ መመሪያዎችን ለመታዘዝ የሚያነሳሳው ይሖዋን ለመታዘዝ ያለው ፍላጎት እንጂ የሚያስጠናውን ሰው ለማስደሰት ብሎ መሆን የለበትም።—ገላ. 6:4, 5

14, 15. (ሀ) አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ ስለ ይሖዋ ምን መማር ይችላል? (ለ) አንድ ተማሪ ስለ አምላክ ባሕርያት ማወቁ የሚጠቅመው እንዴት ነው?

14 ተማሪዎች መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናታቸውና መመሪያዎቹን በተግባር ላይ ማዋላቸው የሚያስገኝላቸው ዋነኛ ጥቅም ይሖዋን ማወቅና መውደድ መቻላቸው ነው። (ኢሳ. 42:8) ይሖዋ አፍቃሪ እንዲሁም የጽንፈ ዓለሙ ፈጣሪና ባለቤት ብቻ ሳይሆን ለሚወዱትና ለሚያገለግሉት ሰዎች ባሕርያቱንና ችሎታውን የሚገልጥ አምላክ ነው። (ዘፀአት 34:6, 7ን አንብብ።) ሙሴ እስራኤላውያንን ከግብጽ ባርነት እንዲያወጣቸው በተላከ ጊዜ ይሖዋ “መሆን የሚያስፈልገኝን ሁሉ እሆናለሁ” በማለት ራሱን ገልጦለታል። (ዘፀ. 3:13-15 NW) ይህም ይሖዋ፣ ከመረጣቸው ሕዝቦቹ ጋር በተያያዘ ያለውን ዓላማ ከግብ ለማድረስ መሆን የሚያስፈልገውን ሁሉ እንደሚሆን ያሳያል። ከዚህ የተነሳ እስራኤላውያን፣ ይሖዋ አዳኝ፣ ተዋጊ፣ ተንከባካቢና ቃሉን የሚፈጽም እንዲሁም በሌሎች መንገዶችም የሚረዳቸው አምላክ መሆኑን ለመገንዘብ ችለዋል።—ዘፀ. 15:2, 3፤ 16:2-5፤ ኢያሱ 23:14

15 መጽሐፍ ቅዱስን የምናስተምራቸው ሰዎች ልክ እንደ ሙሴ በሕይወታቸው ውስጥ ቃል በቃል የይሖዋን ተአምራዊ እርዳታ አላገኙ ይሆናል። የሆነ ሆኖ ተማሪዎቻችን በሚማሩት ነገር ላይ ያላቸው እምነትና አድናቆት እያደገ ሲሄድ እንዲሁም የተማሩትን በተግባር ሲያውሉ ድፍረት፣ ጥበብና መመሪያ ለማግኘት በይሖዋ መታመን አስፈላጊ መሆኑን እንደሚያስተውሉ ጥርጥር የለውም። በይሖዋ መታመናቸው ደግሞ አምላክ ጠቢብና እምነት የሚጣልበት መካሪ፣ እንዲሁም ከለላና የሚያስፈልጋቸውን ሁሉ በደግነት የሚሰጥ መሆኑን እንዲገነዘቡ ያደርጋቸዋል።—መዝ. 55:22፤ 63:7፤ ምሳሌ 3:5, 6

ፍቅራዊ አሳቢነት አሳይ

16. ውጤታማ አስተማሪ ለመሆን በጣም አስፈላጊ የሆነው ነገር የተፈጥሮ ችሎታ አይደለም የምንለው ለምንድን ነው?

16 የምትፈልገውን ያህል ጥሩ የማስተማር ችሎታ  እንደሌለህ ከተሰማህ ተስፋ አትቁረጥ። ይሖዋና ኢየሱስ በዛሬው ጊዜ በዓለም ዙሪያ እየተካሄደ ያለውን የትምህርት ፕሮግራም በበላይነት ይቆጣጠራሉ። (ሥራ 1:7, 8፤ ራእይ 14:6) በመሆኑም የምንናገረው ነገር ቅን በሆኑ ሰዎች ልብ ውስጥ በጎ ተጽዕኖ እንዲያሳድር በማድረግ ጥረታችንን ይባርኩልናል። (ዮሐ. 6:44) አንድ አስተማሪ ተማሪዎቹን ከልቡ የሚወድ ከሆነ ይህ ባሕርይው በተፈጥሮ ሊኖረው የሚችለውን ማንኛውም ዓይነት ጉድለት ይሸፍንለታል። ሐዋርያው ጳውሎስ ምሥራቹን ለሚያስተምራቸው ሰዎች ፍቅር ማሳየት አስፈላጊ መሆኑን ተገንዝቧል።—1 ተሰሎንቄ 2:7, 8ን አንብብ።

17. ለመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቻችን በግለሰብ ደረጃ ልባዊ አሳቢነት ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

17 እኛም በተመሳሳይ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቻችንን በግለሰብ ደረጃ በደንብ ለማወቅ ጊዜ በመመደብ ከልብ እንደምናስብላቸው ማሳየት እንችላለን። ተማሪያችንን የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች ስናስተምረው ያለበትን ሁኔታ መገንዘባችን አይቀርም። ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተማራቸውን አንዳንድ ትምህርቶች በሕይወቱ ተግባራዊ እያደረገ መሆኑን እንመለከት ይሆናል። ይሁን እንጂ በአንዳንድ የሕይወቱ ዘርፎች ማስተካከያ ማድረግ ሊኖርበት ይችላል። የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪው በጥናቱ ወቅት ያገኘውን ሐሳብ በሕይወቱ ውስጥ ተግባራዊ ማድረግ የሚችለው እንዴት እንደሆነ እንዲገነዘብ በመርዳት እውነተኛ የክርስቶስ ደቀ መዝሙር እንዲሆን በፍቅር ልንረዳው እንችላለን።

18. ከተማሪያችን ጋር በምንጸልይበት ወቅት ስሙን ጠቅሰን ስለ እሱ መጸለያችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

18 ከሁሉም በላይ ከተማሪው ጋር በምንጸልይበት ወቅት ስሙን ጠቅሰን ስለ እሱ መጸለይ እንችላለን። ዓላማችን ፈጣሪውን ይበልጥ እንዲያውቅ፣ ወደ እሱ እንዲቀርብና የአምላክን መመሪያ በመከተል ጥቅም እንዲያገኝ መርዳት መሆኑን በግልጽ ማየት መቻል አለበት። (መዝሙር 25:4, 5ን አንብብ።) ተማሪው፣ ያወቀውን በሥራ ላይ ማዋል እንዲችል ይሖዋ ጥረቱን እንዲባርክለት ስንጸልይ ማዳመጡ ‘ቃሉ የሚናገረውን ማድረግ’ ያለውን ጠቀሜታ እንዲገነዘብ ይረዳዋል። (ያዕ. 1:22) ከልብ በመነጨ ስሜት የምናቀርበውን ጸሎት ሲሰማ እሱም እንዴት መጸለይ እንዳለበት ይማራል። የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቻችን ከይሖዋ ጋር የግል ዝምድና እንዲመሠርቱ መርዳት ታላቅ ደስታ ያስገኛል።

19. የሚቀጥለው ርዕስ ምን ይዟል?

19 በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ከ6.5 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ የይሖዋ ምሥክሮች፣ ‘የማስተማር ጥበብን’ ለማዳበር ጥረት እንደሚያደርጉ ማወቃችን ያበረታታናል፤ ይህንንም የሚያደርጉት ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች ኢየሱስ ያዘዘውን ሁሉ እንዲጠብቁ ለመርዳት ነው። በስብከቱ ሥራችን ምን ውጤቶች እየተገኙ ነው? የሚቀጥለው ርዕስ ለዚህ ጥያቄ መልስ ይሰጣል።

ታስታውሳለህ?

• ክርስቲያኖች ‘የማስተማር ጥበብን’ ማዳበር ያለባቸው ለምንድን ነው?

• ውጤታማ አስተማሪ እንድንሆን የሚረዱን የትኞቹ ዘዴዎች ናቸው?

• ከማስተማር ችሎታችን ጋር በተያያዘ በተፈጥሮ ሊኖረን የሚችለውን ማንኛውም ዓይነት ጉድለት የሚሸፍንልን ምንድን ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት እየተካፈልክ ነው?

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ተማሪህ ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ እንዲያነብ ማድረግህ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከተማሪህ ጋር ስትጸልይ ስሙን ጠቅሰህ ስለ እሱ ጸልይ