በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የመጠበቂያ ግንብ መጽሔት አዲሱ የጥናት እትም

የመጠበቂያ ግንብ መጽሔት አዲሱ የጥናት እትም

 የመጠበቂያ ግንብ መጽሔት አዲሱ የጥናት እትም

አሁን እያነበብክ ያለኸው መጽሔት፣ የጥናት እትም ተብሎ የሚጠራውን የመጠበቂያ ግንብ መጽሔት የመጀመሪያ እትም ነው። ይህ መጽሔት ካሉት አዳዲስ ገጽታዎች መካከል አንዳንዶቹን ልናስተዋውቅህ እንወዳለን።

የጥናት እትም የሚዘጋጀው ለይሖዋ ምሥክሮችና እድገት በማድረግ ላይ ለሚገኙ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ነው። ይህ መጽሔት በወር አንዴ የሚታተም ሲሆን አራት ወይም አምስት የጥናት ርዕሶችን ይይዛል። እነዚህ የጥናት ርዕሶች በጉባኤ የሚጠኑበት ፕሮግራም በመጽሔቱ የሽፋን ገጽ ላይ ይገኛል። ይህ እትም ከሚበረከተው የመጠበቂያ ግንብ እትም በተለየ መልኩ በአገልግሎት ላይ ስለማይበረከት የሽፋን ሥዕሉ ከእትም እትም አይለዋወጥም።

በመጽሔቱ ሁለተኛ ገጽ ላይ የእያንዳንዱን የጥናት ርዕስ ወይም ተከታታይ ርዕሶች ዓላማ በአጭሩ የሚከልስ ጠቃሚ መግለጫና የሌሎች ተጨማሪ ርዕሶች ዝርዝር ታገኛለህ። ይህም የመጠበቂያ ግንብ ጥናት የሚመሩ ወንድሞች የጥናት ርዕሶቹን በሚዘጋጁበት ጊዜ በጣም እንደሚጠቅማቸውና ትምህርቱ በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ ሲጠናም ትርጉም ያለው ውይይት ለማድረግ እንደሚያስችላቸው ምንም ጥርጥር የለውም።

የጥናት ርዕሶቹ ከዚህ ቀደም ከነበረው ትንሽ አጠር ያሉ መሆናቸውን ማስተዋልህ አይቀርም። ይህም በመጠበቂያ ግንብ ጥናት ወቅት ቁልፍ በሆኑ ጥቅሶች ላይ ለመወያየት የሚያስችል ሰፋ ያለ ጊዜ ያስገኛል። በየሳምንቱ ለመጠበቂያ ግንብ ጥናት ስትዘጋጅ ምዕራፍና ቁጥራቸው ብቻ የተጠቀሱትን ጥቅሶች በሙሉ እንድታነብ እናበረታታሃለን። ከአንዳንዶቹ ጥቅሶች ቀጥሎ “አንብብ” የሚል ጽሑፍ ታገኛለህ። እነዚህ ጥቅሶች በመጠበቂያ ግንብ ጥናት ወቅት ሊነበቡና ውይይት ሊደረግባቸው ይገባል። ጊዜ በፈቀደ መጠን ሌሎች ጥቅሶችንም ማንበብ ይቻላል። በአንዳንድ የጥናት ርዕሶች ውስጥ ደግሞ “አወዳድር” የሚል ጽሑፍ ያላቸው ጥቅሶች ታገኝ ይሆናል። እነዚህ ጥቅሶች በአንቀጹ ውስጥ ያሉትን ዋና ዋና ነጥቦች በቀጥታ የሚደግፉ ስላልሆኑ በአብዛኛው በስብሰባዎች ላይ አይነበቡም። ያም ሆኖ “አወዳድር” የሚል ጽሑፍ ያለባቸው ጥቅሶች ትኩረት የሚስቡ ተጨማሪ መረጃዎችን ይዘዋል። ወይም ደግሞ እየተጠና ያለውን ሐሳብ በተዘዋዋሪ መንገድ የሚደግፉ ማስረጃዎችን የሚያቀርቡ ሊሆኑ ይችላሉ። በመሆኑም ለመጠበቂያ ግንብ ጥናት ስትዘጋጅ እነዚህን ጥቅሶች እንድታነባቸው እናበረታታሃለን። በስብሰባ ላይ በምትሰጠው ሐሳብ ውስጥ ልታካትታቸው ትችል ይሆናል።

ከ2008 ጀምሮ ዓመታዊው ሪፖርት በመጠበቂያ ግንብ መጽሔት ላይ አይወጣም። ከዚህ ይልቅ በመንግሥት አገልግሎታችን ላይ አባሪ ሆኖ የሚወጣ ሲሆን በዓመት መጽሐፍ ላይም ይወጣል። ይሁን እንጂ ከላይ እንደተጠቀሰው የጥናት እትሙ ከሚጠኑት ርዕሰ ትምህርቶች ባሻገር ሌሎች ርዕሶችንም ያካትታል። ከእነዚህ ርዕሶች ውስጥ አብዛኞቹ በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ የማይጠኑ ቢሆኑም እንኳ በደንብ እንድታነባቸው እናበረታታሃለን። እነዚህ ርዕሶችም ቢሆኑ “ታማኝና ልባም ባሪያ” የሚያዘጋጀውን መንፈሳዊ ምግብ ይዘዋል።—ማቴ. 24:45-47 የ1954 ትርጉም

የጥናት እትም እና የሚበረከት እትም ሁለት የተለያዩ መጽሔቶች አይደሉም። ከዚህ ይልቅ ሁለቱም እትሞች የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ ናቸው። በሁለቱም እትሞች ገጽ 2 ላይ የመጠበቂያ ግንብ መጽሔትን ዓላማ የሚገልጽ ተመሳሳይ አንቀጽ ይገኛል። ሁለቱም እትሞች በየዓመቱ በሚዘጋጀው ጥራዝ ውስጥ ይካተታሉ። በጥናት እትሙ ላይ በሚወጣው፣ “ታስታውሳለህ?” በሚለው አምድ ውስጥ ከሁለቱም እትሞች የተወሰዱ ሐሳቦች ይካተታሉ።

ከ1879 አንስቶ ጦርነት፣ የኢኮኖሚ ችግርና ስደት በነበሩባቸው ጊዜያት ሁሉ የመጠበቂያ ግንብ መጽሔት ስለ አምላክ መንግሥት የሚናገሩ እውነቶችን በታማኝነት ሲያውጅ ቆይቷል። አዲሱ እትምም ይህን ዓላማ ማከናወኑን እንዲቀጥል የይሖዋ በረከት እንዳይለየው ጸሎታችን ነው። ውድ አንባቢ፣ አንተም ከአዲሱ የመጠበቂያ ግንብ የጥናት እትም ጥቅም ለማግኘት የምታደርገውን ጥረት ይሖዋ እንዲባርክልህ እንጸልያለን።