በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ወላጆች፣ የቤተሰባችሁን ፍላጎት አሟሉ

ወላጆች፣ የቤተሰባችሁን ፍላጎት አሟሉ

ወላጆች፣ የቤተሰባችሁን ፍላጎት አሟሉ

‘ለእርሱ ስለ ሆኑት የማያስብ ማንም ቢሆን፣ ሃይማኖትን የካደ ነው። ’—1 ጢሞቴዎስ 5:8 የ1954 ትርጉም

1, 2. (ሀ) ቤተሰቦች በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ በአንድነት ሲገኙ ማየት የሚያስደስተው ለምንድን ነው? (ለ) ቤተሰቦች በስብሰባ ላይ በሰዓቱ ለመገኘት ሊወጧቸው የሚገቡ አንዳንድ መሰናክሎች ምንድን ናቸው?

 ስብሰባ ከመጀመሩ በፊት በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ የተገኙትን ሰዎች ዞር ዞር እያልክ ስትቃኝ ንጹሖችና ጥሩ አለባበስ ያላቸው ልጆች ከወላጆቻቸው አጠገብ ተቀምጠው ትመለከት ይሆናል። እንደነዚህ ያሉት ቤተሰቦች ለይሖዋም ሆነ አንዳቸው ለሌላው ያላቸውን ፍቅር ማየት አያስደስትም? ይሁንና ቤተሰብ ይዞ ስብሰባ ላይ በሰዓቱ መድረስ ምን ያህል ጥረት እንደሚጠይቅ ሳያስተውሉ ማለፍ በጣም ቀላል ነው።

2 አብዛኛውን ጊዜ ወላጆች ቀኑን ሙሉ ሲዋከቡ ይውላሉ፤ ስብሰባ ባለበት ምሽት ደግሞ የቤተሰብ ሕይወት ይባስ በጥድፊያ የተሞላ ይሆናል። ምግብ ማዘጋጀትና አንዳንድ ሥራዎችን ማጠናቀቅ የሚያስፈልግ ሲሆን ልጆች ደግሞ የቤት ሥራቸውን መጨረስ ይኖርባቸዋል። ሁሉም ሰው መለባበሱን፣ መመገቡንና በሰዓቱ ተዘገጃጅቶ መጨረሱን መከታተል የወላጆች ሥራ በመሆኑ ከባዱን ሸክም የሚሸከሙት እነርሱ ናቸው። አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ልጆች አጉል ሰዓት ላይ ያልሆነ ነገር ያጋጥማቸዋል። ትልቁ ልጅ ሲጫወት ሱሪው ይቀደድበታል። ትንሹ ደግሞ የቀረበለት ምግብ ይደፋበታል። ልጆቹ መነታረክ ይጀምራሉ። (ምሳሌ 22:15) እነዚህ ነገሮች ምን ያስከትላሉ? ወላጆች ጥሩ ዕቅድ አውጥተው የነበረ ቢሆንም እንኳ ትርምስ ሊፈጠር ይችላል። ሆኖም አብዛኛውን ጊዜ ቤተሰቡ ስብሰባው ከመጀመሩ በፊት መንግሥት አዳራሽ ይገኛል። እነዚህ ቤተሰቦች ከሳምንት ሳምንት ብሎም ከዓመት ዓመት የጉባኤ ስብሰባ ላይ ሲገኙና ልጆቹም አድገው ይሖዋን ሲያገለግሉ ማየት እንዴት ያስደስታል!

3. ይሖዋ ለቤተሰቦች ከፍ ያለ ግምት እንዳለው እንዴት ማወቅ እንችላለን?

3 ወላጆች፣ የምታከናውኑት ሥራ አንዳንድ ጊዜ አስቸጋሪ ብሎም በጣም አድካሚ ቢሆንባችሁም ይሖዋ ለጥረታችሁ ከፍ ያለ ግምት እንደሚሰጥ እርግጠኛ ሁኑ። የቤተሰብን ዝግጅት ያቋቋመው ይሖዋ ነው። በመሆኑም እያንዳንዱ ቤተሰብ ‘ስያሜ የሚያገኘው’ ማለትም ሕልውና ያገኘው ከይሖዋ መሆኑን ቃሉ ይናገራል። (ኤፌሶን 3:14, 15) ስለዚህ ወላጆች በቤተሰብ ዝግጅት ውስጥ ያላችሁን ኃላፊነት በትክክለኛ መንገድ ለመወጣት ጥረት ስታደርጉ ለጽንፈ ዓለሙ ሉዓላዊ ጌታ ክብር ታመጣላችሁ። (1 ቆሮንቶስ 10:31) ይህ ትልቅ መብት አይደለም? በመሆኑም ይሖዋ ለወላጆች የሰጣቸውን ሥራ መመርመራችን ተገቢ ነው። በዚህ ርዕስ ውስጥ ይህን ሥራ ለቤተሰብ የሚያስፈልገውን ከማሟላት አንጻር እንመለከታለን። አምላክ ወላጆች ለቤተሰባቸው እንዲያሟሉ የሚጠብቅባቸውን ሦስት ነገሮች እስቲ እንመርምር።

ቁሳዊ ፍላጎታቸውን ማሟላት

4. ለልጆች የሚያስፈልጓቸውን ነገሮች ለማሟላት ይሖዋ በቤተሰብ ውስጥ ያደረገው ዝግጅት ምንድን ነው?

4 ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ለእርሱ ስለ ሆኑት ይልቁንም ስለ ቤተ ሰዎቹ የማያስብ ማንም ቢሆን፣ ሃይማኖትን የካደ ከማያምንም ሰው ይልቅ የሚከፋ ነው።” (1 ጢሞቴዎስ 5:8 የ1954 ትርጉም) ጳውሎስ እዚህ ላይ “ማንም ቢሆን” ሲል በአእምሮው የያዘው ማንን ነበር? ስለ ቤተሰብ ራስ እየተናገረ የነበረ ሲሆን አብዛኛውን ጊዜ ይህን ቦታ የሚይዘው አባት ነው። አምላክ ሴት የባሏ ረዳት እንድትሆን በማድረግ ለእርሷም ክብር ያለው ቦታ ሰጥቷታል። (ዘፍጥረት 2:18) በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን ሴቶች ባሎቻቸው ለቤተሰባቸው የሚያስፈልገውን ነገር ማሟላት እንዲችሉ በብዙ መንገዶች ድጋፍ ይሰጡ ነበር። (ምሳሌ 31:13, 14, 16) በዛሬው ጊዜ በአንድ ወላጅ የሚተዳደሩ ቤተሰቦች ቁጥር ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ እየጨመረ መጥቷል። a ነጠላ ወላጅ የሆኑ በርካታ ክርስቲያኖች ለቤተሰባቸው የሚያስፈልገውን በማሟላት ረገድ የሚያከናውኑት ሥራ በጣም ይደነቃል። እርግጥ በአንድ ቤተሰብ ውስጥ ሁለቱም ወላጆች ቢኖሩና አባት ቤቱን ቢያስተዳድር ይበልጥ ተስማሚ ነው።

5, 6. (ሀ) የራሳቸው ለሆኑት የሚያስፈልጉትን ቁሳዊ ነገሮች ለማሟላት የሚጥሩ ወላጆች የሚያጋጥሟቸው አንዳንድ ፈታኝ ሁኔታዎች ምንድን ናቸው? (ለ) ክርስቲያን ወላጆች በጽናት እንዲቀጥሉ የሚረዳቸው ለሥራ ምን ዓይነት አመለካከት መያዛቸው ነው?

5 ጳውሎስ በ1 ጢሞቴዎስ 5:8 ላይ እየተናገረ የነበረው ምን ስለማሟላት ነበር? በጥቅሱ ዙሪያ ያለው ሐሳብ እንደሚጠቁመው እየተናገረ የነበረው ለቤተሰብ የሚያስፈልጉትን ቁሳዊ ነገሮች ስለማሟላት ነው። በዛሬው ጊዜ አንድ የቤተሰብ ራስ ቁሳዊ ነገሮችን ለማሟላት ብዙ እንቅፋቶች ሊያጋጥሙት ይችላሉ። ከሥራ መባረር፣ የሥራ አጥ ቁጥር መጨመርና የኑሮ ውድነት ባለበት በዚህ ዓለም የኢኮኖሚ ችግር በጣም ተስፋፍቷል። አንድ ወላጅ እንዲህ ዓይነት ችግሮች እያሉም በጽናት እንዲቀጥል ምን ሊረዳው ይችላል?

6 አንድ ወላጅ ለቤተሰቡ የሚያስፈልገውን የማሟላት ኃላፊነት የሰጠው ይሖዋ መሆኑን ማስታወስ ይኖርበታል። ጳውሎስ በመንፈስ አነሳሽነት የጻፈው መልእክት፣ አንድ ሰው ይህን መመሪያ መታዘዝ እየቻለ ለማድረግ ግን እምቢተኛ ቢሆን “ሃይማኖትን የካደ” እንደሆነ ተደርጎ እንደሚቆጠር ያሳያል። አንድ ክርስቲያን በአምላክ ፊት እንዲህ ዓይነት ስም እንዳያተርፍ የተቻለውን ሁሉ ያደርጋል። የሚያሳዝነው ግን በዛሬው ጊዜ ያሉ ብዙ ሰዎች “ፍቅር የሌላቸው” መሆኑ ነው። (2 ጢሞቴዎስ 3:1, 3) በእርግጥም ብዙ አባቶች ከኃላፊነታቸው በመሸሽ ቤተሰባቸውን ለችግር ዳርገዋል። ክርስቲያን ባሎች የራሳቸው ለሆኑት የሚያስፈልገውን ነገር ማሟላትን በተመለከተ እንዲህ ዓይነት የጭካኔና የግድ የለሽነት አቋም የላቸውም። ከበርካታ የሥራ ባልደረቦቻቸው በተለየ ክርስቲያን ወላጆች ለሚወዷቸው የቤተሰባቸው አባላት የሚያስፈልጉትን ነገሮች እንዲያሟሉ ስለሚያስችላቸው በጣም የተናቀ የሚባለውን ሥራ እንኳ ክቡርና አስፈላጊ እንዲሁም ይሖዋ አምላክን ለማስደሰት የሚያስችላቸው እንደሆነ አድርገው ይቆጥሩታል።

7. ወላጆች ኢየሱስ በተወው ምሳሌ ላይ ማሰላሰላቸው ጠቃሚ የሆነው ለምንድን ነው?

7 የቤተሰብ ራሶች ኢየሱስ በተወው ፍጹም ምሳሌ ላይ ማሰላሰላቸውም ሊጠቅማቸው ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስ ለእኛ “የዘላለም አባት” መሆኑን የሚገልጽ ትንቢት እንደያዘ አስታውስ። (ኢሳይያስ 9:6, 7) ኢየሱስ “የኋለኛው አዳም” እንደመሆኑ መጠን በእርሱ ላይ እምነት ለሚያሳድሩ ሰዎች አባት በመሆን “የመጀመሪያው ሰው አዳም” የነበረውን ቦታ ይይዛል። (1 ቆሮንቶስ 15:45) ራስ ወዳድ አባት ከሆነው ከአዳም በተለየ መልኩ ኢየሱስ በጣም ጥሩ አባት ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስን በተመለከተ “ሕይወቱን ስለ እኛ አሳልፎ ስለ ሰጠ፣ ፍቅር ምን እንደ ሆነ በዚህ እናውቃለን” ይላል። (1 ዮሐንስ 3:16) አዎን፣ ኢየሱስ ሕይወቱን ለሌሎች በፈቃደኝነት ሰውቷል። ከዚህም በላይ በዕለት ተዕለት ሕይወቱ በትንንሽ ጉዳዮችም እንኳ ከራሱ ይልቅ የሌሎችን ፍላጎት አስቀድሟል። እናንት ወላጆች ኢየሱስ ያሳየውን የራስን ጥቅም የመሠዋት መንፈስ መኮረጃችሁ ለእናንተም ሆነ ለቤተሰባችሁ ጠቃሚ ነው።

8, 9. (ሀ) ወፎች ብዙ ደክመው ጫጩቶቻቸውን ለመመገብ ከሚያደርጉት ጥረት ወላጆች ምን ትምህርት ሊያገኙ ይችላሉ? (ለ) ብዙ ክርስቲያን ወላጆች የራስን ጥቅም የመሠዋት መንፈስ እያሳዩ ያሉት እንዴት ነው?

8 ወላጆች፣ ኢየሱስ ዓመፀኛ ለነበሩት የአምላክ ሕዝቦች “ዶሮ ጫጩቶቿን በክንፎቿ ሥር እንደምትሰበስብ፣ ልጆችሽን ለመሰብሰብ ስንት ጊዜ ፈለግሁ!” በማለት ከተናገረው ሐሳብ ከራስ ወዳድነት ነጻ ስለሆነ ፍቅር ብዙ ትምህርት ማግኘት ይችላሉ። (ማቴዎስ 23:37) እዚህ ላይ ኢየሱስ የተናገረው ምሳሌ አንዲት ዶሮ ጫጩቶቿን በክንፎቿ ስትከልል በዓይነ ኅሊናችን መሳል እንድንችል ያደርጋል። በእርግጥም፣ ጫጩቶቿን ከጉዳት ለመጠበቅ ስትል ራሷን አደጋ ላይ ከመጣል ወደኋላ የማትል ዶሮ በደመ ነፍስ ከምትወስደው እርምጃ ወላጆች ብዙ ትምህርት ማግኘት ይችላሉ። ከዚህም ሌላ ጫጩቶች ያሏቸው ወፎች በየቀኑ የሚያደርጉትን ነገር ማየቱም ያስደንቃል። ምግብ ፍለጋ ያለ ምንም ፋታ ወዲያ ወዲህ ይበርራሉ። ኃይላቸው ተሟጥጦ ባለበት ጊዜ እንኳ ያመጡትን ምግብ አፋቸውን ከፍተው ለሚጠብቋቸው ጫጩቶች ይጥሉላቸዋል። ብዙውን ጊዜ ጫጩቶቹ ያንን ውጠው ተጨማሪ ምግብ እንዲሰጣቸው ይንጫጫሉ። ይሖዋ የፈጠራቸው አብዛኞቹ እንስሳት የልጆቻቸውን ፍላጎት በማሟላት ረገድ “እጅግ ጠቢባን” ናቸው።—ምሳሌ 30:24

9 ከዚህ ጋር በሚመሳሰል መንገድ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ክርስቲያን ወላጆች የሚያሳዩት የራስን ጥቅም የመሠዋት መንፈስ በጣም ይደነቃል። በልጆቻችሁ ላይ አንዳች ጉዳት ከሚደርስ ይልቅ እናንተ ራሳችሁ ብትጎዱ ትመርጣላችሁ። ከዚህ በተጨማሪ ለራሳችሁ ለሆኑት የሚያስፈልጉትን ነገሮች ለማሟላት በየዕለቱ በፈቃደኝነት መሥዋዕቶች ትከፍላላችሁ። አብዛኞቻችሁ የዕለት ጉርስ ለማግኘት ስትሉ አድካሚ ወይም አሰልቺ ሥራ ለማከናወን በማለዳ ትነሳላችሁ። ለቤተሰባችሁ ገንቢ ምግብ ለማቅረብ ብዙ ትደክማላችሁ። ልጆቻችሁ ንጹሕ ልብስ እንዲለብሱ፣ ተስማሚ መጠለያና ጥሩ ትምህርት እንዲያገኙ ከፍተኛ ጥረት ታደርጋላችሁ። ይህንን ደግሞ የምታደርጉት ከቀን ቀን፣ ከዓመት ዓመት ነው። እንዲህ ዓይነቱ መሥዋዕትነትና ጽናት ይሖዋን እንደሚያስደስተው ምንም ጥያቄ የለውም! (ዕብራውያን 13:16) ይሁንና ለራሳችሁ ለሆኑት ማሟላት ያለባችሁ ይበልጥ አስፈላጊ የሆኑ ሌሎች ነገሮች እንዳሉም ትገነዘባላችሁ።

መንፈሳዊ ፍላጎታቸውን ማሟላት

10, 11. ሰዎች የሚያስፈልጋቸው ከሁሉ የላቀው ነገር ምንድን ነው? ክርስቲያን ወላጆች በዚህ ረገድ የልጆቻቸውን ፍላጎት ማሟላት እንዲችሉ በቅድሚያ ምን ማድረግ ይኖርባቸዋል?

10 ቁሳዊ ነገሮችን ከማሟላትም የበለጠ አስፈላጊ የሆነው መንፈሳዊ ነገሮችን ማሟላት ነው። ኢየሱስ “ሰው ከእግዚአብሔር አፍ በሚወጣው ቃል ሁሉ እንጂ በእንጀራ ብቻ አይኖርም” ብሏል። (ማቴዎስ 4:4፤ 5:3) ወላጆች የቤተሰባችሁን መንፈሳዊ ፍላጎት ለማሟላት ምን ማድረግ ትችላላችሁ?

11 በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ላይ የዘዳግም 6:5-7ን ያህል ብዙ ጊዜ የሚጠቀስ ጥቅስ ያለ አይመስልም። እባካችሁ መጽሐፍ ቅዱሳችሁን ገልጣችሁ ጥቅሱን አንብቡ። በመጀመሪያ ወላጆች ለይሖዋ ያላቸውን ፍቅር በመገንባትና ቃሉን በልባቸው በመያዝ የራሳቸውን መንፈሳዊነት እንዲንከባከቡ መታዘዛቸውን አስተውሉ። አዎን፣ መጽሐፍ ቅዱስን ዘወትር በማንበብ እንዲሁም የይሖዋን መንገዶች፣ መሠረታዊ ሥርዓቶችና ሕጎች በትክክል መረዳትና መውደድ እንድትችሉ በዚያ ላይ በማሰላሰል የአምላክን ቃል በቁም ነገር ማጥናት ይኖርባችኋል። እንዲህ ስታደርጉ ልባችሁ አስደናቂ በሆኑ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶች ስለሚሞላ ደስታ የሚሰማችሁ ከመሆኑም ሌላ ለይሖዋ ጥልቅ አክብሮትና ፍቅር ያድርባችኋል። ለልጆቻችሁ የምትነግሯቸው ብዙ መልካም ነገሮች ታገኛላችሁ።—ሉቃስ 6:45

12. ወላጆች ልጆቻቸው የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት እንዲገባቸው ለማድረግ ኢየሱስ የተወውን ምሳሌ መኮረጅ የሚችሉት እንዴት ነው?

12 በመንፈሳዊ ጠንካራ የሆኑ ወላጆች በዘዳግም 6:7 ላይ የሚገኘውን በማንኛውም አጋጣሚ የይሖዋን ቃል ለልጆቻቸው ‘እንዲያስጠኑ’ የተሰጣቸውን ምክር ተግባራዊ ለማድረግ ዝግጁ ናቸው። ‘ማስጠናት’ ወይም መቅረጽ የሚለው ቃል ደጋግሞ በማስተማር እንዳይረሱት ማድረግን ያመለክታል። ይሖዋ ሁላችንም በተለይ ደግሞ ልጆች አንድ ነገር እንዲገባን በተደጋጋሚ ሊነገረን እንደሚገባ ያውቃል። በመሆኑም ኢየሱስ አገልግሎቱን በሚያከናውንበት ወቅት አንድን ነገር ደጋግሞ ይናገር ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ ደቀ መዛሙርቱ የትዕቢትና የፉክክር መንፈስ ከማንጸባረቅ ይልቅ ትሑት እንዲሆኑ ባስተማራቸው ጊዜ የተለያዩ መንገዶች በመጠቀም ያንኑ ጉዳይ ደጋግሞ ተናግሯል። ማስረጃ በማቅረብ፣ ምሳሌ በመጠቀም ብሎም በተግባር በማሳየት አስተምሯቸዋል። (ማቴዎስ 18:1-4፤ 20:25-27፤ ዮሐንስ 13:12-15) ደግሞም ኢየሱስ ትዕግሥት አለማጣቱ በጣም የሚደነቅ ነው። በተመሳሳይ ወላጆች ልጆቻቸው የይሖዋን መመሪያዎች እንዲረዱና በሥራ እንዲያውሉ በትዕግሥት ደጋግሞ በመንገር መሠረታዊ እውነቶችን ማስተማር የሚችሉባቸውን መንገዶች መፈለግ ይኖርባቸዋል።

13, 14. ወላጆች ለልጆቻቸው የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ማስጠናት የሚችሉባቸው አንዳንድ አጋጣሚዎች የትኞቹ ናቸው? በየትኞቹ መሣሪያዎችስ መጠቀም ይችላሉ?

13 የቤተሰብ ጥናት በዚህ መንገድ ለማስተማር የሚያስችል አመቺ ወቅት ነው። በእርግጥም ቋሚ፣ የሚያንጽና አስደሳች የሆነ የቤተሰብ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለቤተሰቡ መንፈሳዊነት ቁልፍ ነገር ነው። በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ክርስቲያን ቤተሰቦች በዚህ ዝግጅት የሚደሰቱ ሲሆን የይሖዋ ድርጅት የሚያዘጋጃቸውን ጽሑፎች በመጠቀም ጥናቱ የልጆቻቸውን ፍላጎት የሚያሟላ እንዲሆን ይጥራሉ። በዚህ ረገድ ከታላቁ አስተማሪ ተማሩ እንዲሁም ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎችና—ተግባራዊ መሆን የሚችሉ መልሶች የተባሉት መጻሕፍት እጅግ ጠቃሚ ሆነው ተገኝተዋል። b ይሁን እንጂ ልጆችን ማስተማር የሚቻለው በቤተሰብ ጥናት ወቅት ብቻ አይደለም።

14 ዘዳግም 6:7 እንደሚያሳየው እናንተ ወላጆች ከልጆቻችሁ ጋር መንፈሳዊ ነገሮችን መወያየት የምትችሉባቸው በርካታ አጋጣሚዎች አሉ። አብራችሁ ስትጓዙም ሆነ ሥራ ስትሠሩ ወይም አብራችሁ ስትዝናኑ የልጆቻችሁን መንፈሳዊ ፍላጎቶች ማሟላት የምትችሉባቸው አጋጣሚዎች ልታገኙ ትችላላችሁ። እንዲህ ሲባል ግን ለልጆቻችሁ ነጋ ጠባ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ እውነት “ንግግር” ትሰጣላችሁ ማለት እንዳልሆነ ግልጽ ነው። ከዚህ ይልቅ በቤተሰባችሁ ውስጥ የሚኖረው ጭውውት ገንቢ የሆነ መንፈሳዊ ይዘት እንዲኖረው ጥረት አድርጉ። ለምሳሌ ያህል፣ ንቁ! መጽሔት በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ በርካታ ትምህርቶች ይዞ ይወጣል። እንደዚህ የመሳሰሉ ርዕሰ ጉዳዮች ይሖዋ ስለፈጠራቸው እንስሳት፣ በዓለም ዙሪያ ስለሚገኙ የሚያምሩ አካባቢዎች እንዲሁም ሰዎች ስላላቸው የተለያየ ባሕልና አኗኗር ለመነጋገር አጋጣሚ ሊከፍቱ ይችላሉ። እንዲህ ያሉት ውይይቶች ወጣቶች የታማኝና ልባም ባሪያ ክፍል የሚያዘጋጃቸውን ጽሑፎች በብዛት እንዲያነብቡ ሊያነሳሳቸው ይችላል።—ማቴዎስ 24:45-47

15. ወላጆች ልጆቻቸው ክርስቲያናዊውን አገልግሎት ደስ የሚልና አርኪ ሥራ እንደሆነ አድርገው እንዲመለከቱት መርዳት የሚችሉት እንዴት ነው?

15 ከልጆቻችሁ ጋር ገንቢ ውይይት ማድረጋችሁ ከሌላም አቅጣጫ መንፈሳዊ ፍላጎታቸውን እንድታሟሉ ያስችላችኋል። ክርስቲያን ልጆች እምነታቸውን ለሌሎች በሚገባ መግለጽ እንዲችሉ ሥልጠና ያስፈልጋቸዋል። መጠበቂያ ግንብ ወይም ንቁ! ላይ ስለወጣ ትኩረታችሁን የሳበ ነጥብ ስትናገሩ ርዕሱን ከአገልግሎት ጋር ለማያያዝ ጥረት ማድረግ ትችላላችሁ። ለምሳሌ ያህል፣ እንዲህ ብላችሁ መጠየቅ ትችላላችሁ:- “ብዙ ሰዎች ይሖዋ ስላደረገው ስለዚህ ጉዳይ ቢያውቁ ጥሩ አይደለም? አንድ ሰው ይህን ጉዳይ ደስ ብሎት እንዲሰማ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?” እንዲህ ያሉ ውይይቶች ልጆች የሚማሩትን ነገር ለሌሎች ለማካፈል ከበፊቱ የበለጠ ፍላጎት እንዲያድርባቸው ሊረዳቸው ይችላል። ከዚያም ልጆቻችሁ አብረዋችሁ አገልግሎት ሲወጡ የተወያያችሁባቸውን ነጥቦች እንዴት በተግባር ማዋል እንደሚቻል ሕያው ማስረጃ ያያሉ። ከዚህ በተጨማሪ አገልግሎት ከፍተኛ እርካታና ደስታ የሚያስገኝ የሚወደድ ሥራ እንደሆነ ሊገነዘቡ ይችላሉ።—የሐዋርያት ሥራ 20:35

16. ልጆች ወላጆቻቸው ሲጸልዩ በመስማት ምን ትምህርት ማግኘት ይችላሉ?

16 ወላጆች በሚጸልዩበት ጊዜም የልጆቻቸውን መንፈሳዊ ፍላጎቶች ማሟላት ይችላሉ። ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን እንዴት መጸለይ እንዳለባቸው ያስተማራቸው ከመሆኑም ሌላ ከእነርሱ ጋር የጸለየባቸው ብዙ ወቅቶች ነበሩ። (ሉቃስ 11:1-13) ከይሖዋ ልጅ ጋር አብረው በመጸለያቸው ምን ያህል ትምህርት እንዳገኙ እስቲ አስብ! በተመሳሳይ ልጆቻችሁ እናንተ ስትጸልዩ በመስማት ብዙ ትምህርት ያገኛሉ። ለምሳሌ ያህል፣ ይሖዋ ያስጨነቀንን ማንኛውንም ነገር ከልባችን በነጻነት እንድንነግረው እንደሚፈልግ ትምህርት ሊያገኙ ይችላሉ። አዎን፣ ወላጆች የምታቀርቡት ጸሎት ለልጆቻችሁ በጣም አስፈላጊ የሆነ መንፈሳዊ ትምህርት ያስገኝላቸዋል፤ ይህም በሰማይ ከሚኖረው አባታቸው ጋር ዝምድና መመሥረት እንደሚችሉ ማወቃቸው ነው።—1 ጴጥሮስ 5:7

ስሜታዊ ፍላጎታቸውን ማሟላት

17, 18. (ሀ) መጽሐፍ ቅዱስ ለልጆች ፍቅር የማሳየትን አስፈላጊነት የሚገልጸው እንዴት ነው? (ለ) አባቶች ለልጆቻቸው ያላቸውን ፍቅር በመግለጽ ረገድ ይሖዋን መኮረጅ ያለባቸው እንዴት ነው?

17 ልጆች ትኩረት የሚያሻው ስሜታዊ ፍላጎት እንዳላቸውም የታወቀ ነው። የአምላክ ቃል ወላጆች ይህን የልጆቻቸውን ፍላጎት ማሟላታቸው በጣም አስፈላጊ እንደሆነ ይናገራል። ለምሳሌ ያህል፣ ወጣት ሴቶች “ልጆቻቸውን እንዲወዱ” ማሳሰቢያ ተሰጥቷቸዋል። (ቲቶ 2:4) በእርግጥም እንዲህ ማድረጉ ተገቢ ነው። በዚህ መንገድ ልጆች ፍቅር ማሳየትን የሚማሩ ከመሆኑም ሌላ ዘላቂ ጥቅም ያገኛሉ። በሌላ በኩል ደግሞ ለልጆች ፍቅር አለማሳየት ትልቅ ስህተት ነው። ይህ ሁኔታ ለከፍተኛ ሐዘን ይዳርጋል እንዲሁም አለፍጽምና እያለብንም ከፍተኛ ፍቅር የሚያሳየንን ይሖዋን መምሰል እንዳልቻልን ያሳያል።—መዝሙር 103:8-14

18 ከዚህም በላይ ይሖዋ በምድር ላይ ያሉ ልጆቹን ቀድሞ ወድዷቸዋል። አንደኛ ዮሐንስ 4:19 “አስቀድሞ ወዶናልና” ይላል። በተለይ አባቶች በእናንተና በልጆቻችሁ መካከል ጠንካራ የፍቅር ሰንሰለት እንዲኖር ለማድረግ ቅድሚያውን በመውሰድ ይሖዋን መምሰል ይኖርባችኋል። መጽሐፍ ቅዱስ አባቶች ልጆቻቸው “ተስፋ እንዳይቈርጡ” ማስመረር እንደሌለባቸው ያሳስባል። (ቈላስይስ 3:21) ልጆች ወላጃቸው እንደማይወዳቸው ወይም ብዙም ትኩረት እንደማይሰጣቸው ከተሰማቸው በጣም ይጎዳሉ። ስሜታቸውን ከመግለጽ ወደኋላ የሚሉ አባቶች የይሖዋን ምሳሌ ማስታወሳቸው ጠቃሚ ነው። ይሖዋ በልጁ ደስ እንደሚሰኝና እንደሚወደው ከሰማይ ሆኖ ተናግሯል። (ማቴዎስ 3:17፤ 17:5) ኢየሱስ ይህን ሲሰማ ምንኛ ተደስቶ ይሆን! በተመሳሳይ ልጆች ወላጆቻቸው እንደሚወዷቸውና እንደሚደሰቱባቸው ከልባቸው ሲናገሩ መስማታቸው ብርታትና ጥንካሬ ይሰጣቸዋል።

19. ተግሣጽ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? በዚህ ረገድ ክርስቲያን ወላጆች ሚዛናዊ መሆን ያለባቸው እንዴት ነው?

19 እርግጥ ነው፣ ወላጆች ለልጆቻቸው ያላቸው ፍቅር በቃል ብቻ አይወሰንም። ፍቅር በዋነኝነት የሚገለጸው በተግባር ነው። በተለይ ወላጆች የልጆቻቸውን ቁሳዊና መንፈሳዊ ፍላጎቶች እንዲያሟሉ የሚያነሳሳቸው ዋነኛው ነገር ፍቅር ከሆነ አድራጎታቸው ልጆቻቸውን እንደሚወዱ ሊያሳይ ይችላል። ከዚህ በተጨማሪ ተግሣጽ የወላጅ ፍቅር የሚገለጽበት አስፈላጊ ድርጊት ነው። በእርግጥም “ጌታ የሚወደውን ይገሥጻል።” (ዕብራውያን 12:6) በአንጻሩ ደግሞ ተግሣጽ አለመስጠት ወላጆች ልጆቻቸውን እንደማይወዱ ያሳያል! (ምሳሌ 13:24) ይሖዋ ምንጊዜም ትክክለኛውን ሚዛን የሚጠብቅ ሲሆን “ተገቢውን” ተግሣጽም ይሰጣል። (ኤርምያስ 46:28) ፍጽምና ለሚጎድላቸው ወላጆች በዚህ ረገድ ሚዛናዊ መሆን ቀላል አይደለም። ይሁን እንጂ በተገቢው መጠን ለመቅጣት ማንኛውንም ጥረት ልታደርጉ ይገባል። ጥብቅና በፍቅር ላይ የተመሠረተ ተግሣጽ አንድ ልጅ ሲያድግ ደስተኛና ትርጉም ያለው ሕይወት እንዲመራ ያስችለዋል። (ምሳሌ 22:6) የትኛውም ክርስቲያን ወላጅ ለልጁ የሚመኘው ይህን አይደለም?

20. ወላጆች ልጆቻቸው ‘ሕይወትን እንዲመርጡ’ ከሁሉ የተሻለውን አጋጣሚ ሊሰጧቸው የሚችሉት እንዴት ነው?

20 እናንት ወላጆች የልጆቻችሁን ቁሳዊ፣ መንፈሳዊና ስሜታዊ ፍላጎቶች በማሟላት ረገድ ይሖዋ የሰጣችሁን አስፈላጊ ሥራ የምትወጡ ከሆነ ታላቅ በረከት ታገኛላችሁ። እንዲህ በማድረግ ልጆቻችሁ ‘ሕይወትን እንዲመርጡ’ የሚያስችላቸውን ከሁሉ የተሻለ አጋጣሚ በመስጠት ‘በሕይወት እንዲኖሩ’ ትረዷቸዋላችሁ። (ዘዳግም 30:19) በዕድሜ እየበሰሉ ሲሄዱ ይሖዋን ለማገልገል የሚመርጡና ወደ ሕይወት በሚያመራው መንገድ የሚቀጥሉ ልጆች ለወላጆቻቸው ከፍተኛ ደስታ ያመጣሉ። (መዝሙር 127:3-5) እንዲህ ዓይነቱ ደስታ ደግሞ ለዘላለም ይዘልቃል! ይሁንና ልጆች በአሁኑ ጊዜ ይሖዋን ማመስገን የሚችሉት እንዴት ነው? የሚቀጥለው ርዕስ ይህን ጉዳይ ያብራራል።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

a በዚህ ርዕስ ውስጥ ለቤተሰብ የሚያስፈልገውን ነገር የሚያሟላው ወገን የሚጠቀሰው በወንድ ፆታ ይሆናል። ይሁን እንጂ መሠረታዊ ሥርዓቶቹ ለቤተሰብ የሚያስፈልጉትን ነገሮች የማሟላቱን ኃላፊነት ለሚወጡ ክርስቲያን ሴቶችም ይሠራሉ።

b በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጁ።

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

ወላጆች የልጆቻቸውን

• ቁሳዊ

• መንፈሳዊ

• ስሜታዊ ፍላጎቶች ለማሟላት ምን ማድረግ ይችላሉ?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ብዙ የወፍ ዝርያዎች ጫጩቶቻቸውን ለመመገብ በጣም ይደክማሉ

[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ወላጆች በመጀመሪያ ደረጃ የራሳቸውን መንፈሳዊነት መገንባት ይኖርባቸዋል

[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ወላጆች ልጆቻቸውን ስለ ፈጣሪ ማስተማር የሚችሉባቸው ብዙ አጋጣሚዎች አሉ

[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ልጆች ወላጆቻቸው ደስ የሚሰኙባቸው ከሆነ ብርታትና ድፍረት ያገኛሉ